Saturday, 12 October 2013 13:25

በጉጉት የተጠበቀው የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የአመራር ምርጫ

Written by  ወልደመድህን ብርሃነመስቀል
Rate this item
(0 votes)

“ልብ የሚያሳርፍ ምርጫ ነው” የቀድሞው የማህበሩ ፕሬዚዳንት
በ97 ዓ.ም 30ሺ ብር የነበረው ካፒታል 2.7ሚ. ብር ደርሷል
ባለፈው ቅዳሜ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር በቅርስ ጥናትና ምርምር አዳራሽ የጠራውን ጠቅላላ ጉባኤ የጀመረው በመርሃ ግብሩ ላይ ከተቀመጠው በአንድ ሰዓት ዘግይቶ ነው፡፡ ቀን ሙሉ ለሚካሄደው ጉባኤ አምስት ያህል አጀንዳዎች ተይዘው ነበር። ከሁሉም በላይ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ግን የማህበሩን አዲስ አመራር የመምረጥ ሂደት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የግማሽ ክፍለ ዘመን ጉዞ፣ ከተከናወኑት ተግባራት ሁሉ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተሰሩ ሥራዎች ላቅ ያሉ እንደሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ሆኖም ማህበሩን ለስምንት ዓመታት የመራውን አመራር የሚተካው ማነው? የሚለው ጥያቄ ብዙ ሲያነጋግር ቆይቷል። በህዳር ወር 2005 ዓ.ም ማህበሩ በጠራው ጠቅላላ ጉባኤ፣ ጥያቄው መልስ ባለማግኘቱ የነባሩ አመራር የስራ ጊዜ ለወራት እንዲራዘም መወሰኑ ይታወሳል፡፡ የመስከረም 25ቱ (ያለፈው ቅዳሜ) የምርጫ አጀንዳም ትኩረት የሳበውና ያጓጓው ብዙ ስላስጠበቀ ይመስላል፡፡
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ በስብሰባው መጀመሪያ ላይ ያደረጉት ንግግር፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት እሳቸውና አመራሩ ያከናወኗቸውን ሥራዎች ውጤት የሚዳስስ ነበር፡፡ በመጋቢት 1997 ዓ.ም የተቀበልነው እጅግ የተጎሳቆለ “ስመ ማህበር”ን ነበር ያሉት አቶ ጌታቸው በለጠ፤ ከዚያ በኋላ ባሉ ጊዜያት ብዙ ውጣ ውረዶችን የጠየቀ ቢሆንም፣ ስኬታማ ስራዎች ማከናወን እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ ይሄም የሆነው በሥራ አመራሩ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የተለያዩ አካላት ያደረጉት አስተዋጽኦ ታክሎበት ነው ብለዋል - አቶ ጌታቸው፡፡
ማህበሩ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ መጻሕፍትና መጽሔቶች ማሳተሙን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ አባላቱ የነፃ ትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረጉንና የአባላት ቁጥር እንዲጨምር መትጋቱን ገልፀዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የመታሰቢያ ቴምብሮችን ማሳተሙን፣ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መክፈቱን፣ የጥበብ ጉዞዎችን ማዘጋጀቱን፣ የመፃሕፍት አውደ ርዕዮችን ማሰናዳቱን፣ የሬዲዮ ፕሮግራም መጀመሩን፣ የሥነ ጽሑፍ ስልጠናዎች መስጠቱንና ማህበሩ ለሚያሰራው የጥበብ እልፍኝ ሕንፃ ከመንግሥት ቦታ መጠየቁን አቶ ጌታቸው ዘርዝረዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰኢድ በበኩላቸው፤ “አንድ ማህበር በአመራሩ ጥንካሬ ለውጤታማ ተግባራት አፈፃፀም የሚጠቅም መስመር ይዞ መጓዝ ቢችልም ለጥንካሬው የማዕዘን ድንጋይ የሚሆኑት በማህበሩ ስር የተደራጁ አባላት ትጋት፣ ቁርጠኝነትና ጥንካሬ ሲኖራቸው ነው፡፡ አምዱ የላላበትና የአባላት መሰረቱ የተሸረሸረበት ማህበር “አለ” ከመባል ውጭ መኖሩን የሚያመለክቱ ተግባራት ሲፈጽም አይታይም” በማለት፣ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የታየው ስኬት የመተባበር፣ የጥረትና የድካም ውጤት መሆኑን መስክረዋል፡፡ በማህበሩ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማሳደግም በዚሁ ዕለት ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል፡፡
የማህበሩን ያለፉት ስምንት ዓመታት የሥራ እንቅስቃሴ የሚቃኝ የጥናት ጽሑፍ ያቀረበው ደራሲ አንዱዓለም አባተ፤ “ከተዘጋጀሁበት ርዕሰ ጉዳዮች ብዙዎቹ በአቶ ጌታቸው በለጠ ስለተገለፀ አሳጥሬ አቀርብላችኋለሁ” በማለት በፕሬዚዳንቱ ያልተነሱ ጉዳዮችን ዳስሷል፡፡
የደራሲ ተመስገን ገብሬ የሕይወት ታሪክና የደራሲ በዓሉ ግርማ የድርሰት ሥራዎች እንዲታተሙ ትልቁን ሚና የተጫወተው ደራስያን ማህበሩ፤ ከዚህም በላይ ታላላቅ ተግባራትን ማከናወን ይችል እንደነበር የጠቆመው ጽሑፍ አቅራቢው፤ የመግባቢያ ሰነዱ ቀደም ብሎ ተፈርሞ ቢሆን ኖሮ ማህበሩ አባላቱን ለማስተማር ዩኒቨርሲዎችን ደጅ አይጠናም ነበር ብሏል፡፡ በደርግ ዘመን ማህበሩ አባላቱን ወደ ውጭ አገራት እየላከ ያስተምር እንደነበርም በማስታወስ፡፡
ማህበሩ አባላቱን የሚያበረታታበትና ዕውቅና የሚሰጥበት ዓመታዊ የሽልማት ፕሮግራም ማዘጋጀት ነበረበት ያለው ደራሲ አንዱዓለም፤ የራሱ ማተሚያ ድርጅትና የመፃሕፍት መሸጫ መደብሮች ቢኖሩት ጥሩ ነው ብሏል፡፡ ለጥበባዊ ጉዞዎች የሚመረጡ አባላት የሚመለመሉበት አካሄድ ግልጽ አለመሆኑን በመጠቆም፤ ጉዳዩ ቅሬታ እያስነሳ ስለሆነ ወጥ የሆነ መስፈርት ሊቀመጥለት ይገባል ሲልም አሳስቧል፡፡
ሌላው የጥናት ጽሑፍ አቅራቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፎክሎር የዶክትሬት ተማሪ የሆነው ገዛኸኝ ፀጋው በበኩሉ፤ ማህበሩ ያሳተማቸውን መፃሕፍትና መጽሔቶች የተመለከተ ዳሰሳ አቅርቧል፡፡ በማህበሩ የግማሽ ክፍለ ዘመን ታሪክ ማህበሩን ከመሩት አምስት የተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ በአንደኛው፣ በሦስተኛውና አምስተኛው የሥራ አስፈፃሚ ዘመናት ስለታተሙት መፃሕፍትና መጽሔቶች ዝርዝር ያቀረበው ገዛኸኝ፤ የአምስተኛውን ዘመን ሥራ “ወርቃማ” ነበር ብሎታል።
ሩብ ጉዳይ፣ የበዓሉ ግርማ ድርሰቶች፣ ከቁጥር 2 በኋላ የታተሙት ብሌን መጽሔቶች፣ በቁጥር 1 እና 2 የታተሙት የዘመን ቀለማት፣ መድብለ ጉባኤ፣ የጥላሁን ገሠሠ የሕይወት ታሪክ፣ ከአርቲስቲክና ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤቶች ጋር በመተባበር የታተሙ 14 መፃሕፍትና መሰል ሥራዎችን በማሳያነት ያቀረበው የጥናት ጽሑፍ አቅራቢ፤ በሥራው ሂደት የታዩ ግድፈቶችና ስሕተቶችን ነቅሶ በማውጣት ልንማርበት ይገባል ብሏል፡፡
በማህበሩ ፀሐፊ በደራሲ እንዳለጌታ ከበደ በቀረበው የሒሳብ ሪፖርት፤ ለጥበብ እልፍኝ ማሰሪያ በዝግ አካውንት የተቀመጠውን 2 ሚሊዮን ብርና በተዘዋዋሪ ፈንድ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ፤ እንዲሁም ያልተሸጡ መፃሕፍትና መጽሔቶችን ዋጋ ጨምሮ ማህበሩ 2.7 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዳለው ተገልጿል፡፡ አመራሩ ማህበሩን በ1997 ዓ.ም ሲቀበል ካፒታሉ 30ሺ ብር እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
ከቀኑ 10 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ላይ ነበር በጉጉት ወደሚጠበቀው ትልቅ አጀንዳ የተገባው፡፡ በደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ የሚመራ ሦስት የአስመራጭ ኮሚቴ ከተሰየመ በኋላ “የማሕበሩ ሕገ ደንብ ላይ አለ የተባለው ክፍተት ተሻሽሎ ምርጫው ይካሄድ፤ ከነባሮቹ ሥራ አመራሮች የተወሰኑት ወደ አዲሱ ሥራ አመራር እንዲገቡ ይደረግ፤ ሙሉ ለሙሉ አዲስ የሥራ አመራር ከመምረጥ ውጭ የሚያስኬድ ምንም ሕጋዊ መሠረት የለም” የሚሉና የሥነ ስርዓት ጥያቄዎች ላይ የሚያተኩሩ ሐሳቦች መንሸራሸር ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም “ያለ ነባሩ አመራር ማህበሩ ሊቀጥል አይችልም በሚል ስጋት አይግባን፤ በዚህ አዳራሽ ውስጥ ማህበሩን ሊመሩ የሚችሉ አባላት አሉ” በሚል በቀረበው ሀሳብ መግባባት በመቻሉ፤ ለውድድር የሚቀርቡ አባላትን የመጠቆሙ ኃላፊነት ለነባሩ ሥራ አመራር ተሰጠ፡፡ 10 እጩዎች ለውድድር ቀርበውም ሰባቱን አሸናፊዎች ለመለየት ድምጽ መስጠት ተጀመረ።
ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ ፕሬዚዳንት፣ ገጣሚ አያልነህ ሙላቱ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ደራሲ አንዱዓለም አባተ ዋና ፀሐፊ ሆነው ሲመረጡ፤ ገጣሚ ገዛኸኝ ፀጋው በሂሳብ ሹምነት፣ ደራሲ አብርሃም መለሰ ደግሞ በኦዲተርነት ተመረጡ፡፡
በስልጣን ሽግግሩ ማጠናቀቂያ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ ባደረጉት ንግግር፤ “ልብ የሚያሳርፍ ምርጫ ነው፤ ተመራጮቹ ለሥራው የተሰጡ ሰዎች ናቸው” ካሉ በኋላ በማህበሩ የተጀመሩ ሥራዎች በተሻለ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለአዲሱ አመራር አደራ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ በበኩላቸዉ፤ እምነት ጥለውባቸው የመረጧቸውን የማህሩን አባላት አመስግነው፤ “ማህበሩ ለዛሬ የደረሰው ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፎ ነው፤ ተከታታይ ትውልዶች ማህበራችንን ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋግረው ለዛሬ አድርሰውልናል፡፡ ያለፉትን አመራሮች ጥንካሬ፣ ትጋትና ሐቀኝነት በእኛም ውስጥ ለማስቀጠል እንሰራለን፡፡
የመረጣችሁን አባላት ትተባበሩናላችሁ፣ አብራችሁን ትቆማላችሁ ብለን ስለምናምን ኃይልና አቅም ሆናችሁን ታላቅ ሥራ እንሰራለን” በማለት ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ የአዳራሹ የግድግዳ ሰዓት 12፡45 ላይ ያመለክት ነበር፡፡

 

Read 2306 times