Saturday, 19 April 2014 12:39

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሟሟቁት የመፅሃፍ ምረቃ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ ethmolla2013@gimal.com
Rate this item
(16 votes)

       ባለፈው ሳምንት የአንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ የአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ፤ ሚያዝያ 2 ቀን 2006 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል ሲመረቅ ከተገኙት እንግዶች አንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ለምሽቱ ልዩ ውበት ሰጥተውት ነበር። ሚኒስትሩ ንግግር አዋቂ ብቻ ሳይሆኑ እየቀለዱ ቁም ነገር ማስተላለፍ እንደሚችሉም አሳይተዋል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቀደም ብለው ንግግር ካደረጉት አንዱ “ያልመከነ ማንነት” ደራሲ ወጣት አበበ አያሌው፤ የመጽሐፍ ዝግጅቱ ሁለት ዓመት እንደፈጀበት፣ ባለታሪኩን በቢሯቸውና በቤታቸው እያገኘ፣ በ22 ካሴቶች ቃለ መጠይቅ ማድረጉን፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ የተለያዩ ሰዎች መረጃና ምስክርነት በመስጠት እንደተባበሩት፣ የአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ የሰነድ አያያዝ ጠንቃቃነት ሌሎችም ሊማሩበት እንደሚገባ፣ ለ5 ሺህ ቅጂዎች ማሳተሚያ የወጣውን 241 ሺህ ብር የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ትብብር ማድጋቸውን አመልክቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሟሟቁት የመፅሃፍ ምረቃ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተሸፍኖ የቀረበው “ያልመከነ ማንነት” መጽሐፍ ከተመረቀ በኋላ ንግግር ያደረጉት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ በበኩላቸው፤ “እግዚአብሔር ከትቢያ አንስቶ ለዚህ ቀን፣ ዘመንና ታሪክ ስላበቃኝ አመሰግነዋለሁ። የማስታወቂያ ሥራን በይፉ ቅዳሜ ገበያ እንደ ቀልድና የትርፍ ጊዜ ተግባር ነበር የጀመርኩት። አሁን ታዋቂ ሆኜበታለሁ። መታወቅ በቅጥና በሥርዓት ካልያዙት አውዳሚ ነው። መታወቅ አዎንታዊም አሉታዊም ውጤት አለው። ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በመጽሐፍ ምረቃዬ ላይ በመገኘታቸው ኩራትና ክብር ተሰምቶኛል” አሉ። ስለ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፤ የተለያዩ ወዳጆቻቸው የሰጡትን ምስክርነት የያዘ አጠር ዘጋቢ ፊልም በቀረበበት መድረክ፤ “ያልመከነ ማንነት” መጽሐፍን ከመረቁ በኋላ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በቀልድ አዋዝተው ያስተላለፉትን ቁም ነገር እንደሚከተለው ነበር ያቀረቡት።

***

አቶ ውብሸት ወርቃለማሁን በግል ስንገናኝ አንተ ብለውም በእንዲህ ህይነት መድረክ አንቱ ማለት ቢኖርብኝም፤ በአንተ እንድጠራው የሚያስገድድ ነገር ገጥሞኛል። ለንግግር ወደ መድረኩ ከመውጣቴ በፊት ቁጭ ብለን ስንነጋገር “ክቡር” እና “የተከበሩ” እየተደበላለቁ ነው አለኝ። ምንድነው ልዩነቱ ስለው “ክቡር መባል ያለበት በመንግሥት የተሾመ ሚኒስትርና ሚኒስትር ዲኤታ ሲሆን፤ የተከበሩ መባል ያለበት ደግሞ በሕዝብ ተመርጦ ፓርላማ የገባ ነው” አለኝ። ታዲያ እኔ በሕዝብ የተመረጥኩና የመንግሥትም ሹም ስለሆንኩ በየትኛው ብጠራ ይሻላል? ስለው “በሚኒስትርነትህ ክቡር ብትባል ይሻልሃል” አለኝ። አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ የምወድለት ብዙ ነገር አለው። አንዱ ድምፁ ነው። “የእርጐ ድምጽ” አለው። በመጽሐፍ ምረቃው ላይ ስለተገኘሁ አመስግኖኛል። ማመስገን ያለብኝ እኔ ነኝ። በዚህ ዕለት እዚህ በመገኘቴ ክብሩ ሊሰማኝ የሚገባኝ እኔ ነኝ። ወደዚህ አዳራሽ ከመምጣቴ በፊት ከቀድሞው የቼልሲ አሰልጣኝ ከአብርሃም ግራንት ጋር ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ስንጨዋወት ነበር። እሱ እንደሚለው “በኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ መሻሻል አለ። ከዚህም በላይ መሄድ ትችላላችሁ።” ተጫዋቾቹ የተፈጥሮ ችሎታ አላቸው። የእግር ኳስ ፍቅር ያለው ሕዝብ አለ። የአእምሮ ጥንካሬ ከጨመራችሁበት እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ትልቅ ቦታ ያደርሷችኋል” ነበር ያለኝ። እነዚህ ሦስት ነገሮች በአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ላይ አያለሁ። ማንም ሳያስተምረው በተፈጥሮ ባገኘው ችሎታ ትልቅ ቦታ ላይ ደርሷል። ለሥራው ያለው ዲስፕሊን፣ የመንፈስ ጥንካሬው፣ በራስ መተማመኑ በጣም ትልቅ ነው። ከዚህ ማንም ሰው ብዙ ነገር መማር ይችላል። ይህንን ኳሊቲ ለየተሰማራንበት የሙያ ዘርፍ ሁላችንም ብናውለው ይጠቅመናል። አቶ ውብሸት ወርቃለማሁን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም እያለሁ በቅርበት አውቀዋለሁ። አገርና ወገኑን ለመርዳት እስኪጠራ አይጠብቅም። ከላይ ከገለጽኩለት ጥንካሬዎቹ ላይ ይህንን ስንጨምርበት የበለጠ ከፍ ያደርገዋል። በዚህ ነው መድረክ በቀረበው ዘጋቢ ፊልም ጓደኞቼ ሲመሰክሩም ሰምታችኋል። ገንዘብ አላፈራም። የሕዝብ ፍቅር ግን አግኝቷል። ገንዘብ ባይኖረውም ሕሊናው ረክቷል። ለዚህ ሁልጊዜ በመንፈስ ኩራት ሙሉ ሆኖ የምናየው። በሕይወት ውስጥ ለዓላማ ጽኑ ሆኖ መገኘት ትልቅ ነገር ነው። በዘጋቢ ፊልሙ ላይ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፤ አገራችን የተፈጥሮ ሀብቷን መጠቀም አለባት ብሏል። ከተፈጥሮ ሀብቷ በላይ ግን የዚህች አገር እጣ ፈንታ ያለው በሕዝቡ ውስጥ ነው። በአመለካከታችን ውስጥ ነው። የሕዝብ አመለካከት ካልተለወጠ ነዳጁ፣ ወርቁ፣ ማዕድኑ…ምንም ነው። ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚሰደደው ሕዝብ ከስደቱ ሊቆም የሚችለው በአገር ውስጥ ሠርቶ መኖር እንደሚችል ሲያምን ነው። በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ ተመላሾችን ስናነጋግር፤ “እዚያ እንደለፋነው እዚህ በአገራችን ብንደክም እራሳችንን እንለውጥ ነበር” ብለውናል። እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሌሎች ተሰድደው የሚመጡባት አገር ነው የምትሆነው። የዲቪ ዕድል መስጠታችንም አይቀርም። እኔ በየዕለቱ ለሥራዬ አቅምና ጉልበት የሚሰጠኝ፤ በከተሞቻችንም በገጠሩም የማየው የለውጥ እንቅስቃሴ ነው። የዛሬው ትውልድ እራሱን ለመስዋዕትነት ያቀረበ አድርጐ ቢያምን ጥሩ ነው። መጪው ትውልድ ተጠቃሚ እንዲሆን ጠንክረን እንስራ። ሌላው በየዕለቱ ስንኖር እንደ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ሚዛን ጠብቀን እንኑር። መሥራት፣ ትዳር መሥርቶ ተተኪ ማፍራት፣ የወለዷቸውን ልጆች አስተምሮ ለቁም ነገር በማብቃት ረገድ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ጥሩ ምሳሌ ነው። በመጨረሻ ወጣት አበበ አያሌው የአቶ ውብሸት ወርቃለማሁን ታሪክ ጽፈህ በዚህ መድረክ ስላገናኘኸን ትመሰገናለህ፤ በርታ። 

* * *

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንን ጨምሮ በርካታ እንግዶች በነበሩበት የመጽሐፍ ምረቃ ምሽት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ንግግር አድርገው ከሄዱ በኋላ፣ የመጽሐፍ ምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ሙቀቱን ጠብቆ መቀጠል አልቻለም። የአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ልጅ አቶ አሐዱን ጨምሮ ሦስት ያህል ሰዎች ንግግር አቅርበዋል። ሌሎች ሰዎችም ንግግር እንዲያቀርቡ ዕቅድ እንደተያዘላቸው የመድረክ አስተዋዋቂው ቢገልጽም በፕሮግራሙ መቀዛዘቅ የተነሳ ቀርቷል። የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በምረቃ ምሽቱ መገኘት ለመድረኩ መሟሟቅ ብቻ ሳይሆን መቀዛቀዝም ሰበብ ሆኗል። ከእሳቸው ንግግር በኋላ ሥነ-ስርዓቱ በአጭሩ ተቀጭቷል።

Read 5912 times