Saturday, 28 September 2013 13:30

ከ1983 የመንግስት ለውጥ በኋላ

Written by  ዶ/ር ጌቴ ገላዬ፣ggelaye@yahoo.com
Rate this item
(6 votes)

የምስራቅ ጎጃም ገበሬዎች የገጠሟቸው ፖለቲካዊ ግጥሞች

የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም
ሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ፣ ጀርመን
ጭማቄ ጽሑፍ (Abstract)
ይህ የጥናት ወረቀት በኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ወዲህ የምስራቅ ጎጃም ገበሬዎች የገጠማቸውን፣ ያዜሟቸውንና ያንጎራጎሯቸውን ፖለቲካዊ ግጥሞች ይመለከታል፡፡ የግጥሞቹ ዋነኛ ጭብጥ በወቅታዊ የገጠር አስተዳደርና በገበሬዎች ማህበራዊ ሕይወት ላይ የሚያተኩር ሲሆን በመንግስት ባለስልጣናት፣ በአገር አንድነት ጥያቄና በተለይም ደግሞ በ1989 ዓ.ም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተካሄደውን የገጠር መሬት ሽግሽግ ፖሊሲ አፈፃፀምና ሽግሽጉ ያስከተለውን ተፅዕኖ ይቃኛል፡፡ በተጨማሪም ባንድ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ እየተባባሰ የመጣውን መንግስትን የመጠራጠር፣ የእርስበርስ ጥላቻና ተቃውሞ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የምግብ እጥረት፣ የምርት ማሽቆልቆል፣ ድህነት፣ ስደትና በሰላም አብሮ የመኖር ተስፋ መጨለም ያሳሰባቸው የጎጃም ገበሬዎች ብቸኛ ሀብታቸው በሆነው ዘይቤያዊና ቅኔ ለበስ አማርኛ ቃልግጥም (Amharic oral poetry) ስሜትን የሚኮረኩሩና ልብን የሚነኩ መልዕክቶች እንደሚሰነዝሩ በምሳሌ በተደገፉ ግጥሞች ትንታኔ ያቀርባል፡፡ የገበሬዎቹ ስነልቦናዊ አስተሳሰብ፣ ባህላዊ ዕውቀትና ስለ አካባቢ ያላቸው ጥልቅ ግንዛቤ፣ ስለ ባህላዊ ዳኝነትና አስተዳደር፣ ስለ ልማትና መሬት አያያዝ ወዘተ የሚያቀርቧቸው ሐሳቦች የሚገልፁበት አንዱ መንገድ ለዘመናት ባካበቱት የስነቃል (oral literature) ቅርስ አማካኝነት በመሆኑ፣ በማህበራዊ ሳይንስና በገጠር ልማት ተመራማሪዎች፣ በስነትምህርት፣ በስነሰብእና፣በስነቃል ምሁራን እንዲሁም በመንግስት ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በጥንቃቄ መሰብሰብና በጥልቀት መጠናት እንዳለበት ይህ የጥናት ወረቀት ያመለክታል፡፡
እንደ ጋዜጣ፣ መፅሄት፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የመሳሰሉትን መገናኛ ብዙን የመጠቀምና ሐሳቡን በፅሁፍ የመግለፅ ዕድል የማያገኘው የገጠሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲደሰትም ሆነ ሲከፋ ስሜቱን የሚገልፀው፣ በደል ሲደርስበት ብሶቱንና ቁጭቱን የሚወጣው በዘፈን፣ በቀረርቶ፣ በፉከራ፣ በእንጉርጉሮ፣ በለቅሶ ዜማና በመሳሰሉት ቃላዊ ቅርሶቹ አማካኝነት ነው፡፡ በአብዛኛው የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ እንደሚስተዋለው ገበሬዎች ቃልግጥምን፣ ዘፈን እንጉርጉሮን፣ ቀረርቶን ፉከራን ወዘተ.በዕለት ተዕለት ህይወታቸው በለዛና በዘይቤ እየቀመሩ ይጠቀሙበታል፡፡ ድንቅ በሆነ የቋንቋ ቅመራ ችሎታቸውም ግጥምን ለጀግና ሙገሳ፣ ለፈሪ ወቀሳ፣ ለኃዘን እንጉርጉሮ፣ ለተበዳይ እሮሮ፣ ለፍቅር መግለጫ፣ ለሀሜት ማሽሟጠጫ፣ ለችሎት ምልልስ፣ ለአቤቱታ ክስ ወዘተ. ለዘመናት ሲገለገሉበት ኖረዋል፡፡ አሁንም ወደፊትም ይገለገሉበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይ እንደኛ ባለ በኢኮኖሚ ታዳጊ አገር የገበሬው ህይወት፣ የጤናው ሁኔታ፣ አለባበሱ፣ አኗኗሩ ወዘተ--- እጅግ አሳዛኝና እጅ ወደ አፍ በሆነበት ድህነት፣ ብሶት፣ ፍትህ ማጣት፣ መበደል፣ ቁጭት፣ ወዘተ…የመሳሰሉት ስሜቶችና ችግሮች የሚገለጹበት አንዱ መንገድ በቃል ግጥም ነው፡፡ ከረጅሙ ታሪካችን እንደምንረዳው በተከታታይ ሥልጣን ላይ የወጡ መሪዎች (መንግሥታት) ገበሬውን በግብር፣ በመዋጮ፣ በዘመቻና በልዩ ልዩ የጉልበት ሥራዎች ከማዋከብ በስተቀር የተሻለ ሕይወት እንዲመራ አላስቻሉትም፡፡ ሌላው ቀርቶ በዚያው ኋላቀር በሆነው የእርሻ መሣሪያ እንኳ መሬቱን አርሶ፣ ልጆቹንና በርካታ ቤተሰቡን እንዳይመግብ በየጊዜው የሚወጡት የመሬት ይዞታ ፖሊሲዎችና አዋጆች እንዲሁም የመንግስት ሹማምንት ያደረሱበትንና እያደረሱበት ያሉትን ማኅበራዊ፣ ሰብአዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ በደሎች ሁሉንም መዘርዘር ያስቸግራል፡፡ ለምሳሌ እስቲ በዓጼው ዘመነ መንግስት፣ ምስኪኑ ገበሬ ለደረሰበት ሰብአዊ በደል ብሶቱንና እሮሮውን በእንጉርጉሮ እንዴት እንደገለፀው ከሚከተሉት ግጥሞች እንመልከት፡፡
በሬዬን አረደው፣ ከብቴንም ነዳው፣ ምሽቴንም ተኛት
ጐጆዬን አቃጥሎ አስተኛኝ መሬት
ሲጨንቀኝ ሲጠበኝ ዘመድ አረግሁት፡፡
ታገር እኖር ብዬ፣ ልጅ አሳድግ ብዬ
ለጭቃው ዳርሁለት ምሽቴን እቴ ብዬ፡፡
“ምሽቴን ማን ተኝቷት?”
“በሬዬን ማን አርሶት?” አይሉም፣ አይሉም
ቀን የከፋ ለታ ይደረጋል ሁሉም፡፡
ግጥሞቹ ለማን እንደተገጠሙ መገመት አያስቸግርም፡፡ በዘመኑ ጭቃ ሹም፣ ነጭ ለባሽ፣ የጐበዝ አለቃ፣ ምስለኔ፣ አጥቢያ ዳኛ እየተባሉ ይሾሙ ለነበሩትና በገበሬው ወይም በጢሰኛው ላይ ላደረሱት በደልና ለሠሩት ግፍ በግጥም የተሰጠ ምላሽ ነበር፡፡ በቅርቡ በደርግ አገዛዝ ዘመን በተግባር የታዩትና በኃይል ለመከናወን የተሞከሩት የግብርና ልማት ፕሮጀክቶች፣ የመንደር ምሥረታና የሰፈራ ፕሮግራሞች፣ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራት እንቅስቃሴዎች፣ የመሬት ክፍፍል አስተዳደራዊ ዕቅዶችና አፈጻጸሞች፣ ወዘተ ለገጠሩ ኅብረተሰብ ያተረፉለት ጐልቶ የሚታይ ፋይዳ የለም፡፡
የጐጃምን ገበሬዎች ሥነ ባሕርይና አስተሳሰብ ለመረዳት፣ ስለ መሬት ወይም ርስት፣ ስለ እርሻ በሬና የጦር መሣሪያ አስፈላጊነትና እንዲሁም ስለ ሚስት ያላቸውን የጠለቀና ሥር የሰደደ አመለካከት በልዩ ልዩ ዘዴዎች መመርመርና ማጥናት ያስፈልጋል። በመሬት ወይም በአባት ርስት የተነሣ ስንቱ ገበሬ ሞቷል፤ ስንቱ ተጋድሏል ወይም ደም ተቃብቷል፣ ስንቱ ሸፍቷል፣ ስንቱ አገር ጥሎ ተሰዷል፡፡ የመሬት ይዞታ ዋስትና ለገበሬው ከሁሉም የበለጠ ክብሩና ማዕረጉ ነው፡፡ መሬት ለገበሬው ሕይወቱ፣ ጉሮሮው፣ ትዳሩ፣ ሀብቱ ማለት ነው፡፡ መሬቱን፣ ሀብት ንብረቱን፣ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ዘመዶቹን ነቅቶ ለመጠበቅና ከጠላት ለመከላከል ደግሞ እንዳቅሙ፣ እንዳካባቢውና እንደዘመኑ ባህላዊ ወይም ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ይይዛል ወይም ይታጠቃል፡፡ ከቻለና ከተፈቀደለት ካላሽንኮቭ፣ ምኒሽር፣ ዲሞትፈር፣ ወይም በልጅግ ይገዛል፡፡ ካልቻለ ደግሞ ጅንፎ ያለው ጠንካራ ሽመል ወይም ዱላ፣ ጦር ወይም አንካሴ፣ ሳንጃ ወይም ጩቤ ይይዛል፡፡ መያዝ ብቻ ሳይሆን በተለይ በቀረርቶና በፉከራ ጊዜ የሚወደውን ዱላ ወይም የጦር መሣሪያ እያሽከረከረ ወንድነቱን፣ ኃይለኛነቱን፣ ገዳይነቱን፣ ጉዛምነቱን፣ እንዲሁም ሀብቱን፣ ባለቤቱን አባቱንና ዘመዶቹን በግጥም እያነሳ ያሞግሳል፡፡ ጠላቱን ያንኳስሳል፡፡ የጐጃም ገበሬዎች እንደሚሉት ቀረርቶ ሲሰሙ እጅግ ይነሸጣሉ፡፡ ቀረርቶውን በተከታታይ ከሰሙ ወይም ራሳቸው ለሚያቅራራው ሰው ግጥም ከሰጡ በኋላ ህሊናቸውን መቆጣጠር ያቅታቸዋል፡፡ ከዚያም፤
ዘራፍ ዘራፍ ዘራፍ
የኮስትር አሽከር የባለ ውሉ
ዓይኑ መነጠር ጠበንጃው ስሉ፡፡
በማለት ዘለው እፉከራ ውስጥ ይገባሉ። እንግዲህ በዚህን እጅግ ስሜታዊና ድራማዊ በሆነው የቀረርቶና ፉከራ ክዋኔ ጊዜ ነው ገበሬው ሆዱንና ልቡን ሲያብሰለስለው የኖረውን ውስጣዊ ብሶት፣ ቅሬታውንና ንዴቱን በሚመስጥ ግጥም የሚገልፀው፡፡ በዚህን ጊዜ ነው በድብቅ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆየው የኮሚቴዎች፣ የቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ የመንግስት ወኪሎች፣ ባካባቢው የተከሰቱ የርስበርስ ግጭቶችና የዘመኑ ዐበይት ችግሮች በሙገሳም ሆነ በትችት መልክ በግጥም የሚወጡትና የሚስተጋቡት። በተለይ በመንግስት አስተዳደራዊ ለውጥ ወቅት የግጥሞቹ ፖለቲካዊ ፋይዳ ጐልቶ ይታያል፡፡ እላይ ወደተነሳንበት የመሬት ጉዳይ እንመለስና እስቲ የሚከተሉት አሥር ግጥሞች የሚያነሷቸውን ጉዳዮች በጥሞና እንመርምር፡፡ ብዙዎቹ የቀረርቶና የፉከራ ግጥሞች ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ የእንጉርጉሮ ወይም የብሶት የሚባሉት ዓይነት ናቸው፡፡ ግጥሞቹ በ1989ዓ.ም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተደረገው የገጠር መሬት ሽግሽግ ፖሊሲ አፈፃፀምና በተለይ የሽግሽግ ፖሊሲው በገበሬው ሕይወት ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ገፅታ ይመለከታሉ፡፡
ወደ ግጥሞቹ እንመለስና የመጀመሪያው ግጥም መሬቱ የተወሰደበት ገበሬ ያቅራራው ነው። ገጣሚው ከመንግስት አገዛዝ፣ ከመሬት ሥሪት፣ ከግብር እና ከመዋጮ ጋር የተያያዙ ሦስት ታሪካዊ እውነታዎችና የመንግስት አገዛዞች ያነፃፅራል። የመጀመሪያው ግጥም በአፄው ዘመነ መንግስት የነበረውን የ “አስራት” ክፍያ እና በደርግ አገዛዝ የነበረውን እህል በግዳጅ የመነጠቅን ወይም “ኮታ”ን “አረፍሁ” ብሎና ተስፋ አድርጎ የነበረው ገበሬ፣ በዘመነ ኢህአዴግ “የኮር አባል” የሚባል ካድሬና ከበፊቶቹ “የባሰ ቀማኛ” መጥቶ መሬቱን በመጫኛ ሰፍሮ እንደወሰደበት ምሬቱን ይገልፃል፡፡
ሁለተኛው ግጥም ደግሞ ይኸው የኮር አባል የሚባለው የኢህአዴግ ባለስልጣን የገጠሩን ህዝብ እንዴት እንዳሰቃየው ገጣሚው ባካባቢው ከሚገኝና “ኮር/ች” ከሚባል እሾኻማ እንጨት ጋር በማነፃፀር በተለዋጭ ዘይቤ ያመሳስለዋል። የኮር አባላት በመሬት ሽግሽጉ ወቅት ገበሬውን በማንገላታት፣ እርስ በርስ በማጋጨትና መሬቱን በመውሰድ፣ለኢህአዴግ መንግስት ታማኝነታቸውን ያስመሰከሩ “የቁርጥ ቀን ልጆች” ናቸው፡፡ እነዚህ የኮር አባላትም ለአገሩ መፍረስ ተጠያቂዎች እንደሆኑ ግጥሞቹ ያመለክታሉ፡፡
አሥራት ቀረ ብዬ አርፌ ስተኛ
ኮር ቀረ ብዬ አርፌ ስተኛ
የኮር አባል መጣ የባሰው ቀማኛ
መሬቴን ወሰደው ሰፍሮ በመጫኛ፡፡

ጣሊያን አልመጣብን ተኩስ አልተተኮሰ
ወይ ወራሪ አልመጣ ችግር አልደረሰ?
በኮር የተነሳ አገሩ ፈረሰ፡፡

ወትሮም ነገረኛ ነበር ተጥንት
ኮር ነው ያስቸገረን ጠማማው እንጨት፡፡

እኔስ አርስ ነበር የገበሬው፣ የገባሩ ልጅ
መሬቴን ቢለኩት ቢወስዱት ነው እንጅ፡፡
ቀጥሎ የቀረቡት ሁለት ረዣዥም ግጥሞች ደግሞ መሬታቸው በኢህአዴግ ካድሬዎች በግድ የተወሰደባቸው የምስራቅ ጎጃም ገበሬዎች የደረሰባቸውን አሳዛኝ ግፍና ኢሰብአዊ በደል ባጠቃላይ ለአገራቸው ለጎጃም ህዝብ በተለይ ደግሞ ባካባቢያቸው ለሚኖሩ የማቻክል፣ የጎዛምን፣ የበረንታ የጥላትግን፣ የእነሴ፣ የጎንቻ፣ የሳር ምድር፣ የአዋበል እና የአነደድ ወረዳዎች ወገኖቻቸው አቤት ይላሉ፣ ጩኸታቸውንና ጥልቅ ኀዘናቸውን ያሰማሉ።
ይታይህ ማቻክል ይሰማህ ጎዛምን
ይታይህ በረንታ ይሰማህ ጥላትግን
እግዚዎ በል እነሴ ጎንቻና ሳር ምድር
እግዚዎ በል አዋበል እግዚዎ በል አነደድ
እንዴት ይወሰዳል መሬታችን በግድ?
ወይ! አገሬ፣ ኧረ! አገሬ ጐጃም
ወሰዱት መሬቴን እርስትና ጉልቴን
የራብ መከልከያ ልብስና ቀለቤን
አያቴ፣ ቅማቴ እስተምንጅላቴ
የወጣሁበትን፣ የገባሁበትን
ገብሬ፣ ቀቅዬ የኖርሁበትን
ወሰዱት መሬቴን ሰፍረው በገመድ
ተእንግዲህ ደካማው ተእንግዲህ አሮጉ
ኧረ! ወዴት ልግባ ኧረ! የት ልሂድ
ገበሬዎቹ ከአያት ቅድማያቶቻቸው የወረሱት የመሬት ይዞታቸው በመነጠቁ የመኖር ህልውናቸው እንዳከተመና እንደሞቱ ያህል ሆኖ ይሰማቸዋል። ከመጀመሪያው ግጥም እንደምንረዳው ላንዱ ገበሬ ያባቱ ባድማ መወሰድ የሞት ያህል ሲሰማው፣ ሌላው የመሬቱ መወሰድ፣ በመሬት እጥረት ምክንያት ወደፊት ሊደርስ የሚችለው የረሃብ አደጋ ያስጨንቀዋል፡፡ ሦስተኛው ገበሬ ደግሞ በኢሕአዴግ ያገዛዝ ዘመን ላይ እሮሮውን ያሰማል። እንደገጣሚው ዋይታ በ “ዘመነ ወያኔ” መሬቱ ስለተወሰደበት “ልጆቼን ምን ላብላቸው”፣ በምን ላሳድጋቸው” እያለ ብሶቱን ያሰማል፡፡ ሌላው ተስፋ የቆረጠ ገበሬ ደግሞ ከነጭራሹ በሮቹም እንደመሬቱ እንይወሰዱበት በስጋት “በሮቼን አምጡልኝ አርጄ ልብላቸው…” በማለት የኢሕአዴግ ካድሬዎችና የቀበሌ ተመራጮች ያደረሱበትን ሰቆቃና በደል ለዘመዶቹ ያዋያል፡፡
አልሞተ መስሎታል እሬሳው አልወጣ
ያባቱን ባድማ ሲካፈሉት በእጣ፡፡
ተዘንድሮው እራብ የከርሞው ይብሳል
መሬቱ ተወስዶ ምኑ ይታረሳል?
ዘመነ ወያኔ ዘመነ ኢሕአዴግ
መሬቴ ተወስዶ ልጅ በምን ላሳድግ
በሮቼን አምጡልኝ አርጄ ልብላቸው
ደሞ እንደ መሬቱ ሳይቆራርጧቸው፡፡
(PROCEEDINGS OF THE XIV INTERNATIONAL CONFERENCE OF ETHIOPIAN STUDIES
November 6-11,2000, Addis Ababa (IN THREE VOLUMES) VOLUME 3 ገፅ 2045- 2064)

Read 4898 times