Saturday, 07 December 2013 13:03

የፀጉር አስተካካዩ ኑዛዜ

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(12 votes)

(በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ አጭር ልብወለድ)

ሰዎች ሲያቆላምጡት “ገብሬ” ይሉታል፤ ሙሉ ስሙ ግን ገብረሚካኤል ነው፡፡ በሰፈራችን ነዋሪነቱ ለብዙ ጊዜ ይታወቃል። ዝምተኛ፣ ለአለባበሱ እምብዛም ትኩረት የማይሰጥና ብዙ ጊዜ ለብቻው መሄድ ብቻ ሳይሆን ማውራትም የሚወድ ነበር፡፡ አንድ ጥዋት የዕድራችን ጥሩንባ ነፊ ከየተኛንበት በጥሩንባው ድምጽ ቀሰቀሰና የገብሬን ድንገተኛ ሞት አረዳን፡፡ ገብሬ ሞቶ የተገኘው በኪራይ በሚኖርባት አንድ ክፍል ውስጥ ራሱን ሰቅሎ ነው፤ አልጋው ላይ የሞቱን ምክንያት የምታስረዳ አንዲት ገጽ ወረቀት ተገኝታለች፡፡ “ይድረስ ለሚመለከታችሁ ሁሉ! ግን የእኔ ጉዳይ ማንን ይመለከታል? ኤልሲን? መንግሥትን? ግለሰቦችን? ቀበሌውን? ወይስ እግዜርን? ሁሉም አይመለከታቸውም፡፡ የሚመለከታቸው ቢሆኑማ ይህን ያህል ዘመን የመከራ ዶፍ ሲወርድብኝ አንዳቸው እንኳ “አይዞህ” ይሉኝ ነበር፡፡ እንዲያውም እኔ በችጋር አለንጋ በተገረፍሁ ቁጥር ከጐኔ ሆነው ከማበረታታት ይልቅ ቁስሌ ይበልጥ እንዲያመረቅዝ በስንጥር ይወጉኝ ነበር፡፡

የሆነ ሆኖ ቢመለከታቸውም ባይመለከታቸውም ፍጻሜዬን ግን ሊያውቁ ይገባል፤ ለዚህ አይደል ይችኑ የኑዛዜ ጽሑፍ ማስፈሬ፡፡ ኤልሲንና ውሽማዋን ያሉት ሞቴ ሊያስደስታቸው ይችል ይሆናል፡፡ ምን ቸገረኝ? ቢፈልጉ ዲጄ ቀጥረው የብሔር ብሔረሰቦችን ዘፈን እያስዘፈኑ ይጨፍሩ፤ ልብ ካላቸውም ለዛሬዋ ዕለት እንኳ ትንሽ ይዘኑልኝ፡፡ ግን ከዛሬ በኋላ ቢያዝኑልኝስ ምን ይፈይድልኛል? ለነገሩ ደብዳቤ የምጽፈውም ዝም ብዬ ነው፤ እኔን ሰው ብሎ ማን ያነብልኛል? አይ መነበብስ ይነበብ ይሆናል፤ የእኛ አገር ሰው በቁም እርዳ አይበሉት እንጂ ወሬ ማዳነቅማ ማን ብሎት? የቤት ሠራተኞችን ለዘበኛና ለመንደር አውደልዳይ ሲያቃጥሩ የሚውሉት ኤፍ ኤሞችስ ለዚህማ ማን ይቀድማቸዋል? ወሬውን እየተቀባበሉ ያራግቡትና ቢያንስ ከንፈራቸውን የሚመጡልኝ “ደጐች” ይኖሩ ይሆናል፡፡ ታሪኬን በአጭሩ መጻፍ ቢጠቅመኝም ባይጠቅመኝም ቢያንስ በዚህ እድሜዬ ለምን ሞቴን እንደመረጥሁ፣ ማንም እንዳልገደለኝ፣ ግን ቤት ያከራዩኝ ሰዎች በተለይ ጋሼ ዋለልኝ በሞቴ ተጠርጥረው አንድ ሌት እንኳ በፖሊስ ጣቢያ እንዳያድሩ ስል ይችን ኑዛዜ መጻፍ ግድ ሆኖብኛል፡፡

እናቴ ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ ነበር የምትኖረው፡፡ አባቴን ግን እንኳን እኔ እስዋም አታውቀውም፡፡ የተረገዝሁት ከአንድ ማንነቱ ከማይታወቅ እረኛ መሆኑን ነግራኛለች፡፡ እናቴ የምትተዳደረው ኩበት ለቅማ፣ እሱኑ ተሸክማ መንደር ለመንደር እየዞረች በመሸጥ ነበር፤ በአንድ ጐደሎ ቀን እንደልማዷ ኩበት ለቀማ መስክ ወርዳ ሳለ፣ ድንገት መዕላከ ሞት የመሰለ እረኛ ተከመረባትና ተረገዝሁ፤ እኔን ለማሳደግ ያላየችው የመከራ አይነት የለም፡፡ ራስዋን እየቀጣች እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ብታስተምረኝም ሊያስቀጥለኝ የሚችል ውጤት አልመጣልኝም፡፡ በመሆኑም ከህጻንነቴ ጀምሬ እሰራው የነበረውን የአገናኝነት ሥራ አጠንክሬ ቀጠልሁበት፡፡ በዚህ ሥራ የማይናቅ ብር አገኝ ነበር። የተሻለ ብር የሚያስገኝልኝ ግን ባለትዳር ሴቶችን አሳምኜ ከሚፈልጓቸው ወንዶች ጋር ሳገናኝ ነበር። ምክንያቱም ባለትዳር ሴቶች እንደ ተማሪዎችና ሴት የመንግሥት ሠራተኞች በቀላሉ አይገኙም፡፡ ቢገኙም ሆቴል መግባት ስለማይችሉ የሚገናኙበትን ቦታ ማዘጋጀትም የእኔ ኃላፊነት ሰለነበር ሥራው አስቸጋሪ ነው፡፡ ደብረ ብርሃን ጠባብ ከተማ በመሆኗ እንኳንስ እንዲህ ላለው ጥብቅ ምሥጢር ለሌላውም ቢሆን አስቸጋሪ ናት፡፡

ስለዚህ ተፈላላጊዎችን የማገናቸው ዘመድ ቤት፣ ወይም ጠበል የሄዱ በማስመሰል ጫካ ውስጥ ነበር፡፡ ዘመድ የሚባለው ብር ተከፍሎት አልጋውን የሚያከራይ ሁነኛ ሰው ወይም ከጓደኞቼ የአንዱ ቤት ሲሆን ሰዋራ ቦታ ሁሉ ብዙ ሥራዎች ተሰርተውበታል፡፡ እነሱ ዓለማቸውን ሲቀጩ ውስጤ በፍትወት እየነደደ የጥበቃ ሥራ ሁሉ አከናውን ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ የአንዱ ዶክተር ሚስት “ወደ ጉር ገብርኤል ጠበል ሄድሁ” ብላ ካዘጋጀሁላት ሰዋራ ቦታ ከሚፈልጋት አንድ ባለ ትዳር ጋር ዓለሟን ስትቀጭ፣ ዶክተሩ ባሏ ለካ ይከታተላት ኖሮ ያረጁ መነኩሴ መስሎና ራሱን በልብስ ለውጦ ከች አለ። ወዲያው አንድ ጥይት ተኮሰና ታፋዬን መታኝ፤ ሚስቱና ውሸማዋ ተኩሱን ሰምተው ከወደቁበት ሲነሱ የተቀባበለ ሽጉጥ ተደግኖባቸው አዩ፡፡ ሚስቱን በሁለት ጥይት ደረቷን ከሰነጠቀ በኋላ፣ ውሽምየው ሱሪውን ሳይታጠቅ ሬሳዋን ተሸክሞ ወደፊት እንዲሄድ ዶክተሩ አዘዘው፤ ውሽምዬው በሃፍረትና በድንጋጤ ክው እንዳለ የታዘዘውን መፈፀም ግዴታው ነበር፡፡ ወደፊት በሄደ ቁጥር ወደ አደገኛው የአሞራ ገደል እየተጠጋ መሆኑን በፍጹም ልብ ያለ አይመስልም፡፡ አሞራ ገደል ጫፉ ላይ ሲደርስ የተሸከመውን አስከሬን ቁልቁል እንዲወረውረው በዶክተሩ ታዘዘና ያለ አንዳች ማቅማማት ፈጸመው። ቀጠለና “ወደኔ ዙር!” የሚል ትዛዝ ሰጠው፤ ውሽምየው በፍርሃት እየራደ ወደ ዶክተሩ ዞረና መሬት መሬቱን ያይ ጀመር፡፡

ወዲያው ራቁት የነበረ ብልቱን በጥይት መታውና ተንገዳገደ፤ በሁለተኛው ጥይት ግንባሩን ሲፈልጠው ወደ ዶክተሩ ክንብል አለ፤ አስከሬኑን የሚስቱ ሬሳ ወደተጣለበት ገደል ወረወረና ይፎክር ጀመር፡፡ ቀጣዩ አስከሬን እኔ እንደምሆን ስለተረዳሁ እንደምንም ተንፏቅቄ ቦታ ቀየርሁ፤ የተመታ እግሬን አንገቴ ላይ በነበረው ፎጣ ግጥም አርጌ አሰርሁና የደሙን ነጠብጣብ ተከትሎ እንዳይመጣ አፈር አለበስሁት፡፡ ግን በደንብ ቢፈልገኝ ብዙም ስላልራቅሁ በቀላሉ ሊያገኘኝ ይችል ነበር፤ ሆኖም እኔን በመፈለግ ፈንታ ሲያቅራራና ሲፎክር ቆይቶ ያቀባበላቸው ጥይቶች እስከሚያልቁ ድረስ ወደ ሰማይ ከተኮሰ በኋላ ሚስቱና ውሽማዋ ወደ ወደቁበት ገደል ራሱን ወረወረ፡፡ አለመሞቴ ቢያስደስተኝም ለሶስት ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኔ አሳዘነኝ፡፡ እንደምንም እየተንፏቀቅሁ አንድ ለጋ ባህር ዛፍ ዘነጠልሁና እሱን ምርኩዝ በማድረግ ወደ መኪና መንገድ አመራሁ፤ እግዜርም እንደ ሰው ጨካኝ አለመሆኑን ያወቅሁት ያንለት ነው፡፡ ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች እንዲያሳፍሩኝ ብማጠናቸውም በጄ የሚሉኝ እንዳንጣሁ ሁሉ አንድ የቤት መኪና የሚያሽከረክሩ አዛውንት ግን ሳልጠይቃቸው አጠገቤ መጥተው መኪናቸውን አቆሙ፡፡ በመንገድ ላይ ማንነቴን ደብቄ፣ እግሬን የተጐዳሁትም በዱርዬ ተደብድቤ መሆኑን እየነገርኋቸው አዲስ አበባ ገባን፡፡ አዲስ አበባን ደሞ ከወሬ በቀር አላውቃትም፤ ግን በመኪናቸው ላመጡኝ አዛውንት አውቶብስ ተራ አካባቢ ዘመድ እንዳለኝ ዋሽቼ ነግሬያቸዋለሁ፡፡

አዲስ አበባ ስደርስ ግራው ገባኝ፤ ረጋ ብሎ መሄድ የሚያስቀጣ ይመስል መኪናውም ሰውም ይጣደፋል፡፡ ለተወሰኑ ቀናት መንገድ ላይ እያደርሁ በበረንዳ አዳሪዎች ስታገዝ ቆየሁ፤ ቁስሌ ቢድንም እንደ ቀድሞ መሮጥ የማይታሰብ ሆነ፡፡ ስለዚህ ጓደኞቼ “ሸንኮ” የሚል ቅጽል አወጡልኝ፡፡ “ሸንካላ” ማለታቸው ነው፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ “ጋሼ አበራ” የሚባሉ ደግ ሰው ሁልጊዜ ጥዋት ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር ከሱቃቸው በረንዳ ላይ መደዳውን ተኝተን ያዩናል፤ እኔን በሸንካላነቴ ምክንያት ያዝኑልኝ ስለነበር ለአንድ የወንዶች ውበት ማሰልጠኛ ብር ከፍለው እንድማር አደረጉ፡፡ በትምህርት አቀባበሌ የተሻልሁ ስለነበርሁ፣ ስልጠናውን እንደጨረስሁ ማሰልጠኛው በመምህርነት ቀጠረኝና ደሞዝ ማግኘት ቻልሁ፡፡ ትንሽ ገንዘብ አጠረቃቅሜ ምስኪን እናቴን ለመርዳት ሳጠያይቅ በድንገት ስለጠፋሁባት እኔኑ ፍለጋ በየቦታው ስትንከራተት ቆይታ፣ በሃዘንና በችጋር ባዶ ቤት ውስጥ ሞታ መገኘቷን ሰማሁ። ራሴን መቆጣጠር ባለመቻሌ በሽተኛ ሆንሁና ለእናቴ ያጠራቀምሁትን ገንዘብ ለህክምና ተቋማት መገበር ግድ ሆነብኝ፡፡ ሥራዬን በተገቢው መንገድ ማከናወን ባለመቻሌም ከውበት ማሰልጠኛው ተባረርሁ። ግን ከአንድ ፀጉር ቤት ተቀጠርሁና መሥራት ጀመርሁ፤ ሆኖም የተደራረቡ ችግሮች ገጠሙኝ። አንደኛ የአንዳንዱ ሰው ፎረፎር አመድ ላይ ተንከባልላ የተነሳች አህያ ይመስል ለማበጠር ትንሽ ስነካው በአፍ በአፍንጫዬ ግጥም ይልና መተንፈስ እስከሚያቅተኝ ድረስ ጤናዬን ያውከዋል፡፡ ሁለተኛ የፀጉሩ ብናኝ ሳንባዬን እየዘጋ እቸገር ጀመር፤ ከሁሉም ችግር የሆነኝ ግን የኤልሲ ጉዳይ ነው፡፡ ኤልሲ ሴተኛ አደራ ብትሆንም በጣም የምወዳት ልጅ ናት፡፡ “የሴተኛ አዳሪነት ህይወት ሰልችቶኛል እንጋባ” ብላ አብረን እየኖርን ሁሉ ትባልግ ነበር፡፡ ከልቤ ስለምወዳት ብቻ እንደማላውቅ ሆኜ አብሬያት ለመኖር ተገደድኩ፡፡

ከእሷ ውጭ ዘመድ የለኝማ! አንድ ቀን ግን መረረኝ፤ ሥራ ላይ ስላመመኝ በጊዜ ነበር ወደ ቤቴ ያመራሁት፡፡ ያችን ምስኪን መዝጊያ እንደ ልማዴ ገፋ አድርጌ ስገባ ኤልሲ ከምኖርበት ቤት ዘበኛ ጋር ክርና መርፌ ሆነው አገኘኋቸው፡፡ ከመደንገጤ የተነሳ እንደ ተወጋ አጋዘን ጓጉሬ ወደቅሁ፡፡ ስነቃ ኤልሲ የለችም፤ ዘበኛው ግን በእሱ ብሶ የጐሪጥ ሲያየኝ ነደደኝ፡፡ የት እንደ ሄደች ልጠይቀው አማረኛና ቅናት አፌን ለጐመው፡፡ ትመጣለች ብዬ ብጠብቃትም በዚያው የውሃ ሽታ ሆነች፡፡ በእጅ ስልኳ ደወልሁለት፤ መጀመሪያ አላነሳችውም፡፡ በሁለተኛው ግን አነሳችና እንደ ዋልጌ ዝንጀሮ አስካካችብኝ፤ ቀጥላም “ዘቡሌውን አየኸው አይደል እንዴት እንደሚሠራ ሸንኮ” ብላ ስልኩን ጠረቀመችው፡፡ ከድርጊቷ ይልቅ ሳቋ ሲያናድድ አይጣል ነው፡፡ ደሞስ “ዘቡሌው እንዴት እንደሚሠራ አየኸው አይደል” ያለችኝ ምን ማለት ፈልጋ ነው? እስከዚያን ቀን ድረስ በወንድነቴ ትኮራና ትደሰትበትም እንደነበር ራሷ በአንደበቷ ነግራኛለች፡፡ ቢሆንም የእጄን ያገኘሁ ያህል ይሰማኛል፤ የሶስት ሰዎች ህይወት በአንድ ቀን እንደ አበባ የተቀጠፈው በእኔ ምክንያት አይደል? ግን ሳላስቀይማት ለምን ታስቀይመኛለች? ሸሌ መሆኗን እያወቅሁ ነው ያገባኋት፡፡ በኤልሲ ድርጊት እየተበሳጨሁ መሥራት ሁሉ ተሳነኝ፡፡

ዘበኛውም በወጣሁ በገባሁ ቁጥር ይገላምጠኛል፤ ብቻዬን ስሆንም አንድ ቀን እንደ ዶሮ አንገቴን ጠምዝዞ ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ እንደሚጨምረኝ ይዝትብኛል፡፡ ከዚህ ይባስ ብለው ትናንት እሱና ኤልሲ በእሷ ስልክ ደወሉልኝና ከአንድ ቤርጐ ውስጥ ዓለማቸውን እየቀጩ መሆናቸውን አረዱኝ፡፡ ሲሳሳሙ ሁሉ በስልክ ያሰሙኝ ነበር፡፡ ቢችሉ ሁለቱም መለመላቸውን ሆነው የሚሠሩትን ቢያሳዩኝ ደስ እንደሚላቸው አፍ አውጥተው ነገሩኝ፡፡ ትላንት የተሰማኝን ስሜት እንዴት መግለጽ እችላለሁ? ሌቱን ሙሉ ሳነባ አደርሁ፡፡ እንባዬ ደግሞ ከዓይኔ ብቻ የሚወርደው አይደለም፤ ልቤ ራሱ ደም ሲያነባ እንዳደረ ይሰማኛል፡፡ እና እንግዲህ ማን ቀረኝ? ምንስ የሚያጓጓኝ ነገር አለ? ለካ ዶክተሩ ሚስቱንና ውሽማዋን ከገደላቸው በኋላ ራሱን በኩራት ወደ ገደል የወረወረው ወዶ አልነበረም፡፡ ስለዚህ እኔም በቃኝ፤ ተሸነፍሁ፡፡ ምንም ድሃ ብሆን፤ አለኝ የምለው አንድ ሰው በምድር ላይ ባይኖረኝም ይች የብር ከሃምሳ የሲባጐ ገመድ በመጨረሻዋ ቀኔ አብራኝ ናትና አመስግኑልኝ፡፡

Read 5168 times