Saturday, 12 October 2013 12:53

የ“ብርሃን ፈለጎች” በ“ግራጫ ቃጭሎች” መንፈስ የተቃኘ ስራ

Written by  ቢላል ከስድስት ኪሎ
Rate this item
(1 Vote)

ከቅርብ ጊዜ ወደዚህ አዳዲስ እየወጡ ያሉ ወጥ የልቦለድ መጽሐፍት በንባብ ጥማት ለሚናውዘው የሃገራችን የስነ-ጽሑፍ አፍቃሪ በበረከትነት የሚታዩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም የወጣት ጸሐፍት ከመቼውም በተሻለ ሁኔታ ብቅ ብቅ ማለት የንባብ አቅርቦትን ከማሳደግ ባሻገር ልብን በሃሴት ይሞላል፡፡
ከወጣት ደራሲያኑ መካከል አለማየሁ ገላጋይን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ጋዜጠኛና ደራሲ መልካም ጅምር ሊባሉ የሚችሉ አዳዲስ የልቦለድ ስራዎቹን አከታትሎ እያሳተመ ይገኛል፡፡ በቅርቡ እንኳን “የብርሃን ፈለጎች” በሚል ርዕስ የጻፈውን ረጅም ልቦለዱን ለንባብ አብቅቷል፡፡ ይሄንን አዲስ መጽሐፍ የማንበብ ዕድሉ ስላጋጠመኝ ስራውን አስመልክቼ ሁለት ነገሮችን ለማለት ፈለግሁ፡፡ አንደኛው የገጸ-ባህሪያትን ቀረፃ ከተአማኒነት አንጻር መቃኘት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደሞ መጽሐፉ ከ”ግራጫ ቃጭሎች” ጋር የሚመሳሰልበትን ጎን በስሱ መዳሰስ ነው፡፡
የ“ብርሃን ፈለጎች” የተተረከበት አንጻር 1ኛ መደብ የሚባለው ነው፡፡ ዋናው ገጸ-ባህሪ ‹እኔ› እያለ ታሪኩን ያወጋናል፡፡ በመሰረቱ በአንደኛ መደብ ተራኪነት የሚቀረጹ ገጸ-ባህሪያት እንቅስቃሴያቸው ጥንቃቄ ያልተለየው ትኩረትን የሚሻ ነው፡፡ የዚህ መደብ ትርክት ጥሩና መጥፎ ጎንም ይኖረዋል፡፡ ‹እኔ› እያለ ታሪኩን የሚተርከው ገጸ-ባህሪ ራሱ የድርጊቱ ተሳታፊ ስለሆነ፣ ያየውንና የሰማውን በቀጥታ ለአንባቢው በማድረስ በኩል በሚኖረው ሚና ጥሩ ጎን አለው፡፡ በሌላ በኩል ግን ‹እኔ› እያለ የሚናገረው ገጸ-ባህሪ በሌለበት ቦታ የታሪኩን ሂደት ለማወቅ ይቸግራል፡፡ በተለይም ተራኪው አብይ ገጸ-ባህሪ ከሆነ፣ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ እንደሚባለው እሱን በተመለከተ የሚናገረው ነገርና የሚከውነው ድርጊት ሁሉ ለግነት የተጋለጠ ነው፡፡ ‹እኔ› እያለ የሚተርከው ገጸ-ባህሪ እንደ ሦስተኛ መደብ ተራኪ ሌሎቹ ገጸ-ባህሪያት በአይምሯቸው ምን እንደሚያስቡ ሊነግረን አይችልም፡፡ ምርጫው የደራሲው ቢሆንም፣ የተራኪ መደብ አመራረጡና የባህሪ ቀረጻው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊቸረው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡
‹‹…እያንዳንዱ የትረካ አኳያ የራሱ የሆነ ጠባይ አለው፡፡ ለምሳሌ ተራኪው ‹‹እኔ›› የሚል ከሆነ፣ ‹‹እኔ›› ባዩ ተራኪ የታሪኩ ድርጊት ተካፋይም ተመልካችም ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴ ‹‹እኔ›› ባዩ ተራኪ የታሪኩ ዋና ባለቤት ሊሆን የሚችልበት ጊዜ አለ፡፡ ታሪኩን ካየና ከሰማ፣ ከዚያም አልፎ በታሪኩ ድርጊት ቀጥተኛ ተሳትፎ ካለው ባለታሪክ አንደበት እውነቱን መስማት ስሜትን ይማርካል። በሌላ በኩል ስንመለከተው፣ ‹‹እኔ›› ባዩ ተራኪ የታሪኩ ዋና ባለቤት ከሆነ፣ አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገጥሙታል፡፡ አንደኛ፣ ተራኪው የታሪኩ ድርጊት ተሳታፊ እንደመሆኑ መጠን እርሱ በሌለበት ምንም ነገር መፈጸም አይችልም፡፡ ከዚህ የተነሳ ‹‹እኔ›› ባይ ተራኪ ስለራሱ ሞት ማውራት አይችልም። ሁለተኛው ችግር፣ ‹‹እኔ›› ባዩ ተራኪ፣ ስለራሱ ደግነት፣ ጀግንነት፣ አዋቂነት ቁንጅና ወዘተ. መናገር አይችልም፡፡ እንዲህ ያለው ንግግር እንደመመጻደቅና እንደ ጉራ ስለሚቆጠር አንባቢን ደስ አያሰኘውም።…›› (አማረ ማሞ፣ የልብ ወለድ ድርሰት አጻጻፍ መሠረታዊ መመሪያ፣ ገጽ 77-78)
የ“ብርሃን ፈለጎች” አንደኛ መደብ ተራኪ፣ መክብብ፣ በዕድሜው ልጅ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ የዚህን ገጸ-ባህሪ ስም ከረጅም የንባብ ጉዞ በኋላ እንድናውቅ የመደረጉ አግባብነት ለእኔ አይታየኝም፡፡ ቀደም ተብሎ ወይም በቅርብ አንባቢ እንዲያውቀው ቢደረግ ጥሩ ነበር፡፡) የሚከተሉት አባባሎች መክብብ ልጅ መሆኑን የሚያስረዱ ናቸው፡፡
የመክብብ እናት፣ ‹‹ልጅ ነው፤ ተፈነከተ፣›› ትላለች፡፡ (ገጽ 14)… ‹‹…እናቴ በእኔ ተናዳ አባቴ ሲመጣ አልጎመጎመችበት፡፡…›› (ገጽ 15) ራሱ መክብብ ደሞ በገጽ 16 ላይ እንዲህ ሲል እናነባለን፣ ‹‹…ቀሚሷን ፈልፍዬ ወሬውን ለመቋደስ ሞከርኩ።…››፣ አክስቱን፣ ‹‹…ጭኗን አንተርሳ ራሴን ታሻሸኛለች፡፡…›› ይላል፡፡ እድሜው ባይገለጽልንም በነዚህና በሌሎች መሰል አባባሎች መክብብ በጣም ልጅ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን፡፡
ባጠቃላይ ዋናው ገጸ-ባህሪ፣ መክብብ፣ በሚያዘወትረው ጨዋታ፣ በሚናገረው ንግግር፣ ከጓደኞቹ ጋር በሚያደርገው መስተጋብርና በመሳሰሉት ባህርያቱ፣ ልጅ መሆኑን መናገር አይከብደንም፡፡ ይሁን እንጂ፣ በመጽሐፉ በርካታ ቦታዎች ላይ እንደ ልጅ ሲያስብ፣ ሲናገርና አስተያየት ሲሰጥ አለመታየቱ የተአማኒነት ጥያቄን እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ መክብብ ከተፈጥሮ አቅሙ ወጣ ባለ ሁኔታ እንደ ትልቅ ወይም በእድሜ እንደገፋ፣ ሙሉና ብስል ሰው ነገሮችን ሲያነሳ እናያለን፡፡ ለምሳሌ በገጽ 96 ላይ ብላቴናው መክብብ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለ እንዲህ ይላል፣ ‹‹…ሒሳብን ለማወቅ ያን ያህል መጣር አልነበረብኝም፡፡ ውጤቱ ልፋት ነው፡፡ ቁጥር መካብ፣ ማፍረስ፣ መልሶ መካብ ለሕይወት ምን ጥቅም ይሰጣል? ምንም!›› አንድ በልጅነት ዕድሜ ላይ ያለ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ በዚህ ዓይነት በአስተማሪው ላይ ‹ይፈላሰፋል› ማለት ከተአማኒነት አንፃር ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ የብርሃን ፈለጎቹን መክብብ በተአማኒነትና በገጸ-ባህሪ የቀረጻ ሚዛን ውስጥ አስገብተን ብንመዝነው ጉድለቱ ከብዶ ይታየናል፡፡
መክብብ በገጽ 117 ላይ የሚከተለውን ጠንከር ያለ አባባል ሲናገር እናነባለን፡፡ ‹‹…ተሯሩጦ እራሱን የሚያስተዳድርን ባተሌ ሰንክሎ በቁስልና በረሃብ መቅጣት እንዴት ያለማነስ ምልክት ሊሆን ይችላል? እራሴን ጠላሁ ሰው መሆንን አነወርኩ፡፡…›› ሌሎች ብዙ ተጨማሪ መረጃዎችን ከየገፆቹ እያነሳን ማየት እንችላለን፡፡
‹‹…ይርገዱ ቂጦ ተፈጥሮ ሚዛኗን ስታ በተሳከረችበት አንድ ወቅት የተፈጠሩ ይመስለኛል።…›› (ገጽ 8) ‹‹…የእናቴ ለወይን ጠጅ የቀረበ ጥቁር ፊት ብዙ ቋንቋ አለው፡፡…›› (ገጽ 8) ‹‹…እንደ ክርስቶስ ሰምራ ሳልሞት ገሃነምን ያስጎበኘኝ ነበር፡፡…›› (ገጽ 65) ‹‹…የሰባተኛው ሰማይን የቅዳሴ ዕጣን ይተካከላል፡፡…›› (ገጽ 101) ‹‹…እንደሷ ያፈረሰ ቄስ መስዬ…›› (ገጽ 173) ‹‹…ቮልቴር የተባለ ታላቅ ሰው ትከሻ ላይ ሆኜ ያየሁት ፈጣሪ አልባ አለም አስደነገጠኝ፤…›› (ገጽ 172)፡፡ እነዚህን ንግግሮች የሚሰነዝረው ብላቴናው መክብብ ነው፡፡ መሰል በሰል በሰል ያሉ አባባሎችን አንድ በልጅነት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ የእውኑ ዓለም ሰው ይናገራል ብሎ ማሰብ በእጅጉ ይከብዳል፡፡ ልቦለድ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው አይደል የሚባል!
እውቁ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ የአንደኛ መደብ ተራኪን አስመልክተው፣ ‹‹..እያንዳንዱ ትእይንት የሚይዘው ራሱ አቢዩ ወይም ንኡሱ ገፀ-ባህርይ እና ወይም በወቅቱ የነበረ ምስክር ገፀ-ባህርይ ካየው ከሰማው፣ ከገባውና በልምዱ ከደረሰበት አንፃር ይሆናል፡፡…›› ይላሉ፡፡ (የጽሑፍ ጥበብ መመሪያ፣ ገጽ 303-304)
የ“ብርሃን ፈለጎቹ” ብላቴና፣ መክብብ፣ በአዲስ አበባ እምብርት ላይ ተወልዶ ያደገ ከተሜ እንደሆነ ከታሪኩ መረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም የሚጠቀምባቸው ቃላትና አባባሎች አንድ የእውኑ ዓለም የከተሜ ልጅ ያውቃቸዋል ወይም ይናገራቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት፡፡ ‹‹አለላ›› (ገጽ 6)፣ ‹‹እንደ ዕሳት ጅረት›› (ገጽ 6) ‹‹እየተግለበለበ›› (ገጽ 6)፣ ‹‹አንፋሽ አከንፋሽ›› (ገጽ 7)፣ ‹‹ወስከንቢያ›› (ገጽ 9)፣ ‹‹በለደለደ ስሜት›› (ገጽ 10)…
በ“ብርሃን ፈለጎች” ውስጥ መክብብ በቴስታ (የጭንቅላት ምት) የሚችለው የሌለ፣ በትግል ጎበዝ የሆነ፣ በአስተማሪው የሚደነቅ፣ ለከንፈር ወዳጅነት በልጃገረዶች የሚፈለግ፣ በገንዘብ አቅሙ ከሌሎች የተሻለ… ተደርጎ የተቀረጸ ገጸ-ባህሪ በመሆኑ፣ ለግነት ሊጋለጥ ችሏል፡፡ ‹‹…ከእኩዮቼ የሚችለኝ ጠፋ። የማያውቁትንና የማይማሩትን የድብድብ ስልት ተገበርኩባቸው፣…›› ይላል፡፡ (ገጽ 37) መክብብ በዚህ ዓይነት ስለራሱ መልካም ጎን አብዝቶ መናገሩ ልቦለዱን ወዳልተጠበቀ የቀረጻ ስህተት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡
ደራሲው፣ አለማየሁ ገላጋይ፣ መክብብን በዚህ መልክ የቀረጸው የእድሜውን የተፈጥሮ ያስተሳሰብ ደረጃ ግምት ውስጥ ሳያስገባና ግነት በጎላበት ሁኔታ ነው፡፡ እንደውም ያለአቅሙ የረቀቁ አስተሳሰቦችን አስታቅፎታል ማለት ይቻላል፡፡ ዘሪሁን አስፋው የገጸ-ባህሪን አቀራረጽ አስመልክተው እንዲህ ይላሉ፤ ‹‹…እያንዳንዱ ገጸባህሪ የሚናገረውና የሚሰራው በእውኑ አለም የኖረው ወይም የሚኖረው መሰሉ ከሚናገረውና ከሚሰራው ተቀራራቢ ሊሆን ይገባል፡፡ ገጸባህሪው ከእድሜው፣ ከትምህርቱ፣ ከኑሮ ደረጃው፣ ከመጣበት አካባቢና ዘመን ጋር የሚጣጣምና የዚህን ሁሉ አሻራ የሚያመለክት ድርጊት ከታየበት አንባቢው ሰው ነው ብሎ ሊቀበለው ይችላል፡፡…›› (የስነጽሁፍ መሰረታውያን፣ ገጽ 161) ስለዚህ ማንኛውም ገጸ-ባህሪ የሚናገረው ወይም የሚሰነዝረው ሃሳብና የሚያከናውነው ድርጊት ከእድሜው ያስተሳሰብ ደረጃ አንጻር የተቃኘ ሊሆን ይገባል፡፡
የ“ብርሃን ፈለጎች” ደራሲ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ዓይነት በልጅ አይምሮ ሊታሰቡ የማይችሉ ጉዳዮችን የተለያዩ የስነ-ጽሁፍ ቴክኒኮችን በመጠቀም መግለጽ ይችል ነበር፡፡ ለምሳሌ “አባቴ እንደነገረኝ… እናቴ ስትል እንደሰማሁት… ሬዲዮ ላይ የሚናገረው ሰውዬ እንዳለው…” በሚሉትና በሌሎች መሰል መግቢያዎች በሕጻን ልጅ የብስለት ደረጃ የማይታሰቡ ጉዳዮችን ማስተላለፍ ይቻላል፡፡
ደራሲ አዳም ረታ “የግራጫ ቃጭሎቹ”ን አብይ ገጸ-ባህሪ፣ መዝገቡን፣ ከልጅነት አቅሙ በላይ የሆነን ነገር ሲያናግረው፣ “ይባላል፣ ይላሉ፣ ይሆናል አሉ…፣” የሚሉ ዓይነት አባባሎችን ተገን አድርጎ ነው፡፡ ‹‹…እንደሰማሁትና እንዳነበብኩት አበበ ቢቂላ ትንሽ መንደር ውስጥ እረኛ ገበሬ ሆኖ ያደገ ነበር …የማራቶን ዕርቀት ከ40 ከ.ሜ ይረዝማል ይባላል፡፡›› (ግራጫ ቃጭሎች፣ ገጽ 76) ‹‹…ቀለበቱ የወለቀ እጅ ቦንብ እንደዚያ ሳይሆን ይቀራል? (እጅ ቦንብ ሁለት ጊዜ አይቻለሁ፡፡ አንድ ግዜ የከተማው ፖሊስ ሲያሳየን…›› (ግራጫ ቃጭሎች፣ ገጽ 118) መስመሮቹ የእኔ ናቸው፡፡ መዝገቡ ካለበት የልጅነት እድሜ አንጻር ነገሮችን እንዲናገር ሲደረግ ጥንቃቄ ባልተለየው ሁኔታ ነው፡፡ “እንደሰማሁት”፣ “እንዳነበብኩት”ና “ይባላል” የሚሉት አገላለጾች በገጸ-ባህሪ አቀራረጽ ረገድ ሊከሰቱ ከሚችሉ የተአማኒነት ችግሮች ደራሲውን አድነውታል፡፡ መዝገቡ ከመሬት ተነስቶ ስለ ቦንብ አያወራልንም። ይልቁንም በዚያች የልጅነት እድሜው ከሌሎች ያገኘውን ልምድ መሰረት አድርጎ ስለ ቦንብ ይተርክልናል፡፡ ‹…ሳይሆን ይቀራል…› በሚል አባባልና የነገሩትን ሰዎች በመጥቀሰ ስለማያውቀው ጉዳይ (ስለቦንቡ) ያጫውተናል፡፡
ደራሲ በእውቀቱ ስዩም የ “ግራጫ ቃጭሎች”ን የገጸ-ባህሪ ቀረጻ አስመልክቶ እንዲህ ይላል፤ ‹‹…አዳም [ረታ] ልጅነትን በልጅነት አእምሮ ሳይበረዝ ሳይከለስ ለማሳየት የሞከረ፣ ሞክሮም የተሳካለት ደራሲ ነው። ለምሳሌ መዝገቡ ‹የጀርመን ሬዲዮ› ሲባል ጀርመን ሃገር የተሰራ ሬዲዮ መሆኑን መዝግቧል፡፡ የአበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ መሄድ ከእንጀራ እናት በደል ምክንያት የመጣ መሆኑን ያውቃል፡፡ ገፀ-ባህሪው በጊዜው እንደተገለጠለት ሊያሳየን መሞከሩ ለአዳም አንድ ስኬት ነው፡፡…›› (ከአምባር› መጽሔት ቅጽ 01 ቁጥር 002 (ጥቅምት 1999) የተወሰደ፡፡)
ባጠቃላይ እንደኔ እንደኔ “የብርሃን ፈለጎች” መክብብ በደራሲው የተዘጋጀለትን የትልቅ ሰው ባህሪ ያለአቅሙ እንዲያጠልቅ የተፈረደበት ምስኪን ልጅ ነው፡፡ በራሱ አቅመ-ሃሳብ እንዲመላለስ አልተደረገም፡፡ ስለዚህም የደራሲው እስረኛ ሆኗል።
ወደ ሁለተኛው ጉዳዬ የምገባው፣ በእኔ አተያይ መሰረት፣ የ “ብርሃን ፈለጎች” የ “ግራጫ ቃጭሎች” በተቀዳበት ሽክና የተጨለፈ ‹ሌላ› ስራ መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡ የተጨለፈ ስል መንፈሱ ያረበበበት፣ ቃናው የተጋባበት፣ በ “ግራጫ ቃጭሎች” እርሾ የተቦካ… ለማለት ነው፡፡ “የግራጫ ቃጭሎቹ” መዝገቡና የብርሃን ፈለጎቹ መክብብ በልጅነት የእድሜ ዘመናቸው ላይ የሚገኙ በ1ኛ መደብ ተራኪነት የተቀረጹ ገጸ-ባህርያት ናቸው፡፡ ሁለቱም የብቸኝነትና የመሰልቸት ጣጣ ተጠቂዎች መሆናቸው ይታያል፡፡ ሁለቱንም አዘውትረው በሚጠቅሷቸው ዘፈኖቻቸውና ግጥሞቻቸው እናውቃቸዋለን፡፡ መክብብ፣ “አሆሆ ገዳማ ገደምዳማዬ፣… “ መዝገቡ ደሞ፣ “እያዩ አለማየት ሆነና ነገሩ፣…” በሚሉ ዓይነት እንጉርጉሮዎች ትረካቸውን ያሽሞነሙናሉ፡፡
በ”ግራጫ ቃጭሎች” ገጽ 5 ላይ መዝገቡ አባቱ አባት እንዳልሆነው፤ እናቱም እንደሞተችበት እናነባለን፡፡ “የብርሃን ፈለጎቹ” መክብብም እናቱን በልጅነቱ በሞት የተነጠቀ (በማይታወቅ ሁኔታ…በዱብእዳ ቢነገረንም…) አባቱም የአባትነት ሚናውን ያልተወጣና ከነአካቴውም ጥሎት የጠፋ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም አባቶች በሚስቶቻቸው አስገዳጅ ውቃቢ የተሸበቡ፣ የወላጅ ሃላፊነት ብዙም የማያሳስባቸው ሆነው እናያቸዋለን።
“የግራጫ ቃጭሎቹ” መዝገቡ እግዚአብሔርን ‹‹…እንደኔ ተቀምጦ ከማየት ሌላ ምን ሰራ?...›› (ገጽ 9) እያለ ሲያማርር፤ “የብርሃን ፈለጎቹ” መክብብ ደሞ በሚከተሉት ሁኔታዎች ፈጣሪውን ያማል፡፡ ‹‹…እግዚአብሔር አባቴን ይመስል እንዴት ዓለምና ፍጡሮቿን መለስ ብሎ ላያይ ኮበለለ? … ጥሎ ለመጥፋት ከሆነ ለየትኛው ደስታ እኛንና የዓለምን ጉድ ፈጠረ?...››፣ (ገጽ 166) ‹‹እግዚአብሔር ሰውን ለአእምሮው ሳይሆን ለሴጣን ትቶት ነው የሄደው፡፡…›› (ገጽ 169) ‹‹…ፈጣሪ አልባ አለም አስደነገጠኝ፤…››፤ (ገጽ 172)
በ“ግራጫ ቃጭሎች” ላይ መዝገቡ መጽሐፍ እንዲያነብ የሚገፋፋው ኤልያስ የተባለ የኢሕአፓ አባል አለ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም የኢሕአፓ አባል የነበረችና ሙና የተባለች መምህሩ የ “ብርሃን ፈለጎቹ” ን መክብብ የንባብ ልምድ ይኖረው ዘንድ ስታግዘው እናነባለን፡፡
መክብብ የሂሳብ መምህሩን፣ ሙናን (ገጽ 94)፤ መዝገቡ ደሞ (ገጽ 51-52) የእርሻና የእንግሊዝኛ መምህራኑን የመጥላታቸው አባዜ ሌላው ሁለቱን መጽሐፍት የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ነው፡፡
በሁለቱም መጽሐፍት ውስጥ የምናገኛቸው ገጸ-ባህሪያት በመሰልቸት የልጅነት ህይወታቸውን ሲገፉት እናያለን፡፡ ‹‹…ሁሌ አንደኛ መሆን አይሰለችም? …ሁሌ መምጣት አይሰለችም?...››፤ ‹‹…ሕልሜ ሰለቸኝ… ማሰቤ ሰለቸኝ… መማሬ ሰለቸኝ… በእግዚአብሔር መፈጠሬ ሰለቸኝ…›› የ “ብርሃን ፈለጎች” (ገጽ125 እና 207)
‹‹…ጠዋት፣ ከሰዓት፣ ማታ…ከሰኞ እስከ እሁድ…ሽሮ መብላት የሚወድ አለ? ይሰለቸኛል፡፡…›› ”ግራጫ ቃጭሎች” (ገጽ 5) መዝገቡ ጉብታው ላይ መቀመጥ የሚሰለቸው… ሰዉ፣ የሰዉ ንግግር የሚቸከው… በጥቅሉ ሁሉም ነገር አሰልቺ የሆነበት ልጅ ነው፡፡ ‹‹…ሲሰለቸኝ ወንዝ ወርጄ ታጠብኩ…›› (ገጽ 105)… ‹‹…እዚህ ከሰለቸኝ ለምን እዚያ አልሄድም…›› መዝገቡ (ገጽ 111)
በሌላም በኩል ሁለቱም ብላቴና ገጸ-ባህርያት አባቶቻቸው በእነሱ ላይ የሚያሳዩትን ጭካኔ በተመሳሳይ ሁኔታ ይገልጹታል፡፡ “የብርሃን ፈለጎቹ” መክብብ፣ ‹‹…አባቴ…እንደጭልፊት አንጠልጥሎኝ ወደ ላይ የበረረ ይመስለኛል፡፡ ምን እንዳደረገኝ ከትውስታዬ ውጭ ነው፡፡ ብቻ ወደ ዳመናው ይዞኝ ወጣ፡፡ ጉዟችን ወደ ሰማየ-ሰማያት ነው። ለፀሐይ ቀረብን መሰለኝ ብርሃን ዋጠኝ፣ ከፀሐይ አልፈን ሄድን መሰለኝ ጨለመ፡፡ ከዚህ የለቀቀኝ እንደሆነ መሬት ለመውደቅ ሰባት ቀን ሳይወስድብኝ አይቀርም፡፡…›› (ገጽ 15) ‹‹…እንደ ክርስቶስ ሰምራ ሳልሞት ገሃነምን ያስጎበኘኝ ነበር፡፡…›› (ገጽ 65) በማለት አባቱ እንዴት አድርጎ እንደሚቀጣው ይነግረናል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም የ “ግራጫ ቃጭሎቹ” መዝገቡ የአባቱን ጭካኔ አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹…የዚያን ማታ የገረመኝ ግን የአባቴ እጅ ነበር፡፡ የአባቴ እጅ ትልቅ ባለጡንቻና ባለሰንበር ነበር፡፡ በጥፊ ሲመታኝ 25 ጣቶች ያሉት ይመስላል። …ፊቴ ላይ ሲያርፍ ለአጭር ጊዜ በሚያቃጥል ጨለማ የተሸፈንኩ መሰለኝ፡፡ ጨለማው በቅፅበት አልፎ ቀያይ ከዋክብት አየሁ፡፡ ቢጫ ከዋክብትም አየሁ። ሐምራዊም አየሁ፡፡ …አልጋ በሚያክል እጁ ፊቴ ላይ መታኝ፡፡… ለረጅም ጊዜ ስንገዳገድ ቆይቼ ውሃ የተጣደበት የከሰል ማንደጃ ላይ በቁመቴ ወደቅሁ።… የትከሻዬና በከፊል የአንገቴ ቆዳ ተገፈፈ።…›› ”ግራጫ ቃጭሎች” (ገጽ 74)
ስነ-ጽሁፍን አስመልክቶ ለሚነሱ የተአማኒነት ጥያቄዎች ወይም ክርክሮች አሳማኝ የሆኑ ምላሾችን መስጠት እንደሚገባ በከፍተኛ የትምህርት ዘመኔ መማሬን አልረሳውም፡፡ በምሳሌ መልክም ይነሱ ከነበሩት የተአማኒነት ጥያቄዎች ውስጥ የ “ፍቅር እስከ መቃብሩ” ጉዱ ካሳ የብስለት ጉዳይ አንዱ ነበር፡፡ ይሄ በገጠር ተወልዶ ያደገው ጉዱ ካሳ የሚባል ገጸ-ባህሪ ካለው የትምህርት ደረጃ አንጻር (በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ አላለፈም) የሚያነሳቸው ‹ምሁራዊ› አስተሳሰቦች ትክክል ናቸው ወይ? ለሚለው የተአማኒነት ጥያቄ በምክንያትነት ይሰጡ ከነበሩት ምላሾች ውስጥ፣ ያለእድሜያቸው የሚወለዱ (ከብዙዎች አንዱ) መሰል ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚለው አንዱ ነው፡፡
“የብርሃን ፈለጎቹ” መክብብ የነዚህ ያለጊዜያቸው በስለው የሚወለዱት ዓይነቶቹ ሰዎች ይሆን? በስነ-ጽሁፉ ዓለም እንደሚነገረን፤ በስነ-ጽሑፋዊ ውይይት/ክርክር ወቅት ዋናውና ተገቢው አካሄድ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ተጨባጭ አስረጂዎችን እየደረደሩ ማሳመን መቻል ነው፡፡ ለዚህም ነው በተለምዶ በተጨባጭ ሁኔታ እመን ወይም አሳምን ወይም በሌላ አባባል There is no concord in literature የሚባለው፡፡
ያለበለዚያ፣ ‹‹…እንደ ብላቴናው ዳዊት የጠጠር ገድል ለመስራት…›› (ገጽ 22) የሚሉና ሌሎች ከፍልስፍና ወደዚህ ያሉ ዓይነት አስተያየቶችን ወይም ንግግሮችን የሚናገር እንደ ስንዝሮ ዓይነት የልጅ ገጸ-ባህሪ በድሮው የተረት ተረት መጽሐፍ ውስጥ ካልሆነ በቀር በእውኑ ዓለም ማግኘት ይከብዳል፡፡ ለዚህም ነው እነዚህንና ሌሎች ተመሳስሎዎችን መሰረት በማድረግ የ “ብርሃን ፈለጎች” በ “ግራጫ ቃጭሎች” መንፈስ የተቃኘ ስራ ነው ለማለት የበቃሁት፡፡

Read 2406 times