Monday, 25 November 2013 10:17

ይህችን ሀገር ማን ይረከባታል?

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(0 votes)

          1 አፈወርቅ ገ/ኢየሱስንና ዘመነኞቹን ወደ ስዊዘርላንድ፣ ተክለሃዋርያት ተ/ማርያምንና ዘመነኞቹን ደግሞ ወደ ሩስያ በመላክ የተጀመረው የዘመናዊ ትምህርት ኀሰሳ፤ በአጼ ምኒልክ ታጋይነት መሠረት ሊይዝ ቢታትርም ብዙ መውጣትና መውረዶችን ዐይቷል፡፡ የምኒልክ ሕልም በልጃቸው በንግሥት ዘውዲቱ ቀጥሎ ነበር፡፡ እውነተኛ ታሪኩ የማን እንደሆነ ባይገባኝም (ለተፈሪ መኮንን የሚሠጡ እንዳሉ ሆነው) ንግሥት ዘውዲቱ ያሠሩትን የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መርቀው ሲከፍቱ፣ እንዲህ መናገራቸው ተዘግቧል - ‹‹ ለኢትዮጵያ ነጻነትና ጽናት ወሰንዋን ጠብቆ፣ አሳፍሮና አስከብሮ ለማኩራትና ለህዝቧ ልብ የታመነ ኃይል እንዲሆነው ለማድረግ መሣሪያው ትምህርትን መማር ነው›› በንግሥቲቱ ንግግር ውስጥ የተቀመጡ ቁልፍ ነጥቦች ነጻነት፣ ጽናት፣ ለህዝብ ልብ መታመን --- የሚሉ ናቸው፡፡ ሀገሬ ሀገር ናት፣ ሀገሬ ማደግ ትችላለች ብሎ ማመን፣ ሀገሬ ሉአላዊት ናት ብሎ ማመን፣ ሀገሬ ለምዕራባዊም ሆነ ምስራቃዊ የማትንበረከክ፣ የማትወድቅ፣ የማታንስ ናት ብሎ ነጻነቷን ማመን፤ አልሰደድም እሰራለሁ፣ አልዋሽም እኖራለሁ፣ አልሸነፍም አሸንፋለሁ፣ አውቃለሁ ቀን አለኝ ብሎ መጽናት፤ አልሰርቅም፣ ጉቦ አልቀበልም፣ አልቀጥፍም፣ ሀገር አልሸጥም፣ ህዝብ ከህዝብ አላለያይም፣ አልከፋፍልም ማለትና ማድረግ--- ለህዝብ ልብ መታመን ! እነዚህን ነጥቦች ሳስብና የእስከዛሬውን የሀገሬን ዘመናዊ ትምህርት ጉዞ ሳስተያይ፣ ብዙ ጥያቄዎች ይፈጠሩብኛል፡፡ የንግሥቲቱ ንግግር ዘመናዊ ትምህርትን ለማስፋፋት የታገሉት አባታቸው ሐሳብ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠሩ ክፋት የለውም። ሰፋ ባለ አእምሮ ስናየው ደግሞ አጼ ምኒልክም የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ እንደመሆናቸው፣ ከቴዎድሮስ የተረከቡት ርዕይ እንደሆነ መረዳቱ አያዳግትም፡፡ በእርግጥ በዘመነ ቴዎድሮስ ከዘመናዊው ትምህርት ሁሉ የውትድርና ትምህርትና ጥበብ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶት እንደነበር አጼው ከእንግሊዝ ጋር ጦር እስከመማዘዝ የደረሱበት ሀቅ ይነግረናል። በገዥዎች መፈራረቅና በጣሊያን ወረራ (ሁለገብ ደባ) የተነሣ የዘመናዊ ትምህርት ጉዞ ሲደነቃቀፍ ቆይቷል፡፡ ለሀገሪቱ የሚበጀው ይሄ መስመር ነው ብሎ ፖሊሲ ነድፎ ሃያ ዓመታት ሙሉ የተንገታገተው የኢህአዴግ መንግሥት ብቻ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ የመለስን እንጅ የምኒልክን ራዕይ የማስፈጸም ኃላፊነት የለብንም እንደሚለኝ ብረዳም ‹‹ነጻነት፣ ጽናትና ለህዝብ ልብ መታመን››ን የማያጐናፅፍ ፖሊሲ ማስፈጸም ግን ውጤት እንደማያመጣ ይገነዘባል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ 

         2 አባት የጭንቀት ፊቱን አውጥቶ ከጎረቤቶቹ ጋር ይወያያል፡፡ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ልጁ ከቤት ከጠፋ አራተኛ ቀኑ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ጎረቤቶቹ ሊያጽናኑት የመጡት፡፡ ልጁ የት፣ እንዴት፣ ለምን እንደጠፋ መረጃ ሳይገኝ ሰንብቷል። የቅርብ ጓደኞቹ አሉበት የተባለ ቦታ ሁሉ ሲፈለግ አዲስ መረጃ ተገኘ፡፡ ሁለቱም ጓደኞቹ ታስረዋል፡፡ ለምን? አባት ምስጢር እንዳይወጣ ይጨነቃል፡፡ በግምት አምስት አመት የሚሆነው ልጁ፤ እግር እግሩ ስር ይንከላወሳል፡፡ ልጁ ቃል እየለቀመ ያዳምጣል፡፡ አባት የጎረቤቶቹን ጉትጎታ ተከትሎ አንድ ቃል ተነፈሰ፤ (የጠፋው ልጅ እና ጓደኞቹ የመነን ተማሪዎች ናቸው) “ትምህርት ቤት ውስጥ ጋንጃ ይዘው (ሲያጨሱ) ተገኝተው ነው” አለ፡፡ ይሄኔ ህጻኑ ጠየቀ ‹‹ጋንጃ ምድን ነው?›› ብስጭት፣ ተስፋ ማጣትና ቁጭት ተደራርበው የሚነበቡበት የአባት ፊት፣ ወደ ህጻኑ ልጅ ዘምበል አለ፡፡ ሊናገር ያልቻለው ግን ፊቱ የሚናገረው አንድ እውነት ነበር “እባክህ አትጨቅጭቀኝ… ደርሰህ ለምትዘፈቅበት” የሚል ዓይነት ስሜት፡፡ አሜሪካዊ ልብወለዶች ወይም ፊልሞች ላይ እያየን ጉድ የምንልባቸው ‹ጋጠወጥነት በትምህርት ቤት› ዛሬ የሀገራችንን ትምህርት ቤቶች ያስጨነቀ ይመስለል፡፡ ለቁጥጥር አይደለም ለማሰብ የሚከብዱና የሚዘገንኑ እውነታዎችን እየሰማን ነው፡፡ በተለይ ከተማ ውስጥ ያሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብዙ ወንጀሎች መፈፀምያ እየኾኑ ነው፡፡ የወሲብ ፊልሞችን በስልክና በአይፓድ ክፍል ውስጥ መመልከት፣ በየአጥሩ ጥጋጥግ ጫት፣ ሲጋራ፣ ኃሺሽ መጠቀም፣ ግቢው ከተመቸ ግቢ ውስጥ አለዚያም የቀን ጭፈራ ቦታዎችን (ፓርቲ ቤቶች) በመጠቀም ልቅ ወሲብ መፈጸም፣ በቡድን እየተከፋፈሉ አምባጓሮና ጸብ መፍጠር፣ አልኮል መጠጥ ወዘተ. ለመምህራንና ለወላጆች የራስ ምታት መሆናቸውን እንሰማለን፡፡ (በተለይ 12ኛ ክፍሎች እንዲያከብሯቸው የሚፈቀዱላቸው (?) ፌስቲቫሎች ለዚህ ዓይነቱ ልቅነት ይበልጡን ምቹ ሆነዋል፡፡

             3 ዕለቱ ሰኞ ነበር፡፡ ከረፋዱ 4 ሰዓት አካባቢ። አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ዋናው ግቢ ቆይቼ ወደ ስቴዲዬም የሚወስደኝን ታክሲ ለመያዝ ወደ መውጫው በር እጣደፋለሁ፡፡ ‹‹በቄንጠኛ ሙድ›› ጸጉሩን ባሳመረ፣ ቁመተኛና አፍንጫ ረጅም ጎረምሳ የሚመሩ ሦስት ሴቶች ከፊቴ ይሄዳሉ፡፡ እየተጓተቱ፣ እየተላፉና እየተሳሳቁ፡፡ ከፊት እየመሩ ወጣን። ወደ ታክሲ ተጠጋን፡፡ አራት ኪሎ የሚል ታክሲ ውስጥ ገባን፡፡ ታክሲው እስኪሞላ የታክሲው ጣሪያ እስኪንቀጠቀጥ የሁካታ ቤት አደረጉት፡፡ የታክሲውን ሒሳብ ሴቶች እንዲከፍሉ ቄንጠኛው ጎረምሳ ተናገረ። የሴቶቹ ቡደን መሪ የመሰለችዋ ተቃወመች፡፡ ‹‹ኧረ እባክህ… ለምነህ ክላስ አስቀጥተኸን ደግሞ ክፈሉ ትለናለህ?›› አፍንጫማው ቀጥሎ የሚጠብቀውን ወጭ እየዘረዘረ ለማሳመን ሞከረ፡፡ ለምን ለምን ሊያወጣ እንደተዘጋጀ በዚህ ጽሁፍ አልገልጸውም። (ፍጹም ጸያፍ ነበር!) የሆኖ ሆኖ ‹‹ሊዝናኑ›› ወደ ቦሌ እየሄዱ ነበር፡፡ የእነዚህን ልጆች ተግባር ስመለከት አንድ ነገር አስታወስኩ፡፡ በ2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የአይሳካ ጉባኤ ላይ ቀረበ ተብሎ አብስትራክቱን ያነበብኩት አንድ ጥናት ነው፡፡ ጥናቱ የተሰራው በዲላ ዩንቨርሲቲ ነው፡፡ በዩንቨርሲቲው ግቢ ውስጥ በየጢሻው፣ በየጅምር ህንጻው፣ በየኳስ ሜዳው ልቅ መሳሳም ፣ ልቅ ወሲብ ብሎም ውርጃ ብርቅ አይደለም ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ ባለፉት ሁለት ዓመታት (ለአንድ መጽሐፍ ዝግጅት) በአዲስ አበባ ፣ በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በጅጅጋ፣ በባህርዳርና በጎንደር ዩንቨርሲቲዎች ‹‹እንዴት ነው?›› እያለ ጠያይቆ ነበር፡፡ ዩንቨርሲቲዎቹ ብዙ የሚያስደንቁ አጉል ነገሮች ይደረግባቸዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አላማ የተማሪዎቹን አጉል ድርጊት እየዘረዘሩ ማስተዋወቅ አይደለምና እዚሁ ላይ ቢበቃ ይሻላል፡፡ እነዚህ ፊደል ቆጠሩ እየተባሉ በየመስሪያ ቤቱ የሚሰገሰጉ ወገኖች፣ ይህን አጉል ልማዳቸውን ማስቀጠል ስለሚፈልጉ ለሥራ ግድ የሌላቸው፣ ጉቦና ጥቅማጥቅም ፈላጊ ሙሰኞች፣ ሰነፎች፣ ከሀገር ለመሰደድ ቀድመው የሚሰለፉ ተስፋ ቆራጮች፣ ሀገር ለመሸጥ የማያቅማሙ ብኩኖች ይሆናሉ፡፡ አስደናቂው ነገር በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ሆነ በዩንቨርሲቲዎች ውስጥ ያሉ እኒህን አጉል ነገሮች ይተገብራሉ ከሚባሉ ተማሪዎች ከፊሎቹ፣ በትምህርት ውጤታቸው የተሻሉ መሆናቸው ነው። ሌሊቱን በጭፈራ ቤት የምታነጋና በቢራ ግብዣ አለያም በገንዘብ ክፍያ ካገኘችው ባለሃብት ጋር ለመሄድ የማትሰንፍ የዩንቨርሲቲ ተማሪ፤ ሌሊቱን ሙሉ የተማረችውን ስትተነትን መስማት አይገድም። ይህን አስመልክቶ አብዛኛው ሰው እርስ በእርሱ የሚጣረስ ነገር ይናገራል፡፡ ‹‹ጣጣ የለውም/የላትም!›› በማለት። ጥሩ “ግሬድ” ካመጡ ቢቀብጡስ እንደማለት ነው፡፡ ለመሆኑ ለአንዲት ሀገር የትምህርት ግብ ምንድን ነው? ጥሩ “ግሬድ” ማምጣት የሚችሉ ብኩን ዜጎችን ማፍራት ነው? በዚህ አጉል ህይወት ውስጥ የሚርመሰመሱ ተማሪዎች፤ የተማሩትን ሲያነበንቡልን፣ አውቀው አውቀው ልባቸው ውልቅ ያለ ይመስለናል፡፡ ዳሩ የተሰጠውን ለመስጠት ቴፕሪኮርደርም አቅም አያጣም፡፡ ትምህርት ሰውን መለወጡን የምናውቀው ከተማሪው ደም ጋር ባለው ውህደትና ‹ተማረ› የተባለው ሰው በሚያሳየው ሁለገብ ግብረገብነት እንጅ የማርክስን ቲዎሪ ያነበነበ ሁሉ ተምሯል ማለቱ ይቸግራል፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ተደጋግሞ ተቃውሞን ሲሰማ፣ በጄ ከማለት ይልቅ ለተቃወመው ሁሉ ቅጽል ስም እያስታቀፈ የሚወነጅለው ኢህአዴግ፤ አቅም ወይስ ቅንነት ይሆን ያጣው? ሀገር ይረከባሉ የሚባሉ ወጣቶች እየባከኑ ሲያይ፣ “አሁንም መስመሬ ልክ ነው” ለማለት ያስደፈረው ያለማወቅ ወይስ ያለመፍቀድ አባዜ ይሆን?

           4 በግሌ ወደመንግስት መሥሪያ ቤት ሄጄ ጥሩ መስተንግዶ አግኝቼ አላውቅም፡፡ ሲወለድ በጥሩ ምግባር የተወለደ አጋጥሞን በጥሩ ሁኔታ ቢያስተናግደንም፣ የእሱ የበላይ ወይም የበታች አመናጭቆና አበሳጭቶ ይሸኘናል፡፡ ወጥ የሆነ ስርዓት ለማየት አልታደልንም፡፡ ዳሩ ግን አሁን ልመሰክር የሚገባኝ አንድ እውነት አለ፡፡ ከክልል ክልል፣ ከከተማ ከተማ ስንዘዋወር ባለው ነገር ሁሉ ተስፋ ቆርጠን “ምን ሥርዓት አለ” በምንልበት ሀገር ውስጥ አንጀት የሚያርስ ስርዓት ስናገኝ እንደነቃለን። በሦስት የተራራቁ ዓመታት፣ በሦስት የተለያዩ ከተሞች፣ በሦስት የተለያዩ ግቢዎች ሄጄ፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ፍጹም ድንቅ የሆነ ስርዓት ያየሁት በሀገር መከላከያ ውስጥ ነው፡፡ በግሌ ያጠናሁት ጥናት የለም። የተጠናና ያነበብሁትም እንዲሁ፡፡ ግን እንዲህ ይሰማኛል፡፡ የስራ ሠዓት አቋርጦ ጫት የሚቅም፣ ጉቦ ካልሰጣችሁኝ የሚል ወይም ጸሐይና ዝናብ የሚበግረው፣ አሊያም ወጥቶ ገብቶ አሜሪካን የሚያልም፣ ለአደንዛዥ እጽና ለብልጭልጭ ነገር ሊሸነፍ የፈቀደ ዜጋ፣ ሀገር መከላከያ ውስጥ መኖሩን አልሰማሁም፡፡ በምኒልክ እምነት ዘመናዊ ትምህርትን ማስፋፋት ያስፈለገው ነጻነት፣ ጽናትና ለህዝብ ልብ መታመንን በዜጎች ውስጥ ለማስረፅ ነው፡፡ እነዚህን አንኳር ነጥቦች የኢህአዴግ የትምህርት ስርዓት ሊፈጥራቸው አልቻለም፡፡ በሀገር መከላከያ ውስጥ ግን ያሉ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ ታግሎ የመጣው ኢህአዴግ፤ ጽናትን፣ ነጻነትን እና በህዝብ ልብ መታመንን ገንዘቡ ያደረገ ትውልድ ለማፍራት መከላከያ ላይ ያለውን የማያወላዳ አቋም፤ በዘመናዊ ትምህርቱ ስርዓትም ቢዘረጋ ጥቅምን እንጅ ጉዳትን አያተርፍም፡፡ ያለዚያማ አሁን ባለው አካሄድ ይህችን ሀገር ማን ይረከባታል?



Read 1925 times