Monday, 07 April 2014 15:46

የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና በቅርቡ ይጀመራል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(10 votes)

ህክምናውን ለማግኘት በርካቶች ተመዝግበው እየተጠባበቁ ነው
ዘርፉ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ባለሙያው ይናገራሉ

    “ሁለቱም ኩላሊቶቼ ከጥቅም ውጪ ሆነው የኩላሊት እጥበት ህክምና (ዳያላሲስ) ከጀመርኩ ሶስተኛ ዓመቴን ይዣለሁ፡፡ ለዚህ ህክምና በየሳምንቱ የምከፍለው 3200 ብር ኑሮዬን ከመሰረቱ ማናጋቱ አይቀርም፡፡ አይኔ እያየ ወደ ሞት አልሄድምና በደህና ጊዜ የገዛኋቸውን ጌጦቼንና ንብረቴን እየሸጥኩ፣ ነፍሴን እስከ ዛሬ አቆይቻለሁ፡፡ ይህንን ሥቃዬንና መንገላታቴን ተመልክቶ፣ ታናሽ ወንድሜ አንድ ኩላሊቱን ሊሰጠኝ ቢፈቅድም ህክምናው ወደ ሚደረግበት ባንክ ለመሔድና ወጪዎቻችንን ለመሸፈን የሚያስችል አቅም አጥቼ ተስፋ ቆርጬ ነበር፡፡ አሁን ህክምናው እዚሁ በአገራችን መሰጠት ሊጀመር እንደሆነ ሰምቼ ተስፋዬ እንደገና ለምልሞ አገልግሎቱን ለማግኘት ከተመዘገቡት ህሙማን መካከል ግንባር ቀደሟ ሆኛለሁ፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ቢፈቅድ ከአመታት ስቃዬ እፎይ የምልበት ዘላቂ የሆነ ህክምና አገኝ ይሆናል፡፡ ይህንን ጊዜም እጅግ በጉጉት እየተጠባበቅሁት ነው፡፡”
ይህንን ያሉኝ በቅርቡ በቅዱስ ጳውሎስ ሪፈራል ሆስፒታል ሊጀመር ለታቀደው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ተመዝግበው ከሚጠባበቁት ህሙማን መካከል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ትዕግስት የሺዋስ ናቸው፡፡ ህክምናው ከገጠማቸው ከፍታ የጤና ችግር የሚፈውሳቸው ብቻ ሳይሆን ከደረሰባቸውም ኢኮኖሚ ቀውስ ሊታደጋቸው የሚችል መሆኑንም ያምናሉ፡፡ “ልጄ እስካሁን በደህና ጊዜ የቋጠርኳትን ጥሪት እያራገፍኩ ነፍሴን አቆየኋት፡፡ ከዚህ በላይ ግን መቀጠል የምችል አይመስለኝም፡፡ ዋጋ ያወጣሉ የሚባሉ ንብረቶቼን ሁሉ ሸጬ ጨርሻለሁ፡፡ አሁን ተስፋዬ በዚህ ህክምና ላይ ብቻ ነው፡፡”
እንደ ወ/ሮ ትዕግስት ሁሉ ይህንኑ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና በአገራችን መጀመር በጉጉት የሚጠባበቁ በርካታ ህሙማን አሉ፡፡ ህክምናው በፍጥነት ተጀምሮ ፈውስ የሚያገኙበትንና በየእለቱ ከሚገጥማቸው ችግርና ከሚደርስባቸው የኢኮኖሚ ድቀት የሚላቀቁበትን ጊዜ በናፍቆት እየተጠባበቁ ነው፡፡ ሆስፒታሉ ህክምናውን በቀጣዩ ሚያዝያ ወር እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ የዘርፉን ባለሙያዎች የሚያሳስባቸው ጉዳይ ህክምናውን በተያዘው ዕቅድ መሰረት መጀመሩ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነቱንም ማረጋገጥ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ቅድመ ዝግጅቱ በአስተማማኝ መልኩ መጠናቀቅ እንደሚገባው ይገልፃሉ፡፡
ለንቅለ ተከላ ህክምናው የሚያገለግሉ 12  መሳሪያዎች ግዥ ተፈፅሞ ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ሲሆን በተጨማሪ አስራ ሁለት ማሽኖች ግዥአቸው ተፈፅሟል፡፡ ጣሊያን ሰራሽ የሆኑ አራት የንቅለ ተከላ ህክምና መሳሪያዎችን ለመግዛትም በሂደት ላይ ነው። የንቅለ ተከላው ህክምና የሚጀምረው በውጪ ሀገር ባለሙዎች ሲሆን የስራውን ቀጣይነት አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችል የባለሙያ ስልጠና እንዲሰጥ ለማድረግ ታስቦ፣ አስራ ስድስት ባለሙያዎችን ወደ ህንድ ሀገር በመላክ፣ በንቅለ ተከላ ህክምና ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡
የንቅለ ተከላ ህክምና ማለት ተግባሩን በአግባቡ ማከናወን የተሳነውን አካል በማውጣት በሌላ ጤነኛ አካል መቀየር ወይንም መለወጥ ማለት ሲሆን ህክምናው በሶስት አይነት መንገዶች ሊከናወን ይችላል፡፡ እነዚህም፡-
እርስ በራስ ንቅለ ተከላ ወይንም (Auto graft)
ከሌላ ሰው የሚወሰድ አካል ተከላ ወይንም (Allograft)
ከእንስሳት ተወስዶ የሚተከል ወይንም (xengraft)ናቸው፡፡

1. እርስ በራስ (Auto graft) ንቅለ ተከላ
ይህ አይነቱ የንቅለ ተከላ ህክምና የሚከናወነው፣ ከራሱ ከታማሚው ሰው አካል የሚወሰድ አካል ለተጎዳው ክፍል በመቀየር ነው፡፡ ለምሳሌ የተጎዳ ቆዳ ቅየራ፡፡
2. ከሌላ ሰው የሚወሰድ አካል ንቅለ ተከላ (Allograft)
አንድ ታማሚ አካል ህብረ ህዋስ ተመሳሳይ ከሆነ ሌላ ሰው ጤናማ አካል ተወስዶ የሚቀየርበት የንቅለ ተከላ ህክምና ዘዴ ነው፡፡ ለዚህ ቀላሉ ምሳሌ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ነው፡፡
3. ከእንስሳት ለሰው ልጅ የሚደረግ የንቅለ ተከላ ህክምና (xengraft)
ይህ አይነቱ የንቅለ ተከላ ህክምና እምብዛም ያልተለመደና ተዘውትሮ የማይፈፀም የንቅለ ተከላ ህክምና ዓይነት ሲሆን ከሰው ልጅ ስነ ተፈጥሮ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን እንስሳት አካል ለሰው ልጅ በመቀየር የሚደረግ ህክምና ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ1823 ዓ.ም በጀርመናዊው የቀዶህክምና ባለሙያ ካርል በንገር የተጀመረው የቀዶህክምና ሥራ፣ የዛሬው እጅግ ዘመናዊና ውስብስብ ህክምና ጥበቦች ላይ ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል፡፡
በኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ታሪክ የመጀመሪያው የተሳካ የንቅለ ተከላ ህክምና የተከናወነው በ1954 ዓ.ም እ.ኤ.አ ሲሆን ሁለቱም ኩላሊቶቹ የተጎዱበት ታዳጊ ከመንትያ ወንድሙ ያገኘውን አንድ ኩላሊት በንቅለ ተከላ ህክምና የተተካበት ሂደት ነበር፡፡
የንቅለ ተከላ ህክምና በአገራችን የተጀመረው ጥቅምት 10 ቀን 1957 ዓ.ም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ በአሁኑ የካቲት 12 ሆስፒታል ውስጥ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ወቅት የተደረገው የንቅለ ተከላ ህክምና፣ የዓይን ብሌን ሽፋን (cornia) ንቅለ ተከለ ህክምና ነበር፡፡ የንቅለ ተከላ ህክምናው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየተደገፈ እጅግ ረቂቅና ውስብስብ ተግባራት ላይ የደረሰ ቢሆንም የሙሉ አካል ክፍል ንቅለ ተከላ ህክምና፣ በአገራችን እስከ አሁንም ድረስ መስጠት አልተጀመረም፡፡ ይህ ሁኔታም የንቅለ ተከላ ህክምናው የሚያስፈልጋቸው በርካታ ህሙማን ህክምናውን ለማግኘት እንዳይችሉ በማድረግ፣ ለከፍተኛ ሥቃይና ለሞት ሲዳርጋቸው ቆይቷል፡፡ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው የፈቀደላቸውና ለጋስ ዘመድ ያገኙ እጅግ ጥቂቶች ህክምናው ወደሚሰጥባቸው አገራት (ህንድ፣ ታይላንድ፣ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አውሮፓና አሜሪካ) እየሔዱ፣ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና አድርገው ይመለሳሉ። ይህ ዓይነቱ ህክምና 95 በመቶ ድረስ የመፈወስ እድል እንዳለውም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ህክምናው በአገራችን መጀመሪያ የገንዘብ አቅማቸው ደካማ የሆኑ ህሙማንን የሚታደግ መሆኑ አሌ የሚባል ጉዳይ ባይሆንም ህክምናውን የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮች መኖራቸው አይካድም፡፡ ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዱና ዋንኛው ደግሞ ዓላማቸው ገንዘብ ማግኘት ብቻ በሆኑ ደላሎች በሚቀርብላቸው አማላይ ክፍያ የሚታለሉ ህፃናት፣ የአደገኛ እፅ ሱሰኞች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የዕለት ጉርስ የራቃቸው ዜጎች፣ ለህገወጥ የአካል ሽያጭ መጋለጣቸው አይቀሬ መሆኑ ነው።  ይህ እጅግ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባና ጥብቅ ቁጥጥር የሚያስፈልገው እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶ/ር አየናው ተሰማ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ፤ “የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና በአገራችን መስጠት መጀመሩ በርካታ ህሙማንን ከሞትና ከሥቃይ የሚታደግ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ሆኖም ጉዳዩ የህገ ወጥ አካል ክፍሎች ግብይትን ሊያስፋፋ የሚችልበት አጋጣሚዎች ይኖሩታል፡፡ ይህም ማለት ገንዘብ ያላቸው ህሙማን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በገንዘብ በማታለል፣ የአካል ሽያጭ እንዲፈፅሙ ያደርጓቸዋል ማለት ነው፡፡፡ ይህንን ችግር ለመቋቋም መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ በቂ ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ችግሩ ባደጉ አገራትም ዘርፉን ሲፈታተን የኖረ ችግር በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል” ብለዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥቁር ገበያ ከፍተኛ ገንዘብ ከሚያወጡና ጠንካራ የገበያ ሰንሰለት ካላቸው ንግዶች መካከል የአካል ሽያጭ አንዱ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተሩ፤ በተለይ ፓኪስታን፣ ህንድ፣ ፊሊፒንስና ቻይና በዚህ ህገወጥ ንግድ ግብይት ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ የዓለማችን አገራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህን ህገወጥ የአካል ሽያጭ ንግድ ለማስቆም የዓለም ጤና ድርጅት የንቅለ ተከላ ህግና መመሪያ በማውጣት፣ አገሮች ህጉን ተከትለው እንዲሰሩ ተፅዕኖ ሲያደርግ መቆየቱንም ዶ/ር አያናው ገልፀዋል፡፡
አሁን ህክምናው በአገራችን ሲጀመር የንቅለ ተከላ ህክምናው በለጋሹ፣ በተቀባዩና በቤተሰቦቻቸው ሙሉ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ መሆኑ በሚገባ መረጋገጥ ይኖርበታል ያሉት ዶክተሩ፤ የመክፈል አቅም ያላቸው ህሙማን በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩትን ዜጎች በገንዘብ አታለው፣ ኩላሊታቸውን እንዲሸጡ ለማድረግ የሚችሉባቸው መንገዶች ሁሉ በቅድሚያ ሊፈተሹና ቅድሚያ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ1987 ዓ.ም ህገወጥ የአካል ግዥና ሽያጭን አስመልክቶ ያወጣውና በ192 የዓለም አገራት ተቀባይነትን ያገኘውን ህግ ካፀደቁት አገራት መካከል አንዷ የሆነችው አገራችን፤ የዘርፉ ህክምና የሚመራበትን ህግና ሥርዓት እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎቹን የስነ ምግባር መመሪያ በማውጣት፣ የንቅለ ተከላ ህክምናውን ለመጀመር በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡
በቀጣዩ ሚያዝያ ወር በቅዱስ ጳውሎስ ሪፈራል ሆስፒታል ለመጀመር እቅድ የተያዘለት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ቀጣይነቱን የማረጋገጡም ተግባር ቸል ሊባል እንደማይገባ ባለሙያዎቹ ይገልፃሉ፡፡
የህክምናው መጀመር በጉጉት ለሚጠባበቁት ህሙማን እጅግ ታላቅ የምስራች የመሆኑን ያህል፣ ከህገወጥ የአካል ንግድና ግብይት ስጋት ነፃ ሆኖ አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረጉ ረገድ መንግስት ተገቢውን ክትትል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

Read 4747 times