Saturday, 12 July 2014 12:17

እየተሰደቡ መጓዝ፤

Written by  ከጉምራ ዙምራ
Rate this item
(3 votes)

በትርፍ እየተጫኑ መሞት - የአዲስ አበባ ታክሲ ተሳፋሪ እጣ!

የጽሁፌ መነሻ የሆነው በከተማችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ብቻ ወደ 5 ሚኒባስ ታክሲዎች ላይ የደረሱ የትራፊክ አደጋዎች፤ በተለይ ደግሞ ብእሬን እንዳነሳ ያደረገኝ እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓ.ም 10፡00 ሰዓት አካባቢ ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ወደ ስድስት ኪሎ 19 ሰዎችን (ልብ አድርጉ 19 ሰዎችን) አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አይ.ሲ ሚኒባስ ተገልብጦ፣ በውስጥ ከነበሩ ሰዎች ይህ ፅሁፍ እስከተቀናበረበት ጊዜ ድረስ የሟቾች ቁጥር 5 የደረሰበት፤ የተቀሩት ደግሞ ቀላል እና ከባድ አካል ጉዳት ደርሶባቸው የህክምና ዕርዳታ በማግኘት ላይ መሆናቸው ነው፡፡
ለነገሩ ተጨራምታ የወደቀችዋን ሚኒባስ ያየ፣ ከሞት እንኳን ቢተርፍ አካል ጉዳት ያልደረሰበት ሰው ይኖራል ብሎ ማሰብ ከንቱ ይሆናል፡፡
ኧረ ጎበዝ ይሄ ነገር ወደ የት እየሄደ ነው? ስንት የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች፤ ለሀገር ለወገን የሚጠቅሙ ስንት የረቀቁ ሃሳቦች የያዙ አእምሮዎ፤ ጨቅላ ህጻናትና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት እንደዋዛ ከመኖር ወደ ሞት እየተሻገሩ ነው። ዋና ሳጅን አሰፋ መዝገቡን ጨምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የትራፊክ ፖሊስ ኃላፊዎች “ይህን ያህል የሞት፤ ይህን ያህል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ ለአደጋው መነሻ በአብዛኛውና በተለመደው ሁኔታ አሽከርካሪዎች ለእግረኛ ቅድሚያ በመከልከላቸው ነው” የሚል ዘገባ ዘወትር ማለዳ እንሰማለን፤ አደጋውም ከመቀነስ ይልቅ (በጥናት የተደገፈ ማስረጃ ባይኖረኝም) እየጨመረ የመጣ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት በልዩ ልዩ ሚዲያዎች ስለ አደጋዎቹ ብዙ ሲባል ነው የሰነበተው፡፡
ታዲያ የዚህን ሁሉ ችግር ኃላፊነት የሚወስደው ማን ነው? መንግስት (መንገድ ትራንስፖርት፣ ትራፊክ ፖሊስ፤ መንገዶች ባለስልጣን) ወይስ እኔ፤ እኛ፤ እናንተ?
የዛሬው ጽሁፌ በዋናነት ወደ መንግስት ያነጣጠረ ሳይሆን ወደ ተጠቃሚዎቹ ወደ እኔና እኛ ላይ ነው፡፡ “መንግስት ጉዳዩ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ አለበት!! በቸልታ ሊያየው አይገባም!!” የሚል የተለመደ ክስና አቤቱታ ለመንግስት ማቅረብ የትም አላደረሰንም፡፡ እና የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን ያህል ጥረት አድርገናል? ለምንስ ነው እንደ ሰርዲን ሲያጭቁን ዝም ብለን የምንታጎረው? መጫን የተፈቀደልህ 11 ሰዎች ብቻ በመሆኑ ትርፍ እንዲጫንብኝ ወይም በትርፍ መጫን አይገባኝም ለምን አንልም? በራሳችን የአኗኗር ዘይቤ ላይ ልናደርገው የሚገባ መስተካከያስ የለም ወይ? ጥዋት በስራ ሰዓት መግቢያና ማታ ወደቤታችን የምንመለስበት ጊዜን አጠቃቀማችን ምን ያህል የተሳካ ነው? ትራንስፖርት ችግሩን መንግስት ብቻ ይፍታው ብለን ከሞትና ከመቁሰል ተርፈናል ወይ? በታክሲ አገልግሎት አጠቃቀም ላይ መብትና ግዴታችንን እናውቃለን ወይ? እናውቃለን ካልን መብታችንን ለምን አናስከብርም? ግዴታችንን ለምን አንወጣም? ካላወቅን ደግሞ የት ሄደን እንወቅ? ማን ያሳውቀን? የሚሉ ጭብጦችን ብሰነዝር፣ የአብዛኞቻችን ተጠቃሚዎች ምላሽ “የትራንስፖርት እጥረት ባለበት ሁኔታ እንዴት ይሄን ጥያቄ እናነሳለን ያው አምላክ ከአደጋ እንዲሰውረን ጸሎት እያደረስን እንሄዳለን እንጂ የሚል ምላሽ ከመስጠት ውጭ የራሳችንን የቤት ስራ በአግባቡ መወጣት አንፈልግም፡፡
ይህን ታሳቢ አድርጌ እኛ ስለራሳችን ማሰብ እንድንጀምርና ቢያንስ ካለፈው ስህተታችን ተነስተን ለቀጣይ የእርምት እርምጃ መውሰድ እንዲያስችለን በእኛ ላይ ብእሬን በማንሳት ለመጦመር ፈቅጃለሁ፡፡ ወደ እኛ ገመና ከመግባቴ በፊት ለንጽጽር እንዲረዳን እስኪ ስለ ምእራባውያን የትራንስፖርት አገልግሎት በአንድ ጽሁፍ ላይ ያነበብኩትን ላቋድሳችሁ፡፡  
“Thank you for riding with us” በጥቅል ትርጉሙ “በእኛ መጓጓዣ ስለተጓዙ እናመሰግናለን” እንደማለት ነው፡፡
ይሄ ጥቅስ በአደጉት አገሮች በአገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ላይ ለዘወትር የሚነበብ አርማ፤ ወይም ሎጎ ነው፡፡ የእነሱን ተሽከርካሪ መርጠው ተሳፍረው ገቢያቸው ከፍ እንዲል ስለረዷቸው አገልግሎት አቅራቢዎቹ ሁሌ ተሳፋሪዎችን ያመሰግናሉ፡፡ “ጥዋት - ማታ በእኛ መጓጓዣ ስለተጓዙ እናመሰግናለን፡፡ ነገም እኛን እንደሚመርጡ ባለ ሙሉ ተስፋ ነን፡፡ የትም አይሂዱብን አደራ፡፡ ያለእርስዎ የኛ ህልውና ዋጋ ቢስ ነው” የሚል ቃና ባለው ዝማሬ መወድስ ያመሰግናሉ፡፡ አሁንም፡፡ አሁንም። አሁንም፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ ግን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ወደ ከተማ የገቡት በተለይ ታክሲ አሽከርካሪዎችም ሆነ ረዳቶቻቸው ሚናቸው ሌላ ነው። “እኔ ካልመጣሁልሽ ማን አባቱ ያጓጉዝሻል?” እያሉ የሚፎክሩ ነገር ናቸው፡፡ እና ተሳፋሪዎች ደግሞ “እውነት ብላችኋል፤ ያለ እናንተ ማን አለን? ከታሪፍ በላይ ውሰዱ፡፡ በትርፍም ጫኑን፡፡ ደራርቡን፡፡ አጭቁን፡፡” ብለን ፈቅደን ህይወታችንን አሳልፈን ሰጥተናቸዋል፡፡ ይባስ ብሎ ብሩክ በሚባል ጸሀፊ በራጅ ወረቀት ላይ በሚፃፉ ተሳፋሪን እና በተለይ የሴቶችን ክብር በሚያጎድፉ ስድብ አዘል ጥቅሶች ታጅበን ልክ ልካችን እየተነገረን በዝምታ እንጓዛለን፡፡ “እናንተ ግን ይህን ጸሁፍ ለምን ትለጥፋላችሁ? ነውር እኮ ነው፡፡” ብሎ ቢያንስ ታክሲ ውስጥ አሊያም ሌላ ቦታ ሃሳቡን የሚቃወም ሰው ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ጥቅሶቹን በአንድ ኢቢኤስ ቲቪ ሾው ላይ ቀርበው ተመልካች እንዲዝናናባቸው ሲደረግ ከማስተዋል በቀር፡፡ እየተሰደቡ መዝናናት፤ አሪፍ ነገር አለው፡፡
ታዲያ አዲስ አበባ እንዴት ሆነን ነው የምንሳፈረው? እንደዚህም አይደል!
በትርፍ መጫን(ጫ-ይጠብቃል)ኢ-ህጋዊ መሆኑ ቀርቶ ህጋዊ ሆኗል
ዛሬ ዛሬ ታክሲ 11 ሰዎችን አሳፍሮ መጓዙ ህጋዊ መሆኑ ቀርቶ ረዳቱ ይሉኝታ ካለው አንድ ሁለት ሰው፤ ካልሆነም ስድስት ሰባት ሰዎችን መደረብ የአሽከርካሪውና ተደርቦ ለመጓዝ የሚመጣው ተሳፋሪ መብት ነው፡፡ ቀድሞ ገብቶ በመደበኛ ቦታው ላይ ላለው ተሳፋሪ ደግሞ ግዴታው ነው። በተለይ ይሄ ችግር እኔ በምኖርበት ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ አገልግሎት በሚሰጡ ታክሲዎች ላይ በአስከፊ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ እኔ አይመቸኝም አልጠጋም ማለት እንደተመጻዳቂ ያስቆጥራል። ሰለጠንኩ ባይ ልትባልም ትችላለህ፡፡ ወይም ልማታዊ ያልሆነ ተሳፋሪ የሚል ስያሜ ያሰጣል፡፡ አልጠጋም፤ እኔም አላስጠጋም ያለ አንድ ተሳፋሪ፣ የታክሲ ረዳቶች በጋራ አድመውበት የሚያሳፍረው ታክሲ አጥቶ እንደነበር እኔ ህያው ምስክር ነኝ፡፡ ትራፊክ ፖሊስ አቅም እንኳን ሙሉ ቀን አደባባይ ላይ ቆሞ ትርፍ እንዳይጫን ሲከላከል የዋለ ተራፊክ ማታ ወደ ቤቱ ሲገባ ኮፍያውን ጃኬት ውስጥ ሸጉጦ፣ በትርፍ ተጭኖ ወደ ቤቱ ሲገባ ማየት የተለመደ ነው።
ታዲያ ይሄ ሁሉ ክፍተት ባለበት አንድ ሰንካላ እሁድ ቀን የሰንበት ሹፌር የሚያሽከረክረው ታክሲ በትርፍ ከጫናቸው 19 ሰዎች ጋር በኢየሱስ መንገድ ቁልቁለት ላይ ሲወርድ ተሽከርካሪው የነበረበት የቴክኒክ ችግርና የሹፌሩ ለማጅ መሆን እንዳለ ሆኖ፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ካፊያ ዝናብ ሲጥል ስለነበር አስፈሪ ቁልዙለት ላይ ሲወርድ ሹፌሩ መኪናውን መቆጣጠር ሳይችል ቀረና ሁለት የመብራት ፖሎችን ገጭቶ የፍሳሽ ጉድጓድ ውስጥ በመግባቱ 5 ሰዎች ሲሞቱ፣ቀሪዎቹ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት አስተናግደው ቀሩ፡፡ አንባቢያን ልብ እንዲልልኝ የምፈልገው ነገር ቢኖር፣ በዚያ ታክሲ ውስጥ ቢያንስ በዚያ ሞት ድግስ መታደም ያልነበራቸው ከ6-7 ተሳፋሪዎች መኖራቸውን ነው። በትርፍ ተሳፈሪ ሲባሉ እምቢ ባለማለታቸውና ቀድመው የተሳፈሩትም “አይመቸኝም፤ አላስጠጋም” ሳይሉ በመቅረታቸውሰ የሞትን ጽዋ ተጎነጩ፡፡ ከሁሉ የገረመኝ ደግሞ በማግስቱ የሌላ ታክሲ ረዳት ስለ አደጋው ለተሳፋሪ ሲያስረዳ፤ “ሾፌሩ ለማጅ፣ ፍሬሽ ነበር” አለ፡፡ ለማጅ ሹፌር ሰው እየገደለ እጅ የሚፈታበት አገር፡፡ ኢትዮጵያ!!
አንባቢ ይህን ጽሁፍ ሲያነቡ፣ በቅሬታም ይሁን በንዴት እኛ ምን እንድናደርግ ነው የሚፈለገው? የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው አይቀርም፡፡ በእኔ በኩል እንደተሳፋሪ ማድረግ የሚገባን ጥቂት ነው። እርሱም የጊዜ አጠቃቀማችንን መልሰን መከለስና ማስተካከል። ምን ማለት ነው? እስከዛሬ በነበረን ልማድ ዘወትር ጥዋት የምንነሳበትን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ አድርገን ቀደም ብለን የመነሳት ባህልን ማዳበርና በተለምዶ ወደ ታክሲ የምንመጣበትን ጊዜ ከ30-45 ደቂቃ ማሻሻል፡፡ በእኔና በእኔ ሰፈር ተሞክሮ ጥዋት ወደ ስራ የምወጣበትን ጊዜ ቢያንስ ከ15-20 ደቂቃ ማስተካከል በመቻሌ፣ ያለምንም ግፊያና ርኩቻ ወደ ስራዬ መድረስ ችያለሁ፡፡ ታዲያ ሁላችንም ይህን ባህል ብናዳብር ታክሲዎቹ ወደ ስራው ለመግባት የሚቸኩል ተሳፋሪ ስለማይኖራቸው ተፈቀደላቸውን 11 ሰዎች ብቻ ይዘው የሚጓዙበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማስረጃው ከ4፡00 ሰዓት በኋላ ታክሲዎቹ በምን አግባብ እንደሚጭኑ ማስተዋል ብቻ ነው፡፡
እኔና እናንተ ይህን ያህል ከተወቃቀስን በመንግስት በኩልስ ምን ያድርግ? በእኔ እይታ በከተማው ውስጥ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል መንግስት ታክሲዎች በስምሪት እንዲሰማሩ ማድረጉና ተሳፋሪም ባልተለመደ መልኩ ሰልፍ ይዞ ለመስተናገድ መሞከሩ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም የታክሲ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ስምሪት የሚገቡ አንዳንድ ታክሲዎች ይዞታ ግን በምን መስፈርት አመታዊ የተሽከርካሪዎች ምዘና እንደሚያልፉ ማሰብ በራሱ አስገራሚ ነው፡፡ እርግጥ ነው እያንዳንዱ ታክሲ በቀን በሚያገኘው ገቢ የሚያስተዳድራቸው ቤተሰቦች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ አሮጌ ታክሲዎች ተጠራርገው ይውጡ እያልኩም አይደለም፡፡
ነገር ግን ሁሉም ታክሲዎች በጥዋት ሲሰማሩ፣ ያለምንም የቴክኒክ ችግር አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ሊረዱ ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን በሁላችንም አእምሮ ውስጥ በሰላም ወጥቶ በሰላም ወደ ቤት ለመግባት ያለንን ምኞት ማሳካት አይችሉም ማለት ነው፡፡ በተለይ እንደ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አይነት አስቸጋሪ መልክአ ምድር ላላቸው ሰፈሮች የሚመደቡት ተሽከርካሪዎች ይዞታ አስተማማኝ መሆን ይኖርበታል። ምንም እንኳን አሁን የሚሰራው መንገድ አስቸጋሪውን ዳገት በመቀነስ በመጠናቀቅ ላይ ያለ ቢሆንም ሌሎች ተመሳሳይ አካባቢዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት የታክሲ ምደባው ላይ የሚመለከተው የመንግስት አካል ጥንቃቄ ሊወስድበት ይገባል፡፡ ከተሳፋሪው በዘለለ መንግስት ትርፍ የሚጭኑ የታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ፤ የተሽከርካሪ አመታዊ ምርመራውን እና የመንጃ ፍቃድ አሰጣጡን ሂደት መልሶ ማጤን እንዲሁም የትራፊክ ህግና አፈጻጸሙን በአግባቡ ሊፈትሸው ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በከተማችን ውስጥ የሚፈጠሩ አደጋዎችን በእነ ዋና ሳጅን አሰፋ መዝገቡ ሪፖርት ብቻ ይቀረፋል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ስለሚሆን፣ የዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ህገ-መንግስታዊ መብትን አደጋ ውስጥ በማስገባት፣ ህዝቡ “መንግስት/ኢህአዴግ የት ነው ያለው? የሚያስተዳድረው ሌላ አገር ነው እንዴ?” የሚል ጥያቄ ማንሳቱ የማይቀር መሆኑ ይሰማኛል፡፡  

Read 3420 times