Monday, 18 November 2013 11:43

“የቃቄ ወርድዎት” ትያትር ሊቀርብ ነው

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(1 Vote)

ከመቶ ሃምሳ አመታት በፊት፣ በጉራጌ የሴቶች መብት ተሟጋች እንደነበረች በሚነገርላት የቃቄ ወርድዎት ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን በጥናት ላይ የተመሰረተ “የቃቄ ወርድዎት” የተሰኘ ትያትር በቅርቡ ለተመልካች እንደሚያቀርብ ብሔራዊ ትያትር ገለፀ፡፡
ትያትር ቤቱ ይሄን ትያትር ለማቅረብ ባለፈው ማክሰኞ ከጉራጌ ዞን አስተዳደር፣ ከጉራጌ ልማት ማሕበር እና ከቤተ ጉራጌ ባሕል ማዕከል ጋር የ1ሚ.259ሺ ብር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርአቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የብሔራዊ ትያትር ቤት ዳይሬክተር ጀነራል አርቲስት ተስፋዬ ሽመልስ፤ ትያትሩ ከፆታ ጋር የተያያዙ የግንዛቤ ችግሮችን ለማስወግድ እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡ “ትያትር ቤቱ ትያትሮች ከኢንተርኔት እየታጨዱ የሚቀርብበት አይደለም” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች ቦታ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው፤ የቃቄ ወርድዎት “ለወንዶች ብዙ ሚስት ከተፈቀደ ለሴቶችም ብዙ ባል መፈቀድ አለበት” ማለቷን በመጥቀስ ለሴቶች መብት መከበር ያደረገችውን አስተዋፅኦ አብራርተዋል። “የቃቄ ወርድዎት” የተሰኘውን ትያትር የደረሰው ፀሃፌተውኔት ጫንያለው ወልደጊዮርጊስ ሲሆን “አዳብና” የተባለውን ትያትር ለመድረክ ያበቃው ዳግማዊ ፈይሳ እንደሚያዘጋጀውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1767 times