Saturday, 12 October 2013 13:32

ኢትዮጵያ ከናይጄርያ - ክፍል 1

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

         ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ከአፍሪካ የሚወከሉትን አምስት ቡድኖች ለመለየት አሥሩ ቡድኖች የጥሎ ማለፍ ትንቅንቃቸውን በመጀመርያ ጨዋታቸው ዛሬ እና ነገ ይጀምራሉ፡፡ በአፍሪካ ዞን ከሚደረጉት አምስት የጥሎ ማለፍ ትንቅንቆች በተለይ ኢትዮጵያ እና ናይጄርያ የሚገናኙበት ፍጥጫ ከፍተኛ ትኩረት እንደሳበ ነው፡፡ በሌሎች ጨዋታዎች ጋና ከግብፅ፤ አይቬሪኮስት ከሴኔጋል፤ ቡርኪናፋሶ ከአልጄርያ እንዲሁም ቱኒዚያ ከካሜሮን ይገናኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ እና የናይጄርያ ጨዋታ ትኩረት የሳበው ያለምክንያት አይደለም፡፡ በሁለቱ አገራት ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ያለው የእግር ኳስ ደረጃ ልዩነትን በማነፃፀር በሚሰጡ ግምቶች፤ የዓለም ዋንጫ ውድድር እንደኢትዮጵያ አይነት በእግር ኳስ ዝቅ ያለ ደረጃ የሚገኝ ቡድንን ለማሳተፍ በፈጠረው እድል አጓጊነት እና በሌሎች ምክንያቶች የሁለቱ ቡድኖች ግጥሚያ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቧል፡፡

ሰሞኑን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የፊፋ ታዛቢ ሆነው የተገኙት የታንዛኒያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት፤ የመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ የእግር ኳስ ምክር ቤት ሴካፋ ፕሬዝዳንት እና የካፍ ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት ሚስተር ሊዮዳር ቴንጋ ‹ ምስራቅን ብቻ ሳይሆን ደቡባዊውን የአፍሪካ ዞን የወከለችው ኢትዮጵያ ናይጄርያን በማሸነፍ ለዓለም ዋንጫ እንድታልፍ እየፀለይኩ ነው› በማለት ተናግረዋል፡፡ ሚስተር ሊዮዳር ቴንጋ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እያስመዘገበ ባለው ውጤት ልትኮሩ ይገባል በማለትም ለጠቅላላ ጉባኤው አባላት ማበረታቻ ሰጥተዋል፡፡ የወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነችው ናይጄርያ ለዓለም ዋንጫ የምታልፍበትን ትኬት ኢትዮጵያን በማሸነፍ ትቆርጣለች ብለው የተማመኑት የናይጄርያው ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን በበኩላቸው ነገ ለሚደረገው የመጀመርያ ጨዋታ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሰጡ ለ200 ደጋፊዎች ቻርተር በረራ መፍቀዳቸው ታውቋል፡፡
ታዋቂው የእግር ኳስ ድረገፅ ጎል ስፖርት እንደገለፀው ኢትዮጵያ ከናይጄርያ የሚገናኙበት የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ በንፅፅር ሲታይ የዳዊት እና የጎልያድ ፍጥጫ ነው፡፡ ይህንንንም በተለያዩ ንፅፅሮች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በትራንስፈርማርኬት ድረገፅ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአጠቃላይ ስብስቡ 23 ተጨዋቾችን ከእነሱ መካከል 5 ፕሮፌሽናሎችን አስመዝግቦ በዝውውር ገበያ 775ሺ ፓውንድ ዋጋ እንዳለው ሲገመት የናይጄርያ አቻው በ24 ተጨዋቾች ስብስቡ 18 ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን አስመዝግቦ የተተመነው 58.5 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውዱ ተጨዋች የተባለው ሰለሃዲን ሰኢድ በትራንስፈር ማርኬት የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመኑ 300ሺ ፓውንድ ሲሆን በአንፃሩ የናይጄያ ውድ ተጨዋች የሆነው ጆን ኦቢ ሚኬል 19.5 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ በኢንተርናሽናል ውድድሮች የ321 ጨዋታዎች ልምድ ያለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አማካይ እድሜው 25.20 ሲሆን ከ361 በላይ ጨዋታዎችን በማድረግ ልምድ ያስመዘገበው የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ 24.10 ነው፡፡
ኢትዮጵያና ከናይጄርያ ከነገው ጨዋታ በፊት በታሪካቸው በ7 ግጥሚያዎች ተገናኝተዋል፡፡ አምስቱን ያሸነፈችው ናይጄርያ ስትሆን ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ አሸንፋ ፤ በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት በ1982 እኤአ ሊቢያ ባስተናገደችው 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነበር፡፡ በወቅቱ ናይጄርያ 3ለ0 ስታሸንፍ ሁለቱን ጎሎች አሁኑ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የሆነው ስቴፈን ኬሺ ሲያስቆጥር ሌላኛዋን ጎል ያስመዘገበው አዴሞላ አዴሺና የተባለ ተጨዋች ነበር፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ለሁለተኛ ጊዜ የተገናኙት ደግሞ በወዳጅነት ጨዋታ በ1993 እኤአ አዲስ አበባ ላይ ሲሆን 1ለ0 ያሸነፈችው ናይጄርያ ነበረች። ከዚህ በኋላ ደግሞ በ1994 እኤአ ላይ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ግጥሚያ ላይ በአዲስ አበባ ሲገናኙ ኢትዮጵያ በወቅቱ ከባድ የነበረውን የናይጄርያ ቡድን 1ለ0 አሸንፋለች፡፡ በመልሱ ጨዋታ ግን ለአራተኛ ጊዜ ሲገናኙ ናይጄርያ በሌጎስ 6ለ0 ማሸነፏ የሚታወስ ሲሆን ግዙፉ አጥቂ ራሺዲ ያኪኒ በዚያ ጨዋታ ሃትሪክ ሰርቶ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እና ናይጄርያ ለአምስተኛ ጊዜ የተገናኙበት ጨዋታ በ2012 እኤአ ላይ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ አዲስ አበባ ላይ ሲደረግ ነበር፡፡
በዚህ ጨዋታ ላይ 2ለ2 አቻ ሲለያዩ ለኢትዮጵያ ሁለት ጎሎችን ሳላዲን ሰኢድ አስቆጥሮ እንደነበር ሲታወስ ለናይጄርያቸ ደግሞ ኡቼ እና አምበሉ ጆሴፍ ዮቦ አስቆጥረዋል፡፡ በዚሁ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ በአቡጃ ለስድስተኛ ጊዜ በተገናኙበት ወቅት ደግሞ በሳምሶን ሲያ ሲያ የሚሰለጥነው የናይጄርያ ቡድን 4ለ0 በሆነ ውጤት ኢትዮጵያን አሸንፎ ነበር፡፡በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ አራቱን ጎሎች ያስቆጠሩት እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ጎሎች ያስቆጠሩት ፒተር ኡታካ እና ኢኬ ኡቼ ናቸው፡፡

ይሁንና በመጀመርያው ጨዋታ በአዲስ አበባ አቻ የተለያየበት ጨዋታ ዋጋ አስከፍሎት ለአፍሪካ ዋንጫ ሳያልፍ ቀርቶ ለአሰልጣኙ መባረር ምክንያት የነበረ ውጤት እንደነበር ይታወሳል። ኢትዮጵያ እና ናይጄርያ ነገ በታሪክ ለስምንተኛ ጊዜ ከመገናኘታቸው በፊት በሰባተኛ ጨዋታቸው ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ተሳትፏዋን ባገኘችበት የደቡብ አፍሪካው 29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ላይ ነበር፡፡
በደቡብ አፍሪካ ከተማ ሩስተንበርግ ተደርጎ በነበረው የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ 3 የመጨረሻ ጨዋታ ላይ የሁለቱ ቡድኖች ትንቅንቅ እስከ 81ኛው ደቂቃ ያለምንም ግብ አቻ ነበር። ነገር ግን በመጨረሻዎቹ የጨዋታ ክፍለጊዜዎች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በተሰሩ ሁለት ጥፋቶች ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶች ለናይጄርያ ተገኙ፡፡ ሁለቱንም ኢሊጎሬዎች ቪክተር ሞሰስ አግብቶ 2ለ0 ድል በማድረግ ናይጄርያ እስከ ሻምፒዮናነት ለመገስገስ ችለዋል፡፡

Read 2643 times