Saturday, 05 July 2014 00:00

ፎርብስ የአመቱን የአለማችን 100 ሃያላን ዝነኞች ይፋ አደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ቢዮንሴ የመጀመሪያዋ ሆናለች
ዘፋኞች ዘንድሮም ቀዳሚነቱን ይዘዋል

ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት በየአመቱ እንደሚያደርገው ሁሉ ዘንድሮም በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በስፖርት፣ በሞዴሊንግ፣ በስነጽሁፍና በሌሎች መስኮች ተሰማርተው የሚገኙ ስኬታማ የ2014 የዓለማችን መቶ ሃያላን ዝነኞችን ዝርዝር በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ አድርጓል፡፡
ፎርብስ ለ15ኛ ጊዜ ያወጣው የዘንድሮው ዝርዝር እንደሚያሳየው፣ ታዋቂዋ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ ከአለማችን ዝነኞች ሁሉ በሃያልነቷ አቻ አልተገኘላትም፡፡ ለ32 አመቷ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ አመቱ የገድ እንደነበር የገለጸው ፎርብስ፣ በገፍ የተቸበቸበላትን በስሟ የሰየመችውን አልበም ለአድማጮቿ ያቀረበችበትና ስኬታማ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን በተለያዩ የአለም አገራት የሰራችበት ወቅት እንደነበርም ጠቅሷል፡፡
ቢዮንሴ በሙዚቃው መስክ ካስመዘገበችው ስኬት በተጨማሪ ያቋቋመችውን የአልባሳት አምራች ኩባንያ በመምራትና ፔፕሲን ከመሰሉ ታዋቂ የዓለማችን ኩባንያዎች ጋር በፈጠረችው አጋርነት ተጠቃሽ ስራ በማከናወኗ በዘንድሮ ዓመት 115 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ለማግኘት ችላለች። ፎርብስም ድምጻዊቷን በአመቱ ባስመዘገበችው ስኬቷ መሰረት የአለማችን ቁጥር 1 ሃያል ዝነኛ አድርጓታል፡፡
እሷን ተከትሎ የሁለተኛነትን ስፍራ የያዘው አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ሊብሮን ጄምስ ሲሆን፣ በአመቱ ከማናቸውም ዝነኞች በላይ የሆነ 620 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኘ የተነገረለት ድምጻዊው ዶክተር ድሬ ሶስተኛ ሆኗል፡፡
ባለፈው አመት የፎርብስ ዝርዝር የዓለማችን ሃያላን ዝነኞች ቁንጮ የነበረችው ጥቁር አሜሪካዊቷ የቶክ ሾው አዘጋጅ ኦፕራ ዊንፍሬይ፣ ዘንድሮ በእነዚህ በሶስቱ ተቀድማ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ሚስቱን ቢዮንሴን ከሁሉም ፊት ያደረገው ድምጻዊው ጄይ ዚ ደግሞ፣ በስድስተኛነት ይገኛል፡፡
ዝነኞቹ በ2014 ብቻ ያገኙትን ገቢ በተመለከተ ፎርብስ ባወጣው መረጃ እንዳለው፤ ቢዮንሴ 115 ሚ፣ ሊቦርን ጄምስ 72 ሚ፣ ዶክተር ድሬ 620 ሚ የአሜሪካ ዶላር ገቢ አግኝተዋል፡፡
እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም ዘፋኞች በላይነቱን የያዙበት የፎርብስ ዝርዝር እንደሚለው፣ ድምጻውያን በአልበም ሽያጭ፣ በኮንሰርትና በመሳሰሉ መንገዶች ጠቀም ያለ ገንዘብ ከማግኘት በተጨማሪ፣ ማህበራዊ ድረገጾችን በመጠቀም እውቅናቸውን በማስፋት ረገድ በአመቱ ስኬታማ ነበሩ፡፡
ፎርብስ የአመቱን ሃያላን በመምረጡ ሂደት የግለሰቦቹን የሃብትና የዝና መጠኖችን፣ የተሰሚነትና በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ላይ ያላቸውን የተጽዕኖ ፈጣሪነት ደረጃ እንደ መስፈርት የተጠቀመ ሲሆን፣ ዝነኞቹ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ምን ያህል ጊዜ በህትመትና በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን ስማቸው ተጠቅሷል የሚለውንም ለማወዳደሪያነት ተጠቅሞበታል፡፡
በተለያዩ የመዝናኛው ኢንዱስትሪ መስክ የተሰማሩ የአለማችን 100 ዝነኞች በተካተቱበት በዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር፣ በቀዳሚነት ከተቀመጡት 25 ዝነኞች መካከል ቢዮንሴ፣ ሪሃና፣ ቡርኖ ማርስ፣ ሌዲ ጋጋ፣ ካንያ ዌስትና ቴለር ስዊፍትን ጨምሮ 13 ያህሉ ድምጻውያን ናቸው፡፡
በ2014 የፎርብስ የአለማችን 100 ሃያላን ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ እስከ አስረኛ ደረጃ ከያዙት መካከል አምስቱ ሴቶች ሲሆኑ፣ ሰባቱ ደግሞ አፍሪካ አሜሪካውያን ናቸው ተብሏል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት መካከል፤ ድምጻዊው ቡርኖ ማርስ፣ የፊልም ተዋንያኑ ብራድሊ ኩፐርና ቪን ዲዝል፣ ሞዴል ኬት አፕተንና ደራሲ ቬሮኒካ ሮዝ ይገኙበታል፡፡
አምና በዝርዝሩ ውስጥ የነበሩና ዘንድሮ ካልቀናቸው መካከልም፤ ታዋቂዋ ድምጻዊት ማዶና፣ እግር ኳስ ተጫዋቹ ዴቪድ ቤካም፣ የፊልም ተዋናዩ ቶም ክሩዝና የቴሌቪዥን ቶክ ሾው አዘጋጁ ዴቪድ ሌተርማን ይጠቀሳሉ፡፡

Read 2714 times