Saturday, 28 September 2013 10:53

“የሀይል መቆራረጥ ኢንዱስትሪውን ጎድቷል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ችግሩን ለመፍታት ከኮርፖሬሽኑ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል

                    በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተፅዕኖ ካሳረፉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የሀይል መቆራረጥ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ አብተው ገለፁ፡፡ ሚኒስትሩ ሀሙስ ረፋድ ላይ በሚኒስቴሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሶስት አመቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ዘርፉ ወደፊት እንዳይራመድ እንቅፋት ናቸው ከተባሉት ውስጥ የሀይል መቆራረጥ እንደሚገኝበት ጠቁመው፤ በቀሪዎቹ ሁለት አመታት የእድገትና ትራንስፎርሜሽኑን ግብ ለመምታት የሀይል አቅርቦትን በተሻለና በማይቆራረጥ መልኩ ለማቅረብ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ስምምንት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ያላት የሀይል አቅርቦት ዋጋ ከሌላው አለም በጣም ርካሽ በመሆኑ የባለሀብቶችን ቀልብ መሳብ ይችላል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሆኖም አቅርቦቱ መቆራረጡ ባለሀብቶች እንደቅሬታ ያነሱት በመሆኑ በቀጣይ ሁለት አመታት ለውጥ እንደሚመጣ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

በሶስት አመቱ የእቅድ አፈፃፀም ላይ እንደ ችግር ከተነሱትና ባለሀብቶችም ቅሬታ ካነሱበት ውስጥ የሚኒስትሩ የድጋፍ ማነስ አንዱ እንደሆነ ገልፀው፤ በቀጣይ በዘርፉ ለተሰማሩና ለሚሰማሩ በቂ ድጋፍ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የሎጂስቲክስ ችግር በዘርፉ ፈተና እንደነበረ በግምገማው ተረጋግጧል ያሉት አቶ አህመድ፤ ከወደብ እስከ ፋብሪካ፣ ከፋብሪካ እስከ ወደብ ያለው የሎጂስቲክስ ሁኔታ በገንዘብም ሆነ በጊዜ ብዙ በመሆኑ ቅሬታ መቅረቡንና ሚኒስቴሩም ይህን ማረጋገጡን ገልፀው፤ የመልቲ ሞዳል ሲስተምን በማስተካከል የደረቅ ወደብን በማፋስስትና በመሳሰሉት የገንዘቡንም ሆነ የጊዜውን ርዝመት ለመቀነስ እቅድ መያዙን አብራርተዋል፡፡

ሌላው “ከሚኒስቴሩ ዝግጅት ጋር አልተጣጣመም” በማለት አቶ አህመድ የገለፁት የለማ መሬት አለመዘጋጀት ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ ባለሀብት ይመጣል አይመጣም በሚል ጥርጣሬ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ “ሼድ የመገንባት ጉዳይ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ ግንባታው ለባለሀብቱ የተተወ ነበር” ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተደረገው የሶስት አመት ግምገማ ግን ባለሀብቱ ከውጭ መጥቶ ሼድ ከሚገነባ ይልቅ የተገነባ ውስጥ ስራ የመጀመር ፍላጐት በማሳየቱ መንግስት ይህን ጉዳይ በአትኩሮት እየተመለከተው ነው ብለዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪን በተመለከተ ሚኒስትሩ ሲናገሩ፤ ባለፉት ሶስት አመታት ወደ ውጭ መላክ የነበረባቸው ምርቶች አብዛኞቹ አገር ውስጥ በመሸጣቸው በውጭ ምንዛሬ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠራቸውንና በቀጣዮቹ ሁለት አመታት የምርቱን 60 በመቶ ወደ ውጭ በመላክ፣ በየአመቱ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመው፤ በየአመቱ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን 23 በመቶ በማሳደግ የእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ እቅድ ለማሳካት እቅድ መያዙን በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

ከ2003 እስከ 2005 ዓ.ም ባለው እንቅስቃሴ ዲያስፖራውን ጨምሮ 887 የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ ለመንቀሳቀስ ፈቃድ መውሰዳቸውን የጠቆሙት አቶ አህመድ፤ ከእነዚህ ውስጥ 23 በመቶው ወደ ምርት መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በዘርፉ ያላቸው ተሳትፎ አዝጋሚ ቢሆንም ከበፊቱ ግን የተሻለ እንደሆነ የገለፁት ሚኒስትሩ፤ በተለይም በመንግስት ይዞታ የነበሩትን የኢንዱስትሪ ዘርፎች ወደ ግል በማዘዋወሩ በኩል የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ መሻሻል አሳይቷል ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው የግብአት አቅርቦትን በተመለከተ ከጥሬ እቃ ይልቅ ኢንዱስትሪው መጓተቱን ጠቁመው፤ በቅባት እህል፣ በምግብ እህል፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ በኩል ግብርናው ከፋብሪካው መቅደሙን ተናግረዋል፡፡ እንደምሳሌም የተቀነባበረ ስጋ ብቻ ወደ ውጭ መላክ አዋጪ ሆኖ ሳለ፣ ኢትዮጵያ ግን በቂ የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ስለሌላት የቁም ከብትም ጭምር እንደምትልክ ጠቁመው፣ የቅባት እህሎችም ተቀነባብረው ከመላክ ይልቅ እንዲሁ ይላካሉ፤ ይህም የሚያሳየው ግብርናው ከኢንዱስትሪው መቅደሙን ነው ብለዋል፡፡

በግብርናው በኩል ችግሮችን ለመቅረፍ አርሶ አደሩን በማደራጀትና በማንቃት በተለይም በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ በማድረግ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል፤ ሚኒስትሩ፡፡ የፋብሪካዎችን የአቅም አጠቃቀም በተመለከተ፤ አብዛኞቹ ከ60 በመቶ እንዳልዘለሉ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ አቅም አጠቃቀም 58 በመቶ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ከ55 በመቶ አለመብለጡን በምሳሌነት አንስተው ይሁን እንጂ ከ75 እስከ 80 በመቶ አቅም የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ በግምገማው መረጋገጡንና እነዚህም በቀጣዮቹ ሁለት አመታት የበለጠ አቅም እንደሚጠቀሙና መንግስትም ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አብራርተዋል፡፡ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሚደረገውን የብድር አቅርቦት ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ ባለሀብቶች 30 በመቶ ይዘው መንግስት ሰባ በመቶውን ያበድር እንደነበር ገልፀው፤ አሁን ግን ሰባ ሰላሳውን ትተን ባለሀብቱን የተሻለ ካፒታል ይዞ እንዲመጣ እያበረታታን ነው ብለዋል፡፡ ለልማት የሚሰሩት ልማት ባንክና ንግድ ባንክ ለዚሁ ስራ መቀላጠፍ እየሰሩ እንደሆነ የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ልማት ባንክ ቁጠባ መሰብሰብ እንደማይችልና ንግድ ባንክ የሚሰበስበው ቁጠባ ወደ ልማት ባንክ እየዞረ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ እየዋለ እንደሆነ በሰፊው አብራርተዋል፡፡ የሶስት አመቱን የስራ አፈፃፀም ጥንካሬዎችና ድክመቶች በዝርዝርና በአሀዝ ያስቀመጠው ሚኒስቴሩ፤ ጥንካሬዎቹን የበለጠ በማሳደግና ድክመቶቹን በማሻሻል ዘንድሮና በ2007 ጠንክሮ በመስራት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

Read 6290 times