Saturday, 31 May 2014 14:27

የጎደለን ይኸው ነው!

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(0 votes)

ርዕስ - የሉሲ ከዋክብትና ሌሎችም (የልጆች መልካም ሥነ ምግባር መጽሐፍ)
የገፅ ብዛት - 145
የሽፋን ዋጋ - 30 ብር
የህትመት ዘመን - 2006 ዓ.ም
ደራስያን - ዊሊያም ጄ.ቤኔትና ሌሎች
ተርጓሚ - ገብረክርስቶስ ኃ/ሥላሴ
ቅድመ ኩሉ
የሃይማኖት ተቋማትና መምህራን የሚያስፈልጉት ከሞት በኋላ ስለሚኖረው ህይወት እንዲሰብኩን ብቻ ሳይሆን ምድራዊው ዓለም ጤናማና የተሳካ እንዲሆን ለማስቻል ጭምር መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ የሃይማኖት መሪዎች መኖርም መሞትም ያለባቸው በየእምነት መጻሕፍቱ የተደነገጉትን የመልካም ሥነ ምግባር ህግጋት በመጠበቅና በማስጠበቅ መሆን አለበት፡፡
የሃይማኖት አባቶች ጠንካሮች ከሆኑ ለመልካም ሥነ ምግባር ተገዥ በመሆን ምዕመናንን ከስህተትና ከበደል ከጠበቁ፣ ሀገር ሰላማዊና የፍቅር ምድር ትሆናለች፤ በአንጻሩ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ከፍቅር፣ ከሰላምና መልካም ሥነ ምግባር ከራቁ፣ ምዕመናኑ ሰው መሆናቸውን ይረሱና የአውሬነት ምግባር ለማከናወን ይደፍራሉ፤ ፈጣሪያቸውን አይፈሩም፣ ፍቅርንና ሰላምን አያውቁም፤ የህይወታቸው ፍልስፍና ሁሉ የአሳማ ይሆናል - ዛሬን ብቻ ቀርበታን መሙላት፡፡
በዚህ መሃል የሀገር ፍቅር፣ የወገን ፍቅርና የቤተሰብ ክብር፣ ወዘተ ብሎ ቁምነገር አይኖርም። ይህ አይነት ድርጊትና እንዲህ አይነት ድፍረት ፈጻሚዎች ሲበዙ ሀገር ራቁቷን ትቆማለች፤ እናም ገመናዋ ሁሉ ሜዳ ላይ የተሰጣ ገብስ ይሆናል። ገመናዋ ከተጋለጠም የአላፊ አግዳሚው ሁሉ መዘባበቻ ትሆናለች፡፡
በሃገራችን ብዙ የልማት ተቋማት በመገንባት ላይ ናቸው፤ የትምህርት ተቋማት፣ የጤና፣ የውሃ፣ የመንገድ፣ የስልክ… ግን ያልተገነባ ትልቅ ቤት አለ - የህዝቡ አዕምሮ፡፡ በየቦታው የትምህርት ማዕከላት ቢገነቡም የትምህርት ጥራት የለም፤ ከክፍል ወደ ክፍል የሚታለፈው በመኮራረጅ መሆኑ በይፋ እየተነገረ ነው፡፡ አንዳንድ የግል ትምህርት ተቋማት እንዲያውም ጠንካራ ተቋማት ለመምሰል ኩረጃን ያበረታታሉ፡፡
“ይህንን ያህል ተማሪ አስፈተንን ይህን ያህሉ አራት ነጥብ እና ከዚያ በላይ አገኙ”  እያሉ ወላጅን ለማጭበርበር ይተጋሉ፤ ግን የትምህርቱ ጥራት የለም፤ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲ ገብተው ስድስት ወር ሳይሆናቸው ተግበስብሰው ይባረራሉ፡፡ በኩረጀ ነዋ እዚያ የደረሱት፤ ጉዳዩ በዚህ ከቀጠለኮ አስኮራጅም ይጠፋና ከቻይና ወይም ከህንድ የኩረጃ አማካሪዎችን ለማስመጣት እንገደድ ይሆናል፡፡
እጅግ በርካታ ህንፃዎች በሚያስደንቅ ፍጥነት ይገነባሉ፡፡ ግን ከመመረቃቸው በፊት እንደ አክርማ መሰንጠቅ ይጀምራሉ፡፡ ይህ የትምህርት ጥራት መውደቅን የሚያመላክት ብቻ ሳይሆን የመልካም ሥነምግባር ህጸፅ ምልክትም ነው፡፡
ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በሺህ የሚቆጠሩ የ”ህግ ባለሙያዎች” በየዓመቱ ይመረቃሉ፤ ግን በፍትህና መልካም አስተዳደር አካባቢ የሚሰማው እሮሮ ገና እልባት አላገኘም፤ ይህም የትምህርት ጥራት መውደቅ አንዱ ምልክት ነው ቢባል ስህተት አይመስለኝም፡፡
በርካታ የጤና ባለሙያዎች በየዓመቱ ይመረቃሉ፤ ግን አሁንም ብቁ ሙያተኞችን ማግኘት አዳጋች እየሆነ ነው፤ ብዙዎቹ የሙያ ብቃት ማነስ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የስነምግባር ጉድለትም አለባቸው። በሰው የሚነግዱ ሞራለቡስ ሃኪሞች በከተማችን እየበዙ ናቸው፡፡ ይህ ጉድለት ከትምህርት ጥራት እና ከስነ ምግባር ጉድለት ጋር ላለመያያዙ ማስረጃ ማቅረብ የሚቸግር ይመስለኛል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት እንደ ዓለማዊው ሁሉ በሙስና እየተድፈቀፈቁ ናቸው፤ በርካታ ባለሥልጣናት እንደ ውሻ እጅ እጅ የሚያዩ ናቸው። ይህ ሁሉ የትምህርቱ ሥርዓትና የሥነምግባር ትምህርት አለመኖር ያመጣብን ጣጣ ነው፡፡ መኮረጅ መስረቅ ነው፤ በኩረጃ ያደገ፣ ሰው ባለሥልጣን ሲሆን የሰው ኪስ መኮረጅ፣ የሃገርን ካዝና መኮረጅ ምን ሊያስደንቅ ይችላል?
አንድ ሰው የሚነቅዙና የማይነቅዙ የእጽዋት ዝርያዎችን ማወቅ ፈልጐ ጓደኛውን “ብሳና ይነቅዛል ጓዴ?” ብሎ ቢጠይቀው “ለእንጨቱ ሁሉ ማን አስተማረው!” አለው ይባላል፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ የትምህርት ቤት ኃላፊዎችና መምህራን ገና በለጋነታቸው ተማሪዎቻቸውን ኩረጃ የሚያስተምሩ ከሆነ፣ ከእነሱ የበለጡ እና እሳት የላሱ ሌቦችን እየመለመለሉ መሆናቸውን ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ ለዛሬ ዳሰሳ የመረጥሁት መጽሐፍ ትኩረት ሊሰጥበት ስለሚገባ የህጻናት ጉዳይ የሚያወሳ ስለሆነ፣ ወቅቱም የ10ኛና 12ኛ ክፍል ፈተና የሚሰጥበት በመሆኑ የሚመለከታቸውን ሁሉ አደራ ማለት ተገቢ ነው ብዬ አምኜያለሁ፡፡

የመጽሐፉ ይዘት
መጽሐፉ በአራት ምዕራፎች ያተኩራል፤ 33 አጫጭር ታሪኮችና ግጥሞችን የያዘ ሲሆን ታሪኮችን የሚያጐሉ ልዩ ልዩ ስዕሎችም ተካትተውበታል። የይዘታቸው አበይት ቁምነገሮችም ሥራና ኃላፊነትን እንዴት መወጣት እንደሚገባ፣ ፍቅር፣ ርህራሄና ጀግንነት አስፈላጊ ጉዳዮች ስለመሆናቸው ሥነስርዓትና ቅንነት ለሰው ልጆች ስለሚያስገኙት ጥቅም፣ እንዲሁም እምነትና ትህትና ምን ያህል የከበረ ማህበራዊ ዋጋ እንዳላቸው የሚያስተምሩ ናቸው፡፡
ታሪኮቹ አጫጭርና ለህፃናት በሚመጥን መንገድ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ አረፍተ ነገሮቹ አጫጭር ስለሆኑ ለንባብ ምቹ ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ የተጻፉበት የፊደል መጠን ጉልህ በመሆኑ ህፃናት በቀላሉ ያነቧቸዋል፡፡
እነዚህ እና መሰል ታሪኮች በልጆች እንዲነበቡ ማድረግና ከተቻለም በሃገሪቱ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተት ጥቅሙ በዋጋ የሚተመን አይሆንም።

የሚጐድለን ይኸው ነው
ትምህርት ቤቶች በየአካባቢው ወይም በየቀበሌው ተሠርተዋል፤ ሆኖም ልጆች ስለመንደርተኛነት እንጂ ስለመልካም ሥነምግባር አይማሩም፤ ስለዘር ጥላቻ እንጂ ስለፍቅር አይዘምሩም፡፡ የሃገር ፍቅር ሳይሆን የገንዘብ ፍቅርን ተምረው ይወጣሉ፣ በኩረጃ ያድጋሉ፤ ሲኮርጁ ይኖራሉ፤ ማነንነታቸውንም አያውቁም”፡፡ የእነሱ ጀግና ከተፎ ሌባ እንጂ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፤ የሃገር ፍቅር የአላዋቂነት ወይም ያለመሰልጠን ምልክት ተደርጐ ይወሰዳል ምክንያቱም ህፃናት እንዲማሩ የተደረገው ይህንን ነዋ!
የሃይማኖት አባቶች ፍቅረ ሰብን ሳይሆን ፍቅረ ንዋይን ይሰብካሉ፤ መስበክ ብቻ አይደለም በገቢር ያሳያሉ፤ ምዕመኑ ፈጥኖ ይከተላቸዋል፡፡ ግን በሃይማኖቱ መጻሕፍት የተቀመጡት ህግጋት አፈር ድሜ በልተዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያቱ የመልካም ሥነምግባር ትምህርት አለመኖር ነው፡፡
ወላጅ ለልጁ ልደት የሚያበረክተው ስጦታ የቻይና ሽጉጥ ወይም ቦምብ እንጂ መጽሐፍ አይደለም፤ ወላጆች እቤታቸው ቁጭ ሲሉ የካራቴ፣ የወንጀል፣ የወሲብና የጦርነት ፊልሞችን ያያሉ እንጂ መጽሐፍ ወይም ጋዜጣ በማንበብ ለልጆቻቸው አርአያ አይሆኑም የቋንቋ መምህራን ክፍል ውስጥ ይዘውት የሚገቡት ከተቀጠሩ ጀምሮ የሚያነበንቧትን ብቻ እንጂ መጻሕፍትን ወይም ጋዜጦችን በማምጣት ምርጥ ታሪኮችን በማንበብ፣ የተማሪዎቻቸውን የንባብ ፍቅር አያበረታቱም፡፡ በአንጻሩ በቦርሳቸው ውስጥ ጫትና ሲጋራ ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ታዲያ ልጆች የት ያዩትንና ከማን የተማሩትን ቁምነገር ሥራ ላይ ያውሉ? ቀጣፊና ገፋፊ ባለሥልጣናት አገሪቱን ያጥለቀለቋት‘ኮ በዚህ ምክንያት ነው፡፡
በመጨረሻም መጽሐፉ በርካታ ቁምነገሮችን ያካተተ የመሆኑን ያህል፣ ስዕሎቹ ባለ ቀለም ቢሆኑ ኖሮ ተፈላጊነቱን ያጐላው ነበር ብዬ አምናለሁ። በተረፈ የትምህርት ሚኒስቴር፣ ወላጆችና አስተማሪዎች ለእንዲህ አይነቱ የመልካም ሥነምግባር ትምህርት ተገቢውን ትኩረት ብንሰጥ፤ ልጆቻችን አምላካቸውን ፈሪ፤ አገራቸውን፣ ወገናቸውንና ወላጆቻቸውን አፍቃሪ፣ ትሁታንና ቅኖች በመሆን እንዲያድጉ የላቀ ሚና መጫወት ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡

Read 1467 times