Saturday, 07 June 2014 13:29

አባትነታቸውን ከካዱ 45 ሰዎች የ41ዱ በዲኤንኤ ምርመራ ተረጋገጠ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

የፌዴራልና ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤቶች በሕፃናት ፍትህ አስተዳደር  የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ

     እናት፣ በበታች ፍ/ቤት አባትነትን ለማረጋገጥ በቂ ማስረጃ ባለማቅረቧ ፋይሉ ቢዘጋም በዚያው አልቀረም፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዘረ - መል ምርመራ እንዲደረግ ለሕፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ላከ፡፡ ማዕከሉ ምርመራውን ከማስደረጉ በፊት ተከራካሪ ወገኖች ጉዳዩን በስምምነት እንዲጨርሱ ለማግባባት ቢሞክርም መልስ ሰጪ (አባት) ከይግባኝ ባይ (እናት) የአንድ ወር ግንኙነት ብቻ እንደነበራቸውና ሕፃኑ የተወለደው ግንኙነታቸው ከተቋረጠ ከአንድ ዓመት በላይ ካለፈው  ስለሆነ አባት አይደለሁም አለ፡፡
እናት ሌላ ማስረጃ ስለሌላት አባትነቱ በዘረ - መል ምርመራ እንዲረጋገጥላት ጠየቀች፡፡ መልስ ሰጪም በአቋሙ ፀና፡፡ አባትነቱ በምርመራው ከተረጋገጠ ማዕከሉ ያወጣውን ወጪ ለመመለስ (ለመክፈል) ተስማምቶና ወዶ ፈርሞ ተለያዩ፡፡  ነገር ግን የሆነው ምርመራ ሳይሆን ሌላ ነው፡፡ ይግባኝ ባይ (እናት) በሁለተኛው ቀን ወደ ማዕከሉ መጥታ፣ መልስ ሰጪ ጉዳዩን በስምምነት መጨረስ ስለፈለገ ሽማግሌ ሊልክባት እንደሆነ፣ መንግሥትም ያለአግባብ ወጪ ማውጣት ስለሌለበት እንደሚከፍል ስለገለጸላት ምን ማድረግ እንዳለባት ምክር ጠየቀች፡፡ ማዕከሉም ሁለቱንም ወገኖች ጠርቶ በማነጋገር መልስ ሰጪ አባትነቱን ስላመነ፣ የእምነት ማረጋገጫውን በጽሑፍ እንዲገልጽና ቀለብ እንዲቆርጥ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ይኼው ለፍ/ቤት ተገልፆ ፍ/ቤቱ የሕፃኑን አባትነት አጽድቋል፡፡
በሌላ ክስ ደግሞ ባልና ሚስት የዘጠኝ፣ የስድስትና የሦስት ዓመት ልጆች አፍርተዋል፡ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት እንደተለያዩ በመግለጽ፣ የቤት እመቤት የሆኑት እናት ወደ ማዕከሉ ቀርበው፣ አባት ለልጆቹ ቀለብ እንዲቆርጥ ለማድረግ የሕግ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ። ማዕከሉ፣ ትዳራቸው እንዳይፈርስ ጉዳዩን በስምምነት እንዲጨርሱ ያደረገው ሙከራ በእናት እምቢተኝነት ሳይሳካ ቀረ፡፡
ስለዚህ አባት ለልጆቹ ቀለብ በወር 2.000 ብር እንዲቆርጥ ተደረገ፡፡ እናት፣ የልጆቿን አባት በአካል ማግኘት ስለማትፈልግ፣ ገንዘቡን በማዕከሉ አስቀምጦ ከዚያ ለመውሰድ ጠየቀች፡፡ በዚሁ መሠረት አባትም የቀለቡን ገንዘቡ እያመጣ በማዕከሉ ያስቀምጥ ጀመር፡፡ ይህ ሁኔታ ከሦስት ወር በላይ አልዘለቀም፡፡ እናት እየቀዘቀዘች በመምጣቷ ማዕከሉ እንደገና የማስማማት ሙከራ አደረገ፡፡ ሁለቱም ወገኖች ለመስማማት ፈቃደኛ ስለሆኑ ታርቀው በትዳር አብረው መኖር ጀምረዋል፡፡
የ8 ዓመት ሕፃን ስትሆን የምትኖረው ከአባቷና ከአያቷ (የአባት እናት) ጋር ነው፡፡ አባቷ በተደጋጋሚ ይደፍራት እንደነበር እናት ከአረብ አገር ስትመጣ ነገረቻት፡፡ በዚህ ጊዜ ወንጀሉን የሰማችው የእናት እህት (የሕፃኗ አክስት) ወደ ማዕከሉ መጥታ የሆነውን ነገር ተናገረች፡፡
ጉዳዩ በቅብብሎሽ ለሚመለከተው ፖሊስ መምሪያ ተላከ፡፡ ፖሊስም ጉዳዩን አጣርቶ አባትን ፍ/ቤት አቀረበ፡፡ ሕፃኗ ከፍተኛ የሥነ - ልቡና ችግር ውስጥ ስለነበረች ማዕከሉ፣ የሥነ - ልቡና ድጋፍና ሕክምና እንድታገኝ አመቻቸላት፡፡
ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ አቃቤ ሕግ ክስ መሠረተ፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው ፍ/ቤት፣ ተጠርጣሪው ጥፋተኛ መሆኑን ወሰነ፡፡ በዚሁ መሠረት አባት በፈፀመው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል 14 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበት ወህኒ ወርዷል፡፡
እናት፣ የሦስት ቀን ሕፃን ይዛ ወደ ማዕከሉ መጥታ፣ የሚያስጠልላት ቤተሰብም ሆነ ዘመድ እንደሌላት፣ የሕፃኑም አባት ሊረዳት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ገልጻ፣ የሕግ ድጋፍ እንዲደረግላት ጠየቀች፡፡ አባት ተጠርቶ ወደ ማዕከሉ ከመጣ በኋላ እንዲረዳት ሲጠየቅ “ሕፃኑ የእኔ አይደለም። ስለዚህ የመርዳት ግዴታ የለብኝም” አለ፡፡ ጉዳዩ የሕግ መስመር እስኪይዝ ድረስም  ሕፃኑና እናትን ከከፋ የጐዳና ሕይወት ለማዳን ወደ ሴቶች ማረፊያ ተላኩ።
ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት ተልኮ በሂደት ላይ እያለ፣ ማዕከሉ፣ ከጊዜያዊ መጠለያ አቅርቦት በተጨማሪ፣ እናትን በሙያ አሠለጠናት፡፡ በመጨረሻም ፍ/ቤት የተከሳሽን አባትነት አረጋግጦ ቀለብ እንዲቆርጥ ወሰነ፡፡ እናትም ከማዕከሉ ወጥታ በሠለጠነችበት ሙያ እየሠራች አባት በሚቆርጠው ቀለብ ላይ ጨምራ ራስዋን እያስተዳደረችና ሕፃኑን እያሳደገች ነው፡፡
ከፍ ሲል የተጠቀሱትና ሌሎች በሕፃናትና ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ በርካታ በደሎችና ወንጀሎች የተገለጹት የፌደራል ፍ/ቤቶች በሕፃናት ፍትህ አስተዳደር ዙሪያ ከክልሎች ጋር ባካሄደው አገር አቀፍ የሕፃናት ፍትህ አስተዳደር የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ ነው፡፡
ለሁለት ቀን የተካሄደው የምክክር መድረኩ ዓላማ፣ የሕፃናትን ፍትህ አስተዳደር ከማሻሻል አኳያ በፌደራልና በክልል ፍ/ቤቶች እንዲሁም በሕፃናት ጉዳይ ዙሪያ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች ድርጅቶች ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግና በፌደራልና በክልል ፍ/ቤቶች ወጥ የሆነ የሕፃናት ፍትህ አስተዳደር እንዲኖር የፌደራልና የክልል ጠቅላይ ፍ/ቤቶች ፕሬዚዳንቶች የመግባቢያ ሰነድ መፈራረም ነበር፡፡
በዚሁ ወቅት ወ/ሮ ሰላማዊት ግርማይ የሕፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ባቀረቡት ጽሑፍ የመ/ቤታቸውን ተግባር ለማስተዋወቅ በሕፃናትና ሴቶች ላይ ስለሚፈፀሙ ጥቃቶችና ወንጀሎች እንዲሁም መብት ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተለያዩ መንገዶች ባደረጉት ጥረትና ሥልጠና፣ ኅብረተሰቡ፣ በሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን እንደቀድሞው አልከስክሶ ከማለፍ ወደ ሕግ ማቅረብ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
ባለፈው ዓመት 140 ጉዳዮች በስምምነት ተፈጽመዋል፡፡ በዚህ ዓመት ባለፉት 6 ወራት 133 ጉዳዮች በማስማማት የታዩ ሲሆን፤ 24ቱ በሂደት ላይ ናቸው፡፡ ከተጠናቀቁት 109 ጉዳዮች ውስጥ 87ቱ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የሕፃናትን ጥቅም በሚያስከብር ሁኔታ ያለቁ ናቸው፡፡ የተቀሩት 22 ጉዳዮች ግን ወደ ፍ/ቤት ክርክር አምርተዋል፡፡
ማዕከሉ ባለፈው ዓመት ውስጥ 28 የዘረ - መል ምርመራ ወጪን የሸፈነ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 26ቱ አባት ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ዓመት የአባትነት ምርመራ ከተደረገላቸው 17 ሰዎች መካከል 15ቱ አባትነታቸው ተረጋግጦ፣ የሕፃናቱ አባታቸውን የማወቅና እንክብካቤ የማግኘት ሕገመንግስታዊ መብታቸው ተከብሯል፡፡
በዚሁ መሠረት ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ከፖሊስና ከፍርድ ቤቶች ጋር በቅንጅት እየሠራ ሲሆን፣ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማና የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች የሴቶችና ሕፃናት ምርመራ ቡድን በመመስረት ከፍተኛ ተግባር እያከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የየካ ክፍለከተማ ፖሊስ የሴቶችና ሕፃናት ክፍል ለተለያዩ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ከመስጠቱም በላይ፣ ጠፍተው ወደ ጣቢያው የሚመጡ ሕፃናትን ከቤተሰብ ጋር ማቀላቀል፣ በሕፃናት ላይ የተፈፀሙ አካላዊም ሆነ ወሲባዊ ጥቃቶች ለክፍሉ ሲመጡ ወይም ጥቆማ ሲደርስ በአፋጣኝ ማስረጃዎችን በመሰብሰብ ከፍ/ቤት ማዘዣ በማውጣት ተከሳሽን ለሕግ ማቅረብ የቀለብ ግዴታ በፍ/ቤት ውሳኔ እስኪያገኝ ጊዜያዊ ግዴታን እንዲፈጽም ማድረግ ካከናወናቸው ተግባራት ተጠቃሽ  መሆኑን ተወካዩ አስረድቷል፡፡
ፖሊስ ክፍሉ ባለፈው ዓመት በሕፃናት ላይ የተለያዩ ወንጀሎች መፈፀማቸውን ጠቅሶ የወንጀሎቹንም ዓይነት ለይቶ አስቀምጧል፡፡ በአስገድዶ መድፈር ከተፈፀሙ 95 ወንጀሎች 60ዎቹ ውሳኔ አግኝተዋል፡፡ 32 በአዋጅ መቋረጣቸውንና 3 ወደዚህ ዓመት መዛወራቸውን አመልክቷል፡፡ በግብረ ሰዶም ከቀረቡ 12 ክሶች 10ሩ ውሳኔ ያገኙ ሲሆን 2 ወደዚህ ዓመት ተላልፈዋል፡፡ በሕፃናት ላይ የደረሰ የአካል ጥቃት 62 ሲሆን 61ዱ ውሳኔ ሲያገኙ አንዱ ብቻ ወደዚህ ዓመት ተሸጋግሯል፡፡ 82 አጥፊ ሕጻናት የቀረቡ ሲሆን ሁሉም ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በሕፃናትና በሴቶች ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ፍ/ቤት ቀርበው ከ6 ዓመት እስከ 19 ዓመት በፅኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው አሉ፡፡ በግብረ ሰዶም ወንጀሎች ፍ/ቤት ቀርበው 2 ዓመት ከ6 ወር ጀምሮ እስከ 19 ዓመት የተቀጡ አሉ፡፡ በዚህ ዓመት 9 ወር ውስጥ 9 ከባድ ወንጀል ተፈጽሞ 8ቱ ውሳኔ አግኝቷል፡፡
ከክልሎች በአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል የተቋቋመው የሕፃናትና የሴቶች ወንጀል ማዕከል አመሠራረትና አሠራር በጥሩ ተሞክሮ ተወስዷል። ሕፃናትና ሴቶች በደረሰባቸው ወንጀል (በተለይ አስገድዶ መድፈር) የተፈፀመባቸው ፍትህ ለማግኘት ሲሉ ዳግም በደል እንዳይደርስባቸው፣ ጉዳያቸው በተመሳሳይ ፆታ መርማሪ እንዲታይ፣ በነፃ አፋጣኝ የአዕምሮና የአካል ሕክምና እንዲያገኙ፣ ጉዳያቸውን ተረጋግተው ማስረዳት የሚችሉበት አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው በአምስት ተቋማት (የኦሮሚያ ፍትህ፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ጤና፣ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮና በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት) የጋራ ቻርተር መሠረት የመቆያ ማዕከል በአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ተመሥርቷል፡፡
በደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት አሠራር በአርአያነት ተሞግሷል፡፡ ጽ/ቤቱ የሕግ ምክርና ድጋፍ አገልግሎት ይሰጣል፤ ክስ ወይም የመከላከያ መልስ፣ የይግባኝ ቅሬታና መልስ፣ የሰበር አቤቱታዎችንና መልስ ያዘጋጃል፣ በሁሉም አኳኋን በፍ/ቤቶች ችሎት ቆሞ አስፈላጊውን ክርክር ያደርጋል፡፡
ከተመሠረተበት ግንቦት 2004 ጀምሮ እስከዚህ ዓመት 9 ወር ድረስ የሦስት ዓመት የሥራ ዕቅድና በጀት በማውጣት፣ የሥራውን ክንውን ሪፖርት ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ተከላካይ ጠበቃ ጽ/ቤት አቅርቧል፡፡
በመጨረሻም አገር አቀፉ የሕፃናት ፍትህ አስተዳደር የልምድ ልውውጥ መድረክ፣ በመላ አገሪቱ ፍ/ቤቶች ውስጥ ወጥ የሕፃናት ፍትህ አስተዳደር እንዲኖር የተዘጋጀውን መመሪያ፣  በፌደራልና በክልል ፍ/ቤቶች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር የፌደራልና ክልል ፍ/ቤቶች ፕሬዚዳንቶች የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

Read 3599 times