Saturday, 08 March 2014 13:33

የኢትዮጵያ ሥነ-ፅሑፍና ዓለምአቀፍ መድረክን የመቀላቀል ተስፋው

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

የ“ፔን ኢትዮጵያ” የሦስት ዓመት ጉዞ በጨረፍታ  

“ፔን ኢንተርናሽናል” አርማው ሉል ነው። ዓለምን በሚወክለው ሉል ላይ የተለያዩ አገራት ለጽሑፍ ከሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች የተወሰዱ ፊደላት ታትመዋል፡፡ ከአማርኛ ቋንቋም ቃ፣ ሁ፣ ል፣ ሂ … ሆሄያት በሉሉ ላይ ከሚታዩ ፊደላት ጋር ተካትተዋል፡፡ ይሄ ዓይነት ዕድል የተገኘው “ፔን ኢትዮጵያ” በአገራችን በመቋቋሙ የተነሳ ሲሆን ማህበሩ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ተመዝግቦ በየካቲት ወር 2002 ዓ.ም ነው ዕውቅና ያገኘው፡፡
ዓለምአቀፉ “ፔን ኢንተርናሽናል” ከተመሰረተ ከ90 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ከአንድ መቶ በላይ በሚሆኑ የተለያዩ አገራት 150 የሚደርሱ አቻ ማህበራትም ተመስርተዋል፡፡ የ “ፔን ኢንተርናሽናል” ምሥረታ ታሪክ የሚጀምረው ከእንግሊዝ ነው። ዋናው ድርጅት አሁን ላለበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ታሪኮችን አሳልፏል። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ ዓለምን በሁለት ጎራ በከፈለው የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን … በርካታ ውጣ ውረዶችን የመጋፈጡን ያህል ቀላል የማይባሉ ስኬቶችንም ተቀዳጅቷል፡፡
ማህበሩ መጀመሪያ ሲመሠረት “Pen” የሚል መጠሪያ ነበረው፡፡ ምህፃረ ቃሉ የሚወክለውም ገጣሚያን፣ ወግ ፀሃፊያንና ደራሲያንን  ነበር፡፡ ማህበሩ ከተመሠረተ በኋላ አቻ ክበባትን በተለያዩ አገራት በአጭር ጊዜ እያስፋፋ በመምጣቱ ምክንያት የ“Pen” ስያሜና ትርጓሜ ላይ ለውጥ ተደረገ። ምህፃረ ቃሉ የሚወክለው ትርጓሜም ከሦስት ወደ አምስት አደገ፡፡ የቃሉ ውክልና ለገጣሚያን፣ ለፀሃፌ ተውኔቶች፣ ለአርታኢዎች፣ ለወግ ፀሃፊዎችና ለደራሲያን እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ መጠሪያውም “ፔን ኢንተርናሽናል” ተባለ፡፡
ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ አቋም ያለው ፔን ኢንተርናሽናል፤በሁሉም አገራት የሚቋቋሙት አቻ ማህበራቱ በጋራ የሚያከናውኑት ግልጽ አላማዎች ቀርፆ ይንቀሳቀሳል፡፡ ማንበብና መፃፍን ያበረታታል፡፡ ሐሳብ የመግለጽ ነፃነት እንዲስፋፋ ይተጋል፡፡ ቋንቋና ባህል እንዲጎለብት ይጥራል፡፡ የዓለም ሠላም አስተማማኝ እንዲሆንና እንዲዳብር ይሰራል፡፡ ምሁራዊ የክርክር መድረኮች እንዲስፋፉ ያበረታታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የትምህርት ዕድል ያላገኙ ወጣቶችና ጎልማሶች መማር እንዲችሉ፤ የመፃሕፍት እጥረት ላለባቸው የተተረጎሙ ጥራዞችና ቤተ መፃሕፍት እንዲያገኙ፤ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የፔን ኢንተርናሽናል አቻ ማህበር አባላት አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት ስልጠና መስጠትና የሀሳብ ልውውጥ ማድረጊያ መድረኮችንም ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ፡፡
ይህንን ዓላማ መሠረት በማድረግም የፔን ኢንተርናሽናል አቻ ክበባት ባሉባቸው አገራት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ስለ ሰብአዊ መብት ለማስተማር በማእከላዊ እስያ፣ ታዳጊዎችን ማትጊያ መድረክ በጋና፣ ወጣት ፀሐፊያንን ለማበረታታት በሀይቲ፣ ማንበብና መፃፍን ለማነቃቃት በማላዊ፣ ስነ ጽሑፍን ለማስተማር በኔፓል፣ ለሕፃናት መፃሕፍትን ተርጉሞ ለማቅረብ በደቡብ አፍሪካ፣ ተንቀሳቃሽ ቤተ መፃሕፍት ለማደራጀት … በፊሊፒንስና መሰል አገራት የተከናወኑ ተግባራት ይጠቀሳሉ፡፡
በፔን ኢንተርናሽናል ስር ከተቋቋሙት ዓለም አቀፍ ክበባት አንዱ የሆነው “ፔን ኢትዮጵያ” በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ዕውቅና ከተሰጠው በኋላ ሥነ ጽሑፍን ርዕስ ያደረጉ ሦስት መድረኮችን አዘጋጅቷል፡፡ በ2004 ዓ.ም “ንባብን ማስፋፋት”፣ በ2005 ዓ.ም “ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ትርጉም ያበረከተው አስተዋጽኦ”፣ በ2006 ዓ.ም ደግሞ “ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት እና ሥነ ጽሑፍ በኢትዮጵያ” በሚሉ ዋነኛ ርዕሶች ስር ተዛማጅ ጉዳዮችን በማካተት ነበር ፕሮግራሞቹ የተከናወኑት።
ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም የተካሄደውን ጨምሮ ሦስቱም መድረኮች አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ባህል ማዕከል አዳራሽ ነው የተስተናገዱት፡፡ “ፔን ኢትዮጵያ” በሦስት ተከታታይ ዓመታት ካሰናዳቸው ክንውኖች የ2004 እና የ2005 ዓ.ም ፕሮግራሞች በምን መልኩ ተግባራዊ እንደሆኑ የሚያመለክቱ ሁለት ዳጎስ ያሉ መፃህፍትን  አሳትሞ አሰራጭቷል፡፡
የ“ፔን ኢትዮጵያ” ፕሬዚዳንት የአቶ ሰለሞን ኃ/ማርያምን ጨምሮ ከፔን ኢንተርናሽናልና ከተለያዩ አገራት አቻ ማህበራት ተወክለው የመጡ እንግዶች የተለያዩ ንግግርና መልዕክት ማስተላለፋቸውን የሚያመለክቱት የጉባኤ ዘገባዎቹ፤ በእያንዳንዱ መድረክ የተጋበዙ ምሁራን ያቀረቧቸው የጥናት ወረቀቶች፣ ጥናቶቹ ከቀረቡ በኋላ ከተሳታፊዎች የተሰነዘሩ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን፣ እንዲሁም በመድረኩ የቀረቡ ግጥሞች በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ቀርበውባቸዋል፡፡
በየካቲት ወር 2004 ዓ.ም በተሰናዳው የመጀመሪያ መድረክ ከአዲስ አበበ ዩኒቨርስቲ የተጋበዙት አብርሃም ዓለሙ “የንባብ ባህል በኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚዎቹና ተግዳሮቶች”፤ ተፈሪ ንጉሴ ደግሞ “የሥነ-ጽሑፍ ህትመት ውጤቶች ዋና ዋና ምቹ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች” በሚል ርዕስ ያዘጋጁትን የጥናት ፅሁፎች አቅርበዋል። በ2005 ዓ.ም በተሰናዳው ሁለተኛ መድረክም “የትርጉም ሚና በኢትዮጵያ” በደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም እና “ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ትርጉም ያበረከተው አስተዋጽኦ” በሚል ደግሞ በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ሁለት የጥናት ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በቀረበው የ“ፔን ኢትዮጵያ” ሶስተኛ መድረክም ተመሳሳይ መርሃ ግብር ተካሂዶበታል፡፡
“ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት እና ሥነ ጽሑፍ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን የ“ፔን ኢንተርናሽናል”ን አቻ ክበባት ወክለው ከተለያዩ አገራት ከመጡት እንግዶች ሁለት እንስት ፀሐፍት “ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ከዓለም አቀፍ ዕይታ አንፃር” በሚል ርዕስ ያሰናዱትን በውይይት መልክ አቅርበዋል፡፡
የ“ፔን ኢትዮጵያ” ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ኃይለማርያም እንዳመለከቱት፤ ማህበሩ የ5 ዓመት እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡  የተለያዩ ችግሮች ቢገጥሙትም የተለያዩ አካላት ባደረጉት ትብብርና እገዛ ሶስቱ ተከታታይ ዝግጅቶች እውን መሆን ችለዋል፡፡ በየመድረኮቹ ከቀረቡት ንግግሮች መረዳት እንደሚቻለው፤ የኢትዮጵያን ሥነ-ጽሑፍና ፀሀፍትን ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር ለማስተዋወቅ “ፔን ኢትዮጵያ” ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተስፋ ተጥሎበታል።
ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም “የትርጉም ሚና በኢትዮጵያ” በሚለው ጥናታዊ ፅሁፋቸው፤ የኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ ስራዎችና ፀሀፍት በአገር ውስጥ ብቻ ተወስነው መቆየታቸውን አመልክተዋል፡፡
“ከአገራዊ ቋንቋ ወደ ውጭ አገር ቋንቋ የተተረጎሙ ስራዎች” በሚል ንዑስ ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍም፤ በዘርፉ የሚያኮራ ስራ አለመሰራቱን ደራሲው ጠቁመዋል፡፡ የጥናት ጽሑፍ አቅራቢውን ጨምሮ የመንግስቱ ለማ፣ የከበደ ሚካኤል፣ የሀዲስ አለማየሁ፣ የአማረ ማሞ፣ የበዓሉ ግርማ፣ የብርሃኑ ዘሪሁን፣ የአስፋው ዳምጤ፣ የዳኛቸው ወርቁና የመሳሰሉ ጥቂት ፀሃፍት ስራዎች ወደ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ሩሲያና ኖርዊጂያን ቋንቋዎች መተርጎማቸውም ተገልጿል፡፡ ይህንን ትልቅ ክፍተት ለመድፈን “ፔን ኢትዮጵያ” ላይ ተስፋ ተጥሏል፡፡ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ኃ/ማርያም ባቀረቡት ንግግር “በኢትዮጵያዊያን አንጋፋና ብርቅዬ የረዥም ልብ ወለድ ፀሀፊዎች፣ ፀሐፊ ተውኔቶች፣ ተርጓሚያንና ገጣሚያን… የተሰሩ በርካታ ስራዎች መኖራቸው ሐቅ ቢሆንም ዓለም ግን እነዚህን ጠቃሚ ኢትዮጵያዊ የስነ ጽሑፍ ስራዎች ሊጋራን ወይም ሊቋደሰን አልቻለም” ብለዋል፡፡
ከአቻ ማህበራት ተወክለው በመድረኩ ላይ ከተሳተፉት የውጭ ዜጎች መካከል የዓለም አቀፉ ፔን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጆን ራልስተን ሶል “ኢትዮጵያዊያን ፀሐፍት በምንም አይነት ሁኔታ ላይ ቢገኙ ፔን ዓለም አቀፍን በመቀላቀላቸው የዓለም አቀፍ ፀሐፍት ቤተሰብ አባላት መሆናቸው እርግጥ ነው” በማለት ክፍተት መድፈኛው መንገድ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡
የታቀዱትና የታለሙት ምን ያህል ውጤታማ ይሆናሉ የሚለውን ወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል። “ፔን ኢትዮጵያ” ባዘጋጃቸው ሶስት መድረኮች ግን የኢትዮጵያ ሥነፅሁፍ የዓለም የሥነፅሁፍ መድረክን መቀላቀል እንደሚችል የተስፋ ጭላንጭል  ታይቷል።
ኢትዮጵያዊያን የስነ-ጽሑፍ ቤተሰቦች ከኖርዌይ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጃፓን… ከመጡ አቻዎቻቸው ጋር በጋራ ቁጭ ብለው መክረዋል፡፡ ዓለም አቀፉን የፀሐፍት መድረክ መቀላቀል እንደሚቻል ይህ አንዱ ምልክት ይመስላል፡፡

Read 2782 times