Saturday, 17 August 2013 11:19

ዶ/ር ዳኛቸው ነገ በሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ገለፃ ያደርጋሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)


ፓርቲው በአባላቱ ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት እንዲቆም ጠይቋል

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ ነገ ረፋድ ላይ በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትምህርት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 
“እኔ ልናገር የምችለው በፍልስፍና ጉዳዮች ዙሪያ ነው” ያሉት ምሁሩ፤ በህግ በሰብአዊ መብት ፣ በፖለቲካ፣ በትምህርትና በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ትምህርት እንደሚሰጡ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
“እሁድ ረፋድ ላይ በማቀርበው ትምህርት ገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የተቃውሞ ጐራውም አካባቢም ሸንቆጥ ይደረጋል” ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተገኝቶ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሀሣብ ማካፈል ይችላል ብለዋል፡፡ ሠማያዊ ፓርቲ በተለያዩ ጊዜያት ምሁራንን እየጋበዘ በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ለማህበረሠቡ ትምህርት እንዲሰጡ የሚያደርግ ሲሆን ዶ/ር ዳኛቸው ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ግብዣ ቀርቦላቸው በስራ ብዛት ሳይመቻቸው እንደቅ አስታውሰው፤ ለነገው ፕሮግራም ግን በዝግጅት ላይ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ሰማያዊ ፓርቲ ትላንትና ባወጣው መግለጫ፤ በአባላቱ ላይ እየደረሰ ያለው የመብት ረገጣና እንግልት እንዲቆምመንግስትን ጠይቋል፡፡
“የሀገራችን የመንግስት አወቃቀር ዋና መሠረቱ ዘርና ቀለም ነው” ያለው ፓርቲው፤ ዜጐች በመልካም አስተዳደር፣ በማንነትና በመሰል ችግሮች ዙሪያ ጥያቄና እሮሮ በማሰማታቸው ከፍተኛ እስርና እንግልት እየደረሰባቸው በመሆኑ፣ ድርጊቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እጠይቃለሁ ብሏል በመግለጫው፡፡ ፓርቲው ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ባካሄደው ሰላማዊ የተቃውም ሰልፍ ካነሳቸው ጥያቄዎች አንዱ የመልካም አስተዳደር እጦት እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፤ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ህገ-ወጥ የመብት ረገጣውን መቀጠሉ በጋሞጐፋ ዞን በቁጫ ወረዳ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ተደጋጋሚ በደል ማሳያ ነው ብሏል፡፡ የቁጫ ወረዳ ነዋሪዎችም የመንግስት ጫና ሳይበግራቸው ሰላማዊ ትግላቸውን እንዲቀጥሉ ያሳሰበው ፓርቲው፤ መንግስት በወረዳው ነዋሪዎች ላይ የሚያደርሠውን እስርና እንግልት በአስቸኳይ እንዲያቆም ሲል አሳስቧል፡፡

Read 27195 times