Saturday, 19 October 2013 11:47

ትንሹ መንግስት

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

           በታላላቆቹ የፖለቲካ ፈላስፎች በእነ ሆብስና ሩሶ አስተምህሮ መሰረት ግለሰቡ/ህዝቡ ስልጣኑንና በጎ ፈቃዱን በስምምነት መንግስት ለሚባለው አካል ማስገዛት አለበት/አለባቸው ይሉናል። መንግስት የህብረተሰቡን ደህንነትና ንብረቱን የመጠበቅ ግዴታ አለበት፤ እንደ ሆብስ አባባል። ለሩሶ ደግሞ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባሩ የህብረተሰቡን መብትና ነጻነት የማስከበር ነው፤ ይህ ግዴታው ያመዝናል። ሁለቱም ፈላስፎች ግብ ያደረጉት የማህበረሰቡ አንድነት እና ሠላም እንዲህ ማድረግ ከተቻለ ሰላማዊ ማህበረሰብ ይገኛልና ነው። የፍላጎት/ጥቅም/interest/ እና የመብት/right/ ውል እየተባሉ ለሁለት ቡድን ተከፍለው ምሁራዊ ትንታኔ ይሰጥባቸዋል፤ የሁለቱ ፈላስፎች ማህበራዊ ውል። የኛ ማህበረሰብ የመንግስት አመሰራረቱ ጥንታዊ ስለሆነ መሰረቱን በመብት ላይ አሊያም በፍላጎት ላይ ያድርገው አጥርተን አልተረዳነውም።

በእኔ ግምት ግን ሃይማኖታዊና መንፈሳዊያን ስለሆንን አንዳች መለኮታዊ መንበር ላይ የተመሰረትን ይመስለኛል።
ይሄ ፍልስፍና የሚባል እራሱን የቻለ ወንበር ዘርግቶ አልተፈላሰፈም የምንለው ህዝባችን፤ ፍልስፍናን ለማህበራዊ፣ለመንግስታዊ እና ሃይማኖታዊ ህይወቱ እንደ ማጣፈጫ ቅመም እየመጠነ በያቅጣጫው ተክሏታል። በማህበራዊ ዘርፉ የስነምግባር መመሪያዎቻችን፣ የጎሳ/አካባቢ ሽምግልና፣ የመንደር ትምህርት ቤቶቻችን እና ሌሎችም መዋቅሮቻችን የፍልስፍና ወዝ ያረፈባቸው ናቸው። በመንግስታዊ መዋቅሮች ውስጥ ነገስታት ፍትሃዊነትን፣የሞራል እና ፈጣሪን የመፍራት እሴቶችን ተላብሰዋል፡፡ በተጨማሪም ነገስታት እራሳቸውን የመግዛት ጥበብን በፍልስፍና ቅባት አብሰው ሽማግሎቻቸው አስተምረዋቸዋል። በሃይማኖታዊ ሥርዓታችን ምንም የማያከራክሩ የፍልስፍና መሰረታዊያንን እናገኛለን።
ማህበረሰባችን ጥንታዊ እንደ መሆኑና እንደ አጥቢያ ኮከብ ሥልጣኔውን ብልጭ አድርጎ እንደ መሰወሩ አንዳች የደበቀው ያልተገለጠልን መንግስት ያለው ይመስለኛል። ርዕሰ ጉዳዩ የሚያምታታ እንዳይሆን ግልጽ ለማድረግ ያህል፣ መንግስት እያልን የምናውቀውን/የሰየምነውን አካል መደበኛ መንግስት እንበለውና፤ ምናልባት ደግሞ በትላልቅ ተቋማት እራሱን ያልገለጸ፣ እንደ የለምለም መስክ ምንጭ ድምጽ ሳያሰማ ኩልል እያለ የሚፈስ፣ ስር ለስር የሚሰራ መንግስት ይኖር እንደሆን ደግሞ ትንሹ መንግስት እንበለው። ትንሹ መንግስት ባህል፣ ወግ፣ ልማድ፣ ሽምግልና፣ ጎሳ መሪ፣ ዕድር፣ እቁብ፣ ሰንበቴ፣ የቡና አጣጭ/ማህበር ወዘተ መገለጫው ሊሆን ይችላል።
የኛ የኢትዮጵያዊያንን ማህበራዊ መዋቅራት በመፈተሽ ምናልባት አንዳች የጋራ ጥቅም ተቋዳሽ ለማድረግ በማሰብ ይጠቅሙኛል የምላቸውን ሙግቶች (ምንም እንኳን በስርዓቱ ባላደራጃቸውም) ለመሰንዘር እሞክራለሁ። በዚያውም የፈረንጆችን የመንግስት መዋቅር በሃገራችን ሲተገበር የፈጠራቸውን ክፍተቶች መነቅነቅና መፈተሽ እፈልጋለሁ። በምርጫ 97 ወቅት በምስራቅ ጎጃም አካባቢ የተከሰተ ታሪክ ሁሌም ይመስጠኛል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ባንድ ገበሬ ማህበር የቅንጅት ተወካዮች ለምርጫ ቅስቀሳ ገበሬውን ፖለቲካ ያጠጡታል፤ ስሜት የሚኮረኩሩና የፖለቲካ መንፈስን የሚያጦዙ ንግግሮች ሲካሄዱ ቆዩና፣ ባላገሮቹ አስተያየትና ጥያቄዎችን መሰንዘር ይጀምራሉ። ከመሃልም አንድ ተሳታፊ “የምን ኮሮጆ፣ የምን ምርጫ ካርድ ነው የምታወሩት? በቃ እዚሁ ለምን አይለይልንም፤ ቅንጅት ነኝ የምትሉ በቀኝ፣ ኢህአዴግ ነኝ የምትሉ በግራ ተሰለፉ” አለ አሉ።

መምረጥ መመረጥ በኛ ባህልና በፈረንጆቹ የፖለቲካ ባህል እንዲህ ነው ልዩነቱ የምርጫ ቀን፣ የምርጫ ካርድ፣ ምስጢራዊ ክፍል፣ የምርጫ ምልክት ይሏቸው ነገሮች ለኛ ሚዛን የሚደፉ አይመስሉም።
በጦርነትና በውስጣዊ ግጭት ምክንያት መደበኛው መንግስት ሲዳከም የማህበረሰቡን አንድነት አስጠብቆ የሚሄደው በትንሹ መንግስት ጥንካሬ ነው፤ መደበኛው መንግስት ጠንከር ሲል ደግሞ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ተቋቁሞ ቋንቋ ሳይገድበው አብሮ እየሰራ መኖር የቻለ ህዝብ። ምናልባትም በጣም ውስብስብና ከባድ ከሆኑት የዓለማችን ማህበረሰቦች ውስጥ አንዱ የኛ ማህበረሰብ ይመስለኛል። እርስ በርሱ እንደ ስውር ስፌት የማይታይና ሲታይም ደግሞ እንደ ሸረሪት ድር የሳሳ የሚመስል ያስተሳሰረው ማህበራዊ ክር አለ። የሶሲዮሎጂና አንትሮፖሎጂ ጥናቶችን በተጨማሪ መዳሰስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። አሁን ባነሳሁት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ግን በኔ ግምት የኛን ማህበረሰብ ትንሹ መንግስት ያለው መሆኑን ማሳያ የሚሆኑ አራት ማህበራዊ እሴቶችን ልጠቀም፦
ሀ)ማህበራዊ ጤናማነት፦ የሽምግልና፣ የእርቅ፣ የምክክር፣ የአካባቢ ደህንነት/ቅራት ወዘተ… ጉዳዮችን ማህበረሰባችን የሚፈታባቸው/የሚያስተናግድባቸው መንገዶችን በቅርበት ብናጠናቸው ማህበራዊ ጤናማነትን ይወክልልናል። ይህ እሴታችን የፖለቲካ ሰዎቻችን (ተቃዋሚውም መንግስትም) የስልጣን ሽኩቻ ሲኖርባቸውና ወደ ጉልበት አንባጓሮ ቢያመራ ጣልቃ በመግባት የማረጋጋልት አቅም አለው።
ለ)ምጣኔ ሃብት፦እቁብ ፣ብድር፣ መዋጮ እና ሌሎች ቤሳ ቤስቲ ሲያጥረን ጎደሏችንን ለመሙላት የምንጠቀምባቸው የባህል ባንኮቻችንን ያጠቃልላል። ትዳር እንዳይፈርስ፣ ቤተሰብ እንዳይናጋ ማህበረሰብ እንዲረጋጋ፣ የራሳቸው ቁልፍ አስተዋጽዖ አላቸው፤ እነዚህ የገንዘብ ተቋማት።
ሐ)ማህበራዊ ፍቅር፦ የጡት አባት፣ ሞግዚት፣ አበልጅ፣ የተረት አባት፣ የሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት የምንባባልባቸው ጎረቤቶቻችን። ከልጅ ልጅ ቢለዩ አመትም አይቆዩ የምንባባልበት መንደራችን። “እንዴ ይሄ ልጅ የእከሌት ልጅ አይደለም እንዴ? ከመቼው እንዲህ ተመዘዘ?” እየተባባልን ጉንጭና ግንባር እየሳምን የምናሰርጸው ማህበራዊ ፍቅር። በግድ አጣብቆ አንድ የሚያደርግ ማህበራዊ ሲሚንቶ ይመስለኛል።
መ)አመራር፦ አባወራዎች/እማወራዎች በየቤታቸው መታፈሪያ የሚሆኑ፤ የተከበሩ ሞገስ ያላቸው፣ ባለትህትና፣ በሞራል የበላይነት ቤተሰቦቻቸውን ቀጥ አድርገው የሚያስተዳድሩ አሉን። እነዚህም በየመንደራችን ብንቆጥራቸው ብዙ ይሆናሉ፤ ከነሱም ደግሞ ደረጃ ደረጃ አላቸው። የክብር የማእረግ ልዩነት። አንተም ተው አንቺም ተይ ማለትና ተጽእኖ ማድረግ የሚችሉ ብዙዎች አሉን። በይሉኝታም የምንታዘዛቸው። እነዚህ ሁሉ የየአካባቢዎቻችን ገዥዎች ናቸው። አስተዳዳሪዎቻችን።
የበጎ ፈቃዱን አብሮ ለመኖር ለባህሉ ያስገዛ ህዝብ ማለት ይሄነው። የሩሶን የሶሻል ኮንትራት ሃልዮትን ለትልቁ መንግስት ሳይሆን ለትንሹ መንግስት እንስጠውና ጉዳዩን ማህበረሰባችን ውስጥ ልክ እንደዚህ ፈትፍተን ስናየው፤ ለራሱ ባህላዊ ተቋማት እራሱን/የበጎ ፈቃዱን/ አስገዝቶ የሚኖር ህዝብ ስለ ሆነ፣ የራሱ ትንሽ መንግስት እንዳለው ፍንትው ብሎ ይታየናል።

ማንም የማንም ባሪያ ሳይሆን፤ ማህበራዊ አንድነቱም ሳይዳከም እራሱን አዋቅሮ መተዳደሪያ ባህላዊ ህጎችን የሰራ ማህበረሰብ። ምልዓተ በጎ ፈቃድ የተላበሰ ነውና ትንሹ መንግስት ብንለው የሚያንስበት አይመስለኝም። ሁሉም በበጎ ፈቃድ እራሱን ለማህበራዊ አንድነቱ በባህልና ልማድ እራሱን ሲያስገዛ እያየነው ነውና።
በሩሶ የመንግስት/social contract/ አስተምህሮ ውስጥ ገዥዎች ብዙ ግዜ የራሳቸውን ጥቅም ማራመድን ያስቀድማሉ ይለናል። ስለዚህም ይላል፤ ለማህበረሰቡ ሲሞግት መንግስታት ለማይገረሰሰው የህዝብ ዳኝነት በአያሌው/ፍጹም ረዳቶች መሆን ይገባቸዋል፤ ስለሆነም የመንግስታት ቅርጽ እንደየ ማህበረሰቡ ስሪት ተስማሚ መዋቅር ሊኖራቸው ይገባል። ይህም ማለት የኛ ዘመናዊ/መደበኛ መንግስታችን የማህበረሰቡን ጥቅም ያስከብር ዘንድ የማህበረሰቡን እሴቶች የሚመስሉ መዋቅሮች ሊኖሩት ይገባል ማለት ነው። ይህንን ለማድረግ ግን የታደልን ማህበረሰብ ነን ብዬ አላምንም። ከማህበረሰባችን እሴቶች ጋር የሚጋጩ ሁልቆ መሳፍርት ችግሮችን እያስተዋልን ነው።
መቼ ተንሻትተን ነው ግን እዚህ ደረጃ የደረስነው? ከመቼው የሃያ ሺህ ብር ሎተሪ የመጀመሪያ እድል ከሚደረግባት ሃገር ወደ አራት መቶ ሺህ ብር ወርሃዊ የቤት ኪራይ የሚከፈልባት ሃገር ደረስን።

በአስር ሺዎች ከሚቆጠር የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደ መቶ ሺዎች አድገናል እኮ። ኢትዮጵያዊነት/ፍቅር ወዴት ዘመም ዘመም ነው ያለች አዝማሪ? ያንጀትን እንዴት ቢናገሩት እንግባባ ይሆን። እንዲህም ይለናል ሩሶ፤ ገዥዎች ስልጣናቸውን የበለጠ ለማጠናከር ማህበረሰባችን ሰላማዊና የተረጋጋ መሆን አለበት፤ ይህንንም ለማሳካት ደግሞ መንግስት፣ህግ እና ቅጣትም ያስፈልገናል። ገዥዎች ይህንን የሚያደርጉት ግን መብትና ፍትህ ለማስከበር ሳይሆን ያልተገባ ጥቅም የሚያገኙበትን መንገድ ለማስጠበቅና ደካማውን የበለጠ ለመጨቆን ነው ይለናል። አንድ የድሃ እንጉርጉሮ ትዝ አለኝ፤ ልማታዊ መንግስታችን የዘነጋንን እኛን ድሆቹን ይወክላል ይመስለኛል።
ያለው ስጋ ይብላ፤ እየዘለዘለ በስለታም ቢላ
የሌለው ባቄላ፤ ሲሻው እያሾቀ ሲሻው እየቆላ
ይህ ነው የድሃ እንጉርጉሮ። ዛሬ ዛሬ ግን ባቄላውንም የምናገኘው አንመስልም፤ በዚህ አካሄዳችን። ባቄላውን የሚያስከብርልን መዋቅር ያስፈልገናል ለዚህ ደግሞ ፈሪሃ ፈጣሪ ካላቸው ከትንሹ መንግስት/የየአካባቢው ሽማግሌዎች ውክልና ውጭ የሚበጀን አናገኝም።የፌደሬሽን ምክር ቤት ሳይሆን የሽማግሌዎች ምክር ቤት ያስፈልገናል። ርዕሰ ብሔሩም መመረጥ የሚገባው ከሃገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት መሆን አለበት። አማርኛው እያጠረኝ ነው መሰለኝ እና በሚከተለው የሩሶ እንግሊዝኛ ሃሳቤን ላጠቃልል።
To renounce liberty is to renounce being a man, to surrender the rights of humanity and even its duties. For him who renounces everything no indentify is possible. Such a renunciation is incompatible with man’s nature; to remove all liberty from his will is to remove all morality from his acts. Finally, it is an empty and contradictory convention that sets up, on the one side, absolute authority, and, on the other, unlimited obedience.

 

Read 2499 times