Saturday, 15 March 2014 13:08

አገር ጥለው የተሰደዱት የሂስና ብሂል ጥበባት!

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(0 votes)

        ሂስ ትምህርት ነው፤ ያወቁትን፣ የታዘቡትን ለሌላው ማስተማር፡፡ ለሌላው ሲባልም ለተመልካቹ፣ ለአንባቢው ወይም ለአድማጩ ብቻ ሳይሆን አንድን ጉዳይ ፈጥሮ ላቀረበው ጭምር ከፈጠረው በላይ በማሰብና በማስተዋል ፈጠራው የተሻለ፣ ያማረ፣ የሰመረ እንዲሆን ትክክለኛውን አቅጣጫ መጠቆም የሃያሲው ድርሻ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሂስን “ከወተት ውስጥ የተጨመረውን መርዝ ለይቶ ማውጣት ነው” በማለት የሂስን ረቂቅነት፣ የሃያሲውን ጥልቅ ብቃት ይገልጻሉ፡፡
ሂስ ዘለፋ፤ ማንጓጠጥ፣ መጠየፍና ማዋረድ የሚሆንበትም አጋጣሚ አለ፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ሂስ በተንሸዋረረ፣ ተንኮልን ባዘለና ቂምን መነሻ አድርጐ ሲቀርብ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ሂስ መርዛም ስለሆነ ፈጠራን ያኮስሳል፣ የፈጣሪውን ሞራል ይገድላል፡፡ በዚህ የተነሳ ኪነጥበብ እንዳያድግ ትልቅ መሰናክል ሊሆን ይችላል፡፡
ነቀፋና ትችት ሁሉ ግን ኪነጥበብን ይገድላል ማለት አይደለም፤ በተንኮልና በምቀኝነት ተነሳስቶ የአንድ ሰው ፈጠራ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኝ ከሚደረግ ዳፍንታዊ ሂስ የተለየ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ሲሆን ሂስ እውነት ይሆናል፤ እውነት ደግሞ መራራ ነው፤ ልክ እንደ መድሃኒት። መድሃኒት እየመረረ፣ እየጐመዘዘ ተውጦ ነው በሽታን የሚፈውሰው፡፡
መድሃኒትነቱም ከአንድ የኪነጥበብ ሥራ ውስጥ ያበጠውን፣ የጐበጠውን፣ የተበላሸውን፣ የቆሸሸውን አካል ብቻ ለይቶ ቁስሉ እንዲጠግግ የሚያደርግ ሲሆን ነው፡፡ ይህ አይነቱ ሂስና የዚህ አይነቱ ሂስ አመንጭ ሊወደስ ይገባዋል፤ ምክንያቱም ለተበላሸው፣ ለቆሸሸው የኪነ ጥበብ ሥራ ፈውስ ያስገኛልና ነው፡፡ ሐኪምን ማን ይጠላዋል?
ወደ ብሂል ስንመለስ ቀድመን ትርጉሙን መናገር ግድ ሊሆን ነው፤ “ብሂል” ማለት አስቀድሞ የተባለ፣ የተነገረ፣ የተጻፈ፣ የተፈጠረ፣ የተዘረፈ፣ የተቀኘ ወዘተ ማለት ነው፡፡ ብሂል ቃሉ ከግዕዝ የተገኘ ሆኖ መሠረቱም “ብህለ አለ” የሚለው ነው፡፡ በዘመናዊው አጠራር “ፕላጃሪዝም (ምሁራዊ ዝርፊያ)” የምንለው መሆኑ ነው፡፡
ብሂል ነውር ነው፤ በጥንታዊው የዕውቀት አባቶችና ደቀመዛሙርት ዘንድ በእጅጉ የሚያስነቅፍና ከሊቃውንት ተርታ የሚያስወርድ ታላቅ ቅሌት! በሊቃውንተ ኢትዮጵያ (የጥንቱ ትምህርት ማዕምራን) ዘንድ ብሂል የረቀቀ፣ የመጠቀ ቦታ አለው፡፡ ሌላው ቀርቶ አንድ ሊቅ የራሱን ቅኔ መልሶ መቀኘት አይችልም፤ ምክንያቱም “ብሂል” ነዋ! አንዴ ቅኔውን ከዘረፈ፣ ከተቀኘ፣ ወይም ከነገረ በኋላ ያ ቅኔ የእሱ ሃብት አይደም፤ የትም ቦታና መቼም ቢሆን መልሶ ሊቀኘው፣ ሊዘርፈው ወይም ሊነግረው አይችልም፤ ይህን ካደረገ ራሱን በራሱ የሚዘርፍ መሳቂያ መሳለቂያ ብቻ ሳይሆን ወራዳም ነው፡፡
ለዚህም ነው ቅኔ በየጉባኤ ቤቱና በየአድባራቱ እንደ ጐርፍ ሲወርድ፣ እንደ መብረቅ ሲንጐደጐድ የሚኖረው፤ ለዚህም ነው “የቅኔ ቋንጣ የለውም” የሚባለው፡፡ አንድ ገጠመኝ ባነሳ አባባሌን ግልጥ ሊያደርገው ይችላል፡፡ አንድ ወቅት ጐጃም፤ ጠቅላይ ግዛት ደ/ማርቆስ አውራጃ ቢቡይ ወረዳ ውስጥ “ገደብ ጊዮርጊስ” ደብር በሰምና ወርቅ ቅኔያቸው ተጠቃሽ ከነበሩት መሪጌታ አድምኡ ተሥፋ ዘንድ ቅኔ እማር ነበር፡፡
መምህሩ አንድ ጠዋት ተነስተው የተለመደ ውብ ቅኔያቸውን ሲዘርፉ የምቀበላቸው እኔ ነበርሁ። በአጋጣሚ ገና ጉባኤ ቃና (የቅኔ መጀመሪያ፣ ባለ ሁለት ቤት ግጥም) ሲዘርፉ ከሁለት ቀናት በፊት ዘርፈውት የነበረው ቅኔ ሆኖ አገኘሁት፤ ተማሪው በጉባኤ ቤቱ ሞልቷል፤ እሳቸው ከወንበራቸው ላይ ቁጭ ብለው ነው ይዘርፉ የነበረው፤ እኔ ብቻ ሁለት እግሬን ገጥሜ ቆሜ ቅኔያቸውን እቀበላለሁ፡፡ የመጀመሪያውን ስንኝ ሲዘርፉ ዝም ብዬ ተቀበልሁ፤ ሁለተኛውን ሲደግሙ መቀበሌን አቆምሁና “እየንታ ይህ ቅኔ ብሂል ነው” አልኋቸው። መምህራችን በጣም ደነገጡና “የማን ቅኔ ነው?” አሉኝ፡፡ “ከትላንት በስቲያ ራስዎ የዘረፉት ቅኔ ነው” ስላቸው ሊያስተባብሉኝ አልፈለጉም፡፡ እንዲያውም “ተቀበል!” አሉኝ ቆጣ ብለው፡፡
“ማዕከለ ብዙኃን አርድዕት ዘኢተገብረ ተገብረ፣ አምጣነ መምሕር ይትናገር ዘይሰምኦ ነገረ” ሲሉም አስገራሚ ጉባኤ ቃና ቅኔ ዘረፉ፤ ትርጉሙ “በብዙ ተማሪዎች መሃል ተደርጐ የማይታወቅ ነገር ተደረገ፤ መምህሩ (ራሳቸውን ማለታቸው ነው) የሰማውን፣ ከዚህ ቀደም የተባለውን ነገር (ቅኔ) መልሶ ተናግሯልና” ማለት ነው፡፡
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ፣ መምህሩ ቅኔውን ሲዘርፉ ከሌላ ሰው እንደ ሰረቁ ራሳቸውን ወቅሰው ለተማሪዎቻቸው የሂስን ሙያ ማስተማራቸው ነው፡፡ ብሂል ያስወቅሳላ! ብሂል በእጅጉ ያሳፍራላ! መምህሩ ይህን ነው በተግባር ያሳዩን እንጂ “ቅኔው የራሴ ነው፤ ምን አገባህ? ተማሪዬ ስለሆንህ ያልሁህን ተቀበል!” አላሉም፤ የብሂልን መጥፎነት ብቻ ሳይሆን ስህተትን በሙሉ ልብና በቅንነት መቀበልንም አስተምረውናል፡፡
የመምህሬን ጉዳይ ባስታወስሁ ቁጥር የዘመኔ ሰዎች ቢሆኑ ኖሮስ? ብዬ ከራሴ ጋር እሟገታለሁ፡፡ በአንድ መጽሐፍ ወይም ፊልም ወይም ተውኔት ላይ የላላ ሂስ ሲሞከር የሚፈጠረውን “እሰጥ አገባ” ሳይ በእጅጉ እደነቃለሁ፡፡ ራስን ከነፋስ በላይ እንደማዋል አድርጌም እቆጥረዋለሁ፡፡
ነገረ ጽሑፌ ስለ “ሂስ” እና “ብሂል” መሆኑ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ አንድ ተማሪ ነበር አሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ቅኔ ይጋፋዋል፤ አንድ ቦታ ሄዶ ቅኔ አዋቂነቱን ያስወራና ቤተክርስቲያን የመቀኘት ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ቅኔ የሁልጊዜ ፈጠራ በመሆኑ በጉጉት የመደመጥ አቅም አለው፡፡ የተማሪውን ቅኔ ለመስማት አሰፍስፈው ሲጠባበቁ የነበሩ ካህናት፣ ዲያቆናትና ደባትር መጨረሻ ላይ አፈሩ፤ ራስ በራሳቸው እየተያዩም በተማሪው ቅኔ ተሳለቁ፤ ከመሃላቸው አንዱም “ቅኔያቸውስ ደርሶናል፤ ለመሆኑ የኔታ ዕገሌ ደህና ናቸው?” ሲሉ ተማሪውን ጠየቁ፡፡
ምስጢሩ “ቅኔው ብሂል ነው፤ ዘራፊውን ከፈለግህም መሪጌታ ዕገሌ ናቸው፡፡ ለምን ትሰርቃለህ?” ማለት ነው፡፡ ብሂል እንኳንስ የሰውን የራስንም ቅኔ መልሶ መቀኘት ውርደት መሆኑን ያመላክታል፡፡ ዛሬ ራሴን ጨምሮ በርካታ ጸሐፊዎች አንድ መድረክ ላይ የሆነች ግጥም አቅርበን ከተጨበጨበልን፣ ያችኑ እንደ ዘወትር ጸሎት መድገም ይቀናናል፤ ከታተመ የግጥም መጽሐፍ ላይ ማንበብም የዘወትር ተግባር ይመስላል፡፡
በመሰረቱ ይህ ብሂል ነው፤ ራስን መዝረፍ፡፡ ራስን መዝረፍ ስለሚበረታታም ፈጠራ ይቀጭጫል። ለዚህም ይመስለኛል ልክ እንደ 1950ዎቹ ሳተና ትውልድ አይነት አገር የሚነቀንቅ ግጥም መስማት የሚናፍቀኝ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ጭፍንና የተሳሳተ ማጠቃለያ ተደርጎ ሊታይ ይችል ይሆናል፡፡ ግን እውነት ነው፤ የማንክደው ነገር ገበያ ላይ በርካታ የግጥም ስራዎች ይታያሉ፤ ግን ብዙዎቹ ግጥም ሳይሆኑ የግጥም ጭንብል ያጠለቁ ማወናበጃዎች ይመስሉኛል፤ አልፎ አልፎ፤ በጣም አልፎ አልፎ ነሸጥ የሚያደርጉ ወይም ፈገግ የሚያሰኙ ሸጋ ግጥሞች መኖራቸውን ሳንዘነጋ፡፡
ከላይ ለጠቀስሁት ችግር ዋናው ምክንያት የሂስና የብሂል መሰረቶች ስለተናጉ ይመስለኛል፤ ሂስ በአገራችን የተደላደለ መሰረት ነበረው፡፡ በጥንታውያኑ ጉባኤ ቤቶች ፈሩን የሳተ ቅኔ ሲቀርብ በመምህሩ፣ በዘራፊው፣ በአስነጋሪዎችና ሌሎች ተማሪዎች የመረረ፣ የከረረ ሂስ ይካሄድበታል፤ በንባብም ሆነ በዜማ ትምህርትም ስርአቱን የለቀቀ፣ መረን የወጣ ተግባር የሚፈጽም ሰው ከተገኘ “ትልቅ ሰው ነውና እንዴት ደፍሬ እናገረዋለሁ” ወይም “እንዲህ ብዬ ስህተቱን ብነግረው ሊቀየመኝ ይችላል” የሚባል ይሉኝታ የለም፤ ልክ ልኩ ይነገረዋል። እሱም “ማን አባቱ ተናግሮኝ!” የሚል “የአላዋቂ ሳሚነት” ተግባር አይፈጽምም፡፡ በመሆኑም የቅኔ ሙያ የተራራ ያህል ሊገዝፍ፣ ንባቡም ሆነ ዜማው በውበት ሊዘልቅ ችሏል፡፡
የሂስ ጥበብ በመዳበሩም ሊቃውንቱ ፀረ ብሂል አቋማቸውን በማጠንከራቸውና ብሂልን እንደ ውርደት ማሳያ በመቀበላቸው ሕግና ሥርዓት ሳይደነግግለት ህያው ሆኖ ዘልቋል፡፡ በዘመናችን የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ግራ ያጋባው ይህ የብሂል ተግባር በመረሳቱ ይመስለኛል፡፡ መንግስት ጸረ ብሂል (የቅጅና ተዛማጅ መብቶች) አዋጅ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ግን ራሱ የብሂል ወንጀለኛ ነው። በሬዲዮና በቴሌቪዥን ጣቢያው የሚለቃቸው ዘፈኖች፣ ግጥምና ሌሎች መሰል ስራዎች ባለቤቶቻቸው ፈቅደው ወይም ተከፍሎባቸው አይደለም፡፡
ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎችማ ድምፅ ማጉያ የጨበጠ ሁሉ ያቅራራባቸዋል፤ የተፈለገው ዘፈን ያለከልካይ ይተላለፍባቸዋል እንጂ በህግና ሥርዓት የሚመሩ አይመስሉም፡፡ ከማህበራዊ ጠቀሜታቸው አንጻር ይዘታቸው ሲታይም አንዳንዶቹ “ምን አለ ቢዘጉ” ያሰኛል፡፡ እንዲህ ስል ሁሉንም ጣቢያዎችና ፕሮግራምች ዕርባና ቢስ እያልሁ አይደለም፡፡ አላማዬ የብሂልና ሂስ ጥበባችን አደጋ ላይ ስለወደቀ፣ በምንጎመራበት ዘመን እየቀጨጭን ነን ለማለት ነው፡፡ ለዚህም የእነሱ ድርሻ የማይናቅ ነውና፡፡
የብሂል ሃብታችን በመሟጠጡ የተሻለ ተቀባይነት ያላቸው የአንዳንድ ደራስያን ስራዎች በአይን አውጣ መንታፊዎች እየተባዙ፤ የጀርባ ሽፋን ዋጋቸው በመሰሪ መንገድ እተፋቀና የተጋነነ ዋጋ እየተለጠፈባቸው ደራሲያንንም አንባቢውንም ለከፍተኛ ብዝበዛ እየዳረጉት ናቸው፡፡
የሂስ ነገርማ ሊያታኩስ ይችላል፤ በዘመናችን ሁሉም ሊቅ፣ ሁሉም ምጡቅ ነኝ ብሎ ያስባል፡፡ ትንሽ ከተነካ በእንጀራው ላይ መርዝ የተነሰነሰበት ይመስል “አገር ይያዝልኝ” ይላል፤ በመሠረቱ ይህ ብላሽ አስተሳሰብ ነው፤ አትክልት የሚለመልመውና የሚያድገው ሲታረም፣ ሲኮተኮትና እንክብካቤ ሲደረግለት ነው፡፡ የኪነ-ጥበብ ስራዎችም እንዲያ ናቸው፤ ሊታረሙ፣ ሊኮተኮቱ ይገባል፡፡ የእነሱ ዕርማትና ኩትኳቶ ሂስና ብሂል ናቸው፡፡
ሂስና ብሂል ፈጠራን ያዳብራሉ ብቻ ሳይሆን የሰላ አእምሮ እንዲኖር ያስችላሉ፤ የማይነጥፍ የጥበብ ምንጭ ለመሆንም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ። በአገራችን ስነ ጥበብ ከታላቁ ዙፋን ላይ  የተቀመጡት ሁሉ የሂስና ብሂል ጥበብ ሞርዶ ያሳደጋቸው ናቸው። ለዚህም ቅዱስ ያሬድን፣ ተዋነይ ዘጎንጅን፣ መሪ እመቤት ገላነሽ ሐዲስን፣ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን፣ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራን አባ ገብረሐናን፣ ሐዲስ አለማየሁን፣ ዘርዓ ያዕቆብና ሌሎች ዕልፍ አዕላፍ የኪነ ጥበብ እና የነገረ መለኮት ሊቃውንትን በእማኝነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ግን ምን ዋጋ አለው? በየአገሩ እየተሰደዱ ለውርደትና ለሞት እንደሚዳረጉት በርካታ ዜጎቻችን ሁሉ ብሂልና ሂስም ተወልደው ካደጉበት አገር ተሰደው እኛን ለጉድ ጐልተውናል፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት በፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረኢየሱስ “አጤ ምኒሊክ” መጽሐፍ ላይ የቀረበው የነጋድረስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ዘመናዊ ሂስ ሊቀጥል አልቻለም፤ ምክንያቱም የሂስና ብሂል ጥበባት አገር ጥለው ተሰደዋላ! መቸ ይመለሱ ይሆን?  

Read 1984 times