Monday, 23 December 2013 09:47

አይወድቁ አወዳደቅ እየወደቅን ነው!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(7 votes)

ትውልድ በሠልፍ እንደሚያልፍ ሠራዊት ነው። ልዩነቱ ሠልፈኛው በየራሱ ተራ ጥሎት የሚሄደው ነገር ለሚቀጥለው ትውልድ የሚኖረው ፋይዳ ወይም የሚያቆየው ጥፋት ነው፡፡ ትናንት ስለ ዛሬው ትውልድ በየመስኩ መሥዋዕትነት የከፈሉ እንዳሉ ሁሉ መራራ ሥር ያቆዩ፣ ትውልዳቸውንና ቀጣዩን ትውልድ በጥቅም የሸጡ ወይም ከዚያ አልፈው በቸልተኝነት አድርባይ ሆነው የኖሩ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በፖለቲካው፣ በኪነጥበቡና በኢኮኖሚው ዘርፍ ያቆየው እኩይና ሠናይ ነገር መገለጫ ነው፡፡
ከላይ ያልኳቸው ነገሮች በየሀገሩና በየፖለቲካ ምህዳሩ ኖረው ዛሬም ድረስ በየትውልዱ ጭንቅላት ላይ በበጐ ወይም በክፉ ይሽከረከራሉ፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካው ዴሞክራሲ መልክ እንዲኖረው አንገታቸውን ገመድ ውስጥ የከተቱ ጐበዞች ነበሩ፤ ለሕዝብ ነፃነት ሣይተኙ አድረው ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ ይህን ያህል ካስተዳደርን ይበቃናል፣ እኛ ዛሬ ከተሳሳትን ቀጣዩ ትውልድ ነገ ይሣሣትበታል ብለው ያበቁ ነበሩ፡፡ ጀፈርስን ሁለት ዙር በፕሬዚዳንትነት ከቆየ በኋላ ሦስተኛ ዙር እንዲወዳደር ሲጠይቁት፤ “ዛሬ በእኔ ካዩት ነገ ይደግሙታል” ነው ያለው። ከዚህ የባሰም አለ፡፡ የሕንዱ ማህተመ-ጋንዲ ለዓመታት የተሰደደለት፣ የታሠረለትና የተንገላታለት የሀገር ነፃነት ጥያቄ መልስ አግኝቶ “እነሆ ሥልጣን!” ሲባል “አሻፈረኝ” ብሎ የፍዳውን ገፈት ለራሱ፣ ነፃነቱንና ሥልጣኑን ግን ለሕዝብ ሰጥቶ ነበር፡፡ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ኔልሰን ማንዴላም ለሃያ ሰባት ዓመታት እሥር ቤት የማቀቁለትን ነፃነት፣ ለሕዝባቸው ካስጨበጡ በኋላ ዙፋን ሞቋቸው፣ ድሎት አጓጉቷቸው “በቀላሉማ አልለቅም!” አላሉም፡፡ ሥልጣኑን ለሕዝብ አስረክበዋል፡፡ ይህ ማንነታቸው ደግሞ ለደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ብቻ ሣይሆን ለመላው ዓለም ብዙ ነገር አስተምሯል፡፡ ወደ እኛ ስንመጣ ብዙ ነገሮቻችን ተበላሽተዋል፡፡ እንኳን በፖለቲካ ሥልጣን ሽግግር፣ ከሞያ ማህበራት እንኳ ሥልጣን መልቀቅ የሚከብዳቸው እንዳሉ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ በሃይማኖት ተቋማትስ ቢሆን? ስንት ሽኩቻ፤ ስንት ዱላ መማዘዝ አለ አይደል? ይህ ሁሉ ግን የውድቀት መጀመሪያ ነው፡፡
አሁን አሁን የምናወራቸው ወሬዎች አዲሱ ትውልድ ላይ ያፈጠጡ ቢሆኑም በቀጥታ የሚመለከቱት ግን ሁላችንንም ነው፡፡ “የማይረባ ትውልድ!” በማለት ዛሬ ለምንወቅሰው ትውልድ ያወረስነው ነገር ቢኖር የጦርነትና ደም መፋሠሥ ታሪክ ነው፡፡ የምንፅፍለት፣ ስለ ጦርነት፣ ቀለል ቢል ስለ ወሲብ ነው፡፡ ያ ብቻም አይደለም። ዘመኑ ከቀደመው ዘመን የተለየና በቴክኖሎጂ የቀበጠ ነው። የዓለም አቀፍ ቅብጠቶችና ዕብደቶች በኢንተርኔት በየጓዳው ይገባሉ፡፡ ፈረንጅ የመምሠል አባዜም ተከትሎ ይመጣል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በጐ ነገር የሚያስተምሩ፣ ራሣቸውን ስለ ሕዝባቸው የሰጡ አርአያዎች የሏትም ማለት አይደለም፡፡ ብዙ ጀግኖች ስለ ነፃነትና የሀገር አንድነት ሞተዋል፡፡ ብዙዎች የጣፈጠ እንጀራቸውን ትተው ከሕዝቡ ጋር ተቆራምደው ዘመናቸውን ጨርሰዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፉት አርባ ዓመታት እንኳ የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር ሲሉ በግንባር ያለፉት ጀግኖች ቁጥር በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
ይሁንና አሁን ግን ወድቀናል ማለት ይቻላል፡፡ የወደቅነው እነማን ነን? ካልን የቀደመው ትውልድ ቅሪቶችን ጨምሮ ሁላችንም ነን፡፡ ለውድቀታችን ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ፣ የጠነከረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት መውደቅ ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ የጐሳ ፖለቲካው በውስጣችን የፈጠረው የመለያየት አባዜ አስተዋፅኦው የላቀ ነው፡፡ እናም ከሠፈር ያለፈ ሕልም በማጣታችን ምክንያት አርቆ ማሠብ የተሣነን ይመሥላል፡፡ አንድ ሰው ከራሱ ክልል ውጭ ማሰብ ካቃተውና ማንነቱን ካጠበበ፣ የቀደሙ ጀግኖችና አዋቂዎችንም በዘር ስለሚሸነሽን፣ ከራሱ ክልል ውጭ የሚያየው አርአያም አይኖረውም፡፡ ከዚህም ባለፈ አንድ ሰው አቅም ኖሮት እንኳ የተወለደበት ብቻ ሣይሆን የክልሉ ተወላጅ ካልሆነ ዕውቀቱን ለሀገሩ የሚያውልበት ዕድል እንኳ እያጣ ነው፡፡ ይህ ዋናው የፖለቲካ ሥርዓቱ ቀውስ ይሁን እንጂ ኪነ-ጥበቡና ሃይማኖቱም ለውድቀታችን ተጠያቂ ናቸው፡፡ በእኛ ዘመን እንደ አቡነ ጴጥሮስ ለነፃነትና ለእውነት ሕይወቱን የሚሰጥ፣ ደረቱን ለጥይት የሚያሰጣ መሪ አለ ወይ? ብሎ መጠየቅ በራስ መሣለቅ ነውና ዝም ብሎ ማለፍ የሚሻል ይመሥለኛል፡፡
በኪነጥበቡ ዘርፍ ከመጣን ደግሞ ኪነጥበቡ ልክ በሀገሪቱ እንዳሉት ብዙ ነገሮች ባለቤት ያጣ ይመሥላል፡፡ ባለቤቶቹ ሊሆኑ የሚገባቸውም በዐይን የሚገቡ ሰዎች፣ በአብዛኛው በጥቅም ራሳቸውን ሸጠዋል፡፡ ስለ ሕዝብ ነፃነት፣ ስለ ጥበብ ዕድገት አያገባቸውም፡፡ የነርሱ ሻሞ ለጭብጨባና ለጥቅማጥቅም ብቻ ነው፡፡ እነርሱ ከ”ሸቀሉ” ሕዝብ ገደል ይግባ! እንኳን ለሕዝብ ለማማጥና ለመታመም ቀርቶ ሕዝብ አልቆ ባዶ መድረክ ላይ ቢነግሱ የሚወድዱ ይመሥላሉ፡፡ ለዚህ እማኝ የሚሆነን የዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ሶማሌ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አከባበርን በተመለከተ የነበሩት ሽኩቻዎች ናቸው፡፡ እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ቅንና ደግ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ብዙዎቻችን እናውቀዋለን፡፡ ሕዝቡን አሁን ካለው ፖለቲካዊ ትርምስ ውጭ ስናየው፣ ውብና ቀለል ያለ ኑሮ የሚመርጥ፣ ጭንቅ የማይወድ፣ ልበ-ሙሉም ነው፡፡ ግን ብዙዎች ይህንን ውበቱን አይደለም፣ ያደነቁት፣ ይልቅስ ኪሱን ነው የነቀነቁት። እርስ በርሱ እንደሚናቆር ጥንብ አንሳ፣ የነበረውን መናቆር ያየና የሰማ ያውቀዋል፡፡
ያለ ምንም ማጋነን ለድንበራቸው እንደሚሞቱት፣ ሕዝባቸውን እንደሚያስቀድሙት አባቶቻችን አይደለንም-ወድቀናል፡፡ በጥበቡ መስክ ተሠልፈናል የምንለው ሰዎች፤ ጥበብ አራት እግርዋን ብትበላ ግድ እንደሌለን የሚያሣዩ ብዙ ጠባሳዎች አሉን፡፡ ስመ-ጥር የተባሉ ሰዎች መጽሐፍትን ሣያነብቡ እንኳ የጀርባ አስተያየት እስከመስጠት ይዘቅጣሉ፤ ሌሎች ለገበያ ሲሉ በአደባባይ ላይ የውሸት ምስክርነት ሲሰጡ ሕሊናቸው አይገስፃቸውም፡፡
የጥበቡን ድንኳን ባይረግጡ እንኳ ደጁ ላይ ነን የሚሉት በየትኛውም ሁኔታ ራሳቸውን ከፍ ከፍ ከማድረግ ያለፈ ሕልም ያላቸው አይመሥሉም፡፡ ለምሳሌ እንኳ ብጠቅስ “ጥርሴ” በሚል ርዕስ አንድ የግጥም መጽሐፍ ያሣተመች ወጣት፤ ከቅንነት ይሁን ከታላቅነት ማማ ላይ በመውጣት ጉጉት ተመሥጣ፣ በመጽሐፍዋ ጀርባ ላይ አስተያየት ያፃፈችው የስፖንጅ ፋብሪካውን ባለቤት አቶ አቤሴሎም ይህደጐንና ሻለቃ ሃይሌ ገብረሥላሴን መሆኑ ገርሞኛል፡፡ ለመሆኑ ጥበብ የራሱ ቤተሰብ የለውም? የጀርባ አስተያየት ለማፃፍስ ጥበቡን ያለ ቦታው መጣል ያስፈልጋል? አንድ ሥነ-ጽሑፍ የሚገመገመው ገንዘብ ወይም ዝና ባለው ሰው ሳይሆን በዘርፉ ላይ ባለው ዕውቀትና አተያይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ይሁንና ያንን የመሳሰሉ ስህተቶች እየተፈፀሙ ነው፡፡ ይህም የዘመናችን ውድቀት አንድ አካል ነው፡፡
ትውልድን መቅረፅ አለበት የምንለው የጥበብ መሥመር፤ ይባስ ብሎ ቁልቁል ወደ ገደል ለመገፍተር በገንዘብ እየተሸቀጠ ነው፡፡ ገበያ አላቸው የሚባሉት ልቅ የወሲብና የፖርኖግራፊ ጽሑፎች ገበያውን እየወረሩት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ “ጭን” በሚለው ርዕስ ሥር እየተፃፉ ትውልዱን ከምርምርና ከዕውቀት ይልቅ የወሲብ ባሪያ ለማድረግ እየተጣደፉ እንደሆነ መናገር ለቀባሪ እንደማርዳት ነው፡፡
ወደ ሙዚቃ ሥራዎቻችንም ሥንሄድ፣ አባቶቻችን ባወረሱን መስመር ላይ አይደለንም። የዘፈን ግጥሞቻችን ትውልድን በበጐ ሥነ-ምግባር ከመቅረፅ ይልቅ፣ አባቶች ያቆዩትን የሥነ ምግባር አጥር እያፈረስን ስድ በመልቀቅ ላይ ነን፡፡ ከዚህ ቀደም የምንሰማቸውን ዓይነት ጥልቅ ሀሣብ፤ የሰው ልጅ ሕይወት ጠቃሽ ፍልስፍናዎችን መሥማት የሕልም እንጀራ ሆኗል፤ ያም ሳይበቃ “ሳይደክሙ ዳር መድረስ” በሚል ፍልስፍና፣ ሌሎች የደከሙበትን ግጥምና ዜማ ነጥቆ ለጆሮ በሚቀፍ ዜማ እንደጅብ መጮህ ተለምዷል።
የሚያሣዝነው የነጣቂው መብዛት ብቻ አይደለም። ሁሉም ነገር ባለቤት ማጣቱ ነው፡፡ በጐ ነገሮቻችን በሙሉ እየተዘረፉ በምትኩ አሣፋሪ ነገሮቻችን ጌጥ ሆነውን አደባባይ ላይ እየተንፏለሉ ነው። አንድ ፊልም ላይ ጥበቃ ሆኖ የሠራው ወይም አጃቢው “አርቲስት እገሌ እባላለሁ” እያሉ-ትከሻ ማሳበጡ ሁሉ የውድቀታችን ደወሎች ናቸው። ደወሉን የሚሠማ ጆሮ ግን የጠፋ ይመሥላል። ጋዜጠኞች ብንሆን፣ ወይ ለመንግስት እናሽቃብጣለን-ለሣንቲም! ወይ ደግሞ በጭፍን እንሣደባለን ለእንጀራ!
የእኛ ነገር ስላለፈው ዘመን ማውራት ብቻ ነው፡፡ የታገል ሰይፉ ግጥም እንዲህ ትለናለች፡-
“ዛሬም የዋርካ ልጅ”
ከዛፍ ግንድ ተቆርጠን …
ከከፍታ ወድቀን … ካፈር ተፍገምግመን
ከእንጨት ተፈልጠን …
ከጭራሮ ደርቀን-በቅጠል ተለቅመን፣
በማድቤት ነበልባል…
ተቃጥለን በፍም እጅ-አመድ ሆነን በነን
“ማናችሁ?” ስንባል…
ዛሬም “የዋርካ ልጅ” የምንል እኛ ነን፡፡
በርግጥም ዛሬም በአንድ እጃችን ምኒልክን ይዘን፣ በሌላው እጃችን ሌላ ይዘን ልንዘምር ይቃጣናል፡፡ የምኒልክ ወይም የአሉላ ልጅ ነን እያልን አሉላን ለመምሠል አንሞክርም! እንደ ጌጥ ስም ማንጠልጠል ሆኗል ስራችን፡፡ ብቻ ወድቀናል፤ ለመነሣት ወደ መሠላሉ ካልተጠጋን እዚያው እንዳንቀር እሰጋለሁ፡፡

Read 1991 times