Monday, 07 April 2014 15:50

“የቀድሞው ጦር” ማለት የምድር ጦር ማለት ነው?

Written by  ካሌብ ንጉሤ
Rate this item
(1 Vote)

የእነ ብ/ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ ታሪክ አሁንም ተድበስብሷል

ንፅፅራዊ ዳሰሳ
የመጽሐፉ ርዕስ - የቀድሞው ጦር (1927-1983)
ከቀድሞው የኢትዮጵያ ምድር ጦር ሠራዊት ወታደሮችና ሲቪል ሠራተኞች
የታተመበት ዘመን - 2006 ዓ.ም
የገጽ ብዛት - 674
የሽፋን ዋጋ - 250.00
ጸሐፊ - ገስጥ ተጫኔ
ህትመት - ዜድኤ ማተሚያ ቤት
የመጽሐፉ አንኳር ይዘት፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በዘመናዊ መልክ መቋቋም ከጀመረበት ከ1927-1983 የነበረውን የአደረጃጀት፣ የስያሜ፣ የማዕረግና የደንብ ልብስን ታሪካዊ ሂደት በማሳየት፤ በተለይ ደግሞ ሠራዊቱ የተሳተፈባቸውን ዋና ዋና የውጊያ አውዶች በመዘከር፣ ትውልዱ ስለዚያ ታላቅ ሠራዊት ተገቢውን ዕውቀት እንዲያገኝ ማድረግና ለሠራዊቱ የተሰጠው “የደርግ ሠራዊት” የሚለው ስያሜ በትክክል ስሙ “የኢትዮጵያ ሠራዊት” ተብሎ እንዲታወቅ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ነው ማለት ይቻላል፡፡
የመጽሐፉ ጠንካራ ጐን
የተለያዩ ፎቶግራፎችን በመጠቀም ታሪኩን ተዓማኒ ለማድረግ በመጣራቸው የታሪኩ ጸሐፊና አዘጋጅ ኮሚቴው ሊመሰገኑ ይገባል፤ የአገራችንን ግዙፍ ሠራዊት ታሪክ ቀርቶ የአንድን ግለሰብ ታሪክ ለመጻፍ ያለው ችግር ቀላል አይደለም። በመሆኑም የቀድሞው የኢትዮጵያ ምድር ጦር ሠራዊት ወታደሮችና ሲቪል ሰራተኞች ማህበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት “የታሪክ ዝግጅትና መረጃ አጠናቃሪ ኮሚቴ” እና “የአርትኦት ኮሚቴ” በማቋቋም ታሪኩ በተቻለ መጠን በጥንቃቄ እንዲጻፍ ያደረገው ጥረት ለሌሎችም መልካም ምሳሌ ሊሆን ይችላል፤ እርግጥ የጋራን ታሪክ በዚህ አይነት መንገድ መጻፍ አዲስ አይደለም፡፡ ለአብነትም የባህር ኃይልንና መሰል ተቋማትን ታሪኮች መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከምክትል አስር አለቃ እስከ ማርሻል ያሉ የጦር ሠራዊት የማዕረግ ምልክቶች በቃል ብቻ ሳይሆን በስዕል (ፎቶ) ጭምር ማቅረቡ ከመጽሐፉ ጠንካራ ጐኖች የሚደመር ነው፡፡ ጠንከር ተደርጐ ባይገለጥም ለዚያ ግዙፍ ሠራዊት አጠቃላይ ውድቀት ምክንያቱ የተቃዋሚው ጐራ ማየል ብቻ ሳይሆን በየደረጃው ያሉ አዛዦች የፈፀሙበት ክህደትና በውስጥ አርበኝነት ተሰልፈው የነበሩ ኃይሎች ያደረሱት በደል መሆኑ መጠቃቀሱም ከጥንካሬ የሚመደብ ነው፡፡
መጽሐፉ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር የፊደል ግድፈትና የአርትኦት ችግር የለበትም፤ ሆኖም ከታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ (1997) “ሞት የተፈረደባቸው 17 ሺህ የኢትዮጵያ ሠራዊት፤ አይ ምጽዋ እና (1999) “የአናብስት ምድር፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት የታሪክ ዘገባ፤ ከ1927 -1983” ጋር በማነጻጸር ስናየው በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳት እንገደዳለን፡፡
የመጽሐፉ ደካማ ጎን
“የቀድመው ጦር ከ1927-1983” መጽሐፍ ከርዕሱ እንደምንረዳው ሊያሳየን የተነሳው፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በተጠቀሱት ዓመታት ያሳለፈውን ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲባልም ምድር ጦር፣ ባህር ኃይልና አየር ሃይል ማለት መሆኑ መዘንጋት የለትም፡፡
ከ1927-1983 ዓ.ም ባለው ጊዜ የነበረውን የሠራዊት ታሪክ ብቻ ለመጻፍ የወሰኑት ኮሚቴዎች ምክንያት የመረጃ ዕጥረት እንዳያጋጥማቸው በመስጋት ይመስላል፡፡ ሆኖም መጽሐፉ የሚጀምረው ከአጤ ካሌብ ይሆንና የአጤ ልብነ ድንግልን ሠራዊት ምስረታ ነካ አድርጐ፣ በብርሃን ፍጥነት ከአጤ ቴዎድሮስ 2ኛ ወታደራዊ ታሪክ ላይ ይደርሳል፡፡
በመሠረቱ ይህ አይነቱ የታሪክ ጉዞ ስህተት ይመስለኛል፤ ምክንያቱም “የቀድሞው ጦር” ተብሎ ገና በርዕሱ የተወሰነው ከ1927-1983 ዓ.ም ነው፡፡ ከአጤ ካሌብ (6ኛ መ.ክ.ዘ) መጀመር ከነበረበትም ርዕሱ ላይ መገደብ አልነበረበትም። በሌላም በኩል “የቀድሞው ጦር” ታሪክ የሚጀምረው ከ1927 ዓ.ም ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልሱ “አይደለም” የሚል ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት ታሪክ የሚጀምረው ኢትዮጵያ በመንግሥትነት ከቆመችበት ዘመን (እስካሁን ባለው ማስረጃ ከዳኣማት ሥርወመንግስት 800 ዓመተ ዓለም በፊት ጀምሮ ነው፡፡
ምን አልባት ለመረጃና ማስረጃ ምቹነት ታስቦ ከሆነም ይህ በትክክል መገለጥ ነበረበት፡፡ ሌላው ጉዳይ “የቀድሞው ጦር” ሲባል ምድር ጦር ብቻ ማለት ነውን? የሚል ጥያቄም ሊነሳ ይችላል፤ በእኔ እምነት የኢትዮጵያ ሠራዊት ወይም ጦር ሲባል ባህር ኃይልን፣ አየር ኃይልንና ምድር ጦርን ማካተት አለበት፡፡ ይህንን እውነት ግን መጽሐፉ ላይ አናገኘውም፡፡ የዚህ ህፀጽ ምክንያቱ ምን አልባት የኮሚቴው አባላት የምድር ጦር አባላት ሊሆኑና “በትክክል እናውቀዋለን” ብለው ሊጽፉ የተነሱትም የዚህኛውን ክፍል ጦር ታሪክ ሊሆን ይችላል፡፡ ያም ከሆነ ርዕሱ መቀየር ነበረበት፡፡
ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ያለውን የጦር ታሪክ ቢጽፉ ኖሮ የተወሰነ እውነት ሊኖር ይችል ነበር፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ባህር አልባ ስትሆን ባህር ኃይሏንም አጥታለችና ነው፡፡ ያም ሆኖ አየር ኃይሏ ዛሬም ህልውናውን ስላላጣ ልክ እንደ ምድር ጦር ታሪክ ሁሉ የባህርና የአየር ኃይሉ ታሪክና የጦር ሜዳ ውሎ ቢዘገብ ኖሮ የታሪክ ሰነድነቱን ያጐላው ነበር፡፡
በ1927 ዓ.ም ተገንብቶ በ1983 ዓ.ም በከሰመው ግዙፍ ሠራዊት ግዳጆች የደረሰ የሞት፣ የምርኮኛ፣ የክህደትና የቁስለኛ፤ እንዲሁም የንብረት ውድመትም በአኃዝ ቢቀርብ ኖሮ ለመጽሐፉ ተገቢውን ክብደት ይሰጠው ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ የታደሰ ቴሌ ሳልበኖ “የአናብስት ምድር፤ ከ1927-1983” ዘገባ የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
የዚህ ምክንያቱ ታደሰ የምድር ጦርን እያንዳንዳቸው በአማካይ 300 ገጾች ያሏቸው 1288 የተለያዩ መዝገቦችን፣ ጥናታዊ ጽሑፎችን፣ የውጊያ ሪፖርቶችን፣ የሰው ኃይልና የጦር መሳሪያ ዝርዝር የያዙ ሰነዶችን መሠረት አድርጐ ስለጻፈ ነው። “የቀድሞው ጦር” ጸሐፊ ሌሎችን ግለታሪኮችና መሠል መጻሕፍትን ዋቢ አድርጐ ሲጽፍ የታደሰን “የአናብስት ምድር” ግምት የሰጠው አይመስልም፡፡
ሌላው ያልገባኝ ነገር በሠራዊቱ ውስጥ ሁለት “ገሥጦች” ነበሩ ወይ? የሚል ነው፡፡ መቶ አለቃ ገስጥ ተጫኔ (ገጽ 404) የሚባሉ የፕሮፖጋንዳ ኃላፊ እንደነበሩ ይተልጣልና ነው፡፡ ማዕረጉ የቀድሞ ነው ዕርባናም የለውም” ብለው ከሆነ ምን አልባት ሊያስኬድ ይችላል፡፡ ግንኮ ሌሎቹ የመረጃ አጠናቃሪም ሆነ የአርትኦት ኮሚቴ አባላት በቀድሞ ማዕረርጋቸው ነው የተዘገቡት፡፡
የምዕራፎች አከፋፈል፣ የገጽ ቅደም ተከተልና የህትመት ጥራት ችግርም ሌላው ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ከሮማውያን ቁጥር አንድ እስከ ሰባት ያሉት የማህበሩ ፕሬዚደንት ስለመጽሐፉ ዝግጅት የሰጡት አስተያየት፣ መቅድም፣ የፀሐፊው ማስታወሻና የምስጋና ገጾች የተቀመጡት ቅጥ አንባሩ በጠፋ መንገድ ነው፡፡
በወረቀት ውድነት እንዳይሳበብ የታተመበት ወረቀትና ውበት ብላሽ ነው፡፡ ይህ የማተሚያ ቤቱን አገልግሎት ጥያቄ ላይ የሚጥል ይመስለኛል፡፡ ይህ አይነቱ የጥራት መጓደል ብዙ የተደከመበትንና በከፍተኛ ዋጋ የተገዛውን መጽሐፍ ተነባቢነት በእጅጉ ሊጐዳው ስለሚችል ኮሚቴውም ሆነ ጸሐፊው ሊያስቡበት ይገባል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ትኩረት ሰጥቼ መጠየቅ የምፈልገውና ምን አልባት ሌሎችንም ግራ ሊያጋባ ይችላል ብዬ ያሰብሁት ጉዳይ የምጽዋ ውጊያ ምስጢር ነው፡፡ የምጽዋን ውጊያ ከሌሎች ለይቼ ትኩረት የማደርግበት በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው ለ30 ዓመታት በኤርትራ ሲካሄድ ለኖረው ዘግናኝ ጦርነት የፍጻሜው መጀመሪያ ድል የተገኘው (በጠላት ጦር ዘንድ) ምፅዋ በመሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እስካሁን ትክክለኛ መልስ ያልተገኘለት ከምጽዋ ውድቀት ጋር ተያይዞ ብዙ ጊዜ ሲነሳ የኖረው የብርጋዲየር ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ በወቅቱ የመክት ዕዝ ወይም የ606 ኮር ዋና አዛዥና ብ/ጄኔራል ዓሊ ሐጂ አብዱላሂ በወቅቱ የ3ኛ ሜካናይዝድ ክ/ጦር ዋና አዛዥ ጉዳይ አሁንም ትክክለኛውን መልክ የያዘ ስላልመሰለኝ ነው፡፡
በቀድሞው ጦር መጽሐፍ (ገፅ 639) “የምጽዋ ውጊያ ሁለት ጐን ትረካ ያለው ነው፡፡ አንድ ጐን የብ/ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ ሲሆን ሌላው ጐን ደግሞ ጄኔራሉን የሚቃወም ወገን ነው፡፡ አንዱ የሌላውን አገላለጽ ይክዳል፡፡ “ይህ መጽሐፍ በተሰናዳበት ወቅት ገለልተኛ ሆኖ ሚዛናዊ መረጃ ሊሰጥ የሚችል የዐይን ምስክር ስለአልተገኘ፣ እንደአስፈላጊነቱ የሁለቱንም ወገን ለማሳየት ይሞከራል” ይላል። እዚህ ላይ ነው የመጽሐፉ ተአማኒነት ጥያቄ ላይ የሚወድቀው፡፡
ምክንያቱም ብ/ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ፤ ለምጽዋ በሻዕቢያ መያዝ ያደረጉት ድጋፍ ካለ ወይም ደግሞ ሾሞ ሸልሞ ማዕረግ ለሰጣቸው መንግሥትና ቃል ለገቡላት አገር የከፈሉት መስዋዕትነት እንዳለ መጀመሪያ በግልጥ መስፈር ነበረበት፤ ይህ ባለመሆኑም “የምፅዋ ውጊያ ሁለት ጐን ትረካ ያለው ነው” የተባለውን አገላለፅ ከፍተኛ ትዝብት ላይ ሊጥለው ይችላል፤ አንድም ከፍርሃት የመነጨ ቸልተኝነት ነው፤ አለዚያም በይሉኝታ ብቻ ጄነራል መኮንኑን ላለማስቀየም የተደረገ ጥረት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የሁለቱም ጎራ ልዩነት በአግባቡ ሰፍሮ ቢያንስ ለህሊና ፍርድ መቀመጥ ነበረበት! ምጽዋ ሲደመሰስ በቦታው የነበሩ የዓይን ዕማኞችም ብዙ ናቸው፡፡
በ1987 ዓ.ም ከጥር 30 እስከ የካቲት ዘጠኝ በነበሩት 10 ተከታታይ የውጊያ ቀኖች ብ/ጄኔራል ጥላሁንና ብ/ጄነራል ዓሊ ሐጂ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች መኮንኖችና ከ5 ሺህ በላይ የሰራዊቱ አባላት በሻዕቢያ ተማርከዋል፡፡
በአንጻሩ ብ/ጄነራል ተሾመ ተሰማና ኮሎኔል በላይ አስጨናቂን የመሰሉ ጀግኖች ደግሞ “ለጠላት እጄን ከምሰጥ ሞቴ ይሻለኛል” ብለው ራሳቸውን አጥፍተዋል፡፡
የምፅዋን ውድቀት በተመለከተ በየካቲት 1983 ዓ.ም መንግሥት ራሳቸውን የሰዉትን እያሞገሰ፤ እጃቸውን ለሻዕቢያ የሰጡትን፤ በተለይ ደግሞ የዕዙን ዋና አዛዥ የነበሩትን ብ/ጄነራል ጥላሁን ክፍlyን እያንኳሰሰ ተከታታይ የውርጅብኝ መግለጫና የስድብ ናዳ ሲያወርድ ነበር፡፡
ይህንን እውነት ለማረጋገጥም “የጀግናው ገድል” (1983) ዕትም፣ ሠርቶ አደር ጋዜጣ (የካቲት 14/1983) እና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ (የካቲት 16/1983 ዕትም) መመልከት በቂ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ጄነራል መኮንኑ ከሻዕቢያ ምርኮ ተለቅቀው በ1984 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው ሲገቡ “ደርግ ባልዋልሁበት ቦታ አውሎ ስሜን አጥፍቶኛል” ብለው ቅሬታቸውን በመገናኛ ብዙኃን ሲገልጡ ሰምቻለሁ፡፡ ለተወሰነ ጊዜም ከኢህአዴግ ሠራዊት ጋር በመምሪያ ኃላፊነት የሰሩ ይመስለኛል፡፡
በወቅቱ ብ/ጄነራል ጥላሁን ከተማረኩ በኋላ የ6ኛ ክ/ጦር ዋና አዛዥ ከነበሩት ብ/ጄነራል ተሸመ ተሰማ ጋር “በሬድዮ ተመላለሱ” ተብሎ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተደጋግሞ የቀረበው ፍሬ ነገር የሚከተለው ነው፡-
“ጄነራል ተሾመ የሬድዮ መነጋገሪያውን አንስተው “ማነህ?”
“ጄነራል ጥላሁን ነኝ”
“ጄነራል ተሾመ “ከሃዲ! ከአንተ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የቀደደ ወያኔ ይሻላል፡፡ አርጅተሃል፤ የወንበዴ መንገድ ሰራተኛ መሆንህ ትከሻህ ላይ የተሸከምከውን አንበሳ (የጄነራልነት ዓርማ ማለታቸው ነው) አሳዝኖታል፡፡ ቀበሮ! ምን ፈለግህ?”
ጄነራል ጥላሁን “ለስድቡ ግዴለም፡፡ ለሻዕቢያ እጅ አትሰጥም?”
ጄነራል ተሾመ “በትከሻየ ላይ የተሸከምሁት አንበሳ ነው፡፡ እንደ አንተ ቀበሮ አይደለም” የሚል መልስ እንደሰጧቸው፤ ከዚያም የምፅዋን ውጊያ እስከ መጨረሻው በጽናት መርተው የሻዕቢያ ኃይል እየበረታ ሲመጣ፣ የወገን ጦር ድጋፍ አለመድረሱንም ሲያረጋግጡ ቀይ ባህር ዳርቻ ላይ ቆመው ሽጉጣቸውን ጠጥተው ማለፋቸውን በእርግጠበኝነት ሲናገር እንሰማና እናነብ ነበር፡፡
በጄነራል ጥላሁን ክፍሌና በጄነራል ተሾመ ተሰማ መካከል “በሬዲዮ ተደርጓል” የተባለው ምልልስ በመሠረቱ መጣራት ያለበት ይመስለኛል፤ ደርግ ያለስማቸው ስም ሰጥቶ ተሳልቆባቸው ከሆነ የጠፋ ስማቸው ሊታደስ፤ አድርገውት ከሆነም በማስረጃ ሊረጋገጥ እና ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል፤ ሳምንት እመለስበታለሁ፡፡  

Read 3222 times