Saturday, 14 December 2013 12:28

በጋዜጠኝነት የራሴ የምትለው ህይወት የለም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

በሃዋሣ ላይ የትራፊክ አደጋ የደረሠበት የ”ኢትዮ-ምህዳር” ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ፤ በአሁኑ ሠአት በኮሪያ ሆስፒታል ከፍተኛ የህክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል፡፡ የህክምና ወጪው ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ ግን በጋዜጠኛው እና በቤተሠቡ እንዲሁም በቅርብ ወዳጆቹ ብቻ ሊሸፈን አልተቻለም፡፡ የሙያ አጋሮቹ ለህክምናው የሚያስፈልገው ገንዘብ እንዳይስተጓጐል በማሰብም ኮሚቴ አቋቁመው፣ በጐ ፈቃደኞችን በማስተባበር ገንዘብ እያሰባሰቡ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ድረስ 40ሺህ ብር ገደማ ተሰብስቦ ለህክምናው የዋለ ሲሆን ለቀጣይ ህክምና ደግሞ ከ180 ሺህ ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ታውቋል።
የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እንደሚሉት፤ በጐ አድራጊዎች እስካሁን ያሣዩት ድጋፍ የሚመሠገን ቢሆንም የታሠበውን ያህል ድጋፍ ግን አልተገኘም፡፡ ለዚህም ተጨማሪ የገቢ ማሠባብ ስራዎች የተጠመዱት፡፡ አትላስ አካባቢ የሚገኘው የ”ኦ ካናዳ” ካፌ፣ ባር እና ሬስቶራንት ባለቤቶች የገንዘብ ማሰባሰቡን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ያላቸውን ፍላጐት አሳይተዋል፡፡ ባለቤቶቹ ከአስተባባሪ ኮሚቴው ጋር በመሆን ታህሣስ 7 እና 8 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ሰአት ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ከልዩ የእራት ፕሮግራም ጋር የፋሽን ሾው እና ሙዚቃን ጨምሮ በአይነቱ ልዩ የሆነ  የገንዘብ ዝግጅት አሰናድተዋል፡፡
ጋዜጠኛ ኤፍሬም ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነትና በኮሚኒኬሽን የት/ት ዘርፍ ከተመረቀ በኋላ ላለፉት አምስት አመታት በተለያዩ የሃገሪቱ ፕሬሶች ላይ ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ሠርቷል፡፡ ለጉዳት የዳረገው አደጋ ያጋጠመውም በዚሁ ሙያው  በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የተፈፀመውን ሙስና የሚያጋልጥ ዘገባ ማቅረቡን ተከትሎ፣ የጋዜጣው አዘጋጆች ለተመሠረተባቸው ክስ አስረጂ ሊሆን ወደ ሀዋሣ በተጓዘበት ወቅት ነበር፡፡
በኮሪያ ሆስፒታል ከፍተኛ የህክምና ክትትል እየተደረገለት ከሚገኘው ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ጋር በጤንነቱና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አጭር ቃለ ምልልስ አድርገናል፡፡ ጋዜጠኛው ከህመም ስሜቱ ጋር እየታገለ በተዳከመ እና በተቆራረጠ ድምፅ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡


ጤንነትህ አሁን እንዴት ነው?    
አሁን ምንም አልልም … ከቀዶ ጥገናው በኋላ አንደኛው ሣንባዬ ላይ ጉዳት ደርሶብኝ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም በኢንፌክሽን ምክንያት ሣንባዬ በጣም ተጐድቶ ነበር፤ ግን መድሃኒት ስለተሠጠኝ አሁን ከዚህኛው ህመም አገግሜያለሁ፡፡
አሁን የሚሠማህ ምንህን ነው?
ከወገቤ በታች ምንም መንቀሣቀስ አልችልም። እግሬም ሠውነቴም መንቀሣቀስ አልቻለም። ጣቶቼም ላይ የመድከም ስሜት ይሠማኛል፡፡ ሠውነቴም ይደክማል፤ ከዚያ ውጪ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ፡፡
ሃኪሞችህ ስለ ጤናህ የነገሩህ ነገር አለ?
ያው እነሡ በየጊዜው ለውጥ አለሀ እያሉኝ ነው። ሁሌም እየመጡ ጤንነቴን ይፈትሻሉ፡፡ ሣንባዬም በፊት በኒሞኒያ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ነበር ጉዳት የደረሠበት፤ አሁን ግን ደህና መሆኑን ነግረውኛል፡፡
በቀጣይስ ምን አይነት ህክምናዎች ይደረጉልሃል?
እንግዲህ ፊዚዮ ቴራፒ ትንሽ ትንሽ ጀምሬያለሁ። ይኸው ህክምና የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡ ሌሎች ተከታታይ ህክምናዎችም አሉ፡፡ በቶሎ አገግማለሁ ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በጋዜጠኝነት ስራህ ላይ ሣለህ ነው ጉዳቱ የደረሠብህ፡፡ እንደው ከሙያው ጋር በተያያዘ የፈጠረብህ ስሜት?
ጋዜጠኝነት መርጬው የገባሁበት ሙያዬ ነው። በጋዜጠኝነት የራስህ ህይወት የለህም፡፡ በገንዘብ ያገኘሁት ትርፍ የለም ነገር ግን ለህዝቡ የሠናፍጭ ቅንጣት ታክልም ቢሆን በሙያዬ አበረክታለሁ ብዬ የገባሁበት ነው፡፡ በዚህ ህይወት ውስጥ ስትኖር እንደዚህ አይነት ነገሮች በኔ ላይ ይከሠታል ብለህ ባታስብም ይከሠታሉ፡፡ በሌሎች ሃገሮች እኮ ከዚህ በበለጠ ጠንካራ ሪፖርት የሚሠሩና በሙያቸው ላይ መስዋዕትነትን እስከ መጨረሻው የሚቀበሉ አሉ፡፡ እናም ጋዜጠኝነትን ስማርም ሆነ ወደ ስራው ስገባ ከዚህም የባሡ ብዙ ፈተናዎች እንደሚኖሩ አስብ ነበር፡፡
ድነህ ስትነሣ በሙያህ ትቀጥላለህ?
አዎ! እቀጥላለሁ፡፡ ሌላም ምርጫ የለኝም። የተማርኩትም ሆነ የልቤ ፈቃድ የሆነው ጋዜጠኝነት ብቻ ነው፡፡ እኔ ዝም ብዬ ቁጭ ልበል ብልም አይሆንልኝም፤ ሣልፅፍ መኖር አልችልም፡፡ ጋዜጠኝነት ደግሞ ራሱ ልትላቀቀው የማትችለው ሱስ ነው፡፡ ብዙ እያጣህበትም ቢሆን ሣትላቀቀው የምትኖርበት ሙያ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶ ጤንነቴ ከተመለሠ የምኖርበት ብቸኛው ሙያዬ ነው፡፡
ጋዜጠኞች (የሙያ አጋሮችህ) አንተን ለመርዳትና አለንልህ ለማለት እየተንቀሣቀሡ መሆኑን ታውቃለህ?  
አዎ! አውቃለሁ፡፡ በእውነት የሙያ አጋሮቼም ሆኑ ከጐናቸው የተሠለፉ አካላትን በሙሉ ምን እንደምል አላውቅም፡፡ ጋዜጠኝነት እንግዲህ ወገን ታፈራበታለህ ማለት ነው፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ይህን አሣይቶኛል፡፡ ማድረግ የምችለው ለተደረገልኝ ሁሉ ምስጋናዬን ማቅረብ ብቻ ነው። እንዲሁም የሙያ አጋሮቼን የበጐነት እንቅስቃሴ ተመልክተው ከጐኔ ለተሠለፉ ባለሃብቶችና ወዳጆቼ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ከዚህ በተሻለ ከጉዳቴ አገግሜ የበለጠውን ምስጋና እንዳቀርብ ደግሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን፡፡  
ህክምናህ እስከመቼ ይቆያል?
አላወቅሁም ግን ከእግዚአብሔር ጋር ብዙም የሚቀረው አይመስለኝም፡፡
የምታስተላልፈው መልዕክት ካለህ…  
ለጋዜጠኞችና ለአሣታሚዎች፣ በኔ ላይ የደረሠው አደጋ በነሡ ላይ እንደደረሠ ተሠምቷቸው ከጐኔ ለሆኑት ሁሉ፣ በተለይ ህይወቴን ለማትረፍ ርብርብ ላደረጉት የኮሚቴው አባላት፣ እግዚአብሔር ውለታችሁን ይመልስልኝ ከማለት ውጪ ሌላ ምን እላለሁ ብለህ ነው፡፡

Read 2042 times