Monday, 23 December 2013 09:54

እምዬ ምኒልክ በ100ኛ ሙት ዓመታቸው!

Written by  በብሩክ ልሣን አልማዝ
Rate this item
(9 votes)

ስመ ገናናው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ ባለፈው ሳምንት 100ኛ የሙት ዓመታቸው ተከብሮላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ 20ኛው ክፍለዘመን እንድትሻገር ፈሩን በመቅደድ  ዘላለም ታሪክ የሚያስታውሳቸው ንጉሥ ናቸው። ሳህለ ማርያም በሚለው ክርስትና ስማቸው የሚታወቁት አፄ ምኒልክ፤ ኢትዮጵያን ለ24 ዓመታት በንጉሠ ነገሥትነት ያስተዳደሩ ሲሆን ዙፋናቸውን የለቀቁት በ69 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ  በንግሥና ዘመናቸው የጣሊያን ወራሪን በአድዋ ጦርነት አሸንፈው ከአገር በማስወጣት፣ ለመላው አፍሪካ እና ቅኝ የተያዙ አገራት ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት በመሆን በዓለም እውቅና አግኝተዋል፡፡ ከአድዋ በኋላ ደግሞ  ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ስልጣኔ በሯን እንድትከፍት አድርገው ብዙ አዳዲስ ነገሮችን አስጀምረዋል። ይህን ሃሳባቸው ለመፈፀም ሲሞክሩ፤ ”ፈረንጆች ሃገራችን ከገቡ ባህላችን ይለወጣል፤ ሃይማኖታችን ይጠፋል፤ ወኔያችን ይሰለባል” በሚሉ ተቃውሞዎች ከፍተኛ ፈተና ተጋፍጠዋል፡፡ የእምዬ ምኒልክን  100ኛ ሙት ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ከታሪክ መጻሕፍት እና ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በማጣቀስ  እንዲህ ይዘከራሉ፡-
“አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚል ርዕስ በተክለ ጻዲቅ መኩርያ በተዘጋጀው መጽሐፍ፤ በ1888 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ፣ ንጉሡ የጣሊያንን ወረራ በቅርብ አረጋግጠው፣ ለአድዋ ጦርነት የክተት አዋጅ በይፋ ነጋሪት ያወጁት  የሚከተለውን መልዕክት በማስተላለፍ ነበር፡- ‹‹እግዚአብሄር በቸርነቱ  እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡  ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም…›› ብለዋል፡፡ (ገፅ 226)
አፄ ምኒልክ ከውጭው ዓለም ጋር በርካታ የዲፕሎማሲ ፈር ቀዳጅ ተግባራትንም በማከናወን ይታወቃሉ፡፡ በ1893 እ.ኤ.አ የሩስያ የዲፕሎማቲክ እና የጦር ሚስዮን ልፁካን ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ነው የዲፕሎማሲ ጥረቱ የተጀመረው፡፡ በአድዋ ጦርነት ማግስት ራሽያ ብቻ ሳትሆን በርካታ የውጭ አገር ዜጎች፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለንግድ፣ ለግብርና፣ ለማዕድን ቁፈራ እና ሌሎች የሚሲዮን ተግባራት ወደ ኢትዮጵያ በብዛት መግባት ያዙ፡፡ ከአድዋ ጦርነትና ድል በኋላ በጠንካራ መሰረት በተጀመረው የኢትዮጵያ እና የራሽያ ዲፕሎማሲ ግንኙነት መነሻነት እስከ 1913 እ.ኤ.አ በሺዎች የሚገመቱ መኳንንቶች እና ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን በራሽያ ስፖንሰርነት ወደዚያው አገር በመሄድ ከፍተኛ የልምድ ልውውጥ ማድረግ ችለዋል፡፡ ከአድዋ ጦርነት በኋላ የሩስያ ቀይ መስቀል ልዑካን አዲስ አበባ ሲገቡ፣ ከንጉሡ ባገኙት ትብብር የመጀመሪያውን ዘመናዊ ሆስፒታል መሥርተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ መዲና ለመሆን የበቃችውን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባን በዘመናዊ መዋቅር የቆረቆሩት አፄ ምኒልክ፤ በኢትዮጵያ በርካታ አዳዲስ ጅማሮዎችን በመፍጠር ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ በግብፆች አስተዳዳሪነት “አቢሲኒያ ባንክ” በሚል ስያሜ የመጀመሪያውን ባንክ፤ የመጀመሪያውን ፖስታ ቤት “አራዳ ፖስታ”፤ በኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ትብብር የተሰራው የመጀመርያው  የባቡር መንገድ፣ የመጀመርያዎቹ የስልክና የቴሌግራፍ አገልግሎቶች፤ የመጀመርያው የሞተር መኪና፤ የመጀመርያው የውሃ ቧንቧ እንዲሁም በመንግሥት አስተዳደር የመጀመርያው የሚኒስትሮችን ካቢኔ አቋቁመዋል፡፡
በ1990ዎቹ መግቢያ ላይ አፄ ምኒልክ የሞት ቅጣት መፈፀሚያ የሆኑ 3 የኤሌክትሪክ ወንበሮች እንዲመጣላቸው አዝዘው እንደነበር ይነገራል፡፡ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አጠገብ ያለች አንዲት ዛፍ፣ በሞት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው ሰዎች ይሰቀሉባት ነበር፡፡ ምኒልክ ያንን ፈረንጆቹ እንዳያዩ ለማድረግ ቢጥሩም አልቻሉም፡፡ ፈረንጆቹ በነሱ አገር የሞት ፍርድ በኤሌክትሪክ ወንበር እንደሚከናወን ነገሯቸው፡፡ ያን ጊዜ ነው ምኒልክ ወንበሮቹን እንዲያመጡላቸው ያዘዙት፡፡ ሆኖም ወንበሮቹ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ሥራ ላይ ሊውሉ አልቻሉም፡፡ በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል አልነበረም፡፡
አፄ ምኒልክ ጥረታቸው ዋጋ እንዳያጣ አስበው፣ የውጭ አገር ሰዎች ከአገራቸው የኤሌክትሪክ ሃይልና ብርሃን እንዲያስመጡ በማድረግ፣ ከሶስቱ የኤሌክትሪክ ወንበሮች አንዱን ለሊቀመኳሳቸው፣ ሌላውን ወደ ግምጃ ቤት አስገብተውታል፡፡ ወንበሩን ለራሳቸው የዙፋን መቀመጫ እንዳዋሉ በቀልድ መልክ የሚነገረውን እንደ እውነተኛ ታሪክ አድርገው የጻፉ ግን አልጠፉም፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በ1930ዎቹ ይሄን ጉዳይ የምኒልክ አስገራሚ ታሪክ አድርጐ የፃፈው አንድ ካናዳዊ ጋዜጠኛ ይጠቀሳል፡፡
ብስክሌት ከመንዳት ጋር በተያያዘ ሌላ አስገራሚ ታሪክም ለአፄ ምኒልክ ይነገርላቸዋል፡፡ ንጉሡ ባንድ ወቅት ዲፕሎማቶች እና መኳንንቶቻቸውን በቤተመንግስት ሰብስበው “ብስክሌት እነዳለሁ” ብለው ተነሱ፡፡ ብስክሌቷ ላይ ተፈናጥጠው  ሲሞክሩ ስድስት ጊዜ ወድቀው በመነሣት፣ በመጨረሻ ቢስክሌት መንዳት የቻሉ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆነዋል፡፡
አፄ ምኒልክ በዘመነ መንግሥታቸው አጋጥሞ ከነበረ የከፋ ድርቅ ጋር በተያያዘም ለአገራቸው ሕዝብ ያስተማሩት መልካም ነገር ነበር፡፡ በወቅቱ ተከስቶ በነበረው ድርቅ፣ የአገሬው ሕዝብ ረሃብ ሲያሰቃየው፣ ንጉሡ ወደ እርሻ ማሳ ወጥተው፣ በዶማ መሬት በመቆፈር፣ ገበሬዎች የማረሻ በሬ ባይኖራቸው እንኳን በእጃቸው መሬት ቆፍረው ማብቀል እንደሚችሉ በተግባር በማሳየት አስተምረዋል፡፡ በዚሁ የድርቅ ወቅት ንጉሡ የግብር ምህረት በማድረግም ወገናቸውን ረድተዋል፡፡
አፄ ምኒልክ ከአድዋ ጦርነት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት በማስገባት የላቀ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የተክለ ጻዲቅ መኩርያ “አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” የተሰኘው የታሪክ መፅሃፍ፤ ወደ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት እንዴት እንደገባ ሲያብራራ፤
‹‹የካቶሊክ እምነት ካላቸው ፈረንሳዮች ፤ፀረ ማርያም ከሚባሉት ከእንግሊዞች መምህርነት በመፈለግ በአገር ውስጥ ጠብ እንኳን ቢቀር ማጉረምረም እንዳይፈጠር ሲሉ፣ የተዋህዶ ኃይማኖት ከመነጨበት፣ ጳጳስ ከሚመጣበት ከእስክንድርያ ወይም ከግብፅ አገር መምህራንን በገንዘብ ቀጥረው ማስመጣትን መረጡ…›› በዚህ መሰረትም በ1900 ዓ.ም የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤትን አቋቁመው፤ የመሳፍንት፣ የመኳንንት፣ የደሃ ልጆችም ቁጥራቸው 150 የሚደርስ ወጣቶች ተደባልቀው ይማሩ ዠመር። አፄ ምኒልክ ስለትምህርት መስፋፋት ያላቸውን የጋለ ምኞት ትምህርት ቤቱ ከመቋቋሙ  በፊት ያወጡት አዋጅ ያሳያል፡፡
“…እስካሁን ማንም የእጅ አዋቂ የነበረ ሰው በውርደት ስራ ይሰራ ነበር፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው ለመማር እና ለመሰልጠን የሚተጋ አልነበረም፡፡ በዚህ ጎጂ በሆነ ሁኔታ ብንኖር፤ ቤተክርስትያኖች ይዘጋሉ፡፡ ይልቁንም ክርስትያንም አይገኝም። በሌሎች አገር እያንዳንዱን ነገር  መማር ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ነገሮችም ይሰራሉ፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ለወደፊት ወንድ ልጆች እና ሴት ልጆች ሁሉ ከስድስት ዓመታቸው በኋላ ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ይሁን፡፡ ልጆቻቸውን ለማስተማር ለማይተጉ ቤተሰቦች፣ ወላጆቻቸው ሲሞቱ ሃብታቸው የልጆቻቸው መሆኑ ቀርቶ ለመንግሥት ይተላለፋል፡፡ ተማሪ ቤቶች እና አስተማሪዎችን የሚያዘጋጀው መንግሥት ነው፡፡››
በአፄ ምኒልክ ጊዜ ሕዝቡ በሸቀጣሸቀጥ፣ በምርትና በአሞሌ ጨው ከመገበያየቱ በቀር ለከፍተኛ ዋጋ የሚጠቀመው ከመካከለኛው ምሥራቅ በ1768 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ በገባው የኦስትሪያ ንግሥት ማርያ ትሬዛ ምስል ያለበት ብር ነበር፡፡ በአክሡምና ከዚያ በፊት መገበያያ ገንዘቦች (ሳንቲሞች) የነበሩ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ተመልሶ ዕቃን በዕቃ መለዋወጥ ተጀመረ፡፡  አፄ ምኒልክ በዚህ ፀፀት ተሰምቷቸውኧ በ1894 እ.ኤ.አ ከፈረንሳይ ኩባንያ ጋር በመዋዋል፣ በመልካቸው እና በስማቸው (ብር ከእነ ቅንስናሹ)  20ሺ ብር አሳትመው በእሱ መገበያየት መጀመሩን የተክለፃድቅ መኩርያ መፅሃፍ ያወሳል፡፡ በፈረንሳዩ ኩባንያ በመጀመርያ የተሰራው አንድ ብር፤ የብር አላድ፤ የብር ሩብ፤ የብር ስምንተኛ ነበር። የብሩ ክብደት እስከ 28 ግራም ሲሆን ባንድ ወገኑ “ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” የሚል፣ “1889” በኢትዮጵያ አሃዝ የተጻፈበትና የራሳቸውን ዘውድ የደፋ ምስል የያዘ ነው፡፡ በግልባጩ ደግሞ ዘውድ የደፋና በቀኝ እጁ ባንዲራ ያለበት ባለመስቀል ሰንደቅ የጨበጠ አንበሳ ሆኖ፣ በዙርያው “ሞዓ አንበሳ እምነገደ ይሁዳ”፣ እንዲሁም አንድ ብር የሚለው ሰፍሮበታል፡፡ ይህ የምኒልክ አዲስ ገንዘብ ሕጋዊ መገበያያ እንዲሆን የተነገረው አዋጅ…
“ከዚህ ቀደም ነጋዴም፤ ወታደርም ባላገርም፤ የሆንክ ሰው ሁሉ በየገበያውና በየመንገዱ በየስፍራው ሁሉ በጥይት ስትገበያይ ትኖር ነበር። አሁን ግን በእኔ መልክ እና ምስል የተሰራ ብር፤ አላድ፤ሩብ፤ተሙን፤ መሃልቅ አድርጌልሃለሁና በዚህ ተገበያይ እንጅ ከእንግዲህ በጥይት መገበያየት ይቅር ብዬሃለሁ፡፡
ይህን አዋጅ አፍርሶ ጥይት እርስ በራሱ ሲሻሻጥ እና ሲገዛዛ የተገኘው… በአንዳንድ ጥይት አንዳንድ ብር ይክፈል..” የሚል ነበር፡፡
ታዋቂው የሙዚቃ ሰው አቶ ተስፋዬ ለማ፤ “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ” ብለው ባዘጋጁት ምርጥ መጽሐፍ፤ አፄ ምኒልክ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ እንዲስፋፋ በነበራቸው ፍላጎት እና በጣሉት መሰረት ስማቸው ተወስቷል፡፡ የአድዋ ድል አንደኛ አመት ሲከበር፣ በወቅቱ የራሽያ ንጉሥ  የነሐስ የሙዚቃ መሳርያዎችን፤ ኮሎኔል ሊኦንቴፍ ከተባለ አሰልጣኝ ጋር ለምኒልክ መላካቸውን የሚገልፀው “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ” የተባለው መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በምኒልክ ዘመን ዘመናዊ ሙዚቃ እንዴት አገር ውስጥ እንደገባ ሲተርክ፤ ‹‹ከሩስያ በመጡት የትንፋሽ መሳርያዎች ለመማርና ለመጫወት የፈቀደ አልነበረም፡፡ ኮሎኔል ሊኦንቴፍም በኢትዮጵያ ሙዚቃ የተናቀ ሙያ መሆኑ ገረመው፡፡ ….. በመጀመርያ ከቤኒሻንጉል እና ከወላይታ የተገኙ ሰዎች ተመልምለው የሙዚቃ መሳርያዎችን ለመጫወት ለሶስት ወራት ሰለጠኑ። አፄ ምኒልክ በተገኙበት አሰሙ፤ ተመስግነው ተሸለሙ፡፡›› ብሏል፡፡
የአፄ ምኒልክ አዝማሪ የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፤ ለመጀመርያ ጊዜ የአማርኛ ዘፈኖችን በርሊን ጀርመን ውስጥ በዲስክ አሳትመው ማሰራጨታቸውን ይሄው መፅሃፍ ከትቦታል፡፡

Read 5973 times