Monday, 14 April 2014 09:35

የሣምንቱ ችሎት ዘገባ በሽብር የተከሰሱት ሙስሊሞች የተከሣሽነት ቃል መሰማቱ ቀጥሏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

           ከአወሊያ ት/ቤት ጉዳይ በተያያዘ መንግስት ጣልቃ ገብቷል በሚል በተፈጠረው ብጥብጥ ሳቢያ በሽብርተኝነት ተከስሰው እንዲከላከሉ ብይን የተላለፈባቸው ተጠርጣሪዎች የተከሳሽነት ቃላቸውን መስጠታቸውን ቀጥለዋል፡፡፡፡
ባለፈው ሰኞ በዋለው ችሎት፣ ሼህ መከተ ሙሄ እና ሣቢር ይርጉ የተከሳሽነት ቃላቸውን ለፍ/ቤቱ ሰጥተዋል፡፡ በጠዋቱ ችሎት የተከሳሽነት ቃላቸውን ከ2 ሰአታት በላይ በወሰደ ጊዜ ያሰሙት ሼህ መከተ ሙሄ፤ በብጥብጡ ወቅት ህዝቡን የማረጋጋት ሚና ከመወጣት ያለፈ ሁከትና ረብሻ አለማነሳሳታቸውን ተናግረዋል፡፡ ተከሳሹ እንደውም በፖሊስ ምርመራ ወቅት ከፍተኛ ቶርቸርና ስቃይ ይፈፀምባቸው እንደነበር ለፍ/ቤቱ አመልክተዋል፡፡  ከሰዓት በኋላ በቀጠለው ችሎት፣ ሣቢር ይርጉ የተከሳሽነት ቃሉን የሰጠ ሲሆን በህገመንግስቱ የተደነገጉትን የሃይማኖት እኩልነት እና የሰዎችን የግል እምነትና አስተሳሰብ እንደሚያከብር ገልፆ፤ እስላማዊ መንግስት ይቋቋም በሚል አስተሳሰብ አለመንቀሳቀሱንም አስረድቷል፡፡ ቤተሰቦቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች መሆናቸውን በመጠቆምም ከኔ ሌላ ሃይማኖት አይኑር የሚል አመለካከት እንደሌለው ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
ተከሣሹ አወሊያን አስታኮ በተፈጠረው ብጥብጥ አለመሳተፉን፣ በሚኖርበት አካባቢ ብጥብጥ እንዳይነሳ ህዝበ ሙስሊሙን የማረጋጋት ሥራ ሲሰራ እንደነበር አመልክቷል፡፡ በምርመራ ወቅትም በተለያየ መንገድ ቶርች ከመደረጉም በላይ ስቃይ የታከለበት ምርመራ እንደተፈፀመበት ለፍ/ቤቱ አመልክቶ፤ ፍ/ቤቱ ንፅህናውን አረጋግጦ በነፃ እንዲያሰናብተው ጠይቋል፡፡
በማክሰኞው ጠዋት ችሎት ተከሣሾች፣ ጠበቆች እንዲሁም ቁጥራቸው በመቶዎች የሚገመት የተከሳሽ ቤተሰቦችና ወዳጆች በችሎቱ ቢታደሙም አቃቤ ህግ ባለመቅረቡ የእለቱ ችሎት እንደማይኖር የገለፀው ፍ/ቤቱ ረቡዕ እለት በሚውለው ችሎት አቃቤ ህግ ለምን በሰአቱ እንዳልደረሰ ከሚገልጽ ምክንያት ጋር ይቅረብ ሲል ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
ረቡዕ 4፡30 ላይ የተጀመረው ችሎትም በመሃል መብራት በመጥፋቱ ተቋርጦ ከሰአት በኋላ የቀጠለ ሲሆን በእለቱ መሃመድ አባተ እና አህመድ ሙስጠፋ የተከሳሽነት ቃላቸውን ለፍ/ቤቱ ሰጥተዋል፡፡
በመዝገቡ 8ኛ ተከሣሽ የሆነው መሃመድ አባተ፤ ሐምሌ 7 ቀን 2004 በአንዋር መስጊድ ለተሰበሰበው ህዝብ በአወሊያ መስጊድ ፖሊስ ሙስሊሞችን ስለገደለ፣ ፀሎትና ሶላት እንዲደረግ መልዕክት አስተላልፎ እንደነበር በችሎቱ ገልፆ፤ በእለቱ የሞተ ሰው አለመኖሩ መረጃ ሲደርሰው ወዲያውኑ ማስተባበሉን ተናግሯል፡፡ በቀጣይ ባለው ሂደትም ህዝቡን የማረጋጋት ስራ ሲሰራ እንደነበር ለፍ/ቤቱ ያመለከተው ተከሣሹ፤ ህዝቡ በስሜታዊነት ተነሳስቶ ከፖሊስ ጋር ግጭት እንዳይፈጥር ጥረት ሲያደርግ እንደነበር አስታውቋል፡፡
ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ፖለቲካዊ ግብ ለማሣካት በህቡዕ አልተንቀሳቀስኩም ያለው ተከሣሹ፤ መንግስት ሃይማኖትን እየከፋፈለ ነው ብሎ በፈቲህ መስጊድ ለህዝብ አለመናገሩንም አስታውቋል፡፡
ሌላው የተከሣሽነት ቃሉን ለችሎቱ የሰጠው አህመድ ሙስጠፋ በበኩሉ፤ “ሃይማኖታዊ መንግስት የማቋቋም አላማ አልነበረኝም፤ አክራሪነትንም አላራመድኩም” ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ የወሰደው ስልጠና የአመፃ ሣይሆን ስለሃይማኖት መከባበርና መቻቻል እንደሆነ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ ከውስጡ በተወሰደ ሃሳብ ውይይት ተካሂዶበታል የተባለው መጽሐፍም ስለ ስልጣኔና የህዳሴ ጉዞ ሣይንሳዊ ትንታኔ የተሰጠበት እንጂ ሃይማኖታዊ መንግስትን ስለማቋቋም የሚያወሣ አይደለም ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡
አቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ ማስረጃ ቀርቦ ብይን ከተሰጠ በኋላ የተከሳሽነት ቃል መሰጠቱ የስነ ስርአት ህጉን የተከተለ አይደለም ሲል ለችሎቱ አቤቱታ  ያቀረበ ሲሆን የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው፤ “አቃቤ ህግ ተከሣሾችን አቋርጦ ጥያቄ ያቀረበው ሃሳባቸውን ለማቋረጥ ነው፤ ጥያቄውም ተገቢ አይደለም” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ ችሎቱም የክርክር ሂደቱ የስነስርአት ህጉን የጣሰ አይደለም ሲል የአቃቤ ህግን ጥያቄ ውድቅ አድርጐ የተከሳሽነት ቃል የመስማት ሂደቱ እንዲቀጥል ብይን ሰጥቷል፡፡ ሃሙስ እለት በነበረው ችሎትም አቃቤ ህግ በድጋሚ ባቀረበው ጥያቄ፤ እያንዳንዱ ተከሳሽ በተመሳሳይ ፍሬ ነገር ላይ ቃሉን እንዲሰጥ መደረጉ ሂደቱን ያራዘመ ነው፤ ለቃል መስጫ ቢበዛ 25 ደቂቃ ተብሎ ይገደብልኝ ሲል አመልክቷል፡፡ ፍ/ቤቱ በሰጠው ብይንም በስነስርአት ህጉ የሰአት ገደብ ሊደረግ ይገባል የሚል ስላልሠፈረ ሂደቱ ባለበት ይቀጥል ሲል በይኗል፡፡  
በመዝገቡ 10ኛ ተከሳሽ የሆነው ሙራድ ሽኩር በእለቱ በሰጠው የተከሳሽነት ቃል “በህገ መንግስቱ የሰፈረውን የእምነት ነፃነት አልተቃረንኩም፣ ለማስከበር ተንቀሳቅሻለሁ እንጂ፣ አህባሽ በመንግስት ታግዞ እኔ ላይ በግድ አስተምህሮቱን ለመጫን ያደረገውን ጥረት ተቃውሜያለሁ፤ ይህን በመቃወሜ ሃይማኖታዊ መንግስት እንዲቋቋም እንደፈለግሁ መታሰብ የለበትም፣ አወሊያ ዘወትር አርብ ሲካሄዱ በነበሩት አብዛኛዎቹ ስብሰባዎች ላይ ተሳትፌያለሁ፤ በወቅቱም ችግር እንዳይፈጠር ህዝቡን የማረጋጋት ስራ ስሰራ ነበር” ሲል አስረድቷል፡፡ በአቃቤ ህግ የታሰሩ የቡድኑን አባላት በህገ ወጥ መንገድ ለማስፈታት ገንዘብ አሰባስቧል ተብሎ ለቀረበበት ክስም ለዘካ በሚውል ከአንድ ግለሰብ 50ሺህ ብር መቀበሉንና ለታሳሪ ቤተሰቦች ችግር መውጫ ከማከፋፈሉ በቀር አንዳችም የማስፈታት እንቅስቃሴ አለማድረጉን አስታውቋል፡፡ በፖሊስ ምርመራ ወቅት ስቃይ የታከለበት ምርመራ እንደተካሄደበትም ተከሳሹ ገልጿል፡፡
“የሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባል አለመሆኑንና የሚዲያ ባለሙያ እንደሆነ የጠቆመው 11ኛ ተከሳሽ አቡበከር አለሙ በበኩሉ፤ አዲስ አድማስን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች የተለያዩ ፅሁፎች ለአንባቢ ያቀርብ እንደነበር ገልጿል፡፡ በመንግስትና በሃይማኖት መካከል ስላለው ግንኙነት የተቸባቸው ጽሁፎች እንዲሁም በቤቱ በተገኘ የእለት ተእለት ማስታወሻ ደብተሩ ላይ የሰፈሩ ጽሁፎች እንደማስረጃ መቆጠራቸውን ጠቅሶ እነዚህን ይዞ መገኘቱ በሽብር ሊያስጠረጥረው እንደማይገባ ተናግሯል፡፡
በምርመራ ወቅት ድብደባን ጨምሮ በተለያዩ የማሰቃያ ዘዴዎች በግድ ቃሉን እንዲሰጥ መደረጉን የገለፀው ተከሳሹ፤ “ኮሚቴው ህገ ወጥ ነው፣ እስላማዊ መንግስት የመመስረት ፖለቲካዊ ግብ ነበረኝ” እንዲል መገደዱን አመልክቶ፤ “እኛ ተራ የሆነ ወዳጅነት እንጂ በህቡዕ አልተደራጀንም፤ በግሌም እስላማዊ መንግስት እንዲመሰረት ፍላጎት የለኝም” ብሏል፡፡ ይህን በመሰለ አስገዳጅ ሁኔታ ለፖሊስ የሰጠው ቃል እንደ ማስረጃ ተቀባይነት እንዳያገኝ ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡
የግል ማስታወሻ ደብተሩ ላይ የሰፈሩ ጽሁፎች ፍሬ ሃሳብን በተመለከተ ለፍ/ቤቱ ያብራራው ተከሳሹ፤ ባለው እውቀትና መረጃ የፀሐፊነት ሙያውን ተጠቅሞ ስለምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ እንዲሁም ስለእስላማዊ መንግስት ምንነት የሚተነትኑ መፅሃፍት ለማዘጋጀት የተለያዩ ቢጋሮች አዘጋጅቶ እንደነበርና ይህን መጽሃፍ ማዘጋጀቱ እስላማዊ መንግስት እንዲቋቋም እንደመሻት ሊያስቆጥርበት እንደማይገባ በሰጠው የተከሳሽነት ቃል አመልክቷል፡፡ አክሎም “ይህን የግል ጽሁፍ ማንም ሰው አላነበበውም፤ በኔ የማስታወሻ ደብተር ላይ በሰፈሩት ሃሳቦች ተነሳስቶ የሽብር ድርጊት የፈፀመ የለም” ሲል ተናግሯል፡፡
“የሙስሊሞች ጉዳይ” የተሰኘ መጽሄት በህጋዊ መንገድ  ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በአክሲዮን ማቋቋማቸውን የጠቆመው ተከሳሹ፤ መጽሄቱ ስለ እስላማዊ መንግስት መመስረት ያንፀባረቀበት ጊዜ የለም ብሏል፡፡ “መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ገባ ብሎ መጠየቅና መተቸትም የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም መዘጋጀት አይደለም” ሲል አክሎ ገልጿል፡፡
ቀደም ሲል ተከሳሾች በማረሚያ ቤቱ እየተፈፀመብን ነው ያሉትን በደል ለፍ/ቤቱ በዝርዝር ማቅረባቸውን ተከትሎ ስለጉዳዩ ማረሚያ ቤቱ ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍ/ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት፣ የማረሚያ ቤቱ የጥበቃ ደህንነት ኃላፊ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት ማሞ ተክሉ ችሎት ቀርበው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከተከሳሾች የቀረቡትን አቤቱታዎች ኃላፊው በዘጠኝ ነጥቦች አደራጅተው ምላሽ የሰጡ ሲሆን ከሌሎች ታራሚዎች በተለየ መልኩ ጠያቂ ቤተሰቦቻችን ይንገላታሉ፤ ሽብርተኛ እየተባሉም  ይሰደባሉ ለተባለው “ውንጀላው ሃሰት ነው፤ በእንክብካቤና በተለየ መልኩ በአክብሮት ነው የምናስተናግደው፤ ይህን ፍ/ቤቱ ባለሙያ ልኮ መታዘብ ይችላል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አሸባሪ እየተባልን እንሰደባለን ለሚለውም ተቋሙ ያልተፈረደባቸው ሰዎች በንፁህ የመገመት መብት እንዳለቸው ይገነዘባል ሲሉ በተከሳሾች የክስ ዋራንት ላይ በሽብር የተከሰሱ ይላል እንጂ የስድብ ቃል አልወጣንም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍ/ቤቱም፤ ተከሳሾች የማረሚያ ቤቱን ደንብ በሚገባ እንዲገነዘቡ ምክር በመስጠት፣ ችግሮቹ በአስተዳደራዊ ውሳኔ እልባት እንዲያገኙ ወስኗል፡፡
አቃቂ በሚገኘውና የቀድሞ የቅንጅት አመራሮች ጉዳይ በታየበት አዳራሽ እየተካሄደ ባለው የፍርድ ሂደት፣ የተከሳሽነት ቃል መሰማቱ ቀጥሏል፡፡

Read 4131 times