Saturday, 05 July 2014 00:00

ግርማ ይፍራሸዋ አዲስ አልበሙን በአሜሪካ ያስመርቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ታዋቂው የፒያኖ ተጫዋችና የሙዚቃ ቀማሪ ግርማ ይፍራሸዋ ‘ላቭ ኤንድ ፒስ’ የሚል ርዕስ ያለውን አዲስ የፒያኖ ሙዚቃ አልበሙን በዚህ ወር መጨረሻ አሜሪካ ውስጥ በሚያቀርበው ኮንሰርት ያስመርቃል፡፡
በሜሪላንድ ቤተሳዳ ውስጥ በሚገኘው ‘ቤተሰዳ ብሉዝ ኤንድ ጃዝ ሱፐር ክለብ’ በሚከናወን ስነስርዓት የሚመረቀው አልበሙ፣ ቀረጻ ባለፈው አመት ኒውዮርክ ብሮክሊን ውስጥ መጠናቀቁን የዘገበው ታዲያስ መጽሄት፤ አልበሙን ለገበያ ያቀረበው ‘አንሲን ሪከርድስ’ የተባለው ታዋቂ የሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያ መሆኑን ገልጿል፡፡
‘አምባሰል’፣ ‘ጨዋታ’፣ ‘ሰመመን’ና ‘እልልታ’ን ከመሳሰሉ በአገርኛ የሙዚቃ ስልቶች የተቀመሩ የሙዚቀኛውን ወጥ ስራዎች በያዘው በዚህ አልበም፤ በታዋቂው ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ሰው በፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የተደረሰው ‘ባለ ዋሽንቱ እረኛ’ የተባለ ተወዳጅ ሙዚቃ በግርማ እንደገና ተሰርቶ እንደተካተተበት ተነግሯል፡፡
በቡልጋሪያ፣ በለንደን ሮያል የሙዚቃ አካዳሚና ጀርመን ውስጥ በሚገኘው ሌፕዚግ የሙዚቃና የቲያትር ተቋም ትምህርቱን የተከታተለው ግርማ ይፍራሸዋ፤ በተለያዩ የአለም አገራት በተዘጋጁ ኮንሰርቶች የሙዚቃ ስራዎቹን በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓትም የኢትዮጵያንና የክላሲካል ሙዚቃን ለማስተዋወቅ በአፍሪካና በአውሮፓ አገራት እየተዘዋወረ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡

Read 2050 times