Saturday, 09 November 2013 11:26

ከዘማሪ ዘርፌ ጋር በጆን ኤፍ ኬኔዲ አውሮፕላን ማረፍያ ያወጋነው---

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(31 votes)
  • አማርኛ ለማይችሉ የአበሻ ልጆች የእንግሊዝኛ መዝሙር ለማዘጋጀት አስቤአለሁ
  • ዩኒቨርስቲ ገብቼ ሙዚቃ በመማር ተሰጥኦዬንና ችሎታዬን ለማሳደግ ተዘጋጅቻለሁ
  • ሥራችንን የሚወድና የሚያከብር ሰው ኦርጂናሉን ካሴት እየገዛ መጠቀም አለበት

                 በኒው ዮርክ የጆን ኤፍ ኬኔዲ አለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ከአንድ ሰዓት በኋላ ወደ ፍሎሪዳ የሚወስደኝን አውሮፕላን እየጠበቅሁ ነበር፡፡ ወዲያ ማዶ እንደኔው አውሮፕላን የምትጠብቅ ከምትመስል ጠይም ቆንጆ ወጣት ጋር ድንገት አይን ለአይን ተጋጨን፡፡ ኢትዮጵያዊቷን ወጣት ወዲያው ነው የለየኋት፡፡ ዘማሪ ዘርፌ ከበደ ናት፡፡ በአይንዋ ውስጥ የተመለከትኩት አንፀባራቂ ፈገግታ ነው ለአፀፋ ምላሽ ያስገደደኝ፡፡ ሞቅ ባለ ፈገግታ የታጀበ ሰላምታ ሰጠኋትና ጠጋ ብዬ ራሴን አስተዋወቅሁ፡፡ ዘማሪዋ ጆሮዋ ላይ የሰካችውን ማዳመጫ (ኢርፎን) አንስታ በጥሞና ታወራኝ ጀመር፡፡ የበረራ ሰዓት እስኪደርስ በነበረችን ጊዜም እንዲህ አወጋን፡፡ የምታደምጭው ነገር ምንድን ነው? ተመስጠሽ ነበር ልበል… /ሳቅ/ አስታውቃለሁ? ከአንድ ወር በኋላ የሚወጣውን አዲሱን መዝሙሬን ስሰማ ነበር፡፡ ወዴት ልትጓዢ ነው? ቅዳሜ እና እሁድን በአገልግሎት ለማሳለፍ ወደ ሲያትል እየሄድኩ ነው፡፡ የአሜሪካን ኑሮ ለመድሽው? በጣም ቆንጆ ነው፡፡ እዚህ አገር መኖር ነፃነት አለው፡፡

መጀመሪያ ወደ አሜሪካ የመጣሁት ለአገልግሎት ነበር፡፡ ዳላስ ያለው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጥሪ አድርጐልኝ ማለት ነው፡፡ በአሜሪካ ስቴቶች እየተዟዟርኩ ሳገለግል በአጋጣሚ የትዳር አጋሬን አገኘሁና እዚሁ ቀረሁ፡፡ እንዴት ነበር የተገናኛችሁበት አጋጣሚ? ሲያትል ገብርኤል ቤተክርስቲያን ለአገልግሎት ሄጄ ነው ያገኘሁት፡፡ በአንድ ወቅት በጋብቻ ላይ ጋብቻ እንደደረብሽ ሲወራ ነበር… ይህ በፍፁም ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ያን ጊዜ እዚህ አገልግሎት ላይ ነበርኩ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛ ነበረኝ፤ ያለመስማማት ተፈጥሮ ተለያየን... ግን ማግባቴ በመገናኛ ብዙሃን ይናፈስ ነበር፡፡ እኔ አላገባሁም፤ መግባባት ስላልቻልንና ከአገልግሎቴ ጋር በተገናኘ ብዙ ችግር ስለገጠመኝ ግንኙነታችንን ገትቸዋለሁ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ነገሩን ሳያውቁና ሳይረዱ “አገባችና ፈታች” እያሉ ወሬ ተናፍሶ ነበር። እውነት ስላልሆነ ግን ምንም አልመሰለኝ፡፡ ባለቤትሽ ለትዳር የጠየቀሽ በድምፅሽ ተማርኮ ነው እንዴ? /ሳቅ/ እሱን ነግሮኝ አያውቅም፡፡ እኔ ግን ሁልጊዜ እግዚአብሄርን ጥሩ ትዳር እንዲሰጠኝ እጠይቀው ነበር፡፡

ትዳር ትልቅ ነገር ነው፤ ከብዙ ነገር የምንጠበቅበት ነው፤ እግዚአብሄር የጠየቅሁትን ሰጥቶኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ቅዳሜና እሁድ በቤቴ አይደለሁም ..ከአስራ አምስት ቀን እስከ አንድ ወር ድረስ ለአገልግሎት በተለያዩ ዓለማት እጓዛለሁ… ባለቤቴ ይህን ስለሚረዳ ይደግፈኛል። እሱም የሥነመለኮት (ቲዎሎጂ) ተማሪ ነው፡፡ አረብኛ፣ ሩስኪና ግሪክን ጨምሮ ሰባት ቋንቋዎችን ይናገራል። የአረቦችና የሶሪያ አንጾኪያ ቤተክርስቲያን መዝሙሮችን እንዳደምጥና እንድመሰጥባቸው ያበረታታኛል፡፡ የተሻሉ መዝሙሮችን እንድሰራ፣ በሌሎች ቋንቋዎችም ችሎታዬን እንዳዳብር ያግዘኛል… በጣም ጥሩ ባል ነው የሰጠኝ፡፡ ወደ መንፈሳዊ መዝሙሮች ከመግባትሽ በፊት አለማዊ ዘፈኖችን ታቀንቅኝ ነበር… ያኔ እንደውም ፍቅርአዲስ ነቃጥበብን ትመስያለሽ ይሉኝ ነበር፡፡ ዘፈኖቼን ለማሳተም ሁሉ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ስጀምረው ታዋቂ ዘፋኝ ሆኜ ትልቅ ሰው የመሆን ህልም ነበረኝ፤ ማንኛውም ሰው እንደሚያስበው ማለት ነው፡፡ በኋላ ላይ ነው ነገሮች የተቀየሩት፡፡ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች፣ እንግሊዝኛ፣ አረብኛና ሱዳንኛ ዘፈኖችንም እዘፍን ነበር፡፡

ስንት ዓመት ዘፈንሽ? . ለአንድ ዓመት ብፅዓት ስዩም ቤት ካዛንቺስ ዘፍኛለሁ፡፡ ከዛ በፊት ደግሞ ባህርዳር የብአዴን ፖሊስ ውስጥ ለሶስት ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ ከዛ በኋላ ዱባይ ሄጄ ለሁለት ዓመት ዘፈንኩ፡፡ አገር ቤት ሳለሽ ፊልም ሰርተሻል… በአንድ ወቅት የራሴን የህይወት ታሪክ የሚያሳይ ፊልም ሰርቼ ነበር፡፡ ዝም ብዬ ዛሬ ላይ የተገኘሁ ሳይሆን እንዴት እንደመጣሁ ስለራሴ የሚያሳይ ታሪክ ነው፡፡ ስለ ህይወት ታሪኬ ያጫወትኩት ደራሲ ነው ሃሳቡን ያመጣው፡፡ ከዚያ ተመካክረን በእኔ ህይወት ሰው መማር የሚችል ከሆነ ልሞክር ብዬ ሞክሬያለሁ፡፡ ከዛ በኋላ ግን ፊልሙ አልቀጠለም። በእኛ አገር መንፈሳዊ ፊልሞች ገና አልተጀመሩም። በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ በፊልም ደረጃ ሊሰሩ የሚችሉ ብዙ ታሪኮች አሉ፤ ነገር ግን መስራት አልጀመርንም፡፡ ከእኔ ጋር ብዙ መስራት የሚችሉ ጓደኞች አሉኝ፤ እንደጌታ ፈቃድ ይሆናል፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት ምን ይመስላል? በጣም ጥሩ ነው፡፡ “እኛን አገልግይ” የሚሉ በርካታ ጥሪዎች ከተለያዩ ቦታዎች ይመጣሉ። አሜሪካ እንደመጣሁ ያወቁ በሙሉ በየስቴቱ ስለሚጠሩኝ እየሄድኩ አገለግላለሁ፡፡ ከአሜሪካ ውጪ ደቡብ አፍሪካና አውስትራሊያ ሄጃለሁ፡፡ በቅርቡ ደግሞ አውሮፓ እሄዳለሁ፡፡ ወደፊትም ብዙ ጥሪዎች ስላሉ በፕሮግራም እየሄድኩ አገለግላለሁ፡፡ ቅዳሜ እና እሁድ ሳይቀር ከአገር አገር እዞራለሁ፡፡ ኒው ዮርክ ለኑሮ ከባድ ነው ይባላል… እንዴት ነው አልከበደሽም?

ኒው ዮርክ ከአሜሪካ ስቴቶች ትንሽ ኑሮው ወደድ ይላል፡፡ ነገር ግን ባለቤቴ ትምህርት ላይ ስለሆነ ለተወሰነ ጊዜ ኒው ዮርክ መቆየታችን አይቀርም፡፡ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ወደ ሌላ ስቴት እንቀይራለን፡፡ ለጊዜው ግን እዚሁ ነን፡፡ ባለቤቴ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነው፤ በዜግነት አሜሪካዊ፡፡ እዚሁ ነው ያደገው፡፡ በተረፈ ግን የትም ሆኜ የእግዚአብሄርን ስራ ልሰራ እችላለሁ፡፡ ወደፊት ደግሞ ልጆች ይኖሩኛል፤ ቤተሰቦቼን እየረዳሁ እኖራለሁ፡፡ ከዘማሪነት ሌላ ምን እየሰራሸ ነው? ትምህርት እየተማርኩ ነው፡፡ ወደፊት ነርስ የመሆን ሀሳብ አለኝ፡፡ ግጥምና ዜማ ትደርሺያለሽ? አዎ… የመዝሙር ግጥምና ዜማ እሰራለሁ፡፡ “መንፈስ ቅዱስ” በሚለው አዲሱ የመዝሙር ካሴቴ ላይ አስራ አንድ ዜማዎች አሉ... ሶስቱን ግጥምና ዜማ ራሴ ነኝ የሰራሁት፡፡ ምንም አልል… እህቴ፡፡ የመጀመሪያ መዝሙርሽ መቼ ነው የወጣው? አምስት አመት ሆነው፡፡ በአገልግሎት ብዙ ስለተጠመድኩ መስራት አልቻልኩም፡፡ ግን በተለያዩ ጊዜ ከሌሎች ዘማሪዎች ጋር በጋራ ያወጣኋቸው መዝሙሮች አሉ፡፡

አሁን ደግሞ በሚቀጥለው ህዳር ወር ላይ የሚወጣ ሙሉ ካሴት ስራውን ጨርሻለሁ። እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ይወጣል፡፡ የኮፒ ራይት ችግር ለዘፋኞች ብቻ ሳይሆን ለዘማሪዎችም አስጨናቂ ሆኗል፡፡ ምን አሰብሽ? አገልጋይ ይለፋል ይደክማል፤ተጠቃሚ ግን አይደለም፡፡ ቢቻል ህዝቡ መተባበር አለበት። አገልግሎታችንን ሊደግፍ የሚችልበት መንገድ ይሄ ብቻ ነው፡፡ ሥራችንን የሚወድና የሚያከብር ሰው ኦርጂናሉን ገዝቶ መጠቀም አለበት። ካልሆነ ግን ለኪሳራ መዳረጋችን አይቀርም። ይሄን እግዚአብሄርም አይወደውም፤ የአንድን ሰው ትክክለኛ ስራ ባልተገባ መልኩ አባዝቶ ሸጦ መውሰድ ስርቆት ነው፡፡ ለህሊና ከባድ ነው፡፡ ህዝቡ ከጎናችን ነው የምንለው በዚህ መልኩ ሲያበረታታን ነው፡፡ ህዝቡ እንዲተባበር እንፈልጋለን፡፡ የእኔን ብቻ ሳይሆን የተለፋበትን የትኛውንም የሰው ፈጠራ ትክክለኛውን ብቻ እንዲገዛ ነው የምመክረው፡፡ ከቀድሞ ሥራሽ አንፃር በአዲሱ ካሴትሽ አድጌያለሁ፣ ተሻሽያለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ? አዎ!! አድጌያለሁ፡፡ እድገቴን ራሴ ነኝ የማየው፡፡ ምን አልባት ብዙ ሰው እድገቴ አይታየው ይሆናል፡፡ ትናንትና እና ዛሬ ግን ብዙ ልዩነት እንዳለኝ አውቃለሁ -- በእግዚአብሄር ቃል አድጌያለሁ፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ካደግሁ ደግሞ የተሻለ እሰራለሁ፡፡

የአሁኑ ስራዬ የተሻለ ነው፡፡ ብዙ ዘማሪዎች ግጥምና ዜማ ራሳቸው ናቸው የሚሰሩት... እንደ ዓለማዊ ዘፈን ከሰው ብዙ አይቀበሉም… የስጦታ ጉዳይ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ አንድ ሰው ካልተሰጠው ምንም ነገር መስራት አይችልም። ከባድ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ስጦታዎች ልዩ ልዩ ናቸው” ይላል፡፡ አንድ ሰው መስበክ፣ ሌላው መዘመር፣ ሌላው ግጥምና ዜማ መድረስ የተሰጠው ሊሆን ይችላል፡፡ ዘማሪ ትዝታውን ካወቅሽው… የራሱን ስራዎች ራሱ ነው የሚሰራው፤ ግጥሙንም ዜማውንም፡፡ በርግጥ አንዳንዴ እኔም እሰራለሁ፡፡ ከእግዚአብሄር ጸጋ ከተሰጠሽ ይቻላል፡፡ አዲሱ ስራሽ በአማርኛ ብቻ ነው ወይስ-- ሌላ ቋንቋ አልተጠቀምኩም፡፡ ወደፊት ግን ብዙ እቅድ አለኝ፡፡ ጌታ ቢፈቅድ ብዙ ልሰራቸው ያቀድኳቸው ነገሮች አሉ፡፡ በእኛ አገር በተለያዩ ቋንቋዎች መዝሙሮች መሰራት አለባቸው፡፡ እዚህ አሜሪካ ብዙ የአበሻ ልጆች አማርኛ መስማት አይችሉም፡፡ ቤተክርስቲያን ይመጣሉ፤ ግን ለማምለክ ብዙ ይቸገራሉ፡፡ በእንግሊዝኛ የተዘመረ መዝሙር የለም፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ነው እየዘመሩ ያሉት፡፡

ለእነሱ በእንግሊዝኛ መዝሙር የመስራት ሀሳብ አለኝ፡፡ ከዚህ በተረፈ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቼ፣ በዩኒቨርስቲ ደረጃ ያለኝን ተሰጥኦና ችሎታ ለማሳደግ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ በቤቴ ውስጥ የሙዚቃ መሳሪያዎች አሉኝ..ባህላዊም ዘመናዊም፡፡ እነሱንም እያጠናሁ ነው፡፡ በአሜሪካ ውስጥ በቤተክርስትያን ደረጃ ሳይቀር የተቃዋሚ፣ የደጋፊ የሚባል ነገር አለ፡፡ በዘርና በጎጥ ክፍፍል መኖሩም ይወራል..በአንቺ ስራ ላይ ችግር አልገጠመሽም? በእኔ ላይ የፈጠረው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም የማገለግለው አንዱን ጌታ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም የሚያገለግሉት ደግሞ አንዱን ጌታ ብቻ ይመስለኛል። ግን ጊዜ ባመጣው ነገር ሰዎች ይጋጫሉ፡፡ ያ ነገር እስኪፈታና እስኪስተካከል ድረስ ቅሬታና መቀያየም ሊኖር ይችላል፡፡ ግን እኔን በየትኛውም ቦታ ሲጠሩኝ፣ የሚጠሩኝን ሰዎች አክብሬ በመሄድ የእግዚአብሄርን ቃል እዘምራለሁ፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኔ የኬፋ ነኝ፣ የአጲሎስ ነኝ..ማን ነው የተሰቀለው›› ብሏል፡፡ የተሰቀለው ክርስቶስ እስከ ሆነ ድረስ እማመልከው እሱን ነው፤ ስለዚህ ስሙን ጠርቼ ታምኜ ወጥቼ እመለሳለሁ---በዚህ ምንም ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ መዝሙሮችሽን የሚያደንቁ የውጭ ሰዎች አልገጠሙሽም? ኢትዮጵያውያኖች ነጮችን ቤተክርስቲያን ይዘዋቸው ይመጣሉ--. አማርኛ አይሰሙም፤ ነገር ግን ዜማውንና የድምፄን ቅላፄ ሲሰሙ ይደነቃሉ፡፡

ለራሴም መጥተው ይነግሩኛል--.‹‹የሚያምር ድምፅ ነው ያለሽ›› ይሉኛል፡፡ አይሰሙትም ግን እንዴት ነው የሚያደንቁት--.እላለሁ፡፡ ሙዚቃ አለማቀፍ ቋንቋ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ በማይገባን ቋንቋ ሙዚቃውን ብቻ ሰምተን ‹‹ቅላፄው ደስ ሲል…ሙዚቃው ደስ ሲል›› የምንልበት ሁኔታ አለ አይደል፡፡ ወደነው የምንቃትትበት ጊዜ አለ--.ምን ማለት እንደፈለጉ ይገባናል እኮ፡፡ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተሸ ገጠር ገጠሩን ብቻ አገልግለሽ ነው የተመለስሺው፡፡ ለምንድነው? የገጠሩ ሰው ቶሎ ቶሎ ይጠራኝ ነበር፡፡ ወንጌልን የተጠማ ህዝብ ነው፡፡ እኛ ጥሪ በቀረበልን ቦታ ነው የምንሄደው። ‹‹እዚህ ቦታ ካልሰበክን፣ እዚህ ቦታ ካልዘመርን›› የሚል ሃሳብ የለንም፡፡ ሊሰበክለት፣ ሊዘመርለት ፈቃደኛ ሲሆን ብቻ ነው ልንሄድ የምንችለው። ፈቃደኛ ሆነው የጠሩን ቦታ ሁሉ እየሄድን እናገለግላለን፡፡ ከተማም ቢሆን…በአዲስ አበባ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን አገልግዬአለሁ፡፡

Read 14711 times