Sunday, 05 January 2014 00:00

“ሓቅ ሓቁን ለህፃናት”

Written by  ካሌብ ንጉሴ
Rate this item
(5 votes)

በጥላቻና በእርግማን የተሞላ “መጽሐፍ”
ባለፈው ሳምንት ከቆምንበት እንቀጥል፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት በማስጠበቅ ረገድ ከቴዎድሮስ ይልቅ ዮሐንስ የተሻሉ እንደነበሩ ጸሐፊው የገለጡበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን አመልክቼ ነበር የተሰነባበትነው፡፡
“የእንግሊዝ ተንኮል ያቅለሸለሻቸው አፄ ዮሐንስ ይህ ሃሳብ ይዞ ለመጣ የእንግሊዝ ልኡክ ተቀብለው ከሃገሬ መሬት ቅንጣት ታክል ቆርሶ የመስጠት ስልጣን የለኝም፡፡ ብለው መለሱት፡፡ አፄ ዮሐንስ የሰሩዋቸው ስራዎች ከሳቸው በፊት የነበሩት ንጉስ አፄ ቴዎድሮስ አልተገበሩትም፡፡ በአፄ ምኒልክም አልተደገመም” (ገጽ 37) ይሉናል፤ ጸሐፊው ዮሐንስን ከቴዎድሮስና ከምኒልክ የግድ የተለዩ የአገር ተቆርቆሪ ለማድረግ፡፡
ሃገርን በመውደድ ረገድ ሶስቱም መሪዎች የሚታሙ አልነበሩም፡፡ ሆኖም ከቴዎድሮስም ሆነ ከምኒልክ ለእንግሉዞች በጣም ቅርብ የነበሩት ዮሐንስ መሆናቸው ደግሞ መካድ የለበትም፡፡ የእንግሊዞችን ከፍተኛ የጦር መሳሪያና የፖለቲካ ድጋፍ ባያገኙ ኖሮ በዝብዝ ካሳ ከደጃዝማችነት የዘለለ ሥልጣን ላይኖራቸው ይችል እንደነበር የታሪክ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡
ለሥልጣን የናወዙ መኳንንትና መሳፍንት ከእንግሊዞች ጐራ ተሰልፈው ባያጨናግፉባቸው ኖሮ ቴዎድሮስ እንኳንስ አገራቸውን ኢየሩሳሌምንም ከቱርኮች አገዛዝ ነፃ የማውጣት ህልም ነበራቸው፡፡ ምኒልክም ቢሆኑ የፈረንጆችን ተንኮል በመቋቋም ረገድ ከሁሉም የተሻለ የሠሩ ለመሆናቸው የአድዋ ድል ብቻ በቂ ነው። ሐረርን ከግብፆች ግዛት ነፃ ያወጧትም ምኒልክ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡
የምኒልክን ጭካኔ ሲገልፁም ፀሐፊው እንዲህ ብለዋል “ግፍ ከመፈጸም አኳያ ግን በትግራይ ህዝብ የፈጸሙት ዘመነሸ(ሸ) እየተባለ የሚታወቅ አሰቃቂ ያ የግፍ ዘመን አልፎዋል፡፡ ሲከተሉት የነበረ ፖሊሲ ከፋፍለህ ግዛ መሆኑ ተደጋግሞ የተነሳ ጉዳይ ነው፡፡ የአፄ ምኒሊክ ለሁለት ከፍለህ መግዛት የስልጣን ስስታምነት የፈጠረው ነው። ይህም እውን የሆነው ትግራይን ለማዳከም ትግራይ ትግርኝን ለሁለት ከፍሎ የኢትዮጵያ ድንበር በመረብ እንዲወሰን ማድረጋቸው ለአሁን ትውልድ ጦስ መሆን አስተዋጽኦ አለው” (ገፅ 59)
የፀሐፊው ሃሳብ “የእምየን እከክ ወደ አብየ” መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ነጥብ ላይ በድፍረት፣ በእውነትና በማስረጃ መከራከር ያስፈልጋል፡፡ የጸሐፊው ስሜታዊነት ጐልቶ ከወጣባቸው አጋጣሚዎች አንዱም ይህ ይመስለኛል፡፡ ኤርትራን ከትግራይ ሳይሆን ከመላው ኢትዮጵያ የነጠላት የምኒልክ ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ አይደለም፡፡ አፍሪካዊው ጀግና ቱርክ ፓሻ አሉላ አባ ነጋ ዶጋሊ ላይ በአንድ ቀን ጦርነት 500 ጣሊያኖችን ድባቅ ሲመቱ፣ አጤ ዮሐንስ ጀግናቸውን በመሾምና በመሸለም ፋንታ “ሳታስፈቅደኝ ለምን የሃገር ጠላት ወጋህ” ብለው ወቅሰዋቸዋልኮ፡፡ ለኤርትራ ከቀረው የኢትዮጵያ ከፍል መነጠል የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸው እውነት ቢሆንም ዋናው ግን እንግሊዞች አጤ ዮሐንስን ማታለላቸውና በግብፆችና በደርቡሾች ጦርነት ምክንያት አሉላን ከአስመራ ማንሳታቸው ነው፡፡
የፀሐፊው መከራከሪያ “ምኒሊክ ኤርትራን በጉልበት አላስመለሱም፤ ውስጥ ውስጡንም ከጣሊያን ጋር ተስማምተዋል” የሚል ነው፡፡ ፖለቲካዊ ድጋፍ ለማግኘትና ዘውድ ለመቀዳጀት ሲል ወገኑን እየከዳ ውስጥ ውስጡን ከፈረንጅ ጋር ያልተዋዋለ ማን አለ? ዮሐንስም’ኮ ሊቋቋሙት ያልቻሉትን ቴዎድሮስን እንዲጥሉላቸው እንግሊዞቹን ከምጽዋ መቅደላ ድረስ መርተው አምጥተዋል፤ ለዚህ ወሮታም በርካታ የጦር መሳሪያ ከጀኔራል ናፒር ተበርክቶላቸዋል፡፡ ለጦር መሳሪያና ለሥልጣን ሲሉ ያገራቸውን ዳር ድንበር በጠላት ያስደፈሩትም ያኔ ነው፡፡ ምኒልክም ከጣሊያኖች ያውም በግዥ የጦር መሳሪያ ማግኘታቸው እውነት ነው፡፡ ግን ጣሊያንን  በራሱ መሳሪያ አላጄ፣ መቀሌና አድዋ ላይ ድባቅ መቱበት እንጂ ለወገናቸው መቅጫ አልተጠቀሙበትም፡፡
በመሠረቱ ኤርትራ የሄደችው ከላይ በገለጽሁትና ማዕከላዊ መንግስት ባለመጠናከሩ ምክንያት ሆኖ ሳለ የምኒሊክን ስም እያነሱ በከንቱ ማጉደፍ ዕርባና ያለው አይመስለኝም፡፡ የሩቁን እንተወውና እስከ 1983 ግንቦት ድረስ’ኮ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ነበረች፡፡
እዚህ ላይ ፀሐፊውን አንድ ጥያቄ ልጠይቅ፡፡ አቶ አታክልቲ ታጋይ የነበሩ መሆንዎን በ”መጽሐፍዎ” ነግረውናል፡፡ እኒያ አምርረው የሚጠሏቸውና “ደቂቀ ምኒሊክ” የሚሏቸው ኃይሎች’ኮ ኤርትራን ከእናት ሀገሯ ቀላቅለዋት ነበር፡፡ ኤርትራን ከእናትዋ የለያት ማን እንደሆነ ያውቁት የለም እንዴ!
በ1974 ዓ.ም በተካሄደው መጠነ ሰፊ የቀይ ኮከብ ዘመቻ’ኮ ሻዕቢያ “እግሬ አውጭኝ” እያለ ወደ ሱዳንና ፈጣሪዎቹ ወደሆኑት የአረብ አገሮች እየፈረጠጠ ነበር፡፡ ለሀገሩ አንድነት ሲዋደቅ በነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ የተኮሰው ማነው? “ከሃዲው” ምኒልክ ይሆን? እባክዎ አቶ አታኸልቲ ቀልድዎን ያቁሙ፡፡ ይህንን ሐቅ’ኮ ባልደረቦችዎ በኩራት በየመድረኩ የሚናገሩት ነው፡፡ “ደቂቀ ምኒሊክ” በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ኤርትራን ከመለሷት ብዙ ጊዜ ነበር፡፡ እናም ኤርትራን ለማስገንጠል ወገኑን ከጀርባ ሆኖ ሲወጋ የኖረና በ1983 ዓ.ም ለሻዕቢያ አሳልፎ የሰጣት፣ የእርስዎን “ትግራይ ትግርኝ” ለሁለት የሰነጠቃት ምኒልክ ሳይሆን እርስዎ በደንብ የሚያውቋቸው የልጆች ፖለቲካ (child politics) አራማጆችና አለአዋቂዎች ናቸው፡፡
“የኤርትራ ህዝብ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው” የሚል አቋም ያራመደውም እርስዎ የታገሉለት ድርጅት እንጂ ምኒልክና ሸዋዎች አይደሉም፡፡ ከሰባ ሺህ በላይ ወጣቶችን ከበላ በኋላ እልባት ባላገኘው የባድመ ጦርነት ላይስ “ድንበሩ የቅኝ ግዛት ጊዜ ውል መሆን አለበት” ብሎ የተከራከረ ማነው? ምንስ ለማግኘት ታስቦ ነው? እና ወዳጄ ታሪክና ስሜት የተለያዩ በመሆናቸው ጥንቃቄ ያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
የምኒልክን ዘረኝነት ሲገልፁም “መጀመሪያ ለከፍተኛ ሹመት የሚመረጡት ከራሳቸው ዘር ሸዋዎች ናቸው፡፡ ከሸዋዎቹም በኋላ የግድ ሆኖ ከሌላ ከተመረጠ አንዳንዱን በዓይነቁራኛነት በሚኖሩበት ሁኔታ ይሆናል፡፡ እንደዚህ ዕድል ሲታጣ የአንዱ አካባቢ የሆነ ታማኝ ሹመኛ ለሌላው እንዲቆጣጠረው በማድረግ ውስብስብ ያደርጉታል” ይሉናል (ገጽ 60) ጸሐፊው፡፡
እዚህ ላይም አቶ አታኸልቲን እየተገረምሁም ቢሆን መጠየቅ ግድ ሆኖብኛል፡፡ ምኒልክ ዘረኛ ነበር ካሉ ለምን የታገሉለት ስርዓት በዘር ላይ የተመሠረተ የአስተዳደር ዘይቤ ተከተለ? ለምንስ ምደባ ላይ ሁሉ (በተለይ በፌደራል መ/ቤቶች) የአንድ ዘር ሹመኞች አለመጠን እንዲበዙ ተደረገ? የምኒሊክን ከሸዋ ብቻ መሾም የምትኮንኑ ከሆነ ለምን ዛሬ ትደግሙታላችሁ? ከምኒልክ የተማራችሁት ከሆነ ለምን ምኒልክን መወንጀል አስፈለገ? ምኒልክ ሲመድቡ ወይም ሸዋዎችን ሲሾሙ ወንጀል ይሆናል፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እርስዎና ድርጅትዎ ሲፈጽሙት ግን ጽድቅ ነው ማለት ነው?
“ራስ አሉላን የአድዋ፤ ራስ ሐጐስን ደግሞ የሽሬ አስተዳዳሪ አርገው በመሾማቸውና የስልጣን አቀማመጡ ያልነበረ በመኖሩ አገዳደሏቸው” ያሉት ማጣቀሻም የምኒልክን ተንኮልና ከፋፋይነት ወይም ዘረኝነት  ሳይሆን ለጋስነታቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ ሁለቱ ታላላቅ ራሶች ራስ በራሳቸው የተገዳደሉትም በዘመኑ በነበረው የስልጣን መስፋፋት እንጂ ምኒልክ የሸዋን ሰው አድዋ ወይም ሽሬ ላይ ስለሾሙ አይደለም፡፡ ሲወነጅሉም በአግባቡ እንጂ አቶ ጸሐፊ፡፡
“ቴሌፎን ወደ ኢትዮጵያ የገባ ለጣሊያን መንግስት የስለላ ሥራ ለማቀላጠፍ እንደነበር ከነ ዝርዝር ማስረጃው ሮማ ውስጥ እንዳለ አይረዱትም” ብለውናል ጸሐፊው፤ ምኒልክ ስልክ በማስገባታቸው የሚያመሰግኗቸውን ሰዎች ሲወቅሱ (ገፅ 63)
ይህ አስተሳሰብ በመሠረቱ ፍጹም የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን ፀረ ስልጣኔም ይመስለኛል፡፡ በኢህአዴግ ዘመን ተንቀሳቃሽ ስልክ እስከ አርሶ አደሩ መንደር እንዲደርስ የተደረገው ለስለላ ነው ማለት ነው? ለነገሩ ምኑን ይሰለላል? ተሰልሎ፣ ተሰልቦ አልቋልኮ፡፡ ስልኩ የገባው ለስለላ ከነበረ ውሃ፣ መብራት፣ ባቡር፣ መኪና፣ ፖስታ ወዘተ ለምን አገልግሎት ነበር የገባው? አቶ አታኽልቲ! ለጣሊያን ወይስ ለፈረንሳይ ጥቅም? ይህም ያልበሰለ አስተያየት ውጤት ነው፡፡
“የአፄ ዮሐንስ ሂዎት የምኒሊክ ክዳትና ተንኮል እንጂ ሌላ ከአገር ውስጥ ያጋጠመው የሚጋነን ችግር አልነበረም-(ገፅ 75)” የሚለው አገላለጽም ለብቻዬ ፈገግ አሰኝቶኛል፡፡ ምኒልክና ዮሐንስ’ኮ ወዳጄ በክህደት ሊወቃቀ አይችሉም፡፡ ምኒሊክ ክህደትን ከማን ተማሩ ነው ጥያቄው፡፡ የመጀመሪየው የክህደት ሰለባ ቴዎድሮስ ናቸው፡፡ ዮሐንስን ጨምሮ የወቅቱ መኳንንትና መሳፍንት ከዷቸውና ለእንግሊዝ ወራሪ ሰራዊት ብቻቸውን አጋፈጧቸው፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ራስዎ “ማስረጃ” ብለው ካያያዟቸው ደብዳቤዎች ውስጥ ካሳ ምራጭ (በኋላ ዮሐንስ) ከንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ ውጭ ከአውሮፓ ነገሥታት ጋር የተላላኳቸው የምሥጢር ደብዳቤዎች የክህደት ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ለጣሊያኖች ደብዳቤ መጻፍ ክህደት ከሆነ የመጀመሪያው የክህደት መምህር ማን እንደ ነበረ ከ“መጽሐፍዎ” መገንዘብ ይችላሉ። ቴዎድሮስንስ ማን አስገደላቸው? “ሓቅ”ማለት ይህን እውነት ሲደፍሩ ነው ወዳጄ!
“ድሮውንም አፄ ምኒሊክ ስለወደብ ሳያውቁ በድንቁርናቸው ትግራይ አደካምኩኝ ዘውዴንም አለመለምኩ ሲሉ ነው ለጣሊያን የሰጡት” (ገፅ 165) ሲሉ ስለ ወደብ የገለጹበት መንገድ ሊያስማማ ይችላል፡፡ የሚያስማማን ታዲያ ምኒሊክ ስለ ወደብ አለማወቃቸው “ደንቆሮ” ስለሆኑ ነው ባሉት ብቻ ነው፡፡ የዛሬዎቹ መሪዎቻችንስ “ወደብ አንፈልግም የአሰብ ጉዳይም የተዘጋ ፋይል ነው” የሚሉን በምን ምክንያት  ይሆን? ዕውቀት ወይስ ድንቁርና?
ለማጠቃለል ያህል “መጽሐፉ” በሩጫና በይድረስ ይድረስ የተጻፈ መሆኑን ከቋንቋው፣ ከመዋቅር እና ከማስረጃ አጠቃቀስ ድክመቱ መረዳት ይቻላል፡፡ በጥድፊያ እንዲጻፍ ሰበብ የሆነውም የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ የግል ጋዜጦች ይጽፉት የነበረው አስተያየትና ዜና ሁሉ በምኒልክ ደጋፊዎችና በሸዋዎች  እንደ ተፈጸመ በማመንዎ ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ ምኒልክንና ሸዋን በከሃዲነት በመፈረጅ በማውገዝና እውነቱን በማውገርገር የሚጠቃለለው፡፡
በመሠረቱ ይህ ታላቅ ድፍረት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው፡፡ ዛሬ ዓለም በሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ወደ አንድ መንደር እየተቀየረች ባለችበት ዘመን፣ አውሮፓን የሚያህል ታላቅ አህጉር ወደ አንድ አገርነት እየተቀየረ ባለበት ጊዜ፣ አፍሪካን አንድ አገር ለማድረግ ወይም በህብረት ለማጣመር ከፍተኛ ትግል በሚደረግበት አገር ላይ ሆነን፣ እነ ማንዴላን የመሰሉ የይቅርታ እና ሰላም አባቶችን አሰልጥነን ለፍሬ ያበቃን ዜጐች፤ ያለቀ፣ የደቀቀ ነገር እየጐተቱ ህዝብን በዘረኝነት መርዝ ለመበከል የሚደረገው የቀን ከሌት ሩጫ ሁሉ ከንቱ የዋህነት ስለሆነ በተለይ “ደራሲ ነኝ፤ ጋዜጠኛ ነኝ፤ ወዘተ” የምንል ሁሉ ነገ ተጠያቂነት እንዳለብን መገንዘብ ይኖርብናል። በአጠቃላይ “መጽሐፉ” በቋንቋም ሆነ በይዘቱ እጅግ ደካማ በመሆኑ ባይታተም ኖሮ  በተለይ ለጸሐፊው የተሻለ ጥቅም ያስገኝ እንደነበር መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡    

Read 1847 times