Saturday, 14 June 2014 11:20

ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ የጥራት ተሸላሚ ሆነ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

“የስኬታችን መሰረት ሰራተኞቻችንን በአግባቡ መያዛችን ነው”

        በኒውዮርክ-አሜሪካ በተደረገው “ዓለም አቀፍ ኳሊቲ ሰሚት” የጥራት ተሸላሚ የሆነው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን፤ በአገር ውስጥም የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት 3ኛ ዙር የጥራት ውድድር አንደኛ ደረጃ የክብር ሽልማት ማግኘቱን ገለጸ፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፉ አምባዬ ሽልማቱን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ግንቦት 16 ቀን 2006 በኒውዮርክ ማሪዮት ማርኪዝ ሆቴል በቢዝነስ ኢኒሸቲቭ ዳይሬክሽንስ (ቢአይዲ) በተደረገው 28ኛው የጥራት ውድድር፣ የተክለብርሃን አምባዬ ኪንስትራክሽን እናት ኩባንያ የሆነው “ታፍ ኮሮፖሬት ግሩፕ” ከ118 አገሮች ከተውጣጡ ታዋቂ ኩባንያዎች ጋር ተወዳድሮ የጥራት ተሸላሚ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አሁን በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ ደረጃ የተሰጡን የጥራት ሽልማቶች፣ ኢትዮጵያ በመላው ዓለም በጥራት መወዳደር የሚችሉ ድርጅቶች እያፈራች መሆኑን አመልካች ነው ያሉት አቶ ሰይፉ፤ ሽልማቶቹ፤ መላው ሰራተኛና አመራሩ፣ ጥራትን መሰረት ያደረገ ሙያዊ የአሰራር ሥነ-ምግባር በድርጅቱ ውስጥ በመዘርጋትና በመተባበር የተገኘ ውጤት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት በቅርቡ ለ3ኛ ጊዜ በሸራተን ሆቴል ባደረገው የጥራት ውድድር፤ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን አንደኛ ደረጃ የማዕረግ ተሸላሚ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስታውቀዋል፡፡ በአገር ውስጥ የጥራት ተሸላሚ መሆን የቻሉበትን ምክንያት ሲገልጹም፤ “ከአሁን በፊት የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ባዘጋጀው ውድድር ተሳትፈን ነበር፤ ልንሸልም ቀርቶ የምስክር ወረቀት እንኳን አልተሰጠንም፡፡ ለምንድነው ያልተሸለምነው? ብለን ጠየቅን፡፡ ‹የቀረቡትን የመወዳደሪያ መለኪያ መስፈርቶች ስላላሟላችሁ ነው› ተባልን፡፡ በተነገረን መሰረት ጉድለቶቻችንን አርመንና አሟልተን እንደገና በመወዳደር፣ ይኼው ለሽልማት በቃን ብለዋል፡፡

ከ21 ዓመት በፊት በ1985 ዓ.ም ኢንጂነር ተክለብርሃን አምባዬ በ5,000 ብር ካፒታልና ከሁለት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ያቋቋሙት ደርጅት፤ ዛሬ 850 ቋሚና 200 ጊዜያዊ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በዓመት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ሥራ አስፈጻሚው የስኬታቸው ምስጢር፣ ሰራተኞቻቸውን በአግባቡ መያዛቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ብዙ ድርጅቶች ያልተለወጡት ሰራተኛው አልምጥ ስለሆነ፣ ሥራ ስለማይወድ እንደሆነ ይገልፃሉ ያሉት አቶ ሰይፉ፤ እውነቱ ግን ያ አይደለም ይላሉ፡፡ “ችግሩ ሰራተኞቻቸውን ስላላቀረቧቸውና የሥራው ባለቤት ስላላደረጓቸው ነው፡፡

እኛ ጋ ግን ሰራተኞቻችን መተኪያ የሌላቸው ሀብታችን ናቸው፡፡ አንድ ሰራተኛ ሲያጠፋ አናባርረውም፡፡ ‹ችግርህ ምንድነው?› ብለን እናወያየዋለን፤ ብዙ ጊዜ የሰራተኛው ችግር የሙያና የእውቀት ማነስ እንጂ 99 ከመቶ ያህሉ ቅንና ሥራ ወዳድ ነው፡፡” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ይሄን የሙያና የእውቀት ጉድለት ለማሟላትም ለስልጠና በዓመት 2ሚ. ብር እናወጣለን ብለዋል፡፡ “ሰራተኛው የሥራው ባለቤት እንዲሆን ኃላፊነትና የመወሰን ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ከማኔጅመንቱ ጋር ከዕቅድ ጀምሮ ይሳተፋል፡፡ ያልመሰለውን ነገር አይቀበልም፡፡ እንዲህ ሲደረግ ውጤቱ እንዲህ ይሆናል በማለት ይቃወማል፡፡ ታዲያ ሰራተኛው አምኖ ያፀደቀው እቅድ እንዴት ውጤታማ አይሆንም?...” በማለት ተናግረዋል፡፡ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን፤ በአሁኑ ወቅት ከአገር ውስጥ አልፎ በአፍሪካ አገራትም መስራት የጀመረ ሲሆን በሱማሌ ላንድ የአውሮፕላን ማረፊያ እየገነባ ነው፡፡ በዩጋንዳም በቤቶች ግንባታ ለመሰማራት በእንቅስቃሴ ላይ ነው ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፡፡

Read 3833 times