Monday, 25 November 2013 10:50

“ከአምስት እስከ አምስት መቶ የሚገመቱ ሰልፈኞች…”

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)

‘በርካታ’ ስንት ነው?

ተፈጥሮ በፊሊፒንስ ላይ ፊቷን አዞረችባት፡፡
ድንገት ከተፍ ያለውና ሱፐር ታይፎን ሃያን የሚል ስም ያወጡለት አሰቃቂ አደጋ አገሪቱን እንዳልነበረች አደረገ፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለርሃብ፣ ለእርዛትና ለአስከፊ መከራ ዳረገ፡፡
ፊሊፒንሳውያን ሸሽተው ሊያመልጡት ያልቻሉት የጥፋት ማዕበል ሳይታሰብ ከተፍ ብሎ  አያደርጉ አደረገና ወደመጣበት ተመለሰ፡፡ አስከሬን በየአቅጣጫው የወደቀባት፣ ይልሱ ይቀምሱት… ይደርቡ ይለብሱት የሌላቸው የጥፋቱ ትራፊዎች አንዳች መላ ፍለጋ አይናቸውን ወደተቀረው አለም አሻግረው የወረወሩባት፣ እንዳታገግም ሆና የተመታች፣ ፍርስራሽ ፊሊፒንስን ትቶ ሄደ፡፡
ከአሰቃቂው ሱፐር ታይፎን ሃያን በተአምር መትረፍ ዕድለኛነትን ይጠይቃል፡፡ ሻለቃ ኢልመር ሶሪያም ከማዕበሉ ካመለጡ ዕድለኛ ፊሊፒንሳውያን አንዱ ነበር፡፡ ነበር ነው ታዲያ!...
የአገሪቱ ብሄራዊ ፖሊስ አባል የሆነው ሻለቃ ኢልመር ሶሪያ፣ ፊሊፒንስን አውድሞ ያለፈው የጥፋት ማዕበል እንደገና ተመልሶ ያጠቃው፣ አሳዛኝ ሰለባ መሆኑን ሮይተርስ ባለፈው ሰሞን ዘግቧል። ዘገባው እንደሚለው ሻለቃ ኢልመርን የዘገየውን የአደጋው የመከራ ጽዋ ያስጎነጨው የአፍ ወለምታ ነው፡፡
የአለማችን ሰሞነኛ መነጋገሪያ የሆነውን አደጋ በተመለከተ መረጃ የፈለጉ ጋዜጠኞች ወደ ሻለቃው ቢሮ ብቅ ይላሉ፡፡ እሱም ስለአደጋው አስከፊነትና ስላደረሰው ሁለንተናዊ ጥፋት መረጃ ሰጥቶ ነበር። “ሱፐር ታይፎን ሃያን ከ10ሺህ በላይ ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት ዳርጓል” በማለት፡፡ ጋዜጠኞቹ ዘገባውን ሰሩ፡፡ ዘገባውን የተመለከቱ ባለስልጣናት በቁጣ ነደው ፊታቸውን ወደ ሻለቃው አዞሩ፡፡
“ከአለቆችህ ጋር ተማክረህ መረጃ እንደመስጠት፣ የምን አፍህ እንዳመጣልህ መዘባረቅ ነው!?... ያልሞተ ሰው ሞቷል እያልክ ክፉ ማውራት ምን እሚሉት ኩሸት ነው?!” አሉት አለቃው፡፡
ሻለቃ ኢልመር ሶሪያ ለአለቃው መልስ ይስጣቸው፣ አይስጣቸው ዘገባው ያለው ነገር ባይኖርም፣ ‘የሟቾችን ቁጥር የማጋነን ወንጀል ፈጽሟልና መቀጣት አለበት’ ተብሎ መወሰኑንና፣ በዚህ የጭንቅ ጊዜ ከስራ ገበታው መባረሩን ነው ሮይተርስ ለአለም ያሰማው፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንትም ይሄን ተከትሎ፣ “የሞቱብን ዜጎች 2500 ያህል ብቻ ናቸው። ይሄ አስር ሺህ ምናምን የሚሉት ነገር ፍጹም የተጋነነ ቅጥፈት ነው!” በማለት ለሲኤንኤን ማስተባበላቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ ተጋኗል የተባለው የአደጋ መረጃው፣ ምስኪኑን ፖሊስ ለሌላ አደጋ ዳርጎታል፡፡
አዎ! ጥሩ አድርጎ መገመት አለመቻል፣ ምስኪኑን ሻለቃ ያልገመተው አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡ እርግጥ ከአደጋው ስፋትና ከፍለጋው አለመቋጨት አንጻር የሞተውን ሰው ትክክለኛ ቁጥር መገመት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ይህን መሰሉ ሰፊ ክስተት ተጠቂ ያደረገውን ሰው ቁጥር በአግባቡ መገመት አለመቻል፣ የሻለቃው ችግር ብቻ አይደለም፡፡ የብዙዎች በተለይ ደግሞ የጋዜጠኞች እንጂ፡፡
*   *   *                
“ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራትን አከናውነን፣ በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበናል”  - መንግስት
“ገዢው ፓርቲ ለበርካታ ዜጎች ስደት፣ ስቃይና እንግልት ተጠያቂ ነው”   - ተቃዋሚዎች
በርካታ ‘በርካታዎች’ን በየመገናኛ ብዙሃኑ ለበርካታ ጊዜያት የሰማችሁ በርካቶች እንደምትሆኑ ይሰማኛል፡፡ “ለመሆኑ በርካታ ስንት ነው?” ብላችሁ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ?
በርካታ፣ አያሌ፣ ዘርፈ ብዙ፣ የተለያዩ፣ መጠነ ሰፊ እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥቅል ቃላት በየዜናው ውስጥ በተደጋጋሚ (ይሄው ቃል ራሱ) ሲነገሩ ይደመጣሉ። እንዲህ ያሉት ቃላት ብዛትን የሚገልጹ መሆናቸው ባይካድም እቅጩን አይናገሩም፡፡ መሰል ቃላት በዜና ውስጥ ተደጋግመው የመሰማታቸው ሰበብ፣ አንድም ከባለ ዜናው ሁለትም ከጋዜጠኛው ይመነጫል፡፡
‘ልማቱን ለማፋጠን በርካታ ተግባራትን አከናውነን፣ በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበናል’ በሚል የሆነን ሚኒስቴር መ/ቤት ሪፖርት የሚያትት አንድ ዜና ውስጥ ሁለት እውነቶች አሉ (ታመኑም አልታመኑም)፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ውጤቶችንም አስመዝግቧል፡፡ ጥያቄው ምን ምን ተግባራት ተከናውነው፣ ምን ምን ውጤቶች ተመዘገቡ ነው፡፡ መሰል ጥያቄዎችን አደባብሶ ማለፊያ የተለመደች መላ ናት - ‘በርካታ’!!
ይህቺ ቃል መግለጫ በሚሰጡ ባለስልጣናትና በሚመለከታቸው ሃላፊዎች ብቻ ሳይሆን በጋዜጠኞችም የተለመደች ናት፡፡ እርግጥ እንዲህ ያለውን አማራጭ ለመጠቀም አስገዳጅ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ፡፡ ጋዜጠኞች መረጃዎችን በቁጥር ለማስቀመጥና ይሄን ያህል ብለው እቅጩን ለመናገር የማይችሉባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለት አማራጮች ይጠቀማሉ፡፡ አንደኛው ግምታዊ መረጃ መስጠት ሲሆን፣ ሌላው ‘በርካታ’ በሚል ቃል ነገርየውን አደባብሶ ማለፍ ነው፡፡
ችግሩ ግምታዊ መረጃ እንደየጋዜጠኛውና እንደየሚዲያ ተቋሙ አቋም የሚለያይ መሆኑ ነው፡፡ “አንድነት” ፓርቲ ከወራት በፊት የጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ በተመለከተ በተሰሩ ዘገባዎች ላይ የተፈጠረውን ልዩነት የምንረሳው አይደለም፡፡ ይሄኛው ‘ይሄን ያህል ህዝብ ተገኝቷል’ ሲል፣ ያኛው ‘የለም ይሄን ያህል ነው’ ብሎ ዘግቧል፡፡ የተሰላፊው ህዝብ ቁጥር መለያየቱም አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡
መሰል ልዩነቶች በአብዛኛው ከሁለት ወገኖች እየቅል የሆነ ፖለቲካዊ ፍላጎት ሊመነጩ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ የአለማቀፍ ጋዜጠኞች ኔትዎርክ ድረገጽ ማኔጂንግ ኤዲተር ጀሲካ ዌስ ግን፣ ችግሩ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ሞያዊም ነው ትላለች፡፡ በጉዳዩ ላይ ያስነበበችው ጽሁፍ፣ እርግጥም በሰልፈኛ ቁጥር የሚወዛገቡት አንድነትና ኢህአዴግ ብቻ እንዳልሆኑ ያሳያል፡፡ ቀጥር አሳነስክ፣ ቁጥር አበዛህ ተብለው የሚታሙም የኛ ጋዜጠኞች ብቻ እንዳልሆኑም ይጠቁማል፡፡ ጉዳዩ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሞያም ጭምር ነው ትላለች - ጄሲካ፡፡
ጀሲካ ዌስ እንደምትለው፣ ብዙ ሰዎችን የሚያሳትፉ ሁነቶችን በተመለከተ በሚሰሩ ዘገባዎች ላይ የሰዎችን ቁጥር መገመት፣ በአለማቀፍ ደረጃ የሚታይ የጋዜጠኞች ፈተና ነው፡፡ ጄሲካ፤ ግብጻውያን የመሃመድ ሙርሲን መንግስት በመቃወም በቅርቡ አደባባይ ወጥተው ያደረጉትን ሰልፍ በዋቢነት ትጠቅሳለች፡፡ እሷ እንደምትለው፣ በወቅቱ አንዳንድ ጋዜጠኞች ይህንን የተቃውሞ ሰልፍ “በአለማችን ትልቁ የተቃውሞ ሰልፍ” በማለት ጠቅሰውታል። እነዚህ ጋዜጠኞች በሰልፉ የተሳተፉትን ሰዎች ብዛት 30 ሚሊዮን አድርሰውታል፡፡ ሌሎች ጋዜጠኞች በአንጻሩ ቁጥሩን ወደ 14 ሚሊዮን ዝቅ አድርገውታል። ይህ ልዩነት ሊፈጠር የቻለው፣ የህዝቡን ቁጥር ለመገመት የሚያስችል መለኪያ ባለመኖሩ ነው ባይ ናት ጀሲካ።
በተለይ ከተቃውሞ ሰልፎች ጋር በተያያዙ ዘገባዎች የተሳታፊዎች ብዛት ከሚዲያ ሚዲያ እጅጉን የተራራቀ እንደሚሆን የጠቀሰችው ጄሲካ፣ ይህም የሚሆነው የተለያየ አቋም ላይ ያላቸው ፓርቲዎች ቁጥሩን ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ለማዋል በመፈለጋቸው ነው ትላለች፡፡
“ምን ያህል ሰው ተሳተፈ?” ለሚለው ጥያቄ መልስ የማይሰጥ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፍ ዘገባ ጎዶሎ ነው፡፡ አንባቢው፣ አድማጩም ሆነ ተመልካቹ የተሳተፈውን ሰው ቁጥር ማወቅ ያጓጓዋል። የዜና ኤዲተሮችም የዜናውን ዋጋ ከሚለኩባቸው መስፈርቶች አንዱ ይሄው ቁጥር ነው፡፡ በመሆኑም መሰል ሁነቶችን ለመዘገብ የተመረጠ ጋዜጠኛ፣ እንደምንም ብሎ የሆነ ቁጥር ይዞ መምጣት ይጠበቅበታል፡፡
ችግሩ ቁጥሩን ለመገመት ያለው ፈተና ብቻም አይደለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በዘገባ ላይ የሚቀርቡ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፍ ተሳታፊዎች ቁጥር ጥያቄና ቅሬታ የሚነሳባቸው ናቸው፡፡ ምክነያቱም የሆነ ወገን ቁጥሩ እንዲበዛ፣ የሆነ ወገን ደግሞ እንዲያንስ ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው ጉዳዩ የጋዜጠኞች ፈተና የሚሆነው፡፡ በተቃውሞ ሰልፎችና በሌሎች መሰል ሁነቶች ላይ የተሳተፈውን እያንዳንዱን ሰው መቁጠርና፣ ‘ይሄን ያህል ህዝብ ተገኝቷል’ ብሎ መዘገብ ፍጹም የማይሞከር ነገር ነው፡፡ ይሄም ሆኖ ግን እቅጩን ባይሆንም፣ ከትክክለኛው ቁጥር ጋር ተቀራራቢ የሆነ ግምት ለመስጠት የሚያስችሉ መላዎች እንዳሉ ጀሲካ ትጠቁማለች፡፡
በሙዚቃ ኮንሰርቶችና በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የተገኘውን ህዝብ ቁጥር ለማወቅ እምብዛም አዳጋች አይደለም፡፡ በስቴዲየሙ ወይም በአዳራሹ የመያዝ አቅም፣ በተቆረጠው ትኬት፣ በተያዘው ወንበር ወዘተ… አማካይነት በስነስርዓቱ ላይ የታደመውን ሰው መገመት ይቻላል፡፡ ድርጊቱ የሚከናወነው ከአዳራሽ ውጭ ወይም አደባባይን በመሳሰሉ ክፍት ቦታዎች ላይ ከሆነ ግን፣ የተገኘውን ሰው ብዛት መገመት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ለነገሩ ለዚህም መላ አለው ባይ ናት ጀሲካ፡፡ ይህ መላ ‘ጃኮብስ ክራውድ ፎርሙላ’ ይሰኛል፡፡
ኸርበርት ጃኮብስ የተባሉ አሜሪካዊ የጋዜጠኝነት ፕሮፌሰር በ1960ዎቹ ያፈለቁት ይህ መላ፣ አደባባዩን ያጥለቀለቀውን ህዝብ በሙሉ መቁጠርን ግድ አይልም፡፡ ዘዴው ቀላል ነው፡፡ መጀመሪያ በተወሰነ ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ ያሉትን ሰዎች መቁጠር፡፡ ተመሳሳይ ስፋት ባላቸው ሌሎች የተወሰኑ ቦታዎች ላይም ተመሳሳይ ቆጠራ ማድረግ፡፡ የቁጥሩን ድምር ለቦታዎቹ ቁጥር በማካፈል አማካዩን ማስላት፡፡ በመጨረሻም ይህንን ቁጥር በአደባባዩ ስኩየር ሜትር ስፋት ማባዛት፡፡ ውጤቱ በአደባባዩ የተሰበሰበውን ሰው ብዛት ያመለክታል፡፡
ሌላው መገመቻ መላ ደግሞ ፎቶግራፍ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከፍ ካለ ቦታ ላይ ሆኖ ህዝቡን ሙሉ ለሙሉ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ማንሳት። ከዚያም ፎቶግራፉን በሰንጠረዥ መከፋፈልና በአንዱ የሰንጠረዥ ክፍል ውስጥ ያለውን የሰው ብዛት፣ በሰንጠረዦቹ ክፍልፋዮች ቁጥር ማባዛት። ውጤቱ እቅጩን ባይሆንም፣ ከዝም ብሎ ግምት ለትክክለኛው የቀረበ የህዝብ ቁጥር ይሰጣል። እርግጥ ይሄኛው መላ የራሱ ችግሮች አሉበት፡፡ ክፍት የሆኑ፣ ከካሜራው እይታ ውጭ የሆኑና የተከለሉ ቦታዎችና ሰዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉና፡፡
ሰልፉ በጎዳና ላይ ከሆነም ሌላ መላ አለ፡፡ እዚህ ላይ ጋዜጠኞች ሰልፈኞች ከሚጓዙበት ጎዳና ዳር በመሆን ቆጠራ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት ግን፣ ጎዳናውን ሞልቶ የሚተመውን ህዝብ አንድ በአንድ መቁጠር አለባቸው አይደለም፡፡ እንዲህ ከሆነማ ምኑን ዘገቡት!... ቁጭ ብለው ሲቆጥሩ መዋላቸው ነው፡፡
 ጀሲካ እንደምትለው፤ ጋዜጠኞች ቀደም ብለው ከመንገዱ ዳር የቆጠራ ቦታ ያዘጋጃሉ፡፡ ሰልፈኛው ማለፍ የጀመረበትን ሰዓትና ደቂቃ ይመዘግባሉ፡፡ ከዚያም ለሶስት ያህል ጊዜ በተወሰነ ደቂቃ ውስጥ በመንገዱ የሚያልፈውን ሰልፈኛ ይቆጥሩና አማካዩን ያወጣሉ፡፡ ይህን አማካይ መነሻ በማድረግ ሰልፉ ተጀምሮ እስኪያልቅ በፈጀው ጊዜ ውስጥ በጎዳናው ላይ ያለፈውን ሰው ማስላት ይችላሉ፡፡
አንዳንዴ ደግሞ የሌሎችን ግምት መነሻ በማድረግ የራስን ግምት መስጠት አማራጭ ሊሆን ይችላል ትላለች ጄሲካ፡፡ ጋዜጠኞች በአንድ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፈውን ህዝብ ቁጥር በተመለከተ ከመንግስት፣ ከፖሊስ አካላት፣ ከሰልፉ አዘጋጆች ወዘተ… የተለያየ መረጃ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ፣ ነገሩን በጥንቃቄ መመልከትና የራስን ድምዳሜ መስጠት ያሻቸዋል፡፡
ጋዜጠኞችን ከህዝብ ቁጥር ግምት ፈተና ይታደጋል የተባለው ሌላኛው መላ ግን፣ ቴፕሪከርደር እየተዋዋሰ ለሚሰራው የኛ አገር ጋዜጠኛ የሚሆን አይመስልም፡፡
ምክንያቱም ነገርየው በኮምፒዩተር የታገዘና በድረገጽ የረቀቁ የሂሳብ ስሌቶችን መስራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይጠይቃል፡፡ ፖፑላር ሜካኒክስ የተሰኘው ድረገጽ እንዳስነበበው፣ ተቀማጭነቱን በዋሺንግተን ዲሲ ያደረገው ‘ዲጂታል ዲዛይን ኤንድ ኢሜጅ ሰርቪስ’ የተባለ ተቋም፣ በሳተላይት ቴክኖሎጂ ከአየር ላይ በሚነሱ ፎቶግራፎች አማካይነት፣ በሰልፎች ላይ የተሳተፉ ሰዎችን በመቁጠር ዘገባ የመስራት አዲስ አማራጭ ለመተግበር ተፍ ተፍ ማለቱን ተያይዞታል፡፡
በተቃውሞ ሰልፍ የተሳተፉ የበእውቀቱ ስዩም ገጸባህሪ፣ “በሰልፉ ምን ይህል ሰው ተሳትፏል?” ተብለው ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ላብቃ…
“ከአምስት እስከ አምስት መቶ የሚገመቱ ሰልፈኞች ሳይሳተፉ አይቀሩም!”

Read 1170 times