Saturday, 19 July 2014 12:27

ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም ስለራሱ ምን ብሎ ነበር?

Written by  ብርሃኑ ሰሙ ethmolla2013@gimal.com
Rate this item
(5 votes)

       አራት ኪሎ ሥላሴ ቤተክርስቲያን ግቢ የሚገኘው የመቃብር ሥፍራ ባለፉት 70 ዓመታት የበርካታ ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን የቀብር ሥነ-ስርአት ተፈጽሞበታል። አንጋፋው ደራሲ መስፍን ሀብተማርያምም አርፎበታል፡፡
ሕልፈቱንና የቀብር ሰዓቱን ደውሎ የነገረኝ አንድ ወዳጄ “መስፍን ስለራሱ የፃፈበትን መጽሔት ይዤልህ እመጣለሁ” ባለኝ መሠረት፣ ሥላሴ ቤተክርስቲያን ቀብር ላይ ስንገናኝ ሰጠኝ፡፡ በየካቲት ወር 1988 ዓ.ም በ“ፈርጥ” መጽሔት ላይ ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም ስለራሱ ማንነት ያቀረበውን ጽሑፍ እንደሚከተለው አሳጥሬ አቅርቤዋለሁ፡፡
ባለ ብዙ ስሞች
በሞጆ ከተማ የተወለደው መስፍን ሀብተማርያም ወላጆቹ 7 ልጆችን አፍርተው ከእንግዲህ በኋላ አንወልድም ባሉበት ሰዓት በመረገዙ እናቱ “የት ነበርክ” የሚል ሥም ሰጡት፡፡ ቤተ ዘመዱ፣ ወዳጅና ጐረቤቱም አዲሱን ሕፃን ይገልፀዋል የሚል ስያሜ መስጠት ጀመሩ፡፡ “የኋላሸት”፣ “ሲሳይ”፣ “እንግዳወርቅ”፣ “ሞጆ” ያሉትም ነበሩ፡፡ እህቱ ያወጣችለት ሥም ግን መጠሪያና መታወቂያው ሆኖ ዘለቀ፡፡
ወ/ሮ ዘቢደር የሚባሉ የእናቱ ጓደኛም “እውነቱ” የሚል ሥም አውጥተውለት እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በዚህ ስም ጠርተውታል፡፡ ይህ መጠሪያ እንዲወጣለት ምክንያት የሆነው፤ ከአራስ ቤት ወጥቶ እናቱን ተከትሎ የተለያዩ ቦታዎች መሄድ በጀመረበት የልጅነት ዘመኑ ነው፡፡ “በልጅነቴ ሞኛ ሞኝና እልኸኛ እንደነበርኩ ትዝ ቢለኝም እውነቱን አፍረጥርጬ በመናገር እታወቅ ነበር” የሚለው መስፍን ሀብተማርያም፤ በአንዱ ዕለት እናቱና ወ/ሮ ዘቢደር እሱን ይዘው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ። ዕለቱ የንግሥ በዓል ስለነበር፣ ታቦት ሲወጣ ሕዝቡ እልልታውን ሲያቀልጠው መስፍን ለእናቱ “ጊዮርጊስን አሳዩኝ” ይላቸዋል፡፡
እናቱ የያዙትን ጥላ ለጓደኛቸው ለወ/ሮ ዘቢደር ይሰጡና መስፍንን ከፍ አድርገው በመሸከም “ያውልህ” ይሉታል፡፡ ደጀ ሰላሙ ላይ የአባቱን ወዳጅና የእሱም ጓደኛ አባት መምሬ የምሩን ብቻ ማየት የቻለው መስፍን፤ “እኔ አሳዮኝ ያልኩት የውነቱን ጊዮርጊስ እኮ ነው” ይላቸዋል፡፡ ይህንን የሰሙት ወ/ሮ ዘቢደር ከዚያን ቀን ጀምሮ መስፍንን “እውነቱ” ብለው ባወጡለት ሥም መጥራታቸውን ቀጠሉ፡፡
ጨረቃን የሚያፈቅረው ልጅ
ተወልዶ ያደገበት የቤተሰቦቹ ግቢ ፓፓያ፣ ኮክ፣ ሮማን፣ ሸንኮራ፣ ጌሾ፣ ጫትና መሰል ፍራፍሬና አትክልቶች የሞሉበት ነበር፡፡ መስፍን ይሄን ግቢያቸውን ሲወደው ለጉድ ነበር፡፡ በልጅነቱ ሞጆ እያለ ማታ በተኛበት የዝናብ ካፊያ ቆርቆሮ ላይ ሲያርፍ መስማት፣ ምሽት ላይ ውሾችና ጅቦች የሚያሰሙት ጩኸት እንዲሁም ምሽት ላይ የምትወጣዋን ጨረቃ መመልከት ያስደስተው ነበር።
ገጣሚ ያደረገው የልዑል መኮንን ሞት
ግንቦት 4 ቀን 1949  ዓ.ም ከሞጆ በ5 ኪሎ ሜትር በሚርቅ ስፍራ ላይ ልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ የመኪና አደጋ በገጠማቸው ማግስት፤ በሞጆ ከተማ የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ስፍራው ሄደው ሀዘናቸውን እንዲገልፁ ተደርጐ ነበር። በዚህ ሥነ ስርዓት ወቅት ሄሊኮፕተር ይመጣና ወረቀት በትኖ ይሄዳል፡፡ ከተበተኑት አንዷን ያገኘው ልጅ መስፍን ሀብተማርያም፤ በሎሚ ዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብሎ በወረቀቱ የሰፈረውን ግጥም ያነባል። የሀዘን ግጥሞቹን ወደ ቤቱ ይዞ በመሄድ ደጋግሞ ካነበባቸው በኋላ፣ በማግስቱ አንድ ገጽ የሀዘን ግጥም ፃፈ፡፡ በግጥሙ ውስጥ
ያ ልዑል መኮንን የድሆች በረንዳ
ተለይቶን ሄደ ጥሎብን ብዙ ዕዳ
 የሚሉ ስንኞች ይገኙበታል፡፡ ይህንን ለአማርኛ አስተማሪው ወስዶ ሲያሳያቸው፣ “በርታ፤ ወደፊት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ጆርናሊዝም (ጋዜጠኝነት) ትማራለህ” አሉት፡፡
ከዳይሬክተር መጽሐፍ የሚዋሰው ተማሪ
ከመደበኛ ትምህርቱ ጐን ለጐን ግጥም በመፃፍና ቴአትር ጽፎ በመተወን ይሳተፍ የነበረው መስፍን ሀብተማርያም፤ “የሰውን አነጋገር፣ አካሄድ…የመሳሰሉትን “ፎርም ማንሳት” እና የሰፈር ልጆችን ሰብስቦ ቀልድ ማሰማት፣ ያየነውን ፊልም ወይም ቴአትር አሰማምሮ እንደገና ለጓደኛና ዘመድ የማጫወት ችሎታው ነበረኝ” ሲል ፅፏል፡፡ ይህ ተሳትፎውና ታዋቂነቱ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የሚያነቧቸውን መፃሕፍት እንዲያውሱት ዕድል ፈጥሮለታል፡፡ ምፅላሉድንግል ሙሉነህ የሚባሉ የአማርኛ መምህሩም ለድርሰት ፍቅር እንዲያድርብኝ አድርገውኛል በማለት ያመሰግናቸዋል፡፡
ከድርሰት ጋር ጋብቻ የፈፀመባት አምቦ
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሞጆ ካጠናቀቀ በኋላ፣ ሁለተኛ ደረጃን ለመቀጠል የሄደባት አምቦ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተፃፉ በርካታ መፃሕፍትን ያነበባት፤ የሥነ ጽሑፍ ዕውቀቱ ከፍ እንዲል የረዱት መምህራንን ያገኘባት፤ ጥቂት የማይባሉ ግጥሞች፣ ቴአትርና ልቦለዶችን የፃፈባት ስፍራ ሆነችለት፡፡ ስለዚያ ዘመን ሲናገር “የድርሰት ሽታው፣ መዓዛው በጭንቅላቴ መቀረጽ የጀመረው የኪነ ጥበብ ፍቅር በእድሜዬ ክልል ጉልህ ሆኖ የታየኝም አምቦ ነው” ብሏል፡፡
ከተደሰተባቸው ቀኖች በአንዱ
ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም ስለራሱ ማንነት በየካቲት ወር 1998 ዓ.ም በፈርጥ መጽሔት ባቀረበበት ወቅት፤ ሁለት የወግና አንድ የአጭር ልቦለድ መፃሕፍትን አሳትሟል፡፡ “አዜብ” የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፉ ታትሞ ከተሰራጨ በኋላ መጽሐፉን ያከፋፈሉለት ነጋዴዎች ትርፍህ ነው ብለው 8 ሺህ ብር እንደሰጡት ጠቅሶ፤ “በሕይወቴ የተደሰትኩበት ቀን” ብሏል፡፡ “ወይ ጉድ ለካ ገንዘብ ማለት አነስተኛም ሆኖ እንዴት ያለ የሥነ ልቦና ቶርች ነው! አጃኢብ ነው…” ሲልም ገልፆታል፡፡
ሞትን የረታባቸው መድረኮች
የ7ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ሞጆ ከተማ በሚገኝ ወንዝ ውስጥ አምስት ሜትር ያህል ወደ ውስጥ ጠልቆ በሞት አደጋ ላይ እያለ ዋና በማይችል ጓደኛው እርዳታ ሕይወቱ ሊተርፍ ችሏል፡፡ ሁለተኛው ገጠመኝ በደርግ ዘመን በ1972 ዓ.ም የተከሰተ ነው። “እኔ የቀበሌ ጥይት በተተኮሰ ቁጥር አንድ መለኪያ እየጠጣሁ የአረቄ ጓደኛ ከመሆኔ በስተቀር እምንም ውስጥ የገባሁ አልነበርኩም” የሚለው ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም፤ በአንዱ ዕለት አምሽቶ ወደ ቤቱ ሲሄድ በሰዓት እላፊ አሳበው ያስቆሙት ታጣቂዎች፣ አንበርክከውት የተቀባበለ መሳሪያቸውን ምላጭ ለመሳብ በተዘጋጁበት ሰዓት “ከምትገድሉኝ ያለኝን ብትወስዱ ይሻላል” የሚል ሃሳብ በማቅረቡ 17 ብርና የእጅ ሰዓቱን አስረክቦ ሕይወቱን አትርፏል፡፡ በ1970 ዓ.ም የአራት አብዮት ጠባቂዎች መሳሪያ ከተደገነበት በኋላ በስድብና በግልምጫ የተለቀቀበት ታሪክም አለው፡፡
በ1959 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ፣ በክረምት ወቅት አስመራ ያሉ መምህራንን እንዲያስተምሩ ከተላኩት 10 ያህል አባላት አንዱ የነበረው መስፍን ሀብተማርያም፤ ለግድያ ከተፈላለጉ ሁለት ጓደኞቹ አንደኛው፤ በመሰለኝ ተሳስቶ መስፍን ላይ የተኮሰው ጥይትም ዒላማውን ስቶ ሕይወቱ የተረፈው “አትሙች ያላት ነብስ ቢኖረኝ ነው” ሲል ፅፏል፡፡
ማጠቃለያ
“በምፅፍበት ወቅት የምመርጠው ቦታና ጊዜ የለም፡፡ የግድ ብቸኛ መሆንም የለብኝም፡፡ ጭንቀትና የኑሮ ክርን ካረፈብኝ ግን ቢጨፈልቁኝም ምንም አይወጣኝም” የሚል ምስክርነት በፈርጥ መጽሔት ላይ የሰጠው ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም፤ ሥራዎቹ ያስገኙለትን ክብር በሕይወት እያለ ማየት ከታደሉት የጥበብ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ 65ኛ የልደት በዓሉን የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር በድምቀት አክብረውለታል፡፡ በያዝነው 2006 ዓ.ም መግቢያም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የዕውቅናና የምስጋና መድረክ አዘጋጅቶ ደራሲ መስፍን ሀብተማርያምን አወድሷል፡፡ የመጨረሻ ማረፊያውም ታላላቅ ሥራ የሰሩ ኢትዮጵያዊያን ማረፊያ በሆነው በሥላሴ ካቴድራል ሆኗል፡፡

Read 3736 times