Saturday, 03 May 2014 12:50

ኢትዮጵያ በትራኮማ በሽታ ስርጭት ከአፍሪካ 2ኛ ናትኢትዮጵያ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

በኢትዮጵያ 800ሺ የሚሆኑ ሰዎች ለዓይነ ስውርነት አደጋ ተጋልጠዋል
41 ሚሊዮን የሚሆኑ የዓለማችን ህዝቦች በትራኮማ ተጠቅተዋል
ትራኮማ በዓለም ዙሪያ 1.3 ሚሊዮን ለሚሆን ዓይነ-ስውርነት መንስኤ ነው
ተወልዳ ካደገችበት የትግራይ ክልል መሰዋክቲ ወረዳ፣ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ከሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡ ወላጆቿ እጅግ በከፋ ድህነት ውስጥ እየኖሩ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ለዓመታት ተፍጨርጭረዋል፡፡ በአናት በአናቱ የወለዷቸውን አምስት ልጆች በአግባቡ ማሳደግና ማስተማር ቀርቶ እህል አቅምሶ ማሳደር እንኳን ከባድ ፈተና ነበር፡፡ ለእርሻ ሥራ የሚጠቀሙበት ተዳፋትና ድንጋያማ መሬት በየዓመቱ በቂ ምርት አለመስጠቱ የእነ አምለሰትን ቤተሰብ ሕይወት የረሃብና የመከራ አድርጎባቸዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ወላጆቿ  ኑሮን ለማሸነፍ መታገላቸው አልቀረም - ከዓመት ዓመት፡፡ ለቤተሰቡ የሚላስ የሚቀመስ ፍለጋ የሚታትሩት ወላጆች ብቻ አልነበሩም - ልጆቻቸውም ጭምር እንጂ፡፡
ልጆች በአካባቢው በብዛት የሚገኘውን የበለስ ፍሬ እየለቀሙ ገበያ በማውጣት ጥቂት ሳንቲም ፍለጋ ይታትራሉ፡፡ የ16 ዓመቷ ታዳጊ አምለሰት ግን እቺንም ዕድል ለመጠቀም አልቻለችም - ደጃፏ ላይ ተቀምጣ ነው የምትውለው፡፡ በሽታው በልጅነቷ ሲጀምራት ለዚህ ደረጃ ያደርሳታል ብሎ ያሰበ ቀርቶ ስለበሽታው ምንነት እንኳን የሚያውቅ አልነበረም፡፡ የዓይኗ የውስጠኛው ክፍል ሽፋን መቆጣትና ቀስ በቀስም እየቀላ መምጣት እንኳንስ ለአምለሰት ቤተሰቦች ለራሷም የታወቃት ዘግይቶ ነው፡፡ አካባቢያቸው በቂ ውሃ የማይገኝበት ሥፍራ በመሆኑ የአካባቢው ህፃናት ፊታቸውን በአግባቡ የመታጠብ ዕድል አልነበራቸውም፡፡ ወላጆቿ የልጃቸው ዓይኖች ሞጭሙጨውና በአይን አር ታጅለው ባዩ ቁጥር በአሮጌ እራፊ እንድትጠራርግ ከመንገር የዘለለ ምንም ሊያደርጉላት አልቻሉም፡፡ ችግሩ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የሚያውቁት ነገር አልነበራቸውም፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን የአምለሰት አይኖች እንደልባቸው ማየት ቀርቶ ብርሃንና ጨለማን መለየት እየተሳናቸው መጡ፡፡ ሁሉም ነገር ጨለማ ሆነባት፡፡ ገና በ14 ዓመት የታዳጊነት ዕድሜዋ የአይን ብርሃኗን ሙሉ በሙሉ አጣች፡፡ ከመኖሪያ አካባቢያዋ ራቅ ብሎ የሚገኘው የዓለምለም ካርል ሆስፒታል ሃኪሞች አምለሰትን ለአይነስውርነት የዳረጋት ትራኮማ ወይንም የአይንማዝ እየተባለ የሚጠራው በሽታ እንደሆነ ነግረዋታል፡፡ በወቅቱ ህክምና ባለማግኘቷና በሽታው ሥር ከሰደደ በኋላ ወደ ህክምና ሥፍራ በመምጣቷ የአይን ብርሃኗን ለመመለስ አለመቻሉንም ገልፀውላታል፡፡ ሁኔታው አምለሰትንና ቤተሰቦቿን ለቁጭት የዳረጋቸው ሲሆን የህክምና ባለሙያዎቹንም በእጅጉ ያሳዘነ ነበር፡፡
ዛሬ አምለሰት በአንድ በጐ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ ባገኘችው የሙያ ስልጠና ከመሰሎቿ ጋር ተደራጅታ በምንጣፍና ጥልፍ ሥራ ላይ ተሰማርታለች፡፡ ተወልዳ ካደገችበት ከትግራይ ክልል አምጥቶ የሙያ ስልጠና እንድታገኝ የረዳት አንድ በጎ አድራጊ ድርጅት መሆኑንና በአካባቢያቸው እንደ እሷ በዓይን በሽታ የሚሰቃዩ በርካታ ታዳጊዎች እንደነበሩ አምለሰት ታስታውሳለች፡፡ እንዲህ አንደአምለሰት ሊከላከሉትና ሊታከሙት በሚችል በሽታ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በየአካባቢው ይገኛሉ፡፡ ለመሆኑ ትራኮማ ምንድነው? መተላለፊያ መንገዶቹ ምንድን ናቸው? ህክምናውስ?
ትራኮማ (የዓይን ማዝ) Chlamydia Tracomatis እየተባለ በሚጠራ በሽታ አምጪ ባክቴሪያ ሳቢያ የሚከሰትና ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ሊተላለፍ የሚችል በሽታ ነው፡፡ ባክቴሪያው ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍባቸው ከሚችልባቸው መንገዶች መካከል በቀላል ንኪኪ፣ በዝንቦች፣ ፎጣና ከአይን ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በመዋዋስ መጠቀም እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በሽታው በአብዛኛው ከድህነት ጋር የሚያያዝና በቂ ውሃ በሌለባቸው አካባቢዎች በስፋት የሚታይ ነው፡፡ በሽታው መኖሩን በቀላሉ ለማወቅ የሚቻል ቢሆንም በሽታው ያለበትን ደረጃና አጠቃላይ ሁኔታውን ለማወቅ ግን የላብራቶሪ ምርመራ ያስፈልጋል፡፡ የትራኮማ (የዓይን ማዝ) በሽታን በቀላሉ መከላከልና በሽታው ከተከሰተም በኋላ በቀላል ህክምና ማዳን የሚቻል ቢሆንም ይህንን ባለማድረግ ብቻ እጅግ በርካቶች ለአይነ-ስውርነት አደጋ እንደሚጋለጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሰሞኑን የዓለም ጤና ድርጅት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ Get 2020 በሚል ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ እንደተጠቆመው፤ትራኮማ በኢትዮጵያ ለአይነ-ስውርነት መንስኤ በመሆን  በሁለተኛነት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከ138 ሺህ በላይ ሰዎች በትራኮማ ሳቢያ ለዓይነ-ስውርነት እንደተዳረጉም በጉባኤው ላይ ተገልጿል፡፡ እ.ኤ.አ በ2020 ትራኮማን ከዓለማችን ለማጥፋት ያቀደው የዓለም ጤና ድርጅት ባዘጋጀው በዚሁ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ኢትዮጵያ በትራኮማ በሽታ ስርጭት ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ካለው የትራኮማ በሽታ 30 በመቶው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ከ800 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ ለዓይነ-ስውርነት አደጋ የተጋለጡ እንደሆኑም  መረጃው ጠቁሟል፡፡
ትራኮማ በዓለማችን ዙሪያ 1.3 ሚሊዮን ለሚደርስ ዓይነ-ስውርነት መንስኤ እንደሆነ ያመለከተው መረጃው፤ በአብዛኛው ሴቶችና ህፃናት የበሽታው ተጠቂ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 እና በ2006 በአገሪቱ የተደረጉ ጥናቶችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የእይታ መቀነስና በትራኮማ ሳቢያ የሚከሰት አይነ-ስውርነት የህብረተሰቡ ዋንኛ የጤና ችግር እንደሆነ አመልክቷል፡፡ 1.28 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ዓይነ-ስውር እንደሆኑና 2.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ አነስተኛ የማየት አቅም ያላቸው እንደሆኑም መረጃው ይፋ አድርጓል፡፡ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት እስከ ዘጠኝ ዓመት የሚደርስ ህፃናት የትራኮማ በሽታ ተጠቂ እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት የትራኮማ በሽታን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎችን (Safe approach to trachoma prevention) ይዞ እንደሚንቀሳቀስና ይህም በሽታውን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስወገድና ለመከላከል ትልቅ ሚና እንደሚጫወት በጉባኤው ላይ ተገልጿል፡፡ SAFE በሚል ምህፃረ ቃል የተሰየመው የትራኮማ መከላከያ ስትራቴጂ-
S - Surgery- በዓይን ለይ የተፈጠረን ጠባሳ በቀላል የቀዶ ህክምና ዘዴ በማስወገድና በማስተካከል ዓይን ለቁስለትና ለዓይን ብርሃን ማጣት እንዳይጋለጥ መከላከል፤
A - Antibiotics - ችግሩ ላጋጠማቸው ወይንም ለችግሩ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ለሚኖሩ ሰዎች መድኃኒቶችን በመስጠት በሽታው የሚያስከትለውን ጥፋት በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረግ፤
F - Facial Cleaning - በቂ ውሃና የንፅህና መጠበቂያ እንዲኖር በማድረግ፣የፊትን በተለይም የዓይንን ንፅህና ለመጠበቅ ጥረት ማድረግና ህብረተሰቡንም ግንዛቤ ማስጨበጥ፤
E- Environmental improvement - የአካባቢን ንፅህና እንዲጠበቅ በማድረግ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ዙሪያ እጅግ በርካቶችን ለዓይነ ስውርነት እየዳረገ ያለውን የዓይን ማዝ (የትራኮማ) በሽታ መከላከል ይቻላል፡፡

Read 6678 times