Saturday, 05 October 2013 11:05

ኤዲፐስ

Written by  ሃምልተን እንደፃፈችው ሌሊሣ ግርማ እንደተረጐመው
Rate this item
(3 votes)

                       ይህን ታሪክ በጥሩ ሁኔታ የተረከው ሶፎክልስ ነው፡፡ ትረካው ለመድረክ ቴአትር እንዲሆን የተቀናበረ ነበረ። ሶፎክልስ በ5ኛው ክ.ዘ (2500 ከክርስቶስ ልደት በፊት) የኖረ ባለቅኔ ነው። የግሪክ ጀግኖችን አፈ - ታሪክ በአፉ እያዜመ በማቅረብ የመጀመሪያው ሆመር ነው፡፡ ሆመር ከክርስቶስ ልደት በፊት አንድ ሺ አመታት ቀድሞ ይኖር የነበረ አይነ ስውር ገጣሚ ነው፡፡
የቴብስ ገዢ የነበረው ንጉስ ላየስ፤ የካዲመስ ዘር ሐረግ ሶስተኛ ትውልድ ነው፡፡ የሩቅ ዘመዱ የሆነችውን ጆካስታ የምትባል ሚስት አግብቶ ይኖር ነበር፡፡ በንጉሱ ላየስ የግዛት ዘመን፣ የአማልክቱ አፖሎን ቃል ተናጋሪ የሆነችው የዴልፒ ኦራክል (ሴት አድባር) በንጉሱ ቤተሰብ ላይ ወሳኝ ሚና ባትጫወት ታሪኩ ልብ አንጠልጣይ አይሆንም ነበር፡፡
እንደሚታወቀው፤ አፖሎ “የእውነት” አማልክት ነው፡፡ እናም በዴልፒ (የአድባሯ መቀመጫ) የተተነበየው ንግርት ያለ ጥርጥር መድረሱ የማይቀር ነው፡፡ ስለሆነም፤ የተነገረ ትንቢትን አቅጣጫ ለማስለወጥ ወይንም ለመቃወም መሞከር…ዋጋ ቢስ ነው፡፡ ከእጣ ፈንታ ግድግዳ ጋር ለመላተም ካልሆነ በቀረ፡፡
ቢሆንም፤ አድባሯ ለንጉስ ላየስ “በራስህ የበኩር ልጅ እጅ ትሞታለህ” ብላ መጥፎውን እጣ ፈንታውን ስታረዳው፣ አሜን ብሎ መቀበል ስላልቻለ ትንቢቱን ለመለወጥ…ለመቃወም ሞከረ፡፡ መሆኑ አይቀሬ የሆነውን ….መሆን የለበትም በሚል፡፡
የንግርቱ መንስኤ የሆነው ህፃን ወንድ ልጅ ሲወለድ… እግር እና እጁን ጥፍር አድርጐ አስሮ፣ ከግዛቱ ውጭ አርቆ በተራራማ ስፍራ እንዲጣል፣ ተጥሎም እንዲሞት ንጉስ ላየስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ይሄ ከተከናወነ በኋላ ምንም የሚያስፈራው ነገር አልነበረም፡፡ ከዚህ ድርጊቱ በኋላ ከአማልክቱ የበለጠ የእሱ መጪ እጣ ፈንታ ወለል ብሎ ታየው። ሞኝነቱ እንጂ የሚገጥመው አበሳ እቤቱ ደጃፍ የሚመጣው በተለየ መንገድ ነው፡፡
ንጉሱ መሞቱ አልቀረለትም ተገደለ፡፡ ግን የተገደለው በመንገድ ላይ እየተጓዘ በወንበዴዎች እጅ በመሆኑ፣ ከእጣ ፈንታው ያመለጠ መሰለው። ጥቃቱን የሰነዘረበት ወንበዴ በመሆኑ፣ አማልክቱ አፖሎ የተናገረው ንግርት እንዳልተሳካ ተቆጠረ፡፡ ነገር ግን ከንጉስ ላየስ ሞት የተረጋገጠው የአማልክቱ ቃል ጠብ እንደማይል ነው፡፡
በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ የሞተው ከቤቱ በጣም ርቆ ስለነበር፣ በተጨማሪም በንግርት ምክንያት እንዲጣል የተደረገው ህፃን ከሞተ እና ከተረሳ ብዙ አመታት አልፎታል ተብሎ ስለታመነ …የገዳዩን ማንነት የጠረጠረ ማንም አልነበረም፡፡
ንጉሱ እና ባለሟሎቹ ሲገደሉ፤ ከመሀላቸው አንድ ሰው ብቻ ህይወቱን አትርፎ ወደ ንጉሱ ግዛት መጥፎውን ዜና ይዞ ተመለሰ፡፡ የንጉሳቸውን አሟሟት በጥንቃቄ ለመመርመር በከተማው የሚኖር ሰው፤ ምንም ተነሳሽነት ወይንም ፋታ አልነበረውም። በወቅቱ የከተማውን ነዋሪ ደህንነት የሚያሸብር አንድ አውሬ ነበርና…ለአውሬው የሚሰጠው አትኩሮት ከፍ ያለ በመሆኑ፣ ለንጉሱ እና ባለሟሎቹ የገጠመው መጥፎ እጣ ፈንታ በቀላሉ ለመረሳት ቻለ፡፡
የከተማው ነዋሪን ሰላም ማሸበሩ የሚወራለት አውሬ፣ “ሲፊንክስ” ተብሎ የተሰየመ ሰውነቱ የአንበሳ የመልኩ ደግሞ የሴት ገጽታ ያለው መሆኑ ይነገራል። ለመንገድ ተጓዦች ትልቅ ሽብር የምትፈጥረዋ እቺ አውሬ፤ እስክትወገድ የቴብስ ከተማ ሰባቱ ትልልቅ በሮች ተዘግተው፣ በረሃብ ማለቅን ነዋሪዎቹ የመረጡበት ወቅት ነበር፡፡ ይህች አውሬ ያጋጠማትን ሰው ገድላ ከመመገቧ በፊት የእንቆቅልሽ ጥያቄ ታቀርብለታለች፡፡ እንቆቅልሹን መመለስ የቻለ ግን ማንም የለም፡፡ የጥያቄው አማራጭም የሚያመራው ወደ ሞት ነው፡፡
ነገራት በዚህ የውጥረት ደረጃ እንዳሉ፣ አንድ እንግዳ የሆነ ወጣት ድንገት በስፍራው ይከሰታል። ወጣቱ በጥንካሬ እና ልበ ሙሉነት የተሞላ፣ አእምሮውም እንደ አካላቱ የቀለጠፈ ወጣት ነው። ስሙ ኤዲፐስ ተብሎ ይጠራል፡፡ ወጣቱ ኤዲፐስ የቆረንጦስ ግዛት ከሚኖር ፖሊበስ ከተባለ ንጉስ የሚወለድ ቢሆንም አገሩን ትቶ በመሸሽ ላይ ሳለ ነው ቴብስ የደረሰው፡፡ አገሩን ጥሎ የተሰደደው በአንድ ትንቢተኛ የወደፊት እጣ ፈንታው ተነግሮት ነው፡፡
“አባትህን ንጉሱ ፖሊበስን የምትገድለው አንተ ነህ” የሚል ነው ትንቢቱ፡፡
ላየስ የተባለው ንጉስ የወሰደውን አማራጭ ወስዶ፣ እጣ ፈንታውን በመሸሽ ከቦታ ቦታ እየተንከራተተ ለመኖር ልዑሉ ኤዲፐስ ቆረጠ። ጓደኛና ሀገር የሌለው ሰው በመሆኑ፣ በህይወት ለመኖር ያለው ፍላጐት የመነመነ ነበር፡፡ በመሆኑም፤ ሰውን እየፈጀ ስላለው አውሬ (ሲፊንክስ) ሲሰማ ለመግደል ይነሳሳል፡፡
አውሬውን ፈልጐም ያገኘዋል፡፡ ሲፊንክሷ ኤዲፐስ ላይ ጉብ ከማለቷ በፊት የተለመደውን ጥያቄዋን አቀረበችለት፡፡ የእንቆቅልሹ ጥያቄ እንደሚከተለው ነው፡፡
“ጠዋት በአራት እግሩ ይሄዳል፤ እኩለ ቀን ላይ በሁለት እግሩ ይራመዳል፤ ወደ ምሽት ገደማ ደግሞ በሦስት እግሩ ይሄዳል ይህ ፍጥረት ምንድን ይባላል” አለችው፤ አውሬዋ፡፡
“የሰው ልጅ” ብሎ ኤዲፐስ መለሰላት፡፡ “በልጅነቱ በአራት እግሩ እና እጁ ይድሐል፡፡ አዋቂ ሲሆን በሁለት እግሩ ቀጥ ብሎ ይራመዳል፡፡ ሲያረጅ በምርኩዝ ተደግፎ ይጓዛል”
ኦዲፐስ ለአውሬዋ የሰጣት ትክክለኛ መልስ ነበር፡፡ ግማሽ የአንበሳ እና ግማሽ የሴት ገጽታ ያላት እቺ አውሬ፤ ባልታወቀ ምክንያት ተበሳጭታ…በዛው ቅጽበት ራሷን አጠፋች፡፡ የቴብስ ግዛት ነዋሪዎች ከሰቆቃቸው ተረፉ፡፡ ኤዲፐስ ከጠበቀው በላይ ብዙ ነገር አገኘ፡፡ የተደሰቱት የግዛቱ ነዋሪዎች በሞተው ንጉሳቸው ላየስ ፋንታ በዙፋን ላይ አስቀመጡት፡፡ የሞተውን ንጉስ ትዳር እና አልጋ ትጋራ የነበረችውን ንግስት ጆካስታንም አገባ። ለብዙ አመታትም በደስታ ኖሩ፡፡ በዚህ የታሪኩ የሂደት ደረጃ የአማልክቱ አፖሎ ትዕንቢት ሳይሳካ የቀረ ይመስላል፡፡ በዚህ የሰላም እና የደስታ ዘመናት ሂደት፣ ንጉሱ ኤዲፐስ እና ሚስቱ ጆካስታ የወለዷቸው ሁለት ወንድ ልጆች አድገዋል፡፡
ከእለታት በአንዱ ቀን ቴብስ በድንገተኛ ወረርሽኝ ተመታች፡፡ ሰዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ከብትና የቤት እንስሶች… ተክል እና አዝርዕት በአንድ ላይ መርገፍ ጀመሩ፡፡ በበሽታው ያልረገፉት በረሃብ ተቀጠፉ፡፡ በዚህ ድንገተኛ መከራ ከንጉሱ ከኤዲፐስ በላይ ግን የተሰቃየ የለም፡፡ ኤዲፐስ ራሱን የግዛቱ አባት አድርጐ ስለሚቆጥር፣ በሀገሩ ህዝብ ላይ የነጋው የጨለመ ቀን የእርሱም ነበር፡፡ የሚስቱን የጆካስታን ወንድም ቻሮንን ወደ ዴልፒ የቀሳውስቱ መቅደስ አምላክን እንዲለማመን ሰደደው፡፡ ቻሮን ጥሩ ዜና ይዞ ተመለሰ፡፡ አማልክቱ አፖሎ “ወረርሽኙ የሰፈነው በአንድ ምክንያት ብቻ ነው” ሲል መልስ ላከ፡፡ ምክንያቱም ተገለፀ፡፡ የንጉስ ላየስ ገዳይ በግዛቷ ውስጥ አለ፡፡ የሟቹን ንጉስ ገዳይ በመቅጣት ብቻ ወረርሽኙ እንዲገታ ማድረግ ይቻላል፡፡ ኤዲፐስ በተሰጠው ምላሽ ከመጠን ያለፈ ተደሰተ፡፡ ተንፈስ አለ፡፡
ንጉሱ ላየስ ከሞተ ብዙ አመታት ቢያልፍም፣ ገዳዩን አፈላልጐ ለማግኘት እንደማይቸገር እርግጠኛ ነበር፡፡ ነፍሰ ገዳዩን ካገኘው ደግሞ እንዴት አድርጐ እንደሚቀጣው ያውቃል፡፡ በንግስቷ ወንድም ቻሮን አማካኝነት የደረሳቸው መልዕክት ለግዛቱ ነዋሪ እንዲነገራቸው ኤዲፐስ አዘዘ፡፡
ማንም ሰው ለዚህ ወንጀለኛ መጠለያ አይስጥ
እንደተረገመ፣ በተስቦ እንደተመታ ባለደዌ
ከቤታችሁ እንዳይገባ አርጉት
የንጉስ ላየስ ገዳይ ሆይ!
በእርኩስ የተከበብክ የረከስክ ለዘላለም ሁን!
ኤዲፐስ፤ የንጉስ ላየስን ገዳይ ለመያዝ በጽኑ ፍለጋ ራሱን ጠመደ፡፡ ቴሪሳያስ ተብሎ የሚጠራውን አይነ ስውር ነብይ ወደ እርሱ ይመጣ ዘንድ ላከባት፡፡ ቴሪሳያስ፤ በመላው ቴብስ የተከበረ ነብያቸው ነው። የሚያውቀውን ይገልጽለት ዘንድ “የንጉሱ ገዳይ ማነው?” ሲል ጠየቀው፡፡ ይግረምህ ሲለው፤ አዋቂ ተብዬው ነብይ፣ በመጀመሪያ መልስ ከመስጠት በእንቢታ ታቀበ፡፡
“የምታውቀው ነገር ካለህ ስለ ፈጣሪ ፍቅር ስትል የጠየቅሁህን ንገረኝ” ሲል ኤዲፐስ ነብዩን ተማፀነው፡፡
“ቂሎች” ሲል ነብዩ ገነፈለ፡፡ “ሞኞች ናችሁ ሁላችሁም፤ ለእናንተ መልስ አልሰጥም”
ኤዲፐስ፤ የንጉሱን ገዳይ እያወቀ አለመናገሩ ከወንጀሉ ጋር ተባባሪ እንደሚያደርገው ነብዩን አስፈራራው…
“አንተ ራስህ ነህ የምትፈልገው ነፍሰ ገዳይ” ብሎ መለሰለት፤ ተበሳጭቶ፡፡
የአይነ ስውሩ ነብይ ንግግር ለኤዲፐስ እብደት ነበር፡፡ ከፊቱ ዞር እንዲል እና ዳግመኛም ሊያየው እንደማይሻ ነግሮት ከቤተመንግስቱ አባረረው። ንግስቲቱ ጆካስታ፤ የአይነ ስውሩን ንግግር የቀበለችው በትምክህት ነው፡፡
“አፈ አማልክቶቹም (የዴልፒ አድባሮችም) ሆኑ ነብያቶቹ ምንም አይነት እውቀት የላቸውም”
ስትል ደመደመች፡፡
ለንጉስ ኤዲፐስ ስለሞተው የቀድሞ ባሏ አጫወተችው …ስለ ንጉስ ላየስ፡፡ “በዴልፒ የሚገኙት የአፖሎ ትንቢት ተናጋሪዎች ‘በወለድከው ልጅህ እጅ ትሞታለህ’ ቢሉትም፤ ንጉስ ላየስ ይህ ንግርት እንዳይፈፀም ማድረግ ችሏል፡፡ አባቱን ይገድላል የተባለውን ህፃን ከማደጉ በፊት እንዲጣል እና እንዲሞት አስደረገ፡፡
ንጉስ ላየስ ግን ባልጠበቀው ሁኔታ በወንበዴዎች እጅ ወደቀ፡፡ ሶስቱ መንገዶች ወደ አንድ በሚገጥሙበት የዴልፒ ጥርጊያ ላይ ነው የሞተው፡፡ በትንቢቱ መሰረት ሳይሆን በአጋጣሚ ነው…” በማለት ወጓን በድል አድራጊነት መንፈስ አጠናቀቀች፡፡
“መቼ ነው ይህ ክስተት የተፈፀመው?” ብሎ ጠየቃት ኤዲፐስ፤ ልዩ በሆነ እይታ እያተኮረባት፡፡
“ልክ አንተ ወደ ቴብስ ከመምጣትህ ትንሽ ቀድሞ ብሎ”
“ላየስ ሲገደል አብረውት የነበሩ ሰዎች ቁጥር ስንት ነው?
“በአጠቃላይ አምስት ነበሩ” በፍጥነት መለሰች፤ ንግስቷ ጆካስታ “አራቱ ተገድለው አንድ ወሬ ይዞ የመጣ ሰው ብቻ ነው የተረፈው”
“ይህንን የተረፈ ሰው ወደኔ እንዲመጣ እፈልጋለሁ፤ አስፈልጊው እና ላኪልኝ”
“በአስቸኳይ እንዳልከው አደርጋለሁ፡፡ ግን ምን አስበህ ልታስጠራው ፈለግህ?”
“እኔ የማውቀውን ሁሉ ታሪኬን እንድታውቂ ስለምፈልግ አድምጪኝ፡፡ ወደ ቴብስ ከመምጣቴ በፊት ወደ ዴልፒ ተጉዤ ነበር፡፡ የተጓዝኩበት ምክንያት በልዑልነት ዘመኔ ያገኘሁት አንድ ሰው የንጉስ ፖሊበስ ልጅ እንዳልሆንኩ ነግሮኝ ግራ በመጋባቴ ነው፡፡
አማልክቱን በዴልፒ ሳነጋግረው የመለሰልኝ የጠየቅሁትን አልነበረም፡፡ በጠየቅሁት ፈንታ… ‘አባትህን ገድለህ እናትህን ታገባለህ፤ ልጆችም ትወልዳለህ፤ ከእናትህ የምትወልዳቸውም ልጆች ሰው ሊመለከታቸው የሚንገሸገሽ ይሆናሉ…’ አለኝ። ስለዚህም ወደ ቆሮንጦስ መመለስ አልቻልኩም። ከዴልፒ ተነስቼ በአንዱ ጐዳና ሳዘግም፣ አንድ ሰውዬ ከአራት ባለሟሎቹ ጋር መንገድ አገጣጠመን። መንገዱን ልቀቅ ብሎ ሰውየው በከዘራው መታኝ። በጣም ንዴቴ ገነፈለ…አራቱንም ገጠምኳቸው፡፡ …የገደልኳቸው ሰዎች መሪ ንጉስ ላየስ ሊሆን ይችላል?”
“ሁሉም አልሞቱም፤ አንድ ሰው ከመሃላቸው ተርፏል፡፡ ስለዚህ ላየስ ሊሆን አይችልም፡፡ ላየስ በዘራፊዎች ነው የተገደለው፡፡
በራሱ ልጅ እጅ አይደለም፡፡ ልጁንማ በተራራው ስፍራ ጥሎታል… እንዲሞት አድርጐታል” አለች ጆካስታ፡፡
አማልክቱ አፖሎ ሊሳሳት ይችል ይሆን? በሚል ጉዳይ ዙሪያ በመከራከር ላይ ሳሉ … ከቆረንጦስ የተላከ መልክተኛ መድረሱ ተነገራቸው። መልዕክተኛውም ገብቶ ንጉስ ፖሊበስ መሞቱን አረዳቸው፡፡
“እናንተ የአማልክቱ አፈ ቀላጤዎች” ብላ ጆካስታ ወደ ዴልፒ ጮኸች፡፡
“የታላችሁ! … የተናገራችሁት ሳይፈፀመ ቀረ! … ንጉስ ፖሊበስ ይሞታል ያላችሁት በልጁ እጅ ነበር። ላየስም ይሞታል ያላችሁት በልጁ እጅ ነው … ግን እንደ ቃላችሁ አልሆነም”
“አባቴን ከምገድል ብሸሽ ይሻላል ብለህ ነው ከቆረንጦስ ግዛት የጠፋኸው?” ለኤዲፐስ ጠየቀ መልዕክተኛው፡፡
“አዎን” መለሰ ኤዲፐስ፡፡
“ኦ ንጉስ! ተሳስተሀል፡፡ ለመሸሽ ምክንያትም አልነበረህም፡፡ ምክንያቱም፤ አንተ ኤዲፐስ የፖሊበስ ልጅ አይደለህም፡፡ እንደ ልጁ አድርጐ አሳደገህ እንጂ ልጁ አይደለህም፡፡
አባትህን ትገድላለህ፤ ብለው በቆረንጦስ እያለህ ትንቢት ቢነግሩህም… ፖሊበስን ትገድላለህ ማለታቸው አልነበረም፡፡ ፖሊበስ አንተን በጨቅላነትህ የተቀበለው ከእኔ እጅ ነው፡፡ እኔ ነኝ መጀመሪያ ተጥለህ አግኝቼህ ያነሳሁህ” አለ መልዕክተኛው፡፡
“ከየት ቦታ ነው መጀመሪያ ያነሳኸኝ?” ብሎ ጠየቀው ኤዲፐስ “ማናቸው አባት እና እናቴ?”
“እኔ ስለ እናት እና አባትህ ማንነት የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ አንድ እረኛ አንስቼው ነው ብሎ ሰጠኝ… እኔም ተቀበልኩት፡፡ እረኛው የንጉስ ላየስ አሽከር ነው”
የጆካስታ ፊት በድንገት ነጭ ሆነ፡፡ ለመግለጽ የሚከብድ ድንጋጤ በውስጧ ተሰራጭቷል፡፡
“ለምን ይሄ አይነት አልባሌ ሰው የሚነግርህን ትቀበላለህ?” ብላ ጮኸች፡፡ “እሱ የሚናገረው ምንም አይነት ነገር ለኛ ጥቅም የለውም” የምትናገረው በፍጥነት ነው፡፡ በፍጥነት እና በሚያስፈራ አኳኋን፡፡ ኤዲፐስ ሊገባው አልቻለም፡፡
“ከዚህ የበለጠ በጥያቄህ አትግፋ” አለችው ጆካስታ፡፡ “እስካሁን የተሰቃየሁት ይበቃኛል” … ድንገት በቆሙበት ጥላቸው ወደ ቤተመንግስቱ ውስጠኛ እልፍኝ ሮጠች፡፡ ልክ በዚሁ ቅፅበት አንድ ሽማግሌ ይገባል፡፡ ኤዲፐስ እና የቆሮንጦሱ መልዕክተኛ እርስ በርስ ተያዩ፡፡ “ይሄ ሰውዬ ራሱ ነው!” ብሎ መልዕክተኛው ወደ ሽማግሌው እየጠቆመ ጮኸ፡፡
“አንተን አምጥቶ በእጄ ያሳቀፈኝ እረኛ እሱ ነው!”
ኤዲፐስ ሽማግሌውን ጠየቀው:- “አንተስ ጨቅላውን የሰጠኸው ሰው ይሄ ነው” ወደ መልዕክተኛው እየጠቆመ፡፡
“ትተዋወቃላችሁ?”
መልዕክተኛው በጉጉት “ታስታውሳለህ… ከብዙ አመታት በፊት አንድ ህፃን ልጅ አግኝተህ … ሰጥተኸኝ ነበር፡፡ … ያ ልጅ ነው ይሄ ከፊትህ የቆመው ንጉስ… ኤዲፐስ፡፡”
“የተረገምክ ሁን!” ሽማግሌው አምባረቀ፤ በመልዕክተኛው ላይ፡፡ “አፍህን መዝጋት አትችልም?!”
“ምን!” አለ ኤዲፐስ፡፡ ግልፍ ብሎታል፡፡ “እኔ ለማወቅ የምፈልገውን ማንነቴን እርስ በርስ ተሻርካችሁ ልትሸሽጉኝ የምትችሉ ይመስላችኋል? … አላወጣም ካላችሁ እውነቱን … እንድታወጡ ማድረጊያ ዘዴዎች አሉ!”
ሽማግሌው ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ “እባክህን ንጉስ ኤዲፐስ አትጉዳኝ፡፡ ህፃኑን ወስጄ ሰጥቼዋለሁ። … ግን ከዚህ የበለጠ እንድነግርህ ስለ እግዜር ፍቅር ብለህ አትጠይቀኝ”
“በድጋሚ እንድትነግረኝ ባዝህ … ያልቅልሀል” ኤዲፐስ ዛተ፡፡
“እመቤቲቱን (ንግስቲቱን) ጠይቃት፤ እሷ ልትነግርህ ትችላለች”
“እሷ ናት ህፃኑን እንድትጥል የሰጠችህ?”
“ህፃኑን እንድገድል ነበር የተላኩት፡፡ በንግርቱ ምክንያት፡፡”
“ህፃኑ አባቱን ይገድላል የሚል ንግርት?” ኤዲፐስ ጠየቀ፡፡
“አዎን”
ከኤዲፐስ አፍ ማቃሰት የመሰለ ትንፋሽ አፈተለከ፡፡ በመጨረሻ ሁሉም ነገር ተገለጠለት፡፡
“ሁሉም እውነት ሆነ! … እኔም የተረገምኩ ነኝ! … ከእንግዲህ ብርሐንን ለማየት አልሻም፡፡ ብርሐንም ለኔ ወደ ጨለማ መቀየር አለበት”
ምንም
መፍትሄ አልነበረውም፡፡ ሁሉም ትንቢት እንደተባለው ደርሷል፡፡ ኤዲፐስ አባቱን ገድሏል። የአባቱን ሚስት እናቱን አግብቷል፡፡ ለእሱም ሆነ ለልጆቹ ምንም መፍትሄ የለም፡፡ ሁሉም የተረገሙ ናቸው፡፡
በቤተመንግስቱ አንድ ጥግ ኤዲፐስ ንግስቷን (እናቱን እና ሚስቱን) አገኛት፡፡ ሞታለች፡፡ እውነቱ ሲገለፅላት ራሷን አጥፍታለች፡፡
ከሞተችው ሚስቱ እና እናቱ ጐን ቆሞ ኤዲፐስም በራሱ ላይ እጁን ለቅጣት አነሳ፡፡ ነገር ግን፤ ቅጣቱ እንደ ሚስቱ ህይወቱን መቅጠፍ ሳይሆን … ብርሐኑን ወደ ጨለማ መቀየር ነበር፡፡ አይኖቹን ደንቁሎ አጠፋ፡፡
የአይነ ስውርነት ጨለማ… ከአለም ፊት ራሱ መወሰሪያ … መሸሸጊያ ሆነው፡፡
“Better to be there than to see with strange shamed eyes the old world that had been so bright”

 

Read 2902 times