Saturday, 15 February 2014 13:00

አሁንም ስለጤፍ…

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(5 votes)

የሆሊውድ ዝነኞች በጤፍ ፍቅር ተለክፈዋል
“የጎጃም ማኛ”… “የዳላስ ሰርገኛ”… ልንል ይሆን?


ጊዜው የጤፍ ሳይሆን አይቀርም…
መንግስት አወጣው የተባለውና በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች የተሰራጨው የእንጀራ የጥራት ደረጃ፣ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
“እንጀራ ይሄን ያህል ሴንቲሜትር ራዲየስና ይሄን ያህል ግራም ክብደት ከሌላት፣ ስትታጠፍም እንክትክት ካለች… እሷ ከጤፍ ሌላ እህል የተቀላቀለባት ፎርጅድ እንጀራ ስለሆነች ከጥራት በታች ናት!” የሚለው የመንግስት መመሪያ፣ ከወረቀት በሳሳ እንጀራ ለተማረሩ የኔቢጤ ‘ሸምቶ በሊታዎች’ ትልቅ የምስራች መሆኑ አልቀረም፡፡
ይህ መመሪያ፣ ለኛ ለምጣድ አልቦዎች የተስፋ… ለዋዘኞች ደግሞ የተረብ ምንጭ ሆኗል፡፡ እንጀራ ጀርባዋ ልሙጥ፣ ፊትለፊቷም አይናማ መሆን እንደሚገባት የሚደነግገውን ይሄን መመሪያ የሰማ አንድ ተረበኛ እንዲህ አለ አሉ…
“መመሪያው ክፍተት አለበት!... እንጀራ ስንት አይን ሊኖራት እንደሚገባ በግልጽ አያስቀምጥም!”፡፡
የአበሻ እንጀራ በሴንቲሜትርና በግራም የምትለካበት፣ አይኗም የሚቆጠርበት ዘመን መጣ ብለን ሲገርመን፣ እነሆ ጤፍም ከብሄራዊነት አልፋ አለማቀፍ አጀንዳ ሆነች፡፡
ያበሻ ጤፍ ከሰሞኑ የአለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆናለች፡፡ ባለፈው ሳምንት ዘ ጋርዲያን፣ ጤፍ በአለማቀፍ ገበያ ተወዳጅ ምርት እየሆነች መምጣቷንና በኪሎ ከ200 ብር በላይ እየተቸበቸበች መሆኗን አስነብቧል፡፡ የአሜሪካና የተለያዩ የአውሮፓ አገራት ገበሬዎች ጤፍ ማምረት መጀመራቸውንም ዘግቧል፡፡
በዚህ ሳምንት ደግሞ ሃፊንግተን ፖስትን ጨምሮ ሌሎች የአለማችን ታዋቂ ጋዜጦችና መገናኛ ብዙሃን ስለጤፍ ሌላ አነጋጋሪ ዘገባ አውጥተዋል። እንደተባለው ከሆነ፣ ጤፍ በሆሊውድ ታዋቂ የፊልም ተዋንያን ዘንድ ተመራጭ ከሆኑ የምግብ ሰብሎች አንዷ ሆናለች፡፡
እነሆ የጎጃም ማኛ እና የአደኣ ነጭ ጤፍ ብቻ ሳይሆን የቴክሳስ ሰርገኛ የሚባልበት ጊዜ ላይ ሳንደርስ አልቀረንም፡፡ ዘንድሮ ጤፍ በ400 ግራም ከረጢት ታሽጋና ሰባት ፓውንድ የሚል ዋጋ ለጥፋ ወደ ሆሊውድ ሰተት ብላ ገብታለች፡፡
የአለማችንን ታዋቂ ሰዎች የምግብ ምርጫ መዝግቦ ይፋ በሚያደርገው ዝርዝር ውስጥ አዲስ ስም ብቅ ብሏል - ጤፍ! የስፓይስ ገርልስ የሙዚቃ ቡድን አባል የነበረችዋ የታዋቂው እግር ኳስ ተጫዋች ዴቪድ ቤካም ባለቤት፣ ቪክቶሪያ ቤካም በጤፍ ፍቅር አቅላቸውን ከሳቱ ዝነኞች አንዷ ናት። እሷ ብቻም አይደለችም፣ የሼክስፒር ኢን ላቭ መሪ ተዋናይ ጂዋይኔዝ ፓልትሮውም ከጤፍ አፍቃሪዎች አንዷ መሆኗ ነው የተነገረው፡፡
“ኢትዮጵያውያን በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዘመናት አጣጥመው ሲበሉት የኖሩት ጤፍ፣ አሁን በተቀረው አለም የሚኖሩ ብዙዎች ነጋ ጠባ ስሙን የሚያነሱት፣ ለማጣጣም የሚሳሱት አዲስ የምግብ እህል ሆኗል” ብሏል ሃፊንግተን ፖስት ስለጤፍ ባስነበበው የሰሞኑ ዘገባው፡፡
ዘገባው እንደሚለው፣ ጤፍ ብረትን ጨምሮ ሌሎች ለጤና ተስማሚ የሆኑ የንጥረነገር አይነቶችን በውስጧ መያዟ ነው፣ ያበሻ መለያ የሆነች ያገርቤት እንጀራ ከመሆን አልፋ በአውሮፓና በአሜሪካ ተወዳጅ ያደረጋት፡፡
በአገር ቤት ሳለች፣ በአገር ልጅ አንደበት “ሆድ ከመሙላት በቀር ጥቅም የላትም” ተብላ ትንኳሰስ የነበረች ጤፍ፣ እነሆ ያላገሯ ስትገኝ “ማን እንደሷ!” ተብላ መሞካሸት ጀመረች፡፡ የጥራጥሬ ዘር በሙሉ ቢሰለፍ፣ እንደ ጤፍ በካልሺየም የበለጸገ አይገኝም ተብሎ ተመሰከረላት፡፡ አንድ ስኒ ጤፍ 123 ሚሊግራም ካልሺየም ትይዛለች ተባለላት፡፡
ምን ይሄ ብቻ… ይህቺው ገበያ የቆመላት እህል፣ በአብዛኛው በጥራጥሬዎች ውስጥ የማይገኘውን ቫይታሚን ሲ አጭቃ ስለመያዟና በፕሮቲን ስለመበልጸጓ ተነግሮላታል፡፡ ኢትዮጵያውያን በምግብ ከሚያገኙት ፕሮቲን ሁለት ሶስተኛውን የምትሰጣቸው ጤፍ እንደሆነችና ከጀግና አትሌቶቿ ስኬታማነት በስተጀርባ ይህቺው ታሪከኛ ቅንጣት ፍሬ እንዳለችም፣ ዘ ሆል ግሬንስ ካውንስል ሰጠኝ ያለውን መረጃ ጠቅሶ ሃፊንግተን ፖስት ጽፏል፡፡
“ጤፍ እንዲህ ዛሬ ቀን ሊወጣላትና የስነምግብ አጥኝዎችን ትኩረት ልትስብ፣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በተለያዩ አገራት የእንስሳት መኖ ነበረች” የሚለውን የሃፊንግተን ፖስት ዘገባ ያነበበ የኛ አገር ሰው፣ “ምን ያሉት ጡር የማይፈሩ ግፈኞች ናቸው!?” ማለቱ አይቀርም፡፡
የሆነው ሆኖ፣ አሁን ጊዜው የጤፍ ሆኗል፡፡ ጣዕሟና በውስጧ የያዘችው ንጥረነገር ከተመራጭ የምግብ ሰብሎች ተርታ አሰልፏታል፡፡ ፕላኔት ኦርጋኒክስ የተባለው የእንግሊዝ የምግብ አቅራቢ ኩባንያ ባልደረባ የሆኑት ቶቢ ዋትስ፣ ጤፍ በኩባንያው በንጥረነገር የበለጸጉ ጥራጥሬዎች ዝርዝር ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የተሰለፈች አዲሷ የምግብ ሰብል መሆኗን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደንበኞቻቸው ዘንድ እየታየ የመጣው የጤፍ ፍላጎትና ተወዳጅነት፣ ገና ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ አይቀርም ባይ ናቸው፡፡
ፕላኔት ኦርጋኒክስ  ጤፍን በተመለከተ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ጤፍ በተመጋቢዎች ላይ አለርጂ የመፍጠር እድሉ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ ከተመገቡት በኋላም በቀላሉ የሚፈጭ ነው፡፡ ለአጥንት፣ ለቆዳና ለመገጣጠሚያ አካላት ጅማቶች ጤንነት እጅግ ጠቃሚ በሆነው ሲሊካ የተሰኘ የሚንራል አይነት የበለጸገ መሆኑም፣ የጤፍን ጠቀሜታ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከአንድ ሲኒ ጤፍ 286 ካሎሪ፣ 56.8 ግራም ካርቦሃይድሬት እና 8.4 ግራም ፕሮቲን እንደሚገኝም ይሄው መረጃ ያሳያል፡፡
ሃፊንግተን ፖስት እንደዘገበው፣ ጤፍ ተደራራቢ ፕሮቲን ያላቸው የምግብ አይነቶችን ለማይመገቡና ለቬጂቴሪያኖች አሪፍ አማራጭ መሆኑ በጥናት ተደርሶበታል፡፡ እንግሊዛዊቷ የስነምግብ ተመራማሪ አሊስ ማኪንቶሽ ለሃፊንግተን ፖስት እንዳሉት፣ ጤፍ ለጤንነታቸው የሚጠነቀቁ ሰዎች ተቀዳሚ ምርጫ መሆኑ አይቀርም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ተፈላጊነቱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ባይ ናቸው ተመራማሪዋ፡፡
የሴትዮዋ አባባል እውነት ሳይኖረው አይቀርም።
ዘ ጋርዲያን ጤፍ በእንግሊዝ ተወዳጅ እሆነ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሳምንት በሰራው ዘገባ፣ አንድ ኪሎ ግራም ጤፍ ከ200 ብር በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ እነሆ በቀናት እድሜ ውስጥ፣ ሃፊንግተን ፖስት በሰራው ዘገባ ሌላ የዋጋ ተመን ይፋ አድርጓል፡፡ ዘገባው እንደሚለው አሁን፣ በእንግሊዝ ገበያ 400 ግራም የጤፍ ዱቄት ከ200 ብር በላይ እየተሸጠ ነው ያለው፡፡ ጤፍ ዝናዋ እየናኘ መሄዷን ተከትሎ ዋጋዋም ሰማይ መንካቱ አይቀሬ እንደሚሆንም ዘገባው ግምቱን ሰጥቷል፡፡
እንግሊዛዊቷ የስነምግብና የአካል ብቃት ባለሙያ ፍራንሲስካ ፎክስ እንደሚሉት፣ ጤፍ ለተመጋቢዎች አጠቃላይ ጤና ተስማሚ የሆነ የጥራጥሬ ዝርያ ነው፡፡ “ፊቴን ከአሳማ ስጋ ወደ ጤፍ ያዞርኩትም፣ በአስገራሚ የንጥረነገር ይዘቱ ሰበብ ነው” ብለዋል - ሴትዮዋ ለሃፊንግተን ፖስት ዘጋቢ፡፡
ፕላኔት ኦርጋኒክስ የተባለው የእንግሊዝ የምግብ አቅራቢ ኩባንያ ባልደረባ የሆኑት ቶቢ ዋትስ ግን፣ እንደ ፍራንሲስካ የጤፍን ጸጋ የተረዱና ጤፍ በልተው ማደር የጀመሩ በርካታ ብልሆች ቢኖሩም፣ አሁንም ድረስ ገና የጤፍ ጥቅም ያልገባቸው ብዙ ናቸው ይላሉ፡፡
“አሁንም ድረስ ስለጤፍ ጠቀሜታ በቂ መረጃ የሌላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ጤፍ መመገብ ለጤናማነት የሚያበረክተውን ጠቀሜታ በሚገባ ያልተረዱ በርካቶች አሉ” በማለት ለዴይሊ ሜል የተናገሩት ዋትስ፣ ደንበኞቻቸው ግሉቲን ፍሪ ተብለው ለሚታወቁ ከፍተኛ የንጥረነገር ይዘት ላላቸው ጥራጥሬዎች ያላቸው ፍላጎት እያደገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጤፍም ከነዚህ የጥራጥሬ አይነቶች አንዱ እንደመሆኑ፣ ስለይዘቱ ለደንበኞች በስፋት በማስተዋወቅ ለወደፊት በገፍ እንደሚሸጡት በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡
እንኳን ስለጤፍ መረጃ የሌላቸው እንግሊዛውያን፣ ስለጤፍ ይሄንኑ ዘገባ ሰርተው ለህዝቡ ይፋ ያደረጉት የዴይሊ ሜል ጋዜጠኞችም ነገርዪውን በቅጡ የሚያውቁት አይመስሉም፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው ደግሞ፣ ስለ ጤፍ የሰሩት ይሄው የራሳቸው ዘገባ ነው፡፡
“የኢትዮጵያ ዋነኛ ሰብል የሆነው ጤፍ” በሚል መግለጫ ጽሁፍ አጅበው በዘገባው ላይ ያወጡት ፎቶግራፍ፣ የጤፍ ሳይሆን የገብስ ነበር!

Read 4262 times