Saturday, 12 October 2013 13:24

የጥበብ ውልደት እና ተመሳሳዮቹ “እውነተኛ ጥበብ ጉዲፈቻ አይፈልግም”

Written by  ቱዋ (ጋርጋንቱዋ)
Rate this item
(0 votes)

             መውለድ ሁሉንም ይቀድማል፡፡ ይበልጣል፡፡ መውለድ ባይኖር (የሚያድግ ነገር ስለሌለ) ስለ ማሳደግ በፍፁም ማውራት ባልቻልን ነበር፡፡ የእንጀራ አባት ወይንም ጉዲፈቻ ለተወለደው ነገር ባለ ውለታም ቢሆንም ወላጁ ግን አይደለም፡፡
ስለ ሰው ልጅ የአካል ውልደት ሳይሆን ስለ መንፈስ ውልዱ ነው ማውራት የፈለግሁት፡፡ ስለ ጥበብ፡፡ ስለ ጥበብ የተዋልዶ ጤና መዛባት በመጨነቄ ይሄንን መረጃ ፍላጐቱ ላለው ሁሉ ለመንገር ፈለግሁ፡፡ ጤናማ ተዋልዶ እንዴት እንደሚካሄድ በተደጋጋሚ ከመዘብዘብ፣ ተዋልዶውን ጤና የሚያሳጡት ዋነኛ በሽታዎቹ የትኞቹ እንደሆነ ባሳብቅ ይሻላል ብዬ ስላሰብኩ ወደ አላማዬ በቀጥታ ላምራ፡፡
እንደ ማንኛውም ውልደት ጥበብም መወለዱን እርግጠኛ እንድንሆን የምንተማመንባቸው ምልክቶች አሉት፡፡

አንደኛው ምልክት ሞት ነው። አዲስ ጥበብ ሲፈጠር ከፈጠራው በፊት የነበሩ ትውልዶችን ወይንም የጥበብ የግንዛቤ ንቃቶችን ያፈራርሳል፡፡ አዲስ ፈጠራ እንደተከወነ እርግጠኛ ከሆንን፣ አዲስ አመለካከትም አብሮት መወለዱ ሊያጠራጥረን አይችልም፡፡ ምንም እንኳን አዲሱ አመለካከት ገና ቁልጭ ብሎ ባይታየንም። ምሳሌዎችን ልጥቀስ - በ1948 እ.ኤ.አ በጀርመን ሀገር የቅዱስ ማሪን የቤተመቅደስ ውስጥ ጥበባዊ ምስሎችን ለማደስ የተቀጠረው ጀርመናዊ፣ አንድ አስደናቂ ግኝት በቤተመቅደሱ ግድግዳዎች ላይ አገኘ፡፡ ያገኘው የጥንታዊ ጐቲክ የግድግዳ ስዕሎችን ነበር፡፡
እነዚህን መሰሎች አዋቂዎቹ ሲመረምሯቸው የጥንታዊ የጐቲክ ዘመን የጥበብ ጉልላት የሚወክሉ በመሆናቸው በአንድ አቋም ተስማሙ፡፡ “የጠፋ ቅርስ ተገኘ” ተባለ፡፡ ግኝቱ በቅርስ ጠባቂዎች ተመዘገበ፡፡ ቤተክርስቲያኑም ጐብኚን መሳብ ጀመረ፡፡ ማንኛውም ተመራማሪ የስራውን ኦርጅናልነት አልጠረጠረም፡፡ አዲስ የተወለደ ነገር ነው፡፡ አዲስ የተወለደ ሳይሆን የተገኘ ነገር ቢሆንም ከአዲስ የጥበብ ፈጠራ ተለይቶ አልታየም፡፡ እነዚህን ስዕሎች ከተደበቁበት ያገኘው ዲትሪች ፌይ የሚባል ሰው ነበር፡፡ የተገኙትን ስዕሎች በዘመናት ውስጥ ያለፉበትን እንግልት መልሶ እንዲያድስ የተቀጠረው ባለሞያ ግን ሉተር ማስካልት ነው ስሙ፡፡ የጥበብ ግኝቱ በመደነቅ እና ተመልካች እየሳበ ብዙ ጊዜ ከቆየ በኋላ (ከእለታት አንድ ቀን) ይኼው የእድሳቱን ስራ ያከናወነው ባለሞያ ህሊናው እረፍት ነሳው መሰለኝ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ እጁን ይሰጣል። ጥፋቱንም ይናዘዛል፡፡ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የተገኙት የጥንታዊ ጐቲክ ልጥፍ የግድግዳ ስዕሎች የተሰሩት በእኔ እጅ ነው፤ የሚል ነው ኑዛዜው። ኑዛዜውን ተመርኩዘው አሁንም የጥበብ ባለ እውቀቶች ስራውን በጥልቀት መረመሩ፤ “ሰውየው የሚለው ስህተት ነው፤ ስዕሎቹ ኦርጅናል ናቸው” አሉ፤ በድጋሚ፡፡
ወንጀለኛ ነኝ በሚል የፀናው ሉተር ማስካልት፤ ቤቱን እንዲፈትሹ ይገፋፋቸዋል፡፡ ወደ ገፋፋቸው ቦታ ሲገቡ የሉተር ስቱዲዮ በተለያዩ ታላላቅ ጥበበኞች የተሳሉ፤ ነገር ግን አለም የማያውቃቸው ማስተር ፒሶች ተሞልቶ ያገኙታል፡፡ የሬምብራት፣ የፒካሶ፣ የካጋል፣ የሉትሪክ ወዘተ፡፡
ከራሳቸው ከጥበበኞቹ በስተቀር ማንም ሊደግማቸውም ሊያስመስላቸውም የማይችሉ የፈጠራ ስራዎች ናቸው፡፡ ላለማመን አንገራገሩ። ግን ለማመን ተገደዱ፡፡ የስእሎቹ ብዛት ራሱ ከተሸሸጉበት ፈልጐ ነው ያገኛቸው ሊያስብሉ የሚችሉ አይደሉም። የእያንዳንዱ አርቲስት አዲስ ስራ በመቶዎች ብዛት ነው በሉተር ማስካልት እስቱዲዮ ውስጥ የሚገኘው።
ውልደት ናቸው ብለው ደምድመው የነበሩዋቸው ስራዎች፤ ከተወለዱ በኋላ በሉተር አስመስሎ ሰሪው ጉዲፈቻነት ያደጉ ናቸው፡፡ ግን ችግሩ ጥበብ መወለዱ ብቻ በቂ ነው፡፡ ሲወለድም ራሱን ችሎ ነው፡፡ አሳዳጊ ወይንም ጉዲፈቻ አይፈልግም፡፡ የጥበብ ኦሪጅናል ስራ በአስመሳይ ሲደጋገም ጉዲፈቻ እያሳደገው ነው ስል እኔ ሰይሜዋለሁ፡፡ ጥበብ ተወልዶ ከነበረ ለማደግ የማንንም እንክብካቤ አይፈልግም፡፡ ጉዲፈቻ ሊኖረው አይችልም፡፡ በአስመሳይ ጥበበኛ የተሰራ ፈጠራ የሚያሳድገው ጥበቡን ሳይሆን ጉዲፈቻውን ነው፡፡ (ከዚህ በፊት በዚሁ ጋዜጣ ላይ እኔ እና ሌሎች ተጠንጠልጣይ ቁልፍ፤ ተገንዳሽ እና የመሳሰሉትን ስንባባል እንደነበር ትዝ ይለኛል) ትክክለኛው ተንጠልጣይ ግን የጉዲፈቻ አርቲስቱ ነው፡፡
የተንጠልጣይነትን ስነልቦና ለማወቅ ትንሽ ጠለቅ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ይኼንኑ የተንጠልጣይነት ስነልቦና የሚወክልልኝ የአንግሊዝኛ ቃል ስፈልግ “Snobbery” የሚለው ልክክ አለልኝ፡፡ በፈረንጆቹ ትንተና መንጠልጠልን አስቲ ለመረዳት ልጣር-
“Snobbery is the result of a mix up between two frames of reference. “A” and “B” with different standards of value; and the consequent misapplication of standard “A” to value judgment referring to “B”
ለምሳሌ የቅድሙ ምሳሌዬ የነበረው (ራሱን እንደ ወንጀለኛ የቆጠረው) ሉተር ማስካልት የታላላቆቹን አርቲስት ዘይቤ እና ክህሎት በማያሻማ መልኩ እንዲያውም እነሱ ፈጥረው በማያውቁት አዳዲስ አርዕስተ ነገር ላይ እየተጠቀመ የጥበብ ስራ ሰርቷል፡፡ የጥበቡ ስራ በእነዛ ታላላቅ ሰዎች እጅ እንደተሰራ አዋቂ ነን ብለው የሚያምኑትም መስክረዋል፡፡ በስራዎቹ ወጥነት እርግጠኛ ሆነው ሳለ በስንት ምርመራ አስመስሎ ፈጣሪው ሉተር ማስካልት፤ የስራዎቹ ወላጅ መሆኑ ሲደረስበት ተመሳስለው የተሰሩት የፈጠራ ውጤቶች ድንገት ከጥበብ ካታሎጐቹ ላይ ተፋቁ፡፡
መንጠልጠል ወይንም እስኖበሪ ያልኩት በሽታ እዚህ ላይ ቁልጭ ብሎ ሊታየን ይገባል፡፡ ያንኑ ስዕል ተመልክተው ሰአሊውን (ሉተር ማስካልት) ታላቅ፤ ከተጋለጠ ወይንም ራሱን ካጋለጠ በኋላ ደግሞ ያንኑ ፈጠራ ውዳቂ የሚያደርግ ሰውኛ አተያይ የሚገልፀው የቅድሙን ሃሊዮት (ቲዎሪ) ነው፡፡ በሉተርም ይሰራ በፒካሶ ስዕሉ ፊት ለፊታችን ቁጭ ብሏል፤ ብለን እናስብ፡፡ ስዕሉን “A” እንበለው። የሰው አስተያየት ደግሞ አለ፤ ማለትም ስዕሉ የአንድ በጣም የታወቀ ሰው ስራ ነው ስንባል “A” አሪፍ የሚሆን ከሆነና …የአንድ ውዳቂ “ስም” ስራ ነው ስንባል “A” አስቀያሚ የሚሆን ከሆነ፤ “A” የሚባለው ነገር ውበቱን የሚለዋውጠው አሊያም በምትሀታዊነት እና አምታችነት መሀል የሚዋልለው በ“B” የሚባል ሌላ ነገር ምክንያት ነው፡፡
ይህ ነገርየውን ከነገርየው ጋር ምንም ግንኙነት በሌለው መለኪያ የሚያስለካን ነገር …”ተንጠልጣይነት” ወይንም “Snobbery” ብዬ ጠርቼዋለሁ፡፡
የዛሬ መቶ ሃምሳ አመታት በፊት በፈረንጆቹ የምግብ ዝርዝር “ኦይስተር” የሚባል የባህር እንቁ ፈጣሪ ቀንዳውጣ መሰል ነገር “የደሀ” ምግብ ነበር። በሀብት በናጠጡት መሀል ምግቡ “ቄስ ይጥራው” የሚባል ነውር እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከመቶ ሃምሳ አመታት በኋላ ተገላቢጦሽ ሆነ፡፡ ደሀ ሳይመገበው ኖሮ ይሞታታል፡፡ ኦይስተር “ፐርል” የተባለውን የባህር እንቁ በውስጡ የሚሰራ ፍጥረት ብቻ ሳይሆን …“የምግብ ብሔሮች”ም እንቁ ሆነ፡፡
ሂትለር የሚባለው ሰውዬ በጀርመን ላይ ከመነሳቱ በፊት ትኖር ስለነበረች አንዲት ፀሃፊ ሴትዮ የሚባለውም የቅድሙን ሃሊዮት የሚያጠናክር ነው፡፡ ፀሃፊዋ ከተለያዩ ወንዶች ጋር የፍቅር ግንኙነት ማድረግ አመሏ ነው ይባልላታል፡፡ ወንዶቹን ለወሲብ ብትመርጣቸውም ለምርጫዋ ዋናው ምክንያት የወንዱ እድሜ፣ ደም ግባት ወይንም የፍቅር አያያዝ ዘይቤው አይደለም፡፡ ከወንዱ ጋር ግንኙነት እንድታደርግ የሚያነሳሳት እንደኛ ሰውዬው ደራሲ መሆን አለበት፡፡ ሁለተኛ የደረሰውን መጽሐፍ ከ20.000 ኮፒዎች በላይ የሸጠ መሆን አለበት፡፡ “ከዚህ ሽያጭ በታች ያሽቆለቆሉት ጋር ለመተኛት ስሞክር ሰውነቴ አልታዘዝ ይለኛል” ብላ እርግጡን ተናግራለች ይባልላታል፡፡
በዚህ በሁለተኛው የፀሃፊዋ ምሳሌ ረገድ “A” የፆታ ግንኙነት እና በወንድና ሴት መሀል ያለው መፈላለግ ልንለው እንችላለን፡፡ “B” ደግሞ ደራሲነት እና የመጽሐፍ ሽያጭ ነው፡፡ በሁለተኛው አማካኝነት የመጀመሪያው “A” የሚንጋደድ ከሆነ፤ የመጀመሪያው ድሮውኑ ብቻውን ትርጉም የለውም ማለት ነው፡፡
የፈጠራ ስራ ብርሐን ነው፡፡ ራሱን የቻለ ነው፡፡ ውልደት ነው፡፡ አሳዳጊም አያስፈልገውም፡፡ የፈጠራ ስራን (ብርሐን) የማፍለቅ አቅምና የፈጠራ ሰውነት ያለው ሰው፤ የጥንቱንም የፈጠራ ውጤት አይታከክም፡፡ ስሙንም በማስተዋወቅ ስራውን ለማስወደድ አይሞክርም፡፡
ስለዚህም ጥበቡ የጉዲፈቻ ወይንም በሌላ ከጥበቡ ውጭ በሆነ ነገር ላይ በመመርኮዝ ጥበቡ እንደተወለደ ሊያረጋግጥልን አይችልም፡፡ ውልድ (ጤነኛ ስነ ተዋልዶ መንገድ) መገኘቱን የሚገልፀው የተፈጠረው ጥበብ ብቻ ነው፡፡ “A” is “A” or “A” is Non “A” but it can’t be “A” and Non “A” at the same time የሚለውን የአሪስጣጢለስ የማንነት ህግ፤ ለጥበብ ማንነትም እንደ መለኪያ መጠቀም እንችላለን፡፡ ግን … ጥበብ ምን ማለት እንደሆነ በማያሻማ መንገድ መግለፅ እስካልቻልን … መወለድም ሆነ መሞት፣ ብርሐንም ሆነ ጨለማ፣ ፈጠራ እና ኢ-ፈጠራ … የቱ የት እንደሆነ መለየት ሳንችል መሳከር ነው የሚሆነው፡፡
(እዚህ መጣጥፍ ላይ ስሜን ፅፌ እንድታነቡት ባደርጋችሁ … የስሜ ማንነት የፅሁፉን ማንነት ከጥሩ ወደ መጥፎ … ሊቀይረው ስለሚችል … ሲችልም ከተፃፈው አስተሳሰብ ጋር እንድታነፃፅሩት ስሜን አድምቄ እፅፈዋለሁ!)

 

Read 1751 times