Saturday, 28 June 2014 11:36

“የነገ ናፍቆት” በአሜሪካን ኤምባሲ ተመረቀ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

         በ1990ዎቹ “እፍታ” በሚል ርዕስ በተከታታይ ለንባብ ከቀረቡት ጥራዞች በአንዱ፤ ስለ አሜሪካ አገር የተፃፈ የጉዞ ማስታወሻ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ በዚያ ጽሑፍ ላይ አሜሪካዊያን “አገራቸው፣ ሰዋቸው፣ ሕንፃዎቻቸው፣ መንገዳቸው፣ ሀሳባቸው…” በአጠቃላይ ሁሉ ነገራቸው ትላልቅ መሆኑ እንዳስገረመ ፀሐፊው ይገልፃል፡፡ እኔም ባለፈው ሳምንት ከ6 ኪሎ ከፍ ብሎ ወደሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ በዘለቅሁ ጊዜ አሜሪካውያን ታላቅነታቸውን ለማሳየት የትኛውንም ቦታና ጊዜ ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይሉ አስተውያለሁ።
በእርግጥ እኔን እግር የጣለኝ ወደ አሜሪካ ልሻገር ቪዛ ፈልጌ አልነበረም፡፡ ባለፈው ዐርብ ምሽት ሰኔ 13 ቀን 2006 ዓ.ም በኤምባሲው ግቢ የተገኘሁት “ፔን ኢትዮጵያ” ያሳተመው “የነገ ናፍቆት” የተሰኘ የአጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሐፍ የምረቃ ሥነስርዓት ላይ ለመታደም ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የተንጣለለ ግቢ ካላቸው ኤምባሲዎች አንዱ የሆነው የአሜሪካ ኤምባሲ፤ በቅርቡ እድሳትና አዳዲስ ግንባታዎችን አከናውኗል፡፡ ይሄም ለግቢውም ሆነ ለአካባቢው ውበትና ግርማ ሞገስን አጐናጽፎታል፡፡
ከውጭ ሲመለከቱት ዓይንና ቀልብን የሚስበው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ውስጥ ሲዘልቁም የሚያስደምሙ ነገሮች ይታዩበታል፡፡ መጽሐፉ ወደሚመረቅበት አዳራሽ ለመግባት በማሽን የታገዘ ፍተሻ የሚደረግባቸው ሁለት ክፍሎችን ማቋረጥ ነበረብን፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ሁለት ነገሮች ቀልቤን ሳቡት፡፡ በአረንጔዴ ዕፅዋት የተሞላው የግቢው ለምለም መስኮችና ግዙፉ የአሜሪካ ባንዲራ፡፡ ያለምንም ማጋነን የአሜሪካ ባንዲራና ሰንደቅ ለግቢው ልዩ ግርማ ሞገስን ቸሮታል ማለት ይቻላል። እውነቱን ለመናገር የአሜሪካ ባንዲራ ወደ ግቢው ሳይገባም ጐልቶ ነው የሚታየው። ምናልባትም አሜሪካውያን ታላቅነታቸውን ከሚያሳዩባቸው ነገሮች አንዱ ባንዲራቸው ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አለኝ፡፡
በኤምባሲው ግቢ የተሰቀለው የአሜሪካን ባንዲራ ትልቅነትና የሰንደቁን ግዝፈት የሚስተካከል የኢትዮጵያ ባንዲራ በአዲስ አበባ ከተማ የትም ቦታ ላይ አላየሁም። በፓርላማ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች… ወዘተ የተሰቀሉትን ባንዲራዎችና ሰንደቃቸውን ብንመለከት በአሜሪካን ኤምባሲ ከሚገኘው ጋር መወዳደር የሚችሉ አይደሉም። ለነገሩ ባንዲራ የሚወክለው አገርን አይደለ!? የአገራችን ባንዲራ መግዘፉና መተለቁ ቢቀር እንኳን አንዳንድ ቦታ እንደሚታየው ቀለሙ ያልደበዘዘና ያልተጨማደደ ቢሆን ስል ተመኘሁ፡፡ በነገራችሁ ላይ አሜሪካኖች ባንዲራቸውን የሚያከብሩት በሰው አገር ብቻ አይደለም፡፡ በራሳቸው አገርም ጭምር ነው፡፡ በየፊልሞቻቸው ላይ የአሜሪካ ባንዲራን በተደጋጋሚ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በትምህርት ቤት መማሪያ ክፍሎች፣ በፍ/ቤቶች፣ በየኩባንያው ቢሮ፣ በውድድር ሜዳዎች ወዘተ…ባንዲራቸው ቀድሞ ይታያል። ይሄ ታዲያ አያስቀናም?!
በፍተሻ ወቅት ሁላችንም እንደሞባይል፣ ሳንቲም፣ ዋሌትና ቁልፎች የመሳሰሉ … ቁሳቁሶች አስቀምጠን በመፈተሽያ ማሽኑ ስናልፍ፣ አንዱ ወዳጄ ግን ማሽኑ እየጮኸበት ሁለት ሦስቴ ለመፈተሽ ተገዶ ነበር፡፡ እኔም በፍተሻው መሃል ጠጋ ብዬ፤ ምን ደብቀሃል ስለው “ደሜ ውስጥ ያለው ቁጣ መሰለኝ ማሽኑን ያስጮኸው” በማለት ከልቤ አስቆኛል- ወኔያችን፤ ዘራፍ ባይነታችን ትዝ ብሎኝ።
ፍተሻዎቹን አልፈን ወደ አዳራሹ ስናመራ፣ በኮሪደሩ ግድግዳዎች ላይ ሌላ ድንቅ ነገር ተመለከትኩኝ፡፡ አሜሪካውያን ለሰዎች ሥራ ክብርና ዕውቅና በመስጠትም ንፉግ እንዳልሆኑ ተገነዘብኩ፡፡ በቅርቡ ባሳየው ኤግዚቢሽኑ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈው የሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ አንድ ስዕል በኤምባሲው አዳራሽ ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ ተመለከትኩ፡፡ የእሱ ብቻ ሳይሆን የሰዓሊ ዘሪሁን የትምጌታ፣ ታምራት ፍቃዱ፣ ኤልያስ ስሜ፣ ደስታ ሀጎስ፣ ወሰኔ ወረቴ (ከስሮፍ)… ስዕሎችም በአዳራሽና ኮሪደሮቹ ግድግዳዎች ላይ ተሰቅለዋል፡፡ እነዚህን የሥነጥበብ ሥራዎች በየትኛው የመንግስት መ/ቤት ወይም ደግሞ የግል ተቋም ውስጥ እናገኛቸው ይሆን? እስካሁን የትም አልገጠመኝም፡፡ ይሄ እንኳን ከስዕል ስራዎች ጋር ያለን ትውውቅ እምብዛም ስለሆነ የመጣ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ክብርና ዕውቅና ለሚሹ ታላላቅ ሰዎቻችን ተገቢውን ክብርና ዕውቅና እየሰጠን ነው ማለት ግን አይቻልም፡፡ ገና ብዙ… በጣም ብዙ ይቀረናል፡፡  
“ፔን ኢትዮጵያ” ያሳተመው “የነገ ናፍቆት” መጽሐፍ የተመረቀበት አዳራሽ ትልቅ የሚባል አይደለም፡፡ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኘው ሰው ቁጥርም ከአንድ መቶ አይበልጥም፡፡ በዚህ ምሽት ሦስት ወጣቶች ግጥሞቻቸውን አቅርበዋል። መጽሐፉን በተመለከተ ሙያዊ አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡
በ188 ገፆች የ13 ደራሲያንን አጭር ልቦለዶች ያካተተው “የነገ ናፍቆት”፤ የአድዋ ጦርነትን፣ የሲዳማን ባህልና የሴት ጀግንነትን፣ የሥነ-ልቦና ሕክምናን፣ ሃይማኖትንና የአንትሮፖሎጂ ጥናትን መነሻና መሰረት ያደረጉ ጭብጦች የሚያንፀባርቁ ታሪኮች ቀርበውበታል፡፡
ከ13ቱ ደራሲያን ሶስቱ ሴት ፀሀፍት ናቸው። የአጭር ልቦለድ ስብስቡ መታተም ተቋርጦ የቆየውን እንቅስቃሴ ዳግም ለማስጀመር ያነሳሳል ብለዋል - የመጽሐፉ አርታኢ ደጀኔ ተሰማ ምህረቴ “የአርታኢው ማስታወሻ” በሚል በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፡፡
በ1970 እና 80ዎቹ በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት እየታተሙ በጋራ ይቀርቡ የነበሩ የአጭር ልቦለድ መድበሎች የአማርኛን ሥነ ጽሑፍ በማሳደግ ረገድ የራሳቸውን አዎንታዊ ሚና እንደተጫወቱ የመሰከሩት አርታኢው፤ ጥረቱ በተጀመረው መልኩ ቢቀጥል ኖሮ የተሻለ ዕድገት ይመዘገብ ነበር ብለዋል።
ደራሲ መጽሐፍ አዘጋጅቶ ብቻውን ለማሳተም ከሚጥር በጋራ ለማቅረብ ቢሞክር ሊሳካለትና በማሳተም ዙሪያ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ይቻለዋል የሚሉት ደጀኔ ተሰማ ምህረቴ፤ አጫጭር የልቦለድ መፃሕፍት በጋራ የማሳተሙ ሌላኛው ጠቀሜታ ጀማሪና ወጣት ፀሐፍትንም ወደ ሥነ ጽሑፉ መድረክ ለማምጣት ያግዛል ባይ ናቸው፡፡ “የነገ ናፍቆት” መጽሐፍ መታተሙ ተስፋን ፈንጣቂ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
መጽሐፉ ለህትመት እንዲበቃ ለ “ፔን ኢትዮጵያ” የተለያዩ እገዛዎችና ትብብር ያደረጉ የኖርዌይ፣ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝና ጀርመን ኤምባሲዎች ስር የሚገኙ የባህል ማዕከላትና ግለሰቦች ለውለታቸው ምስጋናና የስዕል ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ የመጽሐፉ በኤምባሲው መመረቅ ለብዙዎቹ የሥነ-ጽሑፍ ሰዎች ልዩ ስሜት የፈጠረ ይመስላል፡፡ አዲስና በጐ ጅምር ነው በሚል ተቀብለውታል፡፡ ድጋፍና ትብብሩ እንደሚቀጥል ተስፋ በማድረግ፡፡

Read 1413 times