Monday, 25 November 2013 10:21

ህይወትን ህይወት ያደረገው ሞት ነው!

Written by  አገኘሁ አሰግድ
Rate this item
(14 votes)

“ሞት የማያመልጡት ግዴታ ቢሆንም በአሟሟት ሊሸነፍ ይችላል”

       የ”አምላክ” ትልቁ ጥበቡ ሞትን መፍጠሩ ይመስለኛል፡፡ እያንዳንዱ ሃይማኖት እግሩን ያቆመው በሞት ላይ ነው፡፡ ሞት ባይኖር የሰው ልጅ፣ በአምላክ አያምንም ነበር። ሃይማኖቶች እግር ይከዳቸዋል፡፡ …ዘር ካልሞተ/ካልበሰበሰ ፍሬ አይሆንም፡፡ በዚህች ሰከንድ በሰውነታችን ውስጥ ህዋሳት እየሞቱ እራሳቸውን ባያድሱ ህልው መሆን አንችልም፡፡ ሞት እንደብዙዎቻችን እምነት፣ የህይወት ማብቂያ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ህያው አካል ውስጥ የተጐነጐነ ሞት አለ፡፡ ግልፅ ነው ሞት የሌለበት ህይወት፣ ህይወት ሊሆን አይችልም፤ ህይወትን ህይወት ያደረገው ሞት ነው፡፡ ስለዚህ ህይወት ሞት ነው፡፡ ወይም ሞት ህይወት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ህይወት፣ ህይወትና ሞት ነው፡፡ መወለድ የህይወት አካል እንደሆነው፣ ሞትም የህይወት አካል ነው፡፡ ህይወታችንን እንደምንኖር፣ ሞታችንን እንኖራለን፡፡ ሄራክሊተስ የተባለው ፈላስፋ፣ አማልክትን ሟቾች፣ ሰዎችን ግን ሞታቸውን ጭምር የሚኖሩ፣ ህይወታቸውን የሚሞቱ ዘላለማውያን ያደርጋቸዋል… እንዲህ ይላል፤ “gods are mortal, humans immortal, living their death, dying their life” ከሞት የሚያመልጥ ማንም የለም፤ ለሕያዋን ሁሉ የተሰጠ ስጦታ ነው፡፡ ዓለም እስካለች አለ፣ ዓለም ደግሞ ያለ ሞት አትኖርም፡፡ ሞት ሲሞት ዓለም ትሞታለች፡፡ ዓለም ስትሞት ሞት ይሞታል፡፡ “…አስር ዓመትም፣ መቶ ዓመትም፣ ሺ ዓመትም በሕይወት ብትኖር ከሞት ጋር ክርክር የለህም” (መፅሐፈ ሲራክ 41፣4) የሞት መልካምነት “Death destroys a man, but the idea of death saves him” E.M.Forster መፅሐፉ ሞት በአዳምና ሔዋን ጥፋት በኩል እንደመጣብን ይነግረናል፡፡ በልጅነታችን… “አዳምና ሄዋን ባጠፉት ጥፋት እኛ ላይ ደረሰ የዘላለም ሞት” ብለው እያዘመሩ የቄስ አስተማሪዎቻችን አዳምና ሄዋንን አስወቅሰውናል፡፡

እኔ ግን አዳምና ሄዋን ካመጡልን መልካም ነገር አንፃር ሊሸለሙ ይገባቸዋል ነው የምለው (እናመሰግናለን እሺ አዳምዬና ሄዋንዬ… ባላችሁበት ይመቻችሁ!) ለእግዜር ይህን የመሰለ ውለታ ውለውለት “ጥፉ ከዚህ” ብሎ ከገነት ማባረሩ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ሞት ባይኖር በእግዜር የሚያምን ማን ነው? ሃጢያት ብንሰራ አንሞት! (የሃጢያት ደሞዙ ሞት ነው ይለናል)… የንስሃ ጊዜ ያልፍብናል ብለን አንፈራ ነገር፣ ዘላለም ኗሪ ነን። እና ምን ፈልገን አምላክን እናምናለን፡፡ ከሞት በኋላ ያለ ህይወታችንን የተዋበ ለማድረግም አይደል የምናምነው? ሞት ከሌለ ታዲያ የምን ከሞት በኋላ ህይወት አለ፣ ለወዲያኛው ዓለም የተገባልን ቃል፣ ወዲያኛው ዓለም መሄድ የሚባል ነገር ስለሌለ አብሮ ይሞታል፡፡ በእርግጥ ግን በእምነቱ ከሄድን፣ ሞትን የፈጠሩት አዳምና ሄዋን ሳይሆኑ ፈጣሪ ነው፣ አዳምና ሄዋን የፈጠረውን ነው ያፀደቁት! እሱ ሞትን እፀበለሱ ውስጥ ጠቅልሎ አስቀመጠው፣ እነሱ በልተው ፈቱት (just if we take the Biblical point of view) ማንም ይፍጠረው፣ እንዴትም ይፈጠር ሞት አያሌ ጥቅሞች አሉት፡፡ አንዱ ከታካች ህይወት መገላገያነቱ ነው፡፡ ሰው መኖር ቢደክመው እራሱን ያጠፋል፣ ሞት ባይኖር ምን ያደርጋል? እኔ ግን የምር ሞት ባይኖር እራሴን የማጠፋ ነው የሚመስለኝ… (ውይይ ለካ ሞት የለም…) ለመሞት ብለን የተሰቀልንበት ገመድ የአንገት ጌጥ ብቻ ሆኖ ሊያርፍ ነው… መሞት እየፈለጉ፣ መሞት አለመቻል… ሲደብር!!! መፅሐፈ ጥበብ 7፣6 “…የሁሉም ወደዚህ ዓለም አመጣጡ አንዲት ናት፣ የሁሉም መምጣቱ እኩል ናት” ሌላው የሞት ጥቅም የእርጅና መድሃኒት መሆኑ ነው፡፡ ሞት ባይኖር እየጃጁ መኖር እንጂ መሞት አይታሰብም፡፡ ህዋሳትህ ደክመው፣ አይኖች ማየት ተስኗቸው፣ ጉልበት ከድቶህ ስትነሳም ስትቀመጥም ጫን ጫን እየተነፈስክ ትኖራታለህ እንጂ፣ ሞትን ብትለምንም አታገኘውም፡፡

እና ይህን ከመሰለው ኩነኔ መዳኛ አይደለምን? ለዚህ ተክለ ሐዋሪያት ተክለማሪያም፣ “ኦቶባዮግራፊ (የህይወቴ ታሪክ)” በተባለ መፅሐፋቸው ያሉትን ጠቅሼ ልለፍ፤ “ሞት የማይታለፍ እዳ የሆነበት ምክንያት ለካ እርጅናን ለማስወገድ ኖሯል… እንግዲያውስ ሞትን በጣም መጥላት ወይም መፍራት አያስፈልግም፡፡ ጥሩ መድሃኒት ነው፤ ያሳርፋል፡፡” (ገፅ 122) ግልግል ለፈለገውም አለሁ ባይ ነው ሞት፡፡ የሰው ፊት ከማየት ሞትን የመረጠው እንዲህ ይላል፤ “ሞት ይቅር ይላሉ ሞት ቢቀር አልወድም አፈሩ ድንጋዩ ከሰው ፊት አይከብድም” እና ከሰው ፊት ይቀለኛል ያለው ሞት ነው ይቅርበት የምትሉት? ይሄ ሰውዬ ምን አደረጋችሁ-- እስቲ? በስተእርጅናው ለህይወት ጨለምተኛ አመለካከትን የያዘው ጠቢቡ ሰለሞን፣ በመፅሐፈ መክብብ መፅሐፉ በምን እንደሚሻል ባይገልፅም፤ “ከመልካም ሽቶ መልካም ስም፣ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል” ይላል፡፡ ሞትን በአሟሟት! በብዙ ሰው ዘንድ፣ ከሞቱ አይቀር በአሟሟት ሞትን ማሳፈር ይቻላል ተብሎ ይታመናል። “አሟሟቴን አሳምርልኝ” ይላል የኛ ሰው። በጀግንነት ኖረው፣ ሞት ላይ ምላሳቸውን ሲያወጡ እድሜያቸውን አሳልፈው አሟሟታቸው የሚከፋባቸው አሉ፡፡ ጀግና የነበረን ሰው “አይሞቱ አሟሟት ሞተ… እምጵ!” ሲሉለት እንሰማለን፡፡

ይህ ከመሞትም ባለፈ፣ የአሟሟት አይነት እንዳለ ይነግረናል፡፡ የፈሪ ሞት፣ የጀግና ሞት፣ ድንገቴ ሞት፣ አስገራሚ ሞት፣ አሰቃቂ ሞት… እንዲህ ነው የማይሉት ሞት አለ፣ አሉ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ”መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለው መፅሐፋቸው፤ “ሞት የማያመልጡት ግዴታ ቢሆንም በአሟሟት ሊሸነፍ ይችላል” (183) ይላሉ፡፡ ገጣሚው ደግሞ እንዲህ ይላል፣ “አሁን የኔ አሟሟት አሟሟት ነው ወይ ጉች ጉች ያለ ጡት አንድ ቀን ሳላይ” የዚህ ደግሞ የተለየ ነው፣ ጉች ጉች ያለ ጡት አንድ ቀን ባለማየቱ አሟሟቱን አይረቤ ያደርገዋል። ምስኪን! ምናለ በዚህ በኛ ዘመን ተወልዶ ባየው… ጉች ጉች ያለ ጡት በየመንገዱ እዩኝ እዩኝ እያለ ሲማጠን ኖሮ ቢሆን አሟሟቱን በምን ይወቅስ ነበር? መቼም የዛሬ ጡት ከመታየት ወደ ማየት ተሸጋግሯል አይደል፡፡ ሰዎች በአሟሟታቸው ምክንያት ይጀግናሉ። የጀግና ሞት ይባልላቸዋል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስን ጀግንነት ከፍታ ከሰጡት ነገሮች አንዱ አሟሟታቸው ነው፡፡ ሟች አሟሟቱ የፈሪ ከሆነ ደግሞ ይነቀፋል። ዮፍታሔ ንጉሴ በ”አፋጀሽኝ” ቲያትሩ እንዲህ ይለዋል ፈሪውን ሟች፤ “ምንተ ሊቁ፣ ምንተ ሊቁ፣ ምንተ ላሊበላ! ሲሸሽ የሞተ ሰው ተስካሩ፣ ሲሸሽ የሞተ ሰው ተስካሩ አይበላ” ፍትህ የማያውቅ ሞትም አለ፡፡

ፊቱ ሲንጐማለሉበት ዝም ብሎ፣ በሌላ ጊዜ ተልከስክሶ የሚመጣ፣ አልከስክሶ የሚገድል፡፡ እንዲህ ይላል ዮፍታሄ በሌላ ግጥሙ፤ “ዋናውስ በሽታ ምንም አልነካቸው ካገገሙ ኋላ ግርሻ ገደላቸው” ሞት ፈሩትም ደፈሩት ያው ሞት ነው፡፡ የማይቀርን ነገር ከመፍራት ግን በተዛና መንፈስ መቀበሉ የተሻለ ነው፡፡ ሞትን ማወቅ፣ መቀበል… “የሰው ልጅ የመጨረሻው ጥበብ ላይ ደረሰ የሚባለው ሞት መኖሩን ሰያውቅና ሲረዳ ነው” (እኔና ቹ፣ 164) ምን ማለት ነው? ሞት መኖሩን የማያውቅ ሰው አለ፤ አዎ! የማያውቁ ሰዎች አሉ፡፡ በእርግጥ የማያውቁ ከማለት የሚዘነጉ ብንላቸው ይሻላል፡፡ ዘላለም የሚኖሩ ይመስል ሀብት ያጋብሳሉ፣ ይነጥቃሉ። እገድላለሁ ብለው ይፎክራሉ፣ እገድላለሁ ብሎ መሞት እንዳለ ግን ለአፍታም ትዝ አይላቸውም፡፡ ህይወት ሞትን ጨምሮ አይመስላቸውም፣ የሌላው እንጂ የነሱ ሟችነት ትዝም አይላቸው፡፡ የሰው ልጆች በሙሉ ሞትን ቢያውቁ እና ቢረዱ ምድር እጅግ የተዋበች ትሆን ነበር፡፡ ብዙዎች ግን ሌሎች ይሞታሉ እንጂ እነሱ ዘላለማዊ የሚሆኑ ይመስላቸዋል፡፡ ዘርማንዘራቸው በልቶ የማይጨርሰውን ሀብት ሲያከማቹ፣ ለመቼ የሚል ጥያቄ ለአፍታ አዕምሯቸው ውስጥ አይመጣም፡፡ ሞትን ለማወቅና ለመረዳት የሞት ፍርሃትን ማስወገድ ያስፈልጋል (መጀመሪያውንስ ሞት ምኑ ያስፈራል!) ሞት ሊፈራ እንደማይገባ ከሰበኩ ፈላስፎች አንዱ የግሪኩ ኢፒኩረስ ነው። ሊጐዳን እንደማይችል ለማሳየት እቺን አመክንዮ ያስቀምጣል፤ “For when you are, death is not, and when death is, you are not. Therefore, death can not harm you” ይሄው ፈላስፋ (ኢፒኩረስ) የፍልስፍና ዓላማ፣ የደስታ መሰናክል የሆነውን የሞት ፍርሃት በማስወገድ ደስታን እውን ማድረግ እንደሆነ ያምናል፡፡ “በሃይማኖት ምክንያት የተፈጠረብን የሞት ፍርሃት ተረት ነው” ሲልም ይናገራል፡፡ “Death is not evil” ይላችኋል ከፈለጋችሁ፡፡

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም በ”ስልጣን ባህል እና አገዛዝ” መፅሐፋቸው ይህን ይላሉ፤ “ልደት የሞት ዋዜማ ነው፤ ህይወት የሞት ጥሪ ነው፣ ኑሮ የሕይወት ፃዕር ነው፡፡ ሰው መሆን ይህንን እውነት ማወቅ ነው”ሰው ለምን ሞትን ይፈራል? አንደኛው ምክንያት ከሞት በኋላ ያለውን ህይወት አለማወቁ ነው። ሁለተኛ ኢፒኩረስ እንዳለው፣ በሃይማኖቶች ምክንያት የሚፈጠርበት የሞት ፍትሃት አለ፣ ተቃጥልክ ነደድክ፣ ነፈርክ እያሉ ልቡን በፍርሃት ያነዷታል፡፡ ለዛ ሲል ከሞት በኋላ ዋስትና ይሆነኛል ብሎ ለሚያስበው አምላክ ይንበረከካል፡፡ ግንኙነቱ ከለላ ፍለጋ ይሆናል፡፡ ስሙም እምነት ይባላል፡፡ እዚህ ጋ ግን አንድ ጥያቄ እናንሳ፡- አዳምና ሄዋን እፀ በለሲቷን በመብላታቸው ምክንያት ሞት መጣባቸው፡፡ እሺ ይሁን… ሌሎች እንስሳትስ ምን ስለበሉ ሞት መጣባቸው? ሞት የመጣው እፀ በለሲቷን በመብላት ከሆነ፣ ያልበሉት ላይ እንዴት ሊመጣ ቻለ? ወይስ እንስሳት ከአዳም ጋር አንድ ሆድ ነበር የሚጋሩት? 

Read 14554 times