Saturday, 22 February 2014 13:11

የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(10 votes)

ባንግላዲሽ ሲታማ ለኔ ብለህ ስማ---

በባንግላዲሽ ሰዎች ዘንድ ሰውን ትክ ብሎ መመልከት፤ ያውም በቅርበት፤ ነውርነት የለውም። አንዳንዱ ትክ ብሎ ሲመለከትህና “አንተ፤ እገልዬ አይደለህ እንዴ?” ብሎ አቅፎ ሊስምህ ያሰፈሰፈ የሩቅ ዘመድ ሊመስልህ ይችላል፡፡ ትክታው በዝቶብህ፤ ብልጭ ሲልብህ፣ “ምን አባክ አፍጠህ ታየኛለህ? እኔም እንዳንተው ሰው ነኝ፣ አይን አለኝ ጆሮ አለኝ፤…ወይስ ጸጉሬ እንዳንተ የሚያሟልጭ ስላልሆነ ነው?” ብለህ ግብግብ ልትገጥም ሁሉ ትችላለህ። በዚያ ላይ የባንግላዲሽ ሰው ቀጭንም አጭርም ስለሆነ፣ የመጣው ይምጣ ብለህ ትግል ብትያያዝ እንኳ ቢያንስ ከታች እንደማትውል እርግጠኛ ነህ፡፡ በዚህም የተነሳ ለፀብ ልትገፋፋ ትችላለህ፡፡
አብራኝ የነበረችው የጉዞና የስራ ባልደረባዬ ወ/ሮ ህይወት እምሻው፤ ትክታቸው ምርር ብሏት “እኔ የምልህ፤ ተስፍሽ እኔን ብቻ ነው አንተንም ነው እንደዚህ ትክ ብለው የሚያዩት? ቀለሜን አስለቀቁት’ኮ” ብላ ጠየቀችኝ፡፡ “አንቺ ጋ የመጡት እኔን አጠውልገው ነው” ብዬ ላስቃት ሞከርኩ፣ ግን አልተሳካልኝም፡፡ ምክንያቱም፤ ተበሳጭታለች!
ሌላ ደግሞ፤ በባንግላዲሽ ሰዎች ዘንድ አበሻ “ገመና” የሚለው አሊያም ፈረንጆች “ፕራይቬሲ” የሚሉት ነገር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ወደ ባንግላዲሽ ዋና ከተማ ወደ ዳካ ለመጓዝ ዱባይ አውሮፕላን ጣቢያ ላይ የተቀበለኝ ትክታቸው በምን እንደሸኘኝ ልንገራችሁማ፡፡ የሰነበትኩበትን ሆቴል በጠዋት ለቅቄ እቃዬን እንግዳ መቀበያ ክፍል አኑሬ ስለነበር፣ ማምሻዬ ላይ ለጉዞ እንዲመቸኝ ብዬ የሻንጣዬን እቃዎች ወዲያ ወዲህ ሳደርግ፣ የሆቴሉ ባልደረባ ወደኔ መጣ፡፡ መቼም እንግሊዝኛ የለም፤ በምልክት “ልርዳህ?” አለኝ፡፡ ፈቃድ መጠየቁ አልነበረም፡፡ ሰው ተቸግሮ እያዩ ፈቃድ መጠየቅ ምን ያደርጋል? የሚል ይመስላል - “እንግዳ ተቀባይ ወጣቱ” ባንግላዲሽያዊ፡፡
“ታንክ ዩ” አልኩትና ሽከፋዬን ቀጠልኩ፡፡ ያ ሰው ታዲያ አጠገቤ ቆሞ የእቃዬን ዝርዝር ይመለከት ጀመር፡፡ “ሰሞኑን ብርድልብስ ጠፍቶባቸው ይሆን እንዴ?” ብዬ ለራሴ ቀለድኩ፤ በሆዴ፡፡ ይግረምህ ብሎ በጣም ተጠግቶ መመልከት ጀመረ - ክሎዝ አፕ ፎቶ እንደሚያነሳ የሰርግ ፎቶ አንሺ፡፡ ቋንቋዬን ባያውቅም፤ ቀልደኛ ሰው ከራሱም ጋር ይቀልዳልና፤ ልክ ልኩን ልንገረው ብዬ “ምን ይገትርሃል?” አልኩት፤ በአማርኛ፡፡ “ብቆም ምን አለበት? እቃህን በአይኔ ነው እንጂ በእጄ አልነካሁብህ!” ያለኝ መሰለኝ፤ በባንግላዲሽኛ፡፡
የአገሬ ሰው ስለ ገመና፣ ስለ ሰው ምስጢር፣ የሰውን ነገር ያለፈቃድ ስላለማየት ያለውን የ “መመሪያ” ጥራዝ በአይነ ህሊናዬ ለአፍታ አነበብኩ። ባንግላዲሻውያን በሌላኛው ጠርዝ ላይ ነው ያሉት። አበሻም በራሱ መንገድ እንደሚያበዛው ደሞ ልንገራችሁ፡፡ አንቱ የተባለ፤ እኔ ነኝ ያለ ታዋቂ ሰው መጥቶ አጠገባችን ቆመ እንበል፡፡ ስንታችን እንሆን “ጤና ይስጥልኝ፤ እገሌ ነህ አይደል? ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ በጣም እንደማደንቅህ እና እንደማከብርህ ልነግርህ እወዳለሁ” ብለን ለመጨበጥ እጃችንን የምንዘረጋው? ያን ሰው በቆረጣ ስናይ ቆይተን (ሰውየው) ከዚያ ቦታውን ለቆ መንቀሳቀስ ሲጀምር ወይም ርቆ ከሄደ በኋላ “እንትና ነው’ኮ፤ ሾፍከው?” ነው የምንባባለው፡፡ እንኳን ተራን ሰው ዝነኞቻችንን እንኳ ትክ ብለን የማናይ ሰዎች ነን ለማለት ያህል ነው፡፡
ለማንኛውም ሁለቱም ጫፍ ጤናማ አልመሰሉኝም፡፡ ስለራሳችን እናውራ ካልን “ትህትናችን” ከልክ ያልፋል፡፡ ፈታ ፈታ ብለን እንግዶችን እንዲሁም ታዋቂ ሰዎችን ማነጋገር እንልመድ፤ አይመስላችሁም? ወደን በተቀላቀልነው እድር ውስጥ የማናውቀው አባል ከጎናችን ለሰዓት ተቀምጦ ሲነሳ የማነጋግር አለን አይደል? የንግድ ማህበር አባል ሆነንም የማናውቀውን ሰው “እገሌ እባላለሁ፣ የምኖረው … ወዘተ” መች እንላለን? ወይም… እንበል በቃ!
ባንግላዴሻውያን ምግባቸው ቅመም በቅመም ነው፡፡ በተለይ በተለይ በየምግቦቻቸው ውስጥ ሁሉ የምትገባ አንድ ቅመም አለች፡፡ ራት ስንበላ “ይቺን ቅመም የማውቃት መሰለኝ” አልኩ ለወ/ሮ ህይወት፡፡ ከማወቅም አልፎ ልጅ ሳለሁ ተክዬ ወይም ዘርቼ፣ ዘሯን አበርክቼ የማውቅ ሁሉ መስሎ ተሰማኝ፡፡ ትንሽ ቆይቼ ምንነቷና ስሟ ትዝ አለኝ፡፡ ማን መሰለቻችሁ? ድንብላል! ለህይወት ስነግራት “ልክ ነህ ልጄ፤ ድንብላል---አዎ ድንብላል” አለች፤ የዘመዷን ስም የረሳች ያህል እንደተፀፀተች በሚገልጽ ድምፀት ጭንቅላቷን እየናጠች፡፡ “እማ አገርም’ኮ…” ብላ ቀጠለችበት፡፡
የራሴን ትዝብት ላውራችሁና … ድሮ፣ ድሮ ድንብላል ምግባችን ውስጥ ይዘወተር ነበር፡፡ አሁን አሁን ቀረ ልበል? ግን ለምን ይሆን? ትንሽ ስቆይ ጥሌ ሁሉ ከዘፈኖቹ በአንዱ ውስጥ እንዳነሳት አስታወስኩ። “ጥሩ መቼ ጠፋ ከቅመም ድንብላል፤ ከሴት አንችን አየሁ አይንሽ ያባብላል” (መሰለኝ) ብሎላታል፡፡ ከቅመም ምርጡ ድንብላል ነው። ከውበት ደግሞ የማይታለፈው አይን ነው ማለቱ መሰለኝ፤ የዘፈኑ ደራሲ፡፡ እስቲ ሰሞኑን ወደ ቅመም ተራ ወጥቼ የድንብላል ዋጋ ስንት እንደ ደረሰ እጠይቃለሁ፡፡
በዳካ ከተማ ብሎም በሌሎች ባየኋቸው ከተሞች ውስጥ ፌስታል የለም፡፡ እቃ የሚገዛ ሰው የሚያምር የወረቀት ፖስታ ይሰጠዋል፡፡ ፖስታው በጋዜጣ የተሰራ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ከክርታስ ብጤ፡፡ ከትላልቅ የገበያ አዳራሾች ጀምሮ እስከ ዳካ የአየር ጣቢያ የቀረጥ ነጻ ሱቆች ድረስ የሚሰራባቸው ባለማንጠልጠያ ወረቀቶች ናቸው፡፡ ከተማዋ የራስዋ ቆሻሻ አላት፤ ፌስታል ግን የትም አይታይም፡፡ አገሪቱ በአቋም ደረጃ ፌስታልን እንዳገደች መጠየቅ አላስፈለገኝም፡፡ ያ ሁሉ ህዝብ የሚተራመስባት አገር ያለፌስታል መኖር ከቻለች አዲስ አበባ (ቆጨኝ)… እኛ’ኮ እንደ ወፍራም ሸክላ ምጣድ ብዙ የኑሮ እሳት ከለበለበን በኋላ፣ ቆይተን ነው የምንሰማው፡፡
የባንግላዲሻውያን የመኪና አነዳድ ያስጨንቃል። ስርዓት ብሎ ነገር የላቸውም፡፡ “ማሪኝ አዲስ አበባ” ያሰኛል፡፡ አሽከርካሪዎች ከግራ ወደ ቀኝ ጫፍ እየተሽሎከሎኩ ሲበሩ ማየት የየጎዳናው ትዕይንት ነው፡፤ የሚያጣድፍ ጉዳይ ያለውም የሌለውም ይከንፋል፡፡ ሽል ሽል፤ ሽው ሽው፤ ላጥ ላጥ፤ ዘው ዘው- እንደዚያ ነው አነዳዳቸው፡፡ ቀዥቃዣ የተባለ የአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌር ዳካ ደርሶ ቢመለስ ወይ አብዶ አሊያም ሰክኖ ይለይለታል ብዬ አስባለሁ። ባለሁለት እግር፣ ባለሶስት እግር ብስክሌቶች፣ ሞተር ብስክሌቶች፤ ባጃጆች፤ በእንስሳ የሚጎተቱ ጋሪዎች፣ እጅግ ዘመናዊ የሚባሉ አውቶሞቢሎችና ከባድ መኪናዎች ሁሉም ተመሳሳይ አነዳድ ነው ያላቸው - መሬት ይዘው ይበራሉ፡፡ በዚያ ላይ ጥሩንባቸው ለጉድ ነው፡፤ መሪ የጨበጠ አሽከርካሪ (ሾፌር) በሙሉ ይሄ ነው ሊባል በማይችል ምክንያት ጥሩንባ ሲያንጣርር ነው የሚውለው። ወደ አዲስ አበባ ከተመለስኩ በኋላ መንገዶችን ሳዳምጥ በፀጥታ የተሞሉ ሆነው ነው ያገኘኋቸው። ከመሄዴ በፊት አዲስ አበባን በጥሩምባ ብዛት ከዓለም የሚስተካከላት የለም ብዬ በጣም አዝን ነበር፡፡ ብራቮ የአገሬ አሽከርካሪዎች! እባካችሁን ከዚህ የበለጠም እንሁን፡፡ በተለይ ትራፊክ መብራት ገና ከመልቀቁ አምስት ሰከንድ እንኳን ሳይታገሱ ጡሩንባቸውን የሚለቁ አሽከርካሪዎች ከትዕግስት ጋር እንዲለማመዱ እመክራቸዋለሁ፡፡
ባይገርማችሁም በዳካ ከተማ ውስጥ የእግረኛ ማቋረጫ (ዜብራ መንገድ) አላየሁም፡፡ እግረኛው ቁርጡን አውቆ መንገድ የሚያቋርጠው እየሮጠ ነው፡፡ “እግሬ አውጪኝ”፤ ትክክለኛ አገሩ ዳካ መሆን አለበት፡፡ ሁሉም ያዋጣኛል ባለው መንገድ ነው የሚያቋርጠው፡፡ እንደ አዲስ አበባ እግረኛ በሁለት እግሩ (ጫማ) መንገድ እየለካ የሚሄድ የለም፡፡ እንቀራፈፋለሁ ካለ ከከባድ መኪና ቢያመልጥ ከሞተር ብስክሌት አያመልጥማ፡፡ “ለእግረኛ ቅድሚያ ሲዳላ ነው” ብያለሁ፡፡ አስር ሚሊዮን ህዝብ ችርችም ብሎ ባለበት ከተማ ውስጥ “እግረኞች በዜብራ መንገድ ተሻገሩ” ቢባሉ አሊያም “አሽከርካሪዎች ለእግረኛ ቅድሚያ ስጡ” ቢባሉ ማንም የትም መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። በነገራችን ላይ አሽከርካሪምች የግራ፣ የመሃል ወይም የቀኝ መስመራቸውን (ሌናቸውን) ጠብቀው እንደማይነዱት ሁሉ የከተማው ሰውም ለሰልፍ ተራ ደንታ የለውም፡፡ ሰዎች ሰልፍ ይዘው እያለ አንዱ ያለ ምንም ቅሬታ ከመሃል ጥልቅ ሊል ይችላል፡፡ “አሃ” ያልኩት እዚህ ጋ ነው፡፡ አሃ! ኋላ ቀርነትና ስርዓት አልባነት አይነጣጠሉምና!
ዳካ ውስጥ ብዙ ሰዎች በተሽከርካሪ አደጋ ይሞታሉ፡፡ ከዳካ 40ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ ወደምትገኝ ከተማ ለስራ ጉዳይ ሄደን ነበር፡፡ የጤና ጣቢያ ኃላፊው፤ ልጆችን ለህመም የሚዳርጉና ገዳይ የሆኑ በሽታዎችን ሁለት ጠርቶ ሶስተኛውን “የመኪና አደጋ ነው” አለን፡፡ አንደኛ ምክንያት ያለመሆኑም ይገርማል፡፡ አናሳዝንም ግን? እነማን መሰልናችሁ? እኛ በስልጣኔና በሀብት ወደ ኋላ የቀረን፣ ለህይወታችን ዋጋ የማንሰጥ፣ ለንብረታችን የማንጠነቀቅ፣ዝም ብለን በራሳችን ጥፋት የምናልቅ ህዝቦች!
ወጣ ካልንበት ስንመለስ የመኪናችን ሾፌር ጤነኛ አልመስላችሁ አለን፤ ከፊት ለፊት ከሚመጣ መኪና ጋር ለመጋጨት እናም ነፍሱን ለማጥፋት የቆረጠ ይመስላል፡፡ ቀስ በል እንዳንለው በምን አፍ። በዚያ ላይ ብስክሌቱ፣ በበሬ የሚሳበው ተሽከርካሪ፣ አውቶቡሱ ሁሉ የሚተራመሰው በጠባብ መንገድ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባን ጎብኝቶ የመጣ አንድ የስራ ባልደረባችን ባንግላዲሻዊ “ባንግላዲሽ እንደ ኢትዮጵያ አልታደለችም፤ የቀለበት መንገድ የላትም፡፡ ለምን መሰለህ? ከተማዋ በውሃ የተከበበች ናት፡፡ አራት ጊዜ የሚያቋርጣት ወንዝ አለ፡፡ ያንን ሁሉ አርቆ መሰረት አውጥቶ መንገድ መስራት ያስቸግራል” አለኝ፡፡ ለቀለበት መንገድም መታደል ያስፈልጋልና!
የባንግላዲሽ ዋና ከተማ በዛፎች ብዛት የሚስተካከላት ያለ አይመስለኝም - የሰው ግምት ባየው ወይ በሰማው ልክ አይደል እንግዲህ፡፡ ከአውሮፕላን ጣቢያ የተቀበለን ሾፌር እንዲህ ብሎኝ ነበር፤ በተዘበራረቀ እንግሊዝኛ “ዳካ ግሪን ኢዝ”፤ (ዳካ አረንጓዴ ናት ማለቱ ነው፡፡) እውነቱን ነው። ህንፃ ያላረፈባቸው ቦታዎች ሁሉ በትላልቅ ዛፎች ተሸፍነዋል፡፡ የግለሰብ ቤት ግቢዎች፣ የመንገድ ጠርዞች እና ተንጠልጣይ ሳጥኖች ሁሉ ዛፎች፣ ቢያንስ ትናንሽ ተክሎች ይታዩባቸዋል፤ ስደነቅ አደርኩና በነጋታው እግሬን ላፍታታ ማልጄ ወደ ደጅ ወጣ ስል መንገዱን ጦጣዎች ሲንሸራሸሩበት ተመለከትኩ፡፡ ዛፍ ተመችቷቸው ከቅርንጫፍ ቅርንጫፍ ይዘላሉ፡፡ አልፎ ተርፎ ፎቅ ላይ መወጣጫ እየፈለጉ ይጓጓዛሉ። ከመንገደኛው የሚሰጣቸውን ጉርሻም ይቀበላሉ፡፡
ያየሁት ነገር እጅግ ስለደነቀኝ አንድ የአገሩን ተወላጅ ስለ ትዝብቴ ነገርኩት፡፡ ይህ ሰው የአንድ አለም አቀፍ ድርጅት ባልደረባ ነው፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችግር የለበትም፡፡ እና፤ “ልክ ነህ፤ ጥሩ ታዝበሃል፡፡ ከተማችን ብዙ ዛፎች አሏት” አለ ኮራ ብሎ፡፡ ቀጠለበት፤ “እንዴት መሰለህ? ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ንፋስ ይመላለስብን ነበር፡፡ በየጊዜው የሚያላጋ አደጋ ብዙ ሰዎችን ይጨርስብንም ነበር። በኋላ መንግስት መከረበትና ንፋስ-አግድ ዘዴ አድርጎ የዛፍ ተከላን አወጀ፡፡ እንደታሰበው የአደጋው መጠን በእጅጉ ቀነሰ፡፡ ነገርየው የተጀመረው በቅርቡ ቢሆንም አሁን ዛፍ መትከል የዳካ ነዋሪዎች ባህል ነው” አለኝ፡፡
ከዛፎች መልማት በኋላ የሆነውን ነገር ማሰብ አላቀተኝም፡፡ አጅሬ ንፋስ እንደለመደው እየከነፈ ሲመጣ፣ ዛፎች በቅርንጫፎቻቸው ሰነጣጥቀው ሃይሉን ያዳክሙታል፡፡ ከዚያ፤ ካሻው አውሎ ነፋስ ሊሆን እያፏጨ የመጣው ነፋስ፣ የት እንደ ደረሰ ሳይታወቅ ብትንትኑ ይወጣል፡፡
የሳምንት ቆይታዬን አጠናቅቄ ስመለስ ከቡድኔ አባላት ጋር የባንግላዲሽን ዋና ከተማ ዳካን፤ ከዳር እስከዳር የመጎብኘት እድል ገጠመኝ፡፡ አስጎብኚያችን “ያ የምታዩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ነው፡፡ ያኛው ደሞ የፓርላማ ጽ/ቤት ግቢ ነው። ከዚያ ህንጻ ጎን ያለው ትልቁ የዳካ ዩኒቨርሲቲ ነው …” ይለናል፡፡ አቤት የዛፍ ብዛት! መሀል ከተማ ውስጥ ያለውን የወፎች ዝማሬ ድምቀት ለማመን ያስቸግራል፡፡ በዚያ ላይ ዛፎቻቸው በአይነት የተለያዩ ናቸው፡፡ በፎቶግራፍም ሆነ በቴሌቪዥን አይቼ የማላውቃቸው ብዙ ዛፎች አጋጥመውኛል፡፡ የካካዋ ዛፎች በብዛት አሉ፡፡
ወደ መናፈሻ እና መተናፈሻ (ክፍት) ቦታዎች ስንመጣ፣ ዳካ ለወጣትና አዛውንቶቿ ሙት መሆኗን ተረዳሁ፡፡ ለእግር ጉዞ የሚመቹ፣ ግራና ቀኛቸው በትላልቅ ዛፎች የተከለሉ ብዙ መንገዶች እና በርካታ ጊዜ ማሳለፊያ መናፈሻዎች አሏት፡፡ ይታያችሁ! ያውም’ኮ አስር ሚሊዮን ህዝቦች የሚኖሩባት ከተማ ናት፡፡ ብዙ አስቀያሚ ቦታዎች እንዳሏቸውም ሰምቻለሁ፤ አይቻለሁም፡፡ ዛፍ አልባ ግን አይደሉም።
ከዳካ ሳልወጣ አዲስ አበባችንን ቃኘት አደረግሁ - በምናቤ፡፡ አዲስ አበባም’ኮ ህዝቡም የከተማ አስተዳደሩም ተረባርቦ ብዙ ዛፎችን ተክሏል፡፡ (ጋሽ አበራ ሞላ የምስጋና ድርሻውን የሚከለክለው የለም ብዬ ነው፡፡) የመንገድ መሃሎች፤ ለምሳሌ ቸርችል ጎዳና፤ አራት ኪሎ ቀደም ሲል መች ዛፍ ነበራቸው? እያልኩ ተደሰትኩ፡፡ እርግጥ ነው ብዙ አዳዲስ መንገዶች ለዛፍ መትከያ የተተወላቸው ቦታ ጥበቱ ይሰቀጥጣል፡፡ ለወደፊቱ ቀጫጭን እንጂ ወፋፍራም ዛፎች በዚያ ቦታ ላይ የመቆየት እድል አይኖራቸውም፡፡ በተረፈ ግን አዲስ አበባችን ከአንድ ሶስት አመት በኋላ በዛፎች የተዋቡ መንገዶች ይኖሯታል፡፡ አዲስ አበባ የምትተነፍሰውን ኦክስጂን ከየት ለማግኘት አስባ ይሆን ዛፎቿን የጨረሰችው? ብዬ ተገረምኩ፡፡
በኦክስጂን ራሳችንን ስለመቻልም እናስብ እንጂ! መናፈሻማ የማይታሰብ ነገር እየሆነ ነው፡፡ ፒያሳ በሉ አራት ኪሎ የምሳ እቃ ይዞ ከቤቱ የወጣ ሰው፣ ለአንድ አስር ደቂቃ ቁጭ ብሎ የሚነሳበት ጥላ ቦታ የት ነው ያለው? ጊዜው ቆይቷል፤ በብዕር ስሙ “ዳንዴው ሰርቤሎ” የተባለ ፀሃፊ፤በሬዲዮ የተናገረው ይሁን ያነበበው  ነገር መቼም ከጆሮዬ አይወጣም። የመልእክቱ ጭብጥ እነሆ፤ “ጊዮርጊስ አካባቢ፣ ከማዘጋጃ ቤቱ በስተግራ፣ ከአያሌው ሙዚቃ ቤት ፊት ለፊት ባለው ክፍት ቦታ ላይ ህንጻ ተሰርቶ ሳላይ ብሞት ደስ ይለኛል” ነበር ያለው፡፡ ዳንዴው ስለ መናፈሻና መተናፈሻ ያለው ግንዛቤ በወቅቱ አስደስቶኛል፡፡ በዚያ ባለው ቦታ ላይ የህንጻ ስራው ግን ተጀምሯል፡፡ ይህ ሰው እንደዚያ ያለው ከቦታው  ጋር የተለየ ፍቅር ኖሮት ሳይሆን አንድ መናፈሻ-መተናፈሻ ቦታ ፒያሳ ውስጥ ያስፈልጋል ለማለት ፈልጎ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡
ከጥቂት አመታት በኋላ ሀብታም ስንሆን፤የተወሰኑ የአዲስ አበባ ህንፃዎች ተገንድሰው መሬቱም ተጠርጎ መናፈሻ እንደሚሰራ እገምታለሁ። “ጠብ ሲል፤ ስደፍን፣ ጠብ ሲል፤ ስደፍን” የሚለው የቆርቆሮ ማስታወቂያ አሁን የት ደረሰ? ጎበዝ፤ በተለይ ወንዶች፤ ለጊዜው ባሉን ክፍት ቦታዎች ሁሉ አትክልትና ዛፎችን እንትከል እባካችሁ፡፡ ሴቶችማ በየጣሳው፣ በየባልዲ ቁራጩ፣ በየቀለም ቆርቆሮው፣ በየመድፍ ጥይት ቀለኹ ውስጥ ሳይቀር አትክልት እየተከሉ ቤታችንን እያስጌጡ ነው፡፡
ባንግላዲሽ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ እጥረት አለ። የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት እንደነበረች፣ ወዲህም የህንድ ጎረቤት መሆንዋን በማሰብ ብዙ እንግሊዝኛ ተናጋሪ አገኛለሁ የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ አልሆነም፡፡ ከሆቴል አስተናጋጅ እስከ ባለሱቅ ድረስ ያለ እንግሊዝኛ ነው የሚኖሩት፡፡ የሆቴል እንግዳ ተቀባይ እጅግ የተወሰኑ ቃላትን ብቻ ያውቃል፡፡ የባንግላዲሽ በረከት የሆነውን ፐርል የሸጠልኝ ሰውዬም “ሰር ፎር ዩ፤ አዘር ኖ” (ላንተ ብዬ ነው፤ ለሌሎች እንደዚህ ባለ ዋጋ አልሸጥም) ከማለቱ ውጭ ሌላ የተናገረው እንግሊዝኛ ትዝ አይለኝም፡፡ ነጋዴ ሁሉ አንድ ነው አትሉም። አንድ ቀን ያወቀኝን ሰውዬ የነፍስ ደንበኛ አድርጎ ለመደለል መሞከሩ አሳቀኝ፡፡ የመርኬ ነጋዴ ምን ያህል እንዳሰለጠነኝ በምን አፍ ልንገረው። ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር እንግሊዝኛ ተናጋሪ አለባቸው፡፡ ቋንቋውን ቅርጥፍ አድርገው በልተው ቅልጥፍ አድርገው የሚናገሩ ሰዎችን ብዛት አሰብኩ። አየር መንገድ፣ ባንክ፣ ወዘተ፡፡ በሀሳቤ መሀል ሌላ ሀሳብ ሰረቀኝ፡፡ እንደ ባንግላዲሾች እንግሊዝኛን ገሸሽ ብናደርገውስ? እንግሊዝኛ የጣለው የአገሬ ወጣት በአይኔ ላይ ሽው ሽው አለ፡፡
“ኖ ፋይት?” አለኝ፤ኢትዮጵያ ውስጥ ማለቱ ነው።
  “ኖ! እንኳን አገሪቱ በሬም እርስ በርስ መዋጋት ትቷል” አልኩት፡፡
ዳካ የመጨረሻ ደሀ ሰፈር፣ የመጨረሻ አሪፍ ሰፈር አላት፡፡ የድሆቹን ገባ ብዬ አላየሁም፤ የሀብታሞቹን ግን ለማየት ችያለሁ፡፡ በሰባት ሺህ ዶላር የተከራየ ቤት ውስጥ ጥሩ ፒዛ በልቻለሁ፡፡   



Read 4066 times