Saturday, 19 July 2014 12:30

ጋሽ መስፍኔ እና ‘ሰውረስ’

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)

ከአምስት አመታት በፊት…
ከታቦር ተራራ እስከ አላሙራ ጋራ፣ ጉም ጭጋግ የለበሰች… ከአረብ ሰፈር እስከ ፒያሳ፣ በካፊያ የረሰረሰች የቆፈነናት ሃዋሳ…
ካፊያው እስኪያቆም ለመጠበቅ የሚያስችል እንጥፍጣፊ ትዕግስት ያጣን፣ ሁለት ቸኳይ መንገደኞች፣ ከአሞራ ገደል ወደ ፒያሳ የሚያቀናውን መንገድ ተከትለን፣ ነጠቅ ነጠቅ እያል እንጓዛለን - ጋሽ መስፍኔና እኔ፡፡
ፒያሳ ለመድረስ ቸኩለናል፡፡ እዚያ ነው፣ ከሃዋሳ ልጆች ጋር ልንገናኝ የተቀጣጠርነው። በሰዓቱ ለመድረስ አስበን፣ ከፍቅር ሃይቅ ቀደም ብለን ብንነሳም፣ ድንገት መጣል የጀመረው ዝናብ ግን እንቅፋት ሆነብን፡፡ በየጥጋጥጉ እየተጠለልን ልናሳልፈው ብንሞክርም፣ ሄድ መጣ እያለ ጉዟችንን አስተጓጎለው፡፡
በስተመጨረሻም እስኪያባራ ከመጠበቅ፣ ፈጠን ብለን መጓዝ እንደሚሻለን ተስማምተን፣ ብርድ የሚያስረሱ የልጅነት ዘመን ትዝታዎቹን እያስኮመኮመኝ በካፊያ ውስጥ መራመዳችንን ቀጠልን፡፡ በፍጥነት… ከሩጫ በማይተናነስ እርምጃ…
መካከል ላይ…
“እኔ እምለው ጋሼ… ‘የቆንጆ ልጅ ፈተና’ የሚለውን ግጥም፣ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሆነህ ነው የጻፍከው?” ስል ጠየቅኩት፡፡
መልስ አልነበረም፡፡
ከጎኔ ሲጓዝ የነበረው ጋሽ መስፍኔም ከአጠገቤ አልነበረም፡፡
ደንገጥ ብዬ ወደኋላዬ ዞርኩ፡፡ ጋሽ መስፍኔ ጉዞውን አቋርጦ ቆሟል፡፡ ካፊያ እያበሰበሰው አይኖቹን አንድ ቦታ ላይ ተክሎ ቆዝሟል፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ፈረስ ቆሟል፡፡
አጥንቱ የገጠጠ… ጀርባው የተላላጠ… ከስቶ የመነመነ… አይኖቹን የጨፈነ… ቋንጃዎቹ የታጠፉ… ጋማዎቹ የረገፉ… ፈራርሶ ሊወድቅ የደረሰ የቆፈነነው አሮጌ ፈረስ፣ ሞትና ህይወትን በሚያዋስነው ቀጭን ድንበር ላይ እግሮቹን ተክሎ፣ የግንብ አጥር ተከልሎ ይንቀጠቀጣል፡፡ ከመላ አካላቱ ትኩስ ጭስ ሽቅብ ይትጎለጎላል፡፡
“እስኪ አስበው አንተነህ!...” አለኝ ጋሽ መስፍን፣ በትካዜ ተውጦ ፈረሱን አሻግሮ እያየ፡፡
“እስኪ አስበው!... ይሄ የተላላጠ ደካማ ፈረስ፣ በጉብዝናው ወራት የነበረውን ግርማ ሞገስ እስኪ አስበው፡፡ ድካም ሳይጎበኘው፣ ህመም ሳያገኘው፣ እርጅና ሳይጥለው፣ ዕድሜ ሳያዝለው… ይህ ሁሉ ሳይሆን በፊት የነበረውን ጉልበት፣ የነበረውን ውበት እስኪ አስበው!... ዘመን አቅሙን ሳያደቀው፣ ጡንቻውን ሳይሸመቅቀው፣ ህመም ጉልበቱን ሳይነጥቀው፣ ጌታውም አረጀ ብሎ ከጋጣው ፈትቶ ሳይለቀው…. እንዲህ ሳይሆን በፊት፣ እንዴት እንደነበር እስኪ አስበው!...” ፈረሱን እያየ ሃዘን በሰበረው አንደበት፣ የድራማ የሚመስል ግን የገሃድ እና የልብ የሆነ ንግግሩን ቀጠለ፡፡
ፈረሱን ባለበት ትተነው ወደ ፒያሳ ስንጓዝም… ከሃዋሳ ወዳጆቻችን ጋር ደማቋን የቅዳሜ ተሲያት ስናሳልፍም፣ ወደ ደቡብ ከዘለቀው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የተጓዦች ቡድን ጋር ወደ አዲስ አበባ ስንመለስም… ከዚያ በኋላም፣ የጋሽ መስፍኔ ንግግርና የፈረሱ ገጽታ አብረውኝ ነበሩ፡፡
ስለፈረሱና ስለፈረስ ማብሰልሰሌን ቀጥያለሁ፡፡
.           .          .
በዚያች ምሽት…
አፍሪካውያን በንዴትና በቁጭት እርር ድብን ባሉባት በዚያች ምሽት… በደቡብ አፍሪካው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ፣ ጋና የአፍሪካን ተስፋ ለአሜሪካ አሳልፋ በሰጠችበት በዚያች አናዳጅ ምሽት… ውድድሩ በተጠናቀቀበት ቅጽበት… ስልኬ ጠራች፡፡ ወዳጄ ሌሊሳ ግርማ ነበር የደወለልኝ፡፡
“አያሳዝንም!?” አለኝ ሌሊሳ በከፍተኛ ሃዘን ተውጦ፡፡
“በጣም እንጂ!...” የጋና ሽንፈት፣ እሱንም እንደኔ እንዳሳዘነው እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
“በጣም ያሳዝናል!... እንዴት እንደከሳ ልነግርህ አልችልም!... ደሞ ርቦታል!...” ሌሊሳ በስሜት ተውጦ ይናገራል፡፡
“ማነው እሱ?” ግራ ተጋብቼ ጠየቅሁት፡፡
“ፈረሱ!” ሲል መለሰልኝ፡፡
ጆሮዬን ተጠራጠርኩት፡፡
“ጨለማው ውስጥ ቆሞ ሳገኘው አሳዘነኝ!... እኛ ሰፈር አካባቢ ሳር ያለበት ቦታ ፈልጌ ሳስግጠው ቆይቼ፣ የማሳድርበት ቦታ ስላጣሁ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዤው እየሄድኩ ነው!...”
ሌሊሳን ተጠራጠርኩት፡፡
የሆነ ቅዠት ውስጥ ሳይሆን አይቀርም ስል ገመትኩ፡፡ በስልክ የጀመረልኝን የፈረሱን ታሪክ፣ በነጋታው በአካል ተገናኝተን ሲጨርስልኝ ግን፣ ግምቴ ስህተት እንደነበር ገባኝ፡፡ ከፈረሱ ጋር ስላሳለፈው ቀሪ የሌሊት ጉዞ አጫወተኝ፡፡ ፈረሱን ለፖሊስ ለማስረከብ በድቅድቅ ጨለማ ጋማውን ይዞ ያደረገውን ጀብደኝነት የተሞላበት ጉዞ ተረከልኝ፡፡
ያኔ ነው የጋሽ መስፍኔንና የሌሊሳን ፈረሶች ያዳቀልኳቸው… ‘ሰውረስ’ ብዬ የተረክኋቸው፡፡
*   *   *
ከሁለት አመታት በፊት… ጋሽ መስፍኔን መርካቶ አካባቢ አገኘሁት፡፡ “አንተነህ… ፈረሱንኮ አየሁት!” አለኝ ፊቱ በደስታ ወገግ ብሎ፡፡ እኔም አድራሻው ጠፍቶብኝ እንጂ፣ ፈረሱን ላሳየው ፈልጌ ያለበትን ማጠያየቅ ከጀመርኩ ብዙ ጊዜ ሆኖኝ ነበር፡፡“መጨረሻውን ግን አልወደድኩትም!... ፈረሱ እንደተመኘው ታቦር ተራራ አናት ላይ ወጥቶ ሳር ሲግጥ፣ ጠግቦ ሲያንፏርር፣ ከህመሙ አገግሞ ሽምጥ ሲጋልብ ማየት ነበር የምፈልገው!...” ጋሽ መስፍን በስሜት ተውጦ ነበር የሚናገረው፡፡
እውነቱን ነው!...
በ2003 ዓ.ም ለንባብ ባበቃሁት ‘መልስ አዳኝ’ የተሰኘ የአጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሃፌ ውስጥ ያካተትኩት “ሰውረስ” (ሰው እና ፈረስ እንደማለት) የሚል ርዕስ ያለው ታሪክ፣ ፈረሱ ገና ከህመሙ ሳያገግም… የናፈቀውን ሳር ሳይግጥ… ጋሽ መስፍኔ እንደተመኘው ታቦር ተራራ አናት ላይ ሳይደርስ ነበር የቋጨሁት፡፡
*   *   *
ጋሽ መስፍኔ…
እኔም ያንተን መጨረሻ አልወደድኩትም፡፡
ከሁለት ወራት በፊት አዲስ አድማስ ግቢ ውስጥ አግኝቼህ፣ አንድ ነገር ነግረኸኝ ነበር፡፡
“ከዚህ በፊት በጋዜጣው ላይ የታተሙትን ጽሁፎቼን አሰባስቤ ላሳትማቸው ነው የመጣሁት” ብለኸኝ ነበር፡፡
የፈረሴን መጨረሻ እንዳልወደድከው፣ እኔም ያንተን መጨረሻ አልወደድኩትም፡፡
አንተም እንደ ፈረሴ ከህመምህ አገግመህ፣ ባይህ ነበር ደስ የሚለኝ!... የእሱ ምኞት ተሳክቶ ማየት እንደሻትከው፣ እኔም ምኞትህን አሳክተህ ማየት ነበር የምፈልገው፡፡ እንደተመኘኸው ጽሁፎችህን አሳትመህ በደስታ ስትፍለቀለቅ ሳላይ፣ ታሪክህ መቋጨቱን አልወደድኩትም!...
ለነገሩ ባልወደውስ፣ የሆነውን ከመቀበል ውጭ ምን እላለሁ?!... የወጠነውን ታሪክ፣ ይሆናል ባለው መልኩ መጨረስ፤ ያስጀመረውን ጉዞ፣ በመሰለው መንገድ መቋጨት… እሱ የ‘ደራሲው’ ምርጫ ነው!... ባይሆን ‘ክፍል ሁለት’ህን ያሳምርልህ!
ነፍስህን በገነት ያኑራት ጋሼ!!!

Read 1908 times