Monday, 31 March 2014 10:58

በስድስት ወር ውስጥ 41 ሰዎች በመንገድ ጉድጓዶችና ኩሬዎች ውስጥ ገብተው ሞተዋል

Written by 
Rate this item
(5 votes)
  • “በመንገድ ላይ ለሚደርሱ አደጋዎች የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ተጠያቂ ነው”
  • “መንግሥትን በሰራው ጥፋት መክሰስ ህገ-መንግስታዊ መብት ነው” - የህግ ባለሙያ

ለአዛውንቱ አቶ ተስፋዬ ኪዳኔ መስከረም 10 ቀን 2006 ዓ.ም መልካም ቀን አልነበረም፡፡ ከመ/ቤታቸው ወጥተው ወደ ቤታቸው እያመሩ ነበር፡፡ ከ5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ጌጃ ሰፈር በሚወስደው መንገድ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ ሲደርሱ በፍፁም ያልጠበቁት አስደንጋጭ አደጋ አጋጠማቸው፡፡ መንገድ ዳር ከሚገኝ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው እግራቸው ተሰበረ፡፡
ከድንጋጤ ጋር ሙሉ ኃይላቸውን አሰባስበው ባሰሙት የድረሱልኝ ጥሪ፣ የአካባቢው ሰዎችና የእሳት አደጋ ሰራተኞች ተረባርበው ከጉድጓዱ በማውጣት ወደ ባልቻ ሆስፒታል ለህክምና ወሰዷቸው፡፡ በሆስፒታሉ ለ20 ቀን ተኝተው ከ23 ሺህ ብር በላይ አውጥተው ቢታከሙም እንደተመኙት በፍጥነት ከጉዳታቸው አገግመው በእግራቸው ቆመው ለመሄድ አልቻሉም። ይኸውና ላለፉት 7 ወራት ከሰውና ከክራንች ድጋፍ መላቀቅ አቅቷቸዋል፡፡
አሁንም በተመላላሽ ህክምናቸውን እየተከታተሉ ሲሆን አቶ ተስፋዬ ለደረሰባቸው ጉዳት ኃላፊነት የሚወስድ አካል የትኛው እንደሆነ ባለማወቃቸው መብታቸውን ማስከበርና ካሳ ማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራሉ። “መንገዱ ላይ የተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ነው የገባሁት፣ ኃላፊነቱን መውሰድ የሚገባው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ነው የሚል እምነት አለኝ። ነገር ግን አንድ ሰው የዚህ ዓይነት አደጋ ሲደርስበት በየትኛው የህግ አግባብ፣ ማንን መክሰስና መጠየቅ እንዳለበት አላውቅም” ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ተስፋዬ ሁሉ ባለፉት 6 ወራት መንገድ ዳር ተቆፍረው ባልተከደኑ ጉድጓዶችና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ኩሬዎች ውስጥ ገብተው 41 ሰዎች መሞታቸውን፣106 ሰዎች መቁሰላቸውን ከአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠሪያ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ዓምና በግማሽ አመት ውስጥ 28 ሰዎች በተመሳሳይ አደጋ ሲሞቱ፣ 88 ሰዎች ቆስለዋል፡፡ ይህም ዘንድሮ የአደጋው መጠመን መጨመሩን ያመለክታል፡፡  
“በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ በየአምስት ሜትሩ ጉድጓድ አለ፡፡ አብዛኞቹ ጉድጓዶቹ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ለፍሳሽ (ድሬኔጅ) መውረጃ የተቆፈሩ ናቸው፡፡ ለቴሌኮም፣ ለመብራት ኃይል ኬብሎችና ለመሰል አገልግሎት የሚቆፈሩም አሉ፡፡ ጉድጓዶቹ ትላልቅ ስለሆኑ ከሰው ቁመት በላይ እስከ 2 ሜትር ጥልቀት ያላቸው ናቸው” ይላሉ፤የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር የኮሙኒኬሽ ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ፡፡
ጉድጓዶቹ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ክፍት ሊሆኑ ይችላሉ ያሉት አቶ ንጋቱ፤ ሕገ-ወጦች ክዳኑ  ላይ ያለውን ፌሮና ሌሎች ነገሮች ወስደው ክፍት ይተዋቸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የጉድጓዶቹ ባለቤት የሆኑ ድርጅት ሠራተኞች ለሥራ ይከፍቱትና ሳይዘጉ ይተዋቸዋል፡፡ ሁሉም ጉድጓዶች ያሉት መንገድ ላይ ነው፡፡ እነዚህ ጉድጓዶች ብዙውን ጊዜ ጉዳት የሚያደርሱት በክረምትና በጭለማ ነው፡፡ በክረምት ፍሳሹ ሞልቶ አስፋልቱን ስለሚያጥለቀልቀው ጉድጓድ መኖሩ አይታወቅም፡፡ በጭለማም አይታይም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለመንገድ ግንባታ ጉድጓዶች ይቆፈራሉ፡፡ ጧት ሥራ ስትሄድ ያልነበረ ጉድጓድ፣ ማታ ስትመለስ ተቆፍሮ ይጠብቅሃል፡፡ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ጉድጓድ ስለመኖሩ የማያውቅ እንግዳና ሌላውም ሰው ትራንስፖርት ለመያዝ ሲጋፋ ጉድጓዶቹ ውስጥ ወድቆ ሊጎዳ ይችላል፡፡
ይኼ በከተማው መኸልም የሚታይ ነው፡፡ ከመዲናዋ ወጣ ብለው በሚገኙ የልማት ማስፋፊያ አካባቢዎችም ለኢንቨስትመንት በማለት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ አንድና ሁለት፣ ቦሌ ቡልቡላ ወረዳ አንድ፣ ቦሌ ኤርፖርቶች ድርጅት ጀርባ፣ ኮልፌ ቀራንዮ ሚኪሌይላንድ አካባቢ፣ ሐና ማርያም፣ ገርጂ ጊዮርጊስ … አካባቢዎች ድንጋይና ማዕድን ለማውጣት ፈቃድ ወስደው የሚቆፍሩ አሉ። የሚፈልጉትን ነገር ካገኙ በኋላ ለቀው ሲሄዱ የቆፈሩትን ጉድጓድ ሳይከድኑት ክፍቱን ትተው ነው የሚሄዱት፡፡ ያ ቦታ ውሃ ይቋጥርና ኩሬ ይፈጥራል። እዚያ ውስጥ ዋና የማይችሉ ታዳጊዎችና ወጣቶች ገብተው ሲዋኙ ወይም ኮብልስቶን ጠራጊዎች የግል ንፅህና ለመጠበቅ ገብተው ሲታጠቡ ሰምጠው ይሞታሉ፡፡
ሰሞኑን እንኳ ሐና ማርያም አካባቢ ባለ ኩሬ ውስጥ አንድ የ10 ዓመት ታዳጊ ገብቶ ሬሳውን አውጥተናል፡፡ ኩሬው ብዙ ህይወት ነው የቀጠፈው። አቃቂ አካባቢ የውሃ ችግር ስላለ እዚያ አካባቢ ካለ ኩሬ ውሃ ለመቅዳት የሄደ የጋሪ ፈረስ  ከነጋሪው ኩሬው ውስጥ  ሰጥሞ ሞቶ አውጥተናል፡፡
ለእነዚህ አደጋዎች ተጠያቂዎቹ ድንጋይ ወይም ማዕድን ለማውጣት ቦታውን ቆፍረው ሲያበቁ ቦታውን ቀድሞ ወደነበረበት ሳይመልሱ ክፍቱን ትተው የሚሄዱ ድርጅቶችና አስፈጻሚ አካላት ናቸው፡፡ ቦታውን ለመቆፈር ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ፈቃድ ሲያወጡ፣ ሲበቃቸው መልሰው ለመክደን ግዴታ ይገባሉ፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱም “ቃላችሁን ባታከብሩ” ብሎ ጉድጓዱን መክደን የሚያስችል ከፍተኛ ገንዘብ በመያዣ ይቀበላል። ነገር ግን ድርጅቶቹ በቸልተኝነት ወይም በሌላ ምክንያት የቆፈሩትን ጉድጓድ ሳይዘጉ ቢሄዱ አይጠየቁም ወይም አስፈጻሚው አካል ተከታትሎ ለመያዣ በተቀበለው ገንዘብ ጉድጓዱ እንዲዘጋ አያደርግም፡፡ እኛ አገር ጥሩ ጥሩ ሕጎች አሉ፡፡ ነገር ግን ተከታትሎ የሚያስፈጽም አካል የለም፡፡
በዚህ የተነሳ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ብቻ 41 ሰዎች ባልተከደነ የመንገድ ጉድጓድና ኩሬ ውስጥ ገብተው ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከ15 ቀን በፊት ሜክሲኮ ከፌዴራል ፖሊስ ዋና ጽ/ቤት ፊት ለፊት አንድ የ32 ዓመት ወጣት ለቀላል ባቡር መንገድ በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ሞቷል፡፡ ጊዜው ትንሽ ቆየት ብሏል እንጂ አንድ ሰው በቀድሞው የአፍሪካ ኅብረት ድርጅት፣ በአሁኑ የአፍሪካ አንድነት አካባቢ ባለ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ 5 ቀን ከቆየ በኋላ እንዳጋጣሚ ሆኖ ከእነሕይወቱ ሊወጣ ችሏል፡፡ ያ ሰው ዕድለኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንዲት ልጅ በአጋጣሚ ከጉድጓድ ውስጥ ድምፅ ትሰማለች። ለማረጋገጥ ጠጋ ስትል ሰው አየች፡፡ ልጅቷ እዚህ (እሳት አደጋ) የሚሰራ ወንድም ስለነበራት፣ ደውላ ስላየችው ነገር ነገረችው፡፡ በአጋጣሚ ወንድምየው ዕረፍት ላይ ስለነበር፣ ደውሎ ነገረንና ሄደን አወጣነው፡፡ ያ ሰው አሁንም በሕይወት አለ፡፡ የሀይገር ሹፌር ሲሆን ትዳር መስርቶ እየኖረ ነው። ይኼ አደጋው ሲደርስ ዘመድ ወይም በአካባቢው የነበሩት ሰዎች ደውለውልን ያወጣናቸው ናቸው። ለእኛ ሳይደወል ዘመድ ወይም የአካባቢው ሰዎች ከጉድጓድ አውጥተው ወደ ቤትና ወደ ሐኪም ቤት የወሰዷቸው ወይም የቀበሯቸው በርካታ ናቸው፤ ቤት ይቁጠራቸው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር ብዙ ጊዜ ተወያይተናል፡፡ እኔ ራሴ ከባለሥልጣኑ ኃላፊ ከኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ጋር ተነጋግሬአለሁ፡፡ ምንም መፍትሔ ያልተገኘለት ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለልማት ተብሎ ተቆፍሮ በሚፈጠር ኩሬ ውስጥ በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ሰው ገብቶ ይሞታል፡፡ በዚህ የተነሳ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ እኛ ማድረግ የምንችለው ጉድጓድ ወይም ኩሬ ውስጥ ገብተው የሞቱትን ሬሳ አውጥተን ለፖሊስ ማስረከብ፣ አምቡላንስ ስላለን ተጎድተው በህይወት ያሉትን ህክምና ወደሚያገኙበት ማድረስ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ከኩሬ ውስጥ ሬሳ ስናወጣ በአካባቢው ላሉ ሰዎች ትምህርት እንሰጣለን፡፡ ነገር ግን እዋኛለሁ ብሎ ለሚሄድ ሰው ጠባቂ ማቆም አንችልም፡፡ ልማት ሲካሄድ ያለ ቁፋሮ ሊካሄድ አይችልም፡፡ ስለዚህ ጉድጓድ ሲፈጠር መከለል አለበት፡፡ በአካባቢው አደጋ መኖሩን የሚጠቁሙ ዓለም አቀፍ ምልክቶች ስላሉ፣ እነሱ ጉድጓዱ ጋ ከመድረሱ ከ5 ሜትር በፊት መተከል አለባቸው፡፡
ለምሽት ደግሞ አንፀባራቂ ምልክት ማኖር ያስፈልጋል፡፡ በኮንስትራክሽን ቦታዎች ብዙ ጊዜ አደጋ የሚደርሰው በዝቅተኛ ሰራተኞች ላይ ነው፡፡ ባለሙያዎቹማ አደጋ ሊኖር እንደሚችል ስለሚያውቁ ይጠነቀቃሉ፡፡ ስለዚህ ለአደጋ የተጋለጡትን ሰራተኞች ማስተማርና የአደጋ መከላከያ ቆብ እንዲደፉ፣ ቦት ጫማ እንዲያደርጉና ጓንት እንዲያጠልቁ … ማስገደድ ያስፈልጋል በማለት አቶ ንጋቱ አሳስበዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የመስሪያ ቤታቸው አቋም ምን እንደሆነ የተጠየቁት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ፍቃዱ ኃይሌ፣የሚያስተዳድሩት መስሪያ ቤት የከተማዋን መንገድ የሚሰራና የሚያስተዳድር እንደመሆኑ መሰል አደጋዎች ሲደርሱ ተጠያቂ የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለ ይገልፃሉ፡፡
መንገድ ላይ ያሉ ጉዳዮችን እየተከታተለ መዝጋትና መድፈን የባለስልጣኑ ድርሻ ከመሆኑም በላይ ህብረተሰቡም ጥቆማ በመስጠት ሊተባበር ይገባል ያሉት ኢንጂነሩ፤ እስካሁን ወደ መስሪያቤታቸው “ጉዳት ደርሶብኛልና ካሳ ይገባኛል” የሚል አቤቱታ ይዞ የቀረበ ተጎጂ ባይኖርም እንዲህ ያለ አቤቱታ ከቀረበ መስሪያቤታቸው ኢንሹራንስ ገብቶም ቢሆን ማሳከም እንዳለበትና ተጠያቂ መሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
መንገድ ሲሰራ ከሰዎች ንክኪ ተከልሎ መሆን እንዳለበት የሚያስገነዝቡት ኢ/ር ፍቃዱ፤ ከዚህ አግባብ ውጪ የመንገድ ግንባታ ሲከናወን አደጋውን ያደረሰው ሥራ ተቋራጭ ከሆነ ባለስልጣኑ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ተሽከርካሪዎች በእግረኛ መንገድ ላይ ወጥተው የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦ ክዳኖችን መስበራቸው ለጉድጓዶቹ መፈጠር መንስኤ ነው ያሉት ኃላፊው፤ በቀለበት መንገድ ላይ ያሉ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ የብረት ክዳኖችም በሌቦች መዘረፋቸው ለባለስልጣን መስሪያቤቱ ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ተሽከርካሪዎችና እግረኞች በጉድጓድ እየገቡ ከፍተኛ አደጋ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ መረጃው አለን ያሉት ኢ/ር ፍቃዱ፤ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ጠንካራ የህግ አፈፃፀም ያስፈልጋል፤ ኅብረተሰቡም ጉድጓዶች ሲያጋጥሙት ለባለስልጣኑ መጠቆም አለበት ብለዋል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ሰራተኞች የቱቦ ክዳኖችን ከፍተው ቆሻሻ ካፀዱ በኋላ በአፋጣኝ መልሰው እንዲደፍኑ፣ ኮንትራክተሮችም መንገድ ሲሰሩ ከልለው እንዲሰሩ ጥብቅ ትዕዛዝ እየተላለፈ መሆኑን ኢ/ሩ ገልፀዋል፡፡
ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የሕግ ባለሙያ፤ መንገድም ይሁን ህንፃ በአጠቃላይ የመሰረተ ልማት መዋቅር ሲሰራ በሰዎች ደህንነትና አካል ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ መሆን እንዳለበት የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ እንደሚደነግግ ጠቅሰው፤ የግንባታ ስራው ተጠናቅቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ ባለ መንገድ ላይ ለሚደርስ ጉዳት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣አደጋው የደረሰበት መንገድ ተጠቅሶ ክስ ሊቀርብባቸው ይችላል ብለዋል፡፡
በኮንስትራክሽን ሂደት ላይ ባለ መንገድ ውስጥ የደረሰ አደጋ ካጋጠመ ግን፣ ተጎጂው መንገዱን የሚያሠራውን ባለስልጣን መስሪያቤትና ሥራ ተቋራጩን በአንድነት በመጥቀስ ኃላፊነት ሊወስድ የሚገባውን አካል ፍ/ቤት ይወስንልኝ ብሎ ክስ ሊመሰርት እንደሚችል ባለሙያው አብራርተዋል። ይህ የክስ አቀራረብ ተመራጭ የሆነው፤ ሥራ ተቋራጩን መቆጣጠር ያለበት አሠሪው መስሪያ ቤት ስለሆነና በመካከላቸው ያለው ውል ስለማይታወቅ ነው ብለዋል፤ ባለሙያው፡፡
በእኛ ሀገር እንደ ልማድ ሆኖ መንገድ ሲሰራ የጥንቃቄ ምልክቶች እንደማይቀመጡ መታዘባቸውን የተናገሩት ባለሙያው፤ በአንዳንድ የሰለጠኑ ሀገሮች ከ5 ሜትር ርቀት ላይ ምልክቶችና አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ በመጠቆም በእኛም ሀገር ይህ አስገዳጅ ህግ ተፈፃሚ መደረግ አለበት ሲሉ ይመክራሉ፡፡ በቴሌ ኬብል ቀበራ ወቅት ጉድጓዶች ሳይከደኑ ከቀሩም የቴሌ መሆኑን በማረጋገጥ፣ አሊያም ፍ/ቤት ያጣራልኝ በማለት የመንገዶች ባለስልጣንና ቴሌን አጣምሮ ክስ መመስረት ይቻላል ብለዋል፡፡
በእኛ ሀገር የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን በወንጀል መክሰስ (ኮርፖሬት ክሪሚናል ሊያቢሊቲ) በሚለው ፅንሰ ሐሳብ መነሻነት የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ እንደሚከለክል የጠቆሙት የህግ ባለሙያው፤ ተጎጂው የደረሰበትን የጉዳት መጠን ጠቅሶ “ልካስ ይገባኛል” ብሎ የፍትሐብሔር ክስ ማቅረብ ይችላል ብለዋል፡፡ “መንግሥትን ከስሼ ካሣ አገኛለሁ” የሚለው ሐሳብ በራሱ በኛ ሀገር ካለመለመዱም በላይ በፍ/ቤቶች የተንዛዛ አሰራር ምክንያት ተጎጂዎች መብታቸውን እንዳያስከብሩ ዳተኛ ያደርጋል ያሉት ባለሙያው፤ ይህ ባህል መቀረፍ እንዳለበትና ሰዎች ሕጉ የሰጣቸውን መብት እንዲያስከብሩ አሳስበዋል።  
በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት እና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤትን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ሙከራ ስልካቸው ባለመነሣቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡          

Read 5523 times