Saturday, 30 November 2013 11:58

በ“ንግስ” ላይ የነገሰ ድንቅ ሰዓሊ

Written by  ደረጀ ደምሴ
Rate this item
(2 votes)

“ድንቅና ግሩም ስራ ነው” - ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ
“መዝገቡ በኢትዮጵያ ጥበብ ላይ የራሱን አሻራ አስቀምጧል” - ሰዓሊ ታደሰ መስፍን
“እጁ ይባረክ”፤ “የስዕል ስራን ሰቀለው” - በርካታ ሰዓሊያን
ለወትሮው የስዕል አውደርዕይ ለመመልከት የሚመጣ ሰው በጣም ትንሽ ነው፡፡ ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ ግን ይለያል።

“ንግስ” ተብሎ በተሰየመው የመዝገቡ የሥዕል አውደርዕይ ላይ ከእስከዛሬው የተለየ ብዙ የስዕል ተመልካች

አስተውያለሁ። ከተከፈተበት ከህዳር 5 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ በየእለቱ ጠዋት ጠዋት የብሔራዊ ሙዚየሙ አዳራሽ

አካባቢ እስኪከፈት ተሰባስበው የሚጠብቁ ተመልካቾችን አይቻለሁ፡፡ 11 ሰዓት ላይ አዳራሹ ሊዘጋ ነው ሲባሉ

ከዓውደርዕይ ለመውጣት የማይፈልጉ ተመልካቾችም አጋጥመውኛል፡፡
የስዕል ዓውደርዕይ ለማየት የሚመጣ የሰዎች ጐርፍ በእድሜዬ የተመለከትኩት በሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ “ንግስ” የተሰኘው

የስዕል አውደርዕይ ነው፡፡
እንደመነሻ
የሰዓሊና የመምህር መዝገቡ ተሰማ የስዕል ስራዎች የቀረቡበት “ንግስ” እስከመጪው ሰኞ ክፍት ሆኖ ይቆያል ቢባል፤ ቀኑ

እንዲራዘም ከተመልካቾች ጥያቄ እየቀረበ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ የስዕል ተመልካቾችም እየመጡ እንደሆነ

ሰምቻለሁ። የፅሁፌ አንኳር ጉዳይ ግን፣ የሰዓሊውን ትንቢታዊ ሐሳቦች በማንሳት፤ እንዲሁም ከ13 ዓመት በፊት በተለያዩ

ቃለመጠይቆችና ጽሑፎች ያሰፈራቸውን ሃሳቦች ከሁለት ስዕሎች ጋር (ማለትም “ንግስ” እና “የተዘረጋ” ከተኑ ስዕሎቼ

ጋር) በማያያዝ ለአንባቢያን ማካፈል ነው፡፡
የስራዎቹ ይዘት እና የአሳሳል ዘዬው ከሰዓሊውና ከእኛ ጋር ያላቸውን የጠበቀ ግንኙነት እዳስሳለሁ፡፡
በነገራችን ላይ “ንግስ” እና “የተዘረጋ” ከተሰኙት ስዕሎቹ አጠገብ ብቻ ነው መዝገቡ አጫጭር ግጥሞችን ያሰፈረው፡፡

“ንግስ”ን ለመስራት ሶስት ዓመት የፈጀበት ሲሆን፤ “የተዘረጋ” ደግሞ አንድ ዓመት ወስዶቦታል፡፡ በጠቅላላ 15 ስዕሎች

ናቸው በአውደርዕዩ ላይ የቀረቡት፡፡
መዝገቡ ማን ነው?
“የረባ የስዕል ትምህርት በማይሰጥበትና በይሆናል በሚሰራበት ሃገር ውስጥ፣ “ሰዓሊ ለመሆን አስበህ ታውቃለህ ወይ?”

የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስቸግራል፡፡ እኔ እንደአብዛኛው  ኢትዮጵያዊ አንድ የገጠር ከተማ ውስጥ ነው

የተወለድኩት፡፡ ያደግኩበት መሬት፤ ወላጆቼ፣ የማገኛቸው ሰዎች ፣ ከት/ቤትና ከመንደር ጓደኞቼ ጋር የምጫወታቸው

ነገሮች ሁሉ በእኔነቴ ላይ ድርሻ አላቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፈጣሪ እያንዳንዱ ሰው ከሌላው የተለየ ችሎታ

እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ተሰጥኦውን ፈልጐ ያገኘ ሰው እድለኛ ይሆናል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ይህን ሣያውቀው የሚያልፍበት

ሁኔታ አለ” ይላል ሰዓሊና መምህር መዝገቡ ተሰማ፡፡
መዝገቡ ተፈጥሮ ከቸረችው ጥበብ ጋር የት/ቤት መጽሐፍት ላይ የሚያያቸው ስዕሎች ናቸው ልዩ ፍቅር ያሳደሩበት፡፡  

ክፍል ውስጥ በተለይ ደግሞ የወላጆች ቀን በሚከበርበት ዕለት የሚሰራቸውን ስዕሎች የተመለከቱ ሰዎች፤ ከሌሎች

ጓደኞቹ የተሻለ እንደሆነ እየነገሩ ሲያደንቁት  ቀስ በቀስ ስዕል መስራት ጀመረ፡፡ መዝገቡ በልጅነቱ ያደገበትን አካባቢና

መልክዐምድር፣ የተጓዘባቸውን መንገዶችና መስኮች በጭራሽ አይረሳም፡፡ የአካባቢው አኗኗርና ባህላዊ ስርዓቶችም

በአእምሮው ተቀርፀዋል፡፡ በስራዎቹ ላይ የሚያሳየን ግን፣ እውነታውን “ኮፒ” በማድረግ ሳይሆን በምናቡ ቀምሞና

አድምቆ በሚያፈካ የፈጠራ ጥበብ ነው፡፡  የመዝገቡ ስራዎች ከፍተኛ ጉልበትን፣ ሃሳብን፣ ጊዜን፣ ጥበባዊ ክህሎትን

በእጅጉ የተላበሱ ናቸው፡፡  በስዕሎቹ ውስጥ የትላንትን ታሪክ፣ የዛሬውን ማንነት እና የነገን ምኞት በእርግጥ

ትመለከታላችሁ፡፡
ከዚህ ቀደም በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስና በሸራተን አዲስ የመዝገቡን በርካታ ስራዎች ተመልክቼአቸዋለሁ፡፡ ስራዎቹ

ከእለት ወደ እለት፣ ከዓመት ወደ ዓመት፣ በይዘትና በቅርጽ፣ በአሣሣል ዘዬና በቀለም አጠቃቀም….እያደጉና እየመጠቁ

ሲሄዱ አስተውያለሁ፡፡
የመዝገቡ ስራዎች ትላንት እና ዛሬ
ሰዓሊ መምህር መዝገቡ ተሰማ ተወልዶ ያደገበት አካባቢ በስራዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰቡም ላይ ተጽእኖ

እንዳለው በ1993 ዓ.ም በወጣው ፈርጥ መጽሔት ቁ.24 ተናግሯል፡፡ “የአስተዳደግ ተጽእኖ በጣም ብዙ ነው፡፡ አንዳንዴ

በቃላት የሚነገር አይደለም፡፡ ገጠር ውስጥ የሚደረጉና የሚታዩ ነገሮችም አሉ፡፡ በአካባቢያችን ቤተክርስቲያን አለ።

የታቦትና የክብረ በዓላት ንግስ አለ፡፡ ከብቶችን ተከትለህ በእረኝነት ትሄዳለህ፡፡ ከጓደኞችህ ጋር ሆነህ ስትጮህ የገደል

ማሚቱ አለ፡፡ እነዚህ ነገሮች  ዝም ብለው  የትም ዋዥቀው የሚቀሩ አይደሉም። ስላደግህ፣ ስለተማርክ፣ ስላወቅህ

ከውስጥህ አይወጡም፡፡” መዝገቡ ከዛሬ 13 ዓመት በፊት በሰጠው በዚህ ቃለመጠይቅ፤ ወደፊት የሚሰራቸውን ስዕሎች

አመልክቷል፡፡ ሁለቱ ትንቢታዊ ስራዎቹ
በመዝገቡ ስራዎች ውስጥ፣ ከትላንት እስከ ዛሬ፣ የገጠር ህይወት አለ፤ ከብቶች፣ እረኝነት፣ የገጠር ሴት…ስራዎቹ ላይ

ፍንትው ብለው ይንፀባረቃሉ። ለአብነት፣ “ነጭ በነጭ” “ከስራ መልስ”፣ “እሷ” ፣ “የአገር ልጅ” ፣ “ጥበብ” የሚል ስያሜ

የሰጣቸው ቀደምት ስራዎቹ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ዘንድሮ “ንግስ” ብሎ በሰየመው የስዕል ዓውደርዕይ ላይ ደግሞ፣ ጥበቡን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል፡፡ በተለያየ ይዘትና

ቅርጽ፣ ቀምሞና ልቅም አድርጐ፣ የገጠር ህይወትን ከመልከዓምድር ጋር፣ ከብቶችን ያሰማሩ ወጣቶችን ከአካባቢው

አስገራሚ ቋጥኞች ጋር አዋህዶ የሰራቸውን ስዕሎች ስትመለከቱ፣ በልጅነት እድሜ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ሲጮህ

የሚሰማውን የገደል ማሚቶ ማዳመጥ የምትችሉ ይመስላችኋል፡፡
ከዛሬ 13 ዓመት በፊት በሰጠው ቃለመጠይቅ ላይ ሌላ ነገርም ጠቅሷል፡፡  አካባቢያቸው ላይ ቤተክርስቲያን፣  ታቦትና

የክብረ በዓል ንግስ እንዳለ ተናግሮ ነበር፡፡ ይህ የያኔው ቃለምልልሱ፣ የኋላኋላ “ንግስ” የሚል ስራ እንደሚሰራ ለእኔ

ጠቋሚ ነበር፡፡ የስነጥበብ ሰው ወደፊት የሚሰራውን ስራ አስቀድሞ አእምሮው ውስጥ ይታየዋል ማለት ነው ያስብላል፡፡

ደግነቱ፣ መዝገቡ በምናቡ ውስጥ የነበረውን አውጥቶ የመግለጽና የማሳየት ጥበብ ተክኗል፡፡  ይሄውና “ንግስ” የተሰኘውን

5ሜትር በ2 ሜትር ስፋት የተሰራውን ድንቅ ስዕል አበርክቶልናል፡፡ ይህ የስዕል ስራ ከያዘው ሃሳብ ጀምሮ የገፀባህሪያቶቹ

ብዛትና ስብጥር፣ የቀለም አጣጣል፣ የታሪክ አወቃቀርና ቅንብር፣ በአጠቃላይ ልቅም ተደርጐና አምሮ፣  መሰራቱን

ስንመለከት፣ የንግስ ስርዓቱ በእውን እየተከናወነ እንደሆነ ይመስለናል፡፡ ከዚያም በላይ አስደናቂ የክብር እና የሞገስ

መንፈስ ያድርብናል፡፡  
መዝገቡ ስለስራዎቹ ቀድሞ መተንበዩን “ንግስ” በሚለው ስራው ላይ አይተናል፡፡ ከአመታት በፊት በሃሳቦቹ ወጥኖ፣

በምናቡ ውስጥ ፀንሶ ዛሬ በእውን ያቀረበልን ሌሎች ስዕሎችም ነብይነቱን ይመሰክራሉ። ከእነዚህ ስዕሎች መካከል

አንዱ፣ በ1.5 X 3.9 ሜትር ስፋት የተሰራውና “የተዘረጋ” የተሰኘው ስዕል ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ የ“3D” ባህርይ

እንዲጐናፀፍ ተደርጐ የተሰራው ይሄው ስዕል፣ የእንቅስቃሴ ባህርይ ተላብሷል፡፡ ከበስተኋላ ብዙ ርቀት የሚጓዝ የቁጥሮች

መልክዐምድር አለ፡፡ ከብቶች ከተሰማሩበት መስክ ወዲህ ደግሞ በመሃለኛ ስፍራ ከቋጥኝ ላይ የተንጠራራ ወጣት እጁን

ወደፊት ዘርግቷል፡፡
መዝገቡ ዛሬ ያቀረበልን ይህን ድንቅ ስዕል እንደሚሰራ የሚጠቁም ሃሳብ ያካፈለን ከበርካታ አመታት በፊት ነው፡፡
“መስመር፤ በሥነ ጥበብ ንድፈ ሃሳብ ቀማሪዎች እይታ” በሚል ርዕስ “ብርሃንና ጥላ” በተሰኘው ጋዜጣ ላይ ግንቦት 1993

የፃፈው ሃሳብ እንዲህ ይላል:-
“መስመሮች (በስዕል) ጥበብ ቅንብር ውስጥ በአግባቡ እና በጥንቃቄ ካልተያዙ የስዕልን የቅንብር ህብረት ያዛባሉ፡፡

ስዕሉንም ለሁለት እና ከዚያም በላይ የተከፋፈለ፤ እንዲሁም በአላዋቂነት እና በዘፈቀደ የተሰራ ያስመስሉታል፡፡ ለምሣሌ፣

ጣት ወደ አንድ አቅጣጫ ሲቀሰር፣ በፍጥነት ወደተቀሰረበት አካል የምንዞረው፣ በጣቱ እና በአካሉ መሃከል (ምናባዊ)

መስመሮችን እየሞላን ነው”
መዝገቡ ከዚህ የመስመር ንድፈ ሃሳብ በመነሳት፣ ከሰው ሃሳብና እንቅስቃሴ ጋርም አስማምቶ በማጥናት የራሱን ስሜት

የሚገልጽባቸው እውን መስመሮችንና ከሰው እንቅስቃሴ ጋር የሚጣጣሙ ምናካዊ መስመሮችን በማዋሃድ፣ የ3D ባህርይ

የተጐናፀፈ ድንቅ የስዕል ስራ በ “ንግስ” የስዕል ዓውደ ርዕይ ላይ አቅርቦናል፡፡
የመዝገቡ ስዕሎች በሙሉ በከፍተኛ ጥናትና ምርምር የተሰሩ ናቸው፡፡ ያለምክንያት አይደለም። “እኔ ከዓለም አንደኛ የሆነ

ስዕል ለመስራት ነው የምነሳው፡፡ አለምን የሚያነቃንቅ ስራ እንዲሆንልኝ እፈልጋለሁ፡፡” ብሎ ነበር ከዛሬ 13 ዓመት

በፊት፡፡ እውነትም መዝገቡ የትንቢት ቃሉ ዛሬ እውን ሆኖ ድንቅ የሆኑ የስዕል ስራዎቹን አሳየን፡፡
ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ፣ ትልቅ ነገር ተመኝቶ፣ ያንን በሚመጥን ጥረት ቃሉን አክብሯል፡፡  እኔ የሚያሳስበኝ፤ እኛ የዚህ

በረከት ተቋዳሽ ለመሆን የታደልን ሰዎች፤ የተቻለንን ያህል እየተመኘን ለጥረት መነሳትና ቃላችንን ማክበር እንችላለን

ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
እነዚህ ድንቅ የሐገር ሃብት የሆኑ የመዝገቡ ስዕሎች፣ በክብር እንዲቀመጡና ሁሉም ሰው እንዲያጣጥማቸው ማድረግ

ያቅተናልን? የመንግስት አካላትና ግለሰቦች (ባለሃብቶች) በመተባበር ስዕሎቹ በቅርስነት ለህዝብ ዘወትር በቋሚነት

እንዲታዩ ወደ ብሔራዊ ሙዚየም በማስገባት፣ ኃላፊነታችን መወጣት ይገባናል፡፡ ከእንግዲህ የመዝገቡ ስራዎች

የኢትዮጵያ ሃብት ናቸው፡፡
በ “ንግስ” የስዕል ዓውደርዕይ ላይ የቀረቡትን 15 ስዕሎች ለመስራት  6 ዓመት ፈጅቶበታል፡፡ በአጭር ጊዜ ብዙ ስራ

መስራት እየተቻለ፣ ለምን ብዙ ጊዜ የሚወስድ ስዕል ትሰራለህ ብትለኝ የምርጫ ጉዳይ ነው ይላል መዝገቡ፡፡ “በአንድ

ስዕል ላይ ብዙ ጊዜ መውሰዴ ምንም አይቆጨኝም፡፡ ይልቅ ለመስራት እየፈለግሁ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ስጠመድ

ነው የምበሳጨው፡፡” በማለት ለጥበብ ያለውን ፍቅርና ጽናት ይገልፃል መዝገቡ፡፡
የመዝገቡ ተሰማ 15 የስዕል ስራዎች፣ ማንኛውንም ተመልካች የሚያስደንቁ ቢሆኑም ይበልጥ ደግሞ ሰዓሊዎችን

አስደምመዋል፡፡ በርካታ ሰዓሊያን ስራዎቹን እየደጋገሙ ለማየት ሲመላለሱም  አስተውያለሁ፡፡

Read 2715 times