Saturday, 28 December 2013 12:15

ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ

Written by  ሰሎሞን አበበ ቸኮል saache43@yahoo.com, Solomon.abebe.395@facebook.com
Rate this item
(4 votes)

የቋንቋው ሊቅ፣ የቃላት መዝገቡ
ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ “ጥሩ የአማርኛ ድርሰት እንደምን ያለ ነው?” ብለው ጠይቀው ነበር። በርሳቸው አጠያየቅ መንገድ “ጥሩ የቋንቋ ሊቅ እንደምን ያለ ነው?” ስንል የእኛ መልስ “እንደ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ያሉ” ይሆናል፡፡
መቸም የቋንቋን ነገር እጥግ ድረስ የተከታተሉ ሰዎች አሉ ከተባለ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ አንዱ መኾን አለባቸው፡፡ በተለይ በሥነ ልሳን ትምሕርት “ሴማዊ” የሚል ስም በተሰጣቸው ቋንቋዎች (አማርኛ ግእዝ፣ ዓረብኛና ዕብራይስጥ) ላይ የተራቀቁ ነበሩ፡፡
የዶክተር አምሳሉ አክሊሉ የቋንቋ ችሎታ በነዚህ አይወሰንም፡፡ ከአውሮፓውያኑ እንግሊዝኛን፣ ጀርመንንና ጣሊያንኛን ጥርት አድርገው የሚያውቁ ነበሩ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ባንዱ ቋንቋዊ ጉዳዮችን መጻፍና ማስረዳት የሚችሉ ልዩ ሰውም ነበሩ፡፡
“ቋንቋ እውቀት አይደለም፣” ይባላል፤ እውቀትን ማግኚያ እንጂ፡፡ ሁለቱንም የሚኾነው ለባለሞያው ነው። እንደዚያ ከኾነ፣ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ከምር የቋንቋ ሊቅ ነበሩ፡፡ ይህንንም ሊገልጡ በሚችሉ መሠረታዊ ሥራዎቻቸው አስመስክረዋል።
ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ከአባታቸው ከቄስ አክሊሉ ወልደአብ እና ከእናታቸው ከእማሆይ ታንጉት በየነ፣ በ1922 ነሐሴ 27 ተወለዱ፡፡ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን ማብቂያ ላይ የተወለዱት አምሳሉ፤ እዚያው ደሴ አካባቢ የትውፊታዊውን ት/ቤትና የ፩ኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ፈጽመው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ት/ቤት የ፪ኛ ደረጃ ትምሕርታቸው ቀጥለዋል። ይኽንንም በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቃቸው የነፃ ከፍተኛ ትምሕርት ዕድል በማግኘት ወደ ግብፅ ሔዱ፡፡
በግብፅ ካይሮ ውስጥ በሚገኝ መንፈሳዊ ኮሌጅ የስነ መለኮት ትምሕርታቸውን እየተከታተሉ፣ እዚያው ካይሮ ውስጥ ባለው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የሶሺዮሎጂ ትምሕርታቸውን ተምረዋል፡፡ በሁለቱም ትምሕርታቸው በ1949 ዓ.ም በአስደናቂ ውጤት ሁለት ዲግሪ አግኝተዋል።
ከዚያም ወደ ጀርመን በመሔድ በቲዩንቢንገን ዩኒቨርሲቲ በ1954 ዓ.ም የፒኤች.ዲ ዲግሪአቸውን አግኝተዋል፡፡ በጀርመን ቋንቋ ያቀረቡት ወረቀት በታዋቂው ኢትዮፒያኒስት በኦገስት ዲልማን ግእዝ-ጀርመን መዝገበ ቃላት ሥራ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተማሪያቸው ከነበሩትና አኹን በአ.አ.ዩ የቋንቋ ጥናት የፊሎሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ከኾኑት ከዶክተር አምሳሉ ተፈራ ለመረዳት ችለናል፡፡
ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ፤ በ1958 በአ.አ.ዩ ረዳት ፕሮፌሰር፣ በ1969 ተባባሪ ፕሮፌሰር ማዕረግን ያገኙ ሲኾኑ፣ የዩኒቨርሲቲው የቋንቋ ጥናት ተቋም የፕሮፌሰርነት ማዕረግን እንዲያገኙ ለዩኒቨርሲቲው አቅርቦ እንደነበረም ታውቋል፡፡
ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ከቲዩቢንገን የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን እንዳገኙ ወደ ሀገራቸው በመመለስ፣ በብሔራዊ ቤተመዛግብት ወመዘክር የሳይንስ ቡድን ዳይሬክተር በመኾን ለሁለት ዓመት አገልግለዋል፡፡
ከ1956 ዓ.ም. ጀምረው በአ.አ.ዩ. የቋንቋ ትምሕርት ክፍል መምሕር በመኾን የግእዝ፣ የአማርኛ፣ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና መዝገበ ቃላት ማጠናቀርን ለሠላሳ ሁለት ዓመት ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ በ1988 ዓ.ም. ጡረታ እስኪወጡ ድረስ ባገለገሉበት የአ.አ. ዩኒቨርሲቲ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎችንም አከናውነዋል፡፡
በጀርመን ሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና የኢትዮጵያ ጥናት ክፍል የአማርኛ እና ግእዝ መምሕር በመኾን እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡
ከ1996 ዓ.ም በኋላ ቀድሞ ሲያስተምሩ በቆዩበት አ.አ.ዩ፣ በነገረ ጽሕፈት ትምሕርት (ፊሎሎጂ) የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን በማስተማርና በማማከር አገልግሎታቸው የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አፍርተዋል፡፡
ከነዚህም ሌላ ከስምንት ያላነሱ ልዩና መሠረታዊያን የኾኑ መጻሕፍትን በማቅረብ፣ የቋንቋ እውቀታቸውን ከማስመስከራቸውም በላይ፣ እውቀታቸውን ለትውልድ በጽሑፍ ትተው ያለፉ ምሁር ናቸው፡፡
የአምሳሉ አክሊሉን እንግሊዝኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላት የማያውቃት ተማሪ አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ መምሕር ከነበሩት ከጂ.ፒ ሞስባክ ጋር ያዘጋጇት እንግሊዝኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላት፤ በየትኛውም የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ንትብ ብላ እስክታልቅ ድረስ መገልገያ የኾነች ናት። ለበርካታ ጊዜ በተደጋጋሚ ስትታተም የቆየችው ይቺ መዝገበ ቃላት፤ በአማዞን ዶት ኮም እና በ“ጓዳ አታሚዎች” በሕገወጥ ከሚታተመው ውጭ፣ ከአንድ ቀጥተኛ ካልኾነ መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው፣ ከዘጠኝ ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ የታተመች መጽሐፍ ናት፡፡ ከአቀራረቡ ዓይነት ጀምሮ፣ ከቃላት ትርጉምም በላይ የኾነው ሌላው አስደናቂ ሥራቸው ደግሞ አማርኛ-እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ነው፡፡
እጅጉን የከበደ እና ጊዜ ፈጅ የኾነውን የመዝገበ ቃላት ማጠናቀር ሥራ ያስተምሩ የነበሩት ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ፣ ጀርመን-አማርኛ መዝገበ ቃላትንም አሳትመው አቅርበዋል፡፡
ከነዚህም ሌላ ከአቶ ሙኒር አብራር ጋር በመኾን ዓረብኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላትንም ሠርተዋል፡፡ ሙኒር አብራር እንደገለጹልን፤ “አቡጊዳ አማርኛ-እንግሊዝኛ” የተሰኘውን የመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸውን የአርትዖት ሥራም ያከናወኑት እኝኹ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ነበሩ፡፡
ሌላይቱ ምጥን ያለች አስደናቂ ሥራቸው በቡክ ወርልድ የታተመችላቸው የአማርኛ ሞክሼ ፊደላትን አጠቃቀም (አጻጻፍ) በሆሄያት ቅደም ተከተል ያቀረቡባት በኪስ መጠን የታተመችው መጽሐፋቸው ናት፡፡ እያንዳንዱ የአማርኛ ጸሐፊና ጋዜጠኛ ከኪሱ ሊለያት የማይገባው ምርጥ ሥራ ናት፡፡ በአ.አ.ዩ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የታተመው “የአማርኛ ፈሊጦች” መጽሐፋቸው ደግሞ ሌላው የቋንቋ ሰውነታቸውንና ሙያቸውን ማሳያ ጠቃሚ ሥራ ነው፡፡ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ፤ የዩኒቨርሲቲው ህትመት ድርጅት ተጠባባቂ ዳይሬክተር በመኾንም በ1987 ተሾመው ነበር፡፡ ዶክተር አምሳሉ ለዩኒቨርሲቲው የስነ ጽሑፍ ትምሕርት ክፍል መማሪያ መጽሐፍ የሚኾን፣ “የኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ቅኝት” የተባለ መጽሐፍም አቅርበዋል፡፡ ታትሞ በመማሪያነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ በስነ ጽሑፍ በተለይም በአጫጭር ልብወለድ ታሪኮች ብቻዋን ጥሩ በመማሪያነት የምትኾነውና ልጨኛ የኾኑ፣ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የታወቁ ደራሲያን የጻፉዋቸውን አጫጭር ታሪኮች በአማርኛ ያቀረቡባት መጽሐፍም ሌላዋ ተወዳጅ ሥራቸው ናት፡፡
በትክክል በአማርኛ የቀረበች የትርጉም ሥራ ከመሆኗ በላይ፣ የታሪኮቹ ድንቅነት ተጨምሮ ዶክተር አምሳሉ በኢትዮጵያ የልብ ወለድ ሥነጽሑፍም ላይ የድርሻቸውን ጠብ ያደረጉ አባት መምሕር ነበሩ ያስብለናል፡፡
“ጥሩ የአማርኛ ልብወለድ ታሪክ እንደምን ያለ ነው?” የሚለውን ጥያቄ የመለሱ፣ “ለአንድ ሰው ምን ያህል መሬት ይበቃዋል?” ዓይነቶቹን ታሪኮች በትክክለኛ አማርኛ ያገኘንባት መጽሐፍ ናት፡፡
ዶክተር አምሳሉ፤ በአካዳሚክ ተቋማት እጅግ ያስከበሯቸውንና የተለያዩ ማዕረጐችን ያሰጧቸውን ብዙ የምርምርና የጥናት ሥራዎችን ያቀረቡም ነበሩ፡፡ ዓለም ዓቀፋዊ ዕውቅና ባላቸው በተለያዩ መጽሔቶች፣ መጻሕፍት፣ በመዛግብተ ስብእ፣ በዓውደ ጥበባት እና በመድብለ ጉባዔዎች የምርምር ሥራዎቻቸው የታተሙላቸው እንደነበሩ፣ በዜና ሞታቸው ላይ ከቀረበው ታሪካቸው ታውቋል፡፡ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብን በተመለከተ በጣሊያኖቹ ኢትዮ ፕያኒስቶች የቀረቡ ጽሑፎችንም ከሞገቱ ሁለት ሰዎች አንዱ ነበሩ። ምናልባት ከምርምርና ጥናታዊ ሥራዎቻቸው ውስጥ ከት/ቤት እና ዓውደ ምርምር ወጥቶ የተነበበ ጽሑፋቸው ይሄ ብቻ ሳይኾን አይቀርም፡፡
ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ በእርግጥም “የቋንቋ ሊቅ እንደምን ያለ ነው” ተብሎ ቢጠየቅ “እንደ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ” ብለው ቢመልሱ፣ የማይበዛባቸው ታላቅ መምሕር፣ ታላቅ አባት ነበሩ።
እኝህ አባት መምሕር ናቸው ባለፈው ሳምንት በ84 አመታቸው ታኅሣሥ 11 ቀን 2006 ዓ.ም ዐርፈው በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ የሙያ ባልደረቦቻቸውና ተማሪዎቻቸው እንዲሁም በሥራዎቻቸው የሚያውቋቸውና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት ቀብራቸው የተፈፀመው፡፡
ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ በ1959 ዓ.ም ጥቅምት 13 ከወ/ሮ ቀለመወርቅ ጋር ሕጋዊ ጋብቻ በመፈፀም የሦስት ወንዶችና የሁለት ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ የስድስት ልጆች አያትም ነበሩ፡፡  

Read 4315 times