Monday, 25 November 2013 11:21

የወረቀት አሦች ምናባዊ ወግ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

ከአምስት ደቂቃዎች በፊት የሆነ ሃሳብ ከእንቅልፌ አባነነኝ፡፡ ስለምን እንደሆነ ባላውቅም ጥቅል ስሜቱ ግን ሀዘን የተሞላ ነበር፡፡ መፃፍ ፈለኩ፡፡ ከአልጋው ተነስቼ ወደ ጠረጴዛው ሄድኩ፡፡
ይመስለኛል፤ መፃፍ የፈለኩት ሰለ እሷ ነው። ስለ ሐና፡፡ እዚሁ ክፍል ውስጥ አሁን አለች፡፡ ዞሬ ብመለከታት…እኔ አሁን ስለ እሷ እያሰብኩ፣ እየተመለከትኳት እንደሆነ አታውቅም፡፡ ተኝታለች፡፡
እሷ ተኝታ እኔ ነቅቼ የራሳችንን ህልሞች እያለምን ነው፡፡ እዚህ … አሁን…፡፡
ሐና፤ በእየለቱ ስትተኛ ህልም ታያለች። ያየችውን … ከህልም እስር ቤቷ ስትወጣ፣ ጠዋት ላይ ትነግረኛለች፡፡ እኔ ህልም ማየት ካቆምኩ ብዙ አመታት አልፈውኛል፡፡ ምናልባት፤ እኔም እንደሷ በየዋህ እድሜ ሳለሁ ጠዋት ስነቃ የማስታውሰውን ህልም ተንጋልዬ አይ ነበር፡፡ ሐና ሃያ አንድ አመቷ ነው፡፡ ሰአሊ ናት፡፡ በአሁኑ አመት ከስዕል ትምህርት ቤት ትመረቃለች፡፡
ህልም አይቼ አላውቅም፡፡ ህልም በእንቅልፌ ሰአት… አይኔን ስከድን ስለማይጐበኘኝ፣ በቀን ህልም አያለሁ፤ የቀን ህልሜን ቀና ባለ ወንበር ላይ ተቀምጬ፣ ወረቀት ጠረጴዛ ላይ ደፍቼ…ህልሜን በነጩ ላይ ጥቁር አድርጌ እነቅሳለሁ፡፡
ይህ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ያየሁት ህልም ግን በቀን ከማየው ህልም እጅጉን የተለየ ነው፡፡ እኔ ሆን ብዬ የሰራሁት ድርሰትም አይደለም፡፡ እኔ የቀረፅኩት ፊልምም አይደለም፤ እንደ ቀኑ ህልሜ ቁጭ ተብሎ በተገለጠ አይን የሚታይ፡፡ ይሄንን ህልም ተኝቼ ነው ያየሁት…ከሐና ጐን፡፡ በሰላሳ አምስት አመታቴ አጠገብ የሃያ አንድ ዓመቷ ኮረዳ በተኛችበት ጥቅል ስሜቱ ሀዘን የወረሰው ህልም አየሁ፡፡ (ህልሙን ከመናገሬ በፊት አንድ ሲጋራ ባጨስ ደስ ይለኛል፤ በአይኔ ፈለኩት፡፡ አንድ ሲጋራ ከአልጋው ጐን መሬት ላይ ወድቋል፡፡ ከጐኑ መተርኮሻ ዋንጫ መስሎ ቆሟል፡፡
(መተርኮሻው በመሰረቱ ለእጣን ማጨሻነት በሸክላ ሰሪው የተጠፈጠፈ ነበር፤ የዛሬን አያድርገውና)
ስነሳ እግሬ ስር ያለውን ሃይላንድ ውሃ ተሳስቼ ገጨሁት፡፡ ደፋሁት፡፡ ክፍት ሆኖ ከተቀመጠ ቆይቷል፡፡ ክዳኑን መክደን አስባለሁ፤ ክዳኑ በአካባቢው የለም፡፡ ዛሬ በለበስኩት ሱሪ ኪስ ውስጥ ክዳኑን ዳስሼው እንደነበር ትዝ አለኝ፡፡ ከደፋሁት በኋላ፡፡ በፍጥነት ጐንበስ ብዬ የተደፋውን አቃናሁት፡፡ የፈሰሰው ውሃ አሮጌው ምንጣፍ ላይ በቅጠል ላይ እንደሚንከባለል የውሃ እንቁ ተድቦለቦለ፡፡ እንደተድቦለቦለ ግን አልቀረም፡፡ የተደፋበትን እንባ በቀጣይ እድሜው ሊያመነጨው ይችል ዘንድ አሮጌው ምንጣፍ ዋጠው፡፡ ወደ ከርስ ጨርቅነቱ መጠጠው፡፡ እጣን ማጨሻውንና ሲጋራውን ከተቀመጥኩበት ተነስቼ አመጣኋቸው፡፡ ክብሪቱ ሁለት ፍሬ ብቻ ነው ያለው፡፡ አንዱ ፍሬ ዘር የለውም፡፡ አንዱ ፍሬ ግን እሳት ወለደ፡፡ አፌን አሞጥሙጬ እሳቱን በሲጋራው ስስም “እረብሻት ይሆን?” እያልኩ እያሰብኩ ነው፡፡ እኔ በቅዠት አማካኝነት ከእንቅልፌ እንደነቃሁት፣ ሐና ደግሞ በሲጋራ ሽታ እንድትነቃቃ አልፈለኩም፡፡
እስኪሪብቶው ጐን ተቀምጬ እያጣጣምኩ ማሰብ ያዝኩ፡፡ በሲጋራ ክንፍ መንሳፈፍ የሚችለው ሃሳብ ብቻ ነው፡፡ በቂ ፀጥታ ካለ፡፡ እየጣጣምኩ ያለሁትም እሱን ነው። እስኪሪብቶው በተጋደመበት አሸልቦ ቅዠት እያየ መሰለኝ። የተጋደመ እስኪሪብቶ በመሀደሩ ተቆልፎበት ከተቀመጠ ሽጉጥ የበለጠ ያስቃል። ፈገግ ማለት ተሳነኝ፡፡
ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰአት ተኩል ላይ ፈገግ የሚል ሰው በአለም ዙሪያ የለም። እስኪሪብቶውም ቀጣዩን ታሪክ እንዴት አድርጐ እንደሚጽፍ እያለመ ነው፡፡ ሳይተኩስ በተጋደመበት ሞቶ ሊቀር ይችላል፡፡ ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰአት ተኩል፡፡ …አሁን ያለሁበት ቅጽበት … ነገ ነው የሚባለው? ወይንስ ዛሬ? ወይንስ ትናንት?...
እስክሪፕቶው ከተጋደመበት ሲነቃ እኔ ከደቂቃዎች በፊት ተጋድሜ ያየሁትን ህልም መግለጽ ብቻ ሳይሆን መፍታት መቻል አለበት። እስኪሪብቶውን ከመቀስቀሴ በፊት ህልሜን በትውስታ ከለስኩት፡፡
ይመስለኛል፤ አንድ ትልቅ ባህር ነው፡፡ ባህሩ እኔ እንዳልሆንኩ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ባህሩ እኔ ብሆን አልፈራውም ነበር፡፡ ጥቁር ነው ባህሩ፤ የሆነ የማይነጋ ሌሊት እንደሰማይ መክደኛ ሆኖ በባህሩ ላይ ተደፍቷል፡፡ ሰማዩ፤ እንደ ሃይላንዱ ክዳን በኪሴ ውስጥ ልይዘው የምችለው ክዳን ግን አይደለም፤ በጣም ተቆጥቷል፡፡ ቁጣው በእኔ እንዳልሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግን እርግጠኛ ነኝ ምንም … አንዳችም አላጠፋሁም፡፡ የክዳኑን ቁጣ ባህሩ ያስተጋባል፡፡ ከላይ የተቆጣ ሰማይ ከታች የተቆጣ ምድር፡፡ ባህሩ፤ ከመጥቆሩ የተነሳ፤ በተረጋጋበት ሰአት ውኃ ነበር ብሎ ለማመን ያዳግታል፡፡ አስፋልት እንደ ባህር ግርግዳ እየቆመና እየተነጠፈ፣ በላዩ ላይ የተገኙትን ሁሉ እያራገፈ ይመስላል፡፡
እኔ ባህሩ ላይ እየተንሳፈፍኩ ነው፡፡ እንደ አንዲት ትንሽ ጀልባ፡፡ ከጀልባም የወረቀት ጀልባ። ከጐኔ ሐና አለች፡፡ እየሳቀች ነው፡፡ ሐና እየሳቀች ነው፡፡ ባህሩ እየተቆጣ እንደሆነ እየሞተችም ሳለ የምታውቅ አትመስልም፡፡ እኔ ብቻ ጣር ላይ ነኝ፡፡ እሷ ግን እንድታውቅ አልፈለኩም፡፡ መፍራቴንም ሆነ የሚያስፈሩ መሆናቸውን የተቆጡት ሰማይ እና ምድር፡፡
የወረቀት ጀልባው እኔ ነኝ፡፡ በብረት ባህር ላይ በወረቀት ራሴን ሰርቼ ያንሳፈፍኩ፡፡ ሐናም እንደኔው ናት፡፡ በጥቁሩ ባህር ላይ የጀልባዋን ሸራ በደማቅ ቀለሞች ቀብታለች፡፡ ታሳዝናለች፡፡ እንደምታሳዝነኝ እሷ ማወቅ የለባትም፡፡  
“እንባሽ እንዳይመጣ እሺ እንዳታለቅሺ…ሳቂ እሺ” እላታለሁ፡፡ በህልም እንባ እንደማይወጣ ህልመኛው አያውቅም፡፡
ከሰማዩ የእሳት ዶፍ ይዘንባል፤ ከባህሩ ውስጥ መብረቅ ይጮሃል፡፡ ከእኔና ከሐና ጐን የሚንሳፈፉ ትልልቅ መርከቦች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ የጦር መርከቦች ናቸው፡፡ እነሱ ለመንሳፈፍ በሚፈጥሩት መንቦጫቦጭ የእኔና የሐና ጀልባ እንዳይሰምጥ እፈራለሁ፡፡
“የወረቀት ጀልባ?! ... የድንጋዩ መርከብ እንኳን የዘንድሮውን ቁጣ አይሸከመውም” ይንሾካሾካሉ አሳዎቹ፡፡
አሳዎቹ ባህሩ ማምረሩን አይተው ደረቅ መሬት ላይ ወጥተው ጢማቸውን እያፍተለተሉ፤ እርስ በራሳቸው እየተወያዩ ነው፡፡ ባህሩ ላይ ሆኖ ለሚንገላታው የሰው ልጅ ከንፈር ይመጣሉ፡፡
“የወረቀት ጀልባ…በዚህ ማዕበል የት ያደርሳል?! ባይሆን ወረቀቱ ረጥቦ እንዳይቀደድ ባዝሊን ቢቀባ ጥሩ ነበር፡፡ የወረቀት እና የጨርቅ ጀልባ በመሆን ፋንታ … የወረቀት ዓሶች እና የጨርቅ ዶልፊኖች ቢሆኑ እንኳን ከማዕበሉ ቁጣ በታች … ወደ ስር ገብተው በዋኙ ነበር፡፡ ያሳዝናል፡፡ ወይ ብረቶቹ መርከቦች ላይ ቢሳፈሩ በህብረት ጀግና የሆኑ ይመስላቸው ነበር፡፡ ሲያሳዝኑ” እያሉ አሶቹ ያወራሉ፡፡
ሐና ቀልድ መስሏታል፡፡ ትስቃለች፡፡ እጇን ልይዛት እፈልጋለሁ፡፡ ጀልባ እጅ የለውም፡፡ ጀልባ…ያውም የወረቀት፡፡ ወረቀቱ ላይ ሲሚንቶ ባስገርፍ ጥሩ ነበር፤ እንዲጠነክር እያልኩ እያሰብኩ…በግድ ፈገግ እላለሁ፡፡ ለሐና ቁጣው የቀልድ እንደሆነ ለማረጋገጥ፡፡
በዚህ መሃል ነው በጥፊ ሀይል በተከፈተ ቀዳዳ … ተገፍትሬ … ድንገት ባንኜ የነቃሁት፡፡
ተረፍኩ ማለት ነው፡፡ ከህልሙ፡፡ እኔ ብተርፍም ብቻዬን ነው፡፡ ሐናን እዛው ጭንቅ ውስጥ ነው ብቻዋን ጥያት የወጣሁት፡፡ ህልሜ ውስጥ ያገኘሁዋትን ሐና ከህልሜ በመንቃቴ ብቻዋን ቀረች፡፡
በመንቃቴ ተለያየን፡፡ እኔ ለህልሙ ሞትኩ፤ በመንቃቴ፡፡ እሷ ለንቃት ሞተች፤ ህልሜ ውስጥ በመቅረቷ፡፡
ነቅቼ ስመለከት፤ አልጋው ላይ ሌላ ሐና አለች፡፡ ገና ልጅ ናት፡፡ የገባንበት ባህር መሬት ይመስላታል። ድንገት መሬቱ ሰማይ፣ ሰማዩ…መብረቅ፣ ድፍኑ ስንጥቅ እንደሚሆን አታውቅም፡፡ ገና ልጅ ናት፤ እንቅልፍ ላይ ናት፡፡
የቅዠቱ ትዝታ እዚህ ላይ ተጠናቀቀ፡፡ እኔም ሲጋራዬን አጠፋሁ፡፡
ማጨስ ከመጀመሬ በፊት በተቀሰቀስኩበት ሀይል ለመፃፍ እንድችል የተጋደመውን እስክሪብቶ ቀሰቀስኩት፡፡ ብዕሬ እና እኔ ስንነቃ የፃፍኩት ግን እኔና ብዕሬ ተኝተን ያለምነውን አልነበረም፡፡ ፅሁፍ ራሱ በንቃት ውስጥ ያለ … ቀና ባለ ወንበር ተቀምጠው የሚያልሙት ህልም ነው፡፡ ቀና ባለው ወንበር ተቀምጬ እየፃፍኩ ባለምኩት ህልም … ወደ ጥቁሩ ባህር ተመልሼ … እንደ ሰማይ መክደኛ በተደፋው የማይነጋ ሌሊት ውስጥ … ሐናን ፈልጌ ሳገኛት እና … ሳቋ ወደ ለቅሶ ሳይቀየር በፊት ከቅዠቴ ውስጥ አውጥቼ ወደ ደህንነት ሳደርሳት አየሁ፡፡ ያየሁት፣ የታየኝ ተፅፎ ህልሜ ተጠናቀቀ፡፡
የማይነጋ የሚመስለው ሌሊት ነግቶ ፀሐይ ወጥታለች፡፡ ሐና ጐን ተመልሼ ጋደም አልኩ፡፡ በንቃት መጋደም፡፡ 

Read 1551 times