Saturday, 28 December 2013 12:19

የእሾህዋ ወፍ!

Written by  ሌ.ግ
Rate this item
(11 votes)

“ብዙ ዜማ እንድትሰራ እሾኩ ዱልዱም ቢሆን ብዬ ተመኘሁ”

ከተራ ግለሰብነት ወደ ዝና ተራራ መውጣት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ አንዳንዶች መውጣት የጀመሩት ተራራ እድሜ እና እድል አብሮአቸው ስላለ፣ በስኬት ሜዳልያ ተጥለቅልቀው ጉዞአቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡ ሞታቸውም የድፍን ሀገር ሀዘን ይሆናል፡፡ እኔ ግን ስለእነዚህ አይደለም የማዝነው። እኔ የማዝነው ሰው አይን ገብተው “እንትፍ እደጉ!” እንኳን ለመባል ጊዜ ሳያገኙ ሞት የቀደማቸውን ነው፡፡
እኔ ሚካያ በኃይሉን የማውቃት አብሮ አደጌ ስለሆነች አይደለም፡፡ በእሷ ተወክለናል ከሚሉ የአስተማሪ ጐሳዎች አባልም አይደለሁም፡፡ እኔ ሚካያን የማውቃት በጆሮዬ ነው፡፡ በጆሮዬ አወቅኋት፡፡ በጆሮዬ ለመድኳት፡፡ ከትላንት ወዲያ ደግሞ በሬዲዮ በኩል በጆሮዬ በገባ ዜና መሞቷን ሰማሁ፡፡
እንዴት ተደርጐ መታዘን እንዳለበት የማይታወቅ ሀዘን ግን በልቤ ውስጥ ተሰማኝ፡፡ ጆሮዬ እሷን አስተዋወቀኝ፣ ጆሮዬ ድምፅዋን እንድለምድ እና እንድወድ አደረገኝ፣ ጆሮዬ እንደሞተች ነገረኝ…ጆሮ ግን የልብን ሀዘን ማድመጥ አይችልም፡፡
እስካሁን ከሰማሁት ዘፈኖቿ ውጭ አዲስ ዘፈን ከሚካያ ቅላፄ ወጥቶ ከእንግዲህ ወደኔ ነብስ አይደርስም፡፡ መኖር ብትቀጥል፤ የድምጿ እድገት የት ሊደርስ እንደሚችል መገመት አልችልም፡፡ ድምጿን የማነፃጽርበት መለኪያ የለኝም፡፡ ድምጿና እኔ ባንተዋወቅ ይሻለኝ ነበር እንዴ?
እኔ የመገናኛ ብዙሐን ተወካይ አይደለሁም፡፡ የመገናኛ ብዙሐን ሀዘን የምናውቀው ነው፡፡ ለአንድ ወይንም ለሁለት ሳምንት ብቻ የሚዘልቅ… እንጨት እንጨት የሚል፣ ሥራ ሥራ፣ እጅ እጅ የሚል ሀዘን ነው፡፡ የእውነት አይደለም፡፡ እውነተኛ ሀዘን ያለው እሷን በሰውነቷ ከሚያውቋት ዘመዶቿ፣ ጓደኞቿ … እና በምርጥ ዘፋኝነቷ ከሚወዷት የዘፈኗ አድናቂዎች ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ሌላው የወሬ ፍጆታ ነው፡፡
እኔ በ1999 መጨረሻ አካባቢ የሷን ዘፈን ለመጀመሪያ ጊዜ ስሰማ የተሰማኝ ስሜት፣ በድርሰት ንባብ ላይ ምርጥ ታሪክ ሳነብ ከሚያቁነጠንጠኝ ስሜት ጋር አንድ አይነት ነበር፡፡ ስሜቱን ማንም ዝም ብሎ ሊፈጥርብኝ አይችልም፡፡ ስሜቱን የፈጠረችብኝ ዘፋኝ እና እኔ የአንድ የውበት ቀለም እና የሀሳብ ዘመን ሰዎች ነን፡፡
“ምን ሆና ነው የሞተችው?” ብዬ ስጠይቅ፤ አጥጋቢ መልስ እንደማይሰጡኝ አውቄአለሁ። እንደተለመደው “ታማ” ነበር አሉኝ፡፡ በመጠየቄ አላፈርኩም፡፡ ትርጉም የማይሰጥ ዘመን፣ ትርጉም የማይሰጥ ህይወት እና ሞት ትርጉም ከማይሰጥ መልስ እና ጥያቄ ጋር አንድ ናቸው፡፡
ታምማ ነበር!
ማን ያልታመመ አለ፡፡ መታመሙን ያላወቀ ነው እንጂ… ያልታመመ ማን አለ፡፡ ማን መሞት ያልጀመረ አለ፤ ሞቶ እስኪጨርስ ያለማወቅ ጉዳይ እንጂ!
ለነገሩ ሚካያ ዩኒቨርስቲ ገብታ ተምራ የተመረቀች ሴት መሆኗ ራሱ፣ መታመሟን የማወቋ ምልክት ነበር፡፡ መታመማቸውን ያላወቁትማ ዘፋኝ ለመሆን መማር አያስፈልጋቸውም፡፡ እነሱ፤ የድምጽ እድገት ከአስተሳሰብ እድገት ጋር የተያያዘ መሆኑን መገንዘብ አይጠበቅባቸውም፡፡ የትኛዋ ዘፋኝ ናት መምህርት ሆና የምታውቅ?! ይህም ከህመም በማወቋ ለመዳን ብዙ የመሞከሯ ምልክት ነው፡፡
ሞክራለች፤ የሚሞከረውን ሁሉ፡፡
ለድንገተኛ ሞቷ ትርጉም ለማግኘት በማደርገው ሙከራ፣ የሷን ድምጽ ያሳጣንን ነገር ለመወንጀል ተመኘሁ፡፡ አንድ ነገር ከሆነ! እንክብካቤ የነፈጋት ማነው? ችላ ያላት ማነው? በጆሮው ድምጿን የበላው ህዝብ፤በዙሪያዋ እያለ ስትታመም ዝም ብሎአት ሲያበቃ… የሞቷን ወሬ ለመንገር ከመሮጥ ለምን ነው አብሮ የህመሟን ምክንያት ያልመረመረው?
ሀገርን ወክላ “ለኮራ” የሙዚቃ ሽልማት ስትታጭ፤ “ተባረኪ” ያላት ህዝብ፣ ሽልማቱን አሸንፋ መመለስ ሲያቅታት “ደባ ተሰርቶብኛል በውድድሩ ላይ” ስትል ምነው ጆሮውን ነፈጋት፡፡ ይህ ጆሮአችን “ድልን” እና “ብልጽግናን” ብቻ መስማት ወዶ “ድል” እና “ብልጽግና” የሚመጡት ለጥበበኛው ምን ሲሟላለት እንደሆነ መስማት እንዴት አቃተው?
“ደስተኛ አልነበረችም” አሉ…እኛን ግን በዜማዎቿ ደስተኛ አድርጋናለች፡፡ ድሮ፤ ጥበበኛን እንደ “እሾክ ወፍ” አድርጌ ስመስል፣ ተምሳሌቱ ሙሉ በሙሉ እውነት መሆኑን አምኜ አልነበረም፡፡ አሁን ግን እውነት መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡ ነገሩ እንደዛ ነው። ሚካያ በሀይሉም የእሾኳ ወፍ ናት፡፡ የእሾኳ ወፍ የምትዘምረው አንዴ ነው፡፡ ለመዘመር ዝግጁ ስትሆን ረጅም እና ሹል በሆነው እሾክ ላይ ደረቷን ታስደግፍና ማዜም ትጀምራለች፡፡ እሾኩ ደረቷን እየወጋ፣ እያስጨነቃት በሄደ ቁጥር የዜማዋ ድምጽ እያማረ፣ እየጠነከረ… አሳዛኝ እየሆነ ይሄድና…በስተመጨረሻ እሾኩ ደረቷን በስቷት ሲገባ…ዜማዋና ህይወቷ…አንድ ላይ ይጠናቀቃሉ፡፡
እሾኩ ደረቷን እየወጋት ስታዜም ያዳምጣት የነበረ ሕዝብ… የሚፈልገው ዜማውን ብቻ በመሆኑ ስለ ወፏም ሆነ ስለ እሾኩ አያገባውም፡፡ ህመሟ ምንድነው? ብሎ ማን ጠየቀ?...የሚፈልገው ዜማውን ብቻ ነው፡፡ ህዝብ መስዋዕት ይወዳል፡፡ ብዙ ዜማ እንድትሰራ እሾኩ ዱልዱም ቢሆን ምናለበት ብዬ ተመኘሁ፡፡ የምኞት ጊዜ ግን አልፏል ለሷ፡፡
የጥበብ ታዳሚ ወርቁን እንጂ ሰሙን አይፈልግም። ስለ ዜማው እንጂ ዜማው ከምን ውስጥ እንደመነጨ አይገደውም፡፡ የወፍን ድምጽ ቀርፆ መሸጥ፣ ለራሱ ስሜት ማሟያ መክፈት፣ ከወፏ  የሚገኘውን የድምጽ ደም ዋጋ በብር መልክ መቅዳት እንጂ…ስለ ወፏ ህመም አያገባውም፡፡ ምናልባት የሚካያ ህመም ምክንያት መታመሙን የማያውቀው ህዝብ ሊሆንም ይችላል። ወፏ ከሞተች በኋላ እሾኩ መኖሩን ይቀጥላል። ከዚህ በፊት ብዙ ምርጥ ቀለም ያላቸው የጥበብ ወፎችን እየወጋ ገድሏል፡፡ ወደፊትም የሚመጡ አዳዲስ ድምፆች መግደል እንዲችል ተዘጋጅቶ፣ ሾሎ እየተጠባበቀ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ የተሰማኝ ሀዘን የራሴ ነው፤ የመገናኛ ብዙሐንን ተዝካር የምወክል አይደለሁም፡፡ ያዘንኩት ለጥበበኞች የ40 ቀን እድል ነው፡፡ ለጥበበኞች አዲስ ዘመን አልመጣም፡፡ የድሮው ሰው አዲስ ጭምብል ለብሶ ነው የጥበብ ታዳሚ ነኝ የሚለው፡፡ ያሳዝናል፤ ያማል፡፡ “ምን ሆና ሞተች?” ስል “ታምማ ነበር” ነው ያሉኝ፡፡ እኔ አዝኛለሁ፤ ግን እጽናናለሁ፡፡ የእሷን ድምጽ ግን አባብሎም ሆነ አጽናንቶ የሚመልሰው ማንም ከእንግዲህ የለም፡፡     


Read 4040 times