Tuesday, 29 July 2014 14:55

በ“ሽብርተኝነት” የተከሰሰችው ማፊ

Written by  በዳዊት ንጉሡ ረታ
Rate this item
(15 votes)

ባለፈው ሳምንት አዲስ አድማስ ጋዜጣ “ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ በሽብርተኝነት ተከሰሱ፤ ተከሳሾቹ ከግንቦት ሰባትና ከኦነግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተገለፀ”  በሚል ርዕስ በፊት ለፊት ገጹ ያወጣውን ዘገባ ሳነብ የተሰማኝ ድንጋጤና ሃዘን ይህ ነው የማይባል ነው፡፡ አዕምሮዬ ደጋግሞ ከጦማሪያኑ መካከል አንዷ የሆነችውንና በአሁኑ ሰዓት በእስር ላይ የምትገኘዋን ማህሌት ፋንታሁንን (ማፊ) አስታወሰ፡፡
ወጣት ናት፡፡ እኔ እስከማውቃት ድረስ ይህ ነው የማይባል የአገር ፍቅር ያላት! መሻሻል፣ መለወጥ፣ ማደግ የምትሻ ቀልደኛ! ማንበብና መወያየት አጥብቃ የምትወድ …. በቃ እኔ የማውቃት ማፊ እቺ ናት፡፡  
እኔ፣ ማፊና ሌሎች ወጣቶች
ጊዜው 1999 ዓ.ም ላይ መሆኑ ነው፡፡ የዓለም ባንክና ብሪትሽ ካውንስል፣የወጣቶችን የአመራር ብቃት ለማዳበርና ለማብቃት የሚያግዝ አንድ ስልጠና ለመስጠት ማስታወቂያ ያወጣሉ። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚታገዙ የወጣት ድርጅቶች አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ በግል የቢዝነስ ስራ የተሰማሩና ሌሎችም ስልጠናውን ለመሳተፍ አመለከትን፡፡ ለስልጠናው የሚፈለገው የተወሰነ ወጣት ስለነበር፣ የመለያ መመዘኛዎች ወጥተውልን በግምት 25 የምንሆን ወጣቶች ስልጠናውን የመካፈል ዕድል አገኘን፡፡ ከእነዚያ ተሳታፊዎች መካከል ማህሌት ፋንታሁን (ማፊ) አንዷ ነበረች፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነው እኔና ማፊ የተዋወቅነው፡፡
“Debate to Action!”
የዓለም ባንክና ብሪቲሽ ካውንስል እኛን ለማሰልጠን የተጠቀሙበት መሪ ቃል “Debate to Action!” የሚል ሲሆን ስልጠናው፣ ውይይትና ክርክር አንድን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው የሚያስገነዝብ ነበር፡፡ እውነትም በወቅቱ በበርካታ አገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በቡድን  እየተከፋፈልን ውይይትና ክርክሮችን አደረግን፡፡
በዚያ ስልጠና ከማፊ ሌላ ሊሳተፉ መጥተው ከተዋወቅኋቸውና በኋለኛው ዘመኔም ወዳጅ ካደረግኋቸው ወጣቶች መካከል ከወር በፊት “ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ፎቶ ስታነሳ ታይተሃል” ተብሎ ለአጭር ቀን ታስሮ የተለቀቀው የህግ ባለሙያው ኪያ ፀጋዬ፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሚሰራው ዶ/ር ኤፍሬም ተክሌ፣ በአፍሪካና በተለይም በምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀውና በወቅቱ “አፍሮ ፍላግ” የተሰኘውን የወጣቶች መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በመምራት ላይ የነበረው ኢዮብ ባልቻ፣ በፈረንሳይ ፓሪስ በአካባቢ ጥበቃ “ሞዴል ወጣት” ተብሎ የተሸለመውና በአሁኑ ሰዓት በዓለም የሙቀት መጠን መጨመር ዙሪያ እየሰራ የሚገኘው አለማየሁ አካሉ (ሶረኔ)፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተርሷንና ከቤልጂየም ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ ዲግሪዋን ያገኘቺው ሶፊያ ዓሊ፣ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቶ ከማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ማስተርሱን ያገኘውና በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ የሰላምና ልማት ዓለም አቀፍ ተቋም ባልደረባ የሆነው  ይነበብ ንጋቱ ---- ይገኙበታል፡፡
ከዚያ ስልጠና በኋላ አብዛኞቻችን ስለአገራችን በተለየ መልኩ ማሰብ ጀመርን፡፡ የእኛ ተሳትፎ እስካልታከለበት ድረስ አገር ወደ የትም ማደግ እንደማትችል ገባን፡፡ የዘር፣ የቀለም፣ የጎሳ ወዘተ ልዩነት ሳናደርግ በአገር ጉዳይ ሁላችንም ተገቢውን ውይይትና ክርክር በማድረግ፣ ለአገር ይበጃል ያልነውን ለመንግስታችንና ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለማድረስ የየበኩላችንን ጥረት ማድረግ ቀጠልን፡፡
በጋዜጦች፣ በመፅሄቶች፣ በተለያዩ ስልጠናዎች፣ በትምህርት ቤቶችና ከትምህርት ቤቶች ውጪ በተመሰረቱ የወጣት ክበባት፣ ማህበራትና ድርጅቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በሙያ ማህበራትና በመሳሰሉት ውስጥ ንቁ ተሳታፊዎች በመሆን “እኛም ስለአገራችን ያገባናል! “ አልን። ከስልጠናው ተሳታፊዎች ውስጥ እንደነ ስዩም ቲቶና ተክለሚካኤል (ቲ.ማይክ) የመሳሰሉ ሃቀኛ  የኢህአዴግ ደጋፊዎች ቢኖሩም ሁላችንም በዕውነተኛ ወዳጅነት ውይይታችንን በነፃነት ስናካሂድ ቆይተናል፡፡  
ማንም ማንንም አይፈርጅም፤ ማንም የማንንም ሃሳብ እንጂ ማንነት አያጣጥልም፡፡ ማንም በማንም ተፅዕኖ ስር አይወድቅም፡፡ ሁላችንም ከዚያ ስልጠና በተማርነው ፅኑ ስነ-ስርዓት መሰረት፣ ለክርክርና ለውይይት ደንብና ስርዓት ተገዢዎች ነበርን፡፡
እኔ በወቅቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት፣ የህፃናትና የወጣቶች ፕሮግራም አዘጋጅ ስለነበርኩ ከሁሉም ተሳታፊዎች ጋር በቀላሉ ለመግባባት አልቸገረኝም፡፡ ታዲያ በእኔ ግምት በዕድሜም ሆነ በትምህርት ደረጃ እንደዚሁም በልምድም ቢሆን ከሁላችንም የምታንሰው ማህሌት ፋንታሁን (ማፊ) ነበረች፡፡
የስልጠናችን ትኩረት
“Debate to Action!” በይበልጥ ያተኮረው በዓለምና በተለይም በአፍሪካ አገራት የዕድገት ሞዴሎች፣ በምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች፣ በአመራር ጥበብና በአጠቃላይ በልማት ዙሪያ የወጣቶች ሚና ምን መሆን አለበት በሚሉት ጉዳዮች ላይ ነበር። የድህነታችን መንስኤዎች፣ በድህነታችን ሳቢያ እየኖርነው ስላለው አሳፋሪ የኑሮ ደረጃ፣ ድህነትን ስለሚቀንሱልን የልማት ሞዴሎች፣ ስለአደጉ አገራት ተመክሮ፣ ስለ አስተሳሰባችን፣ ስለጊዜ አጠቃቀማችን ወዘተ---የስልጠናችን ዋና ዋና ትኩረቶች ነበሩ። ስልጠናውን ከሰጡን ባለሙያዎች መካከል፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የመንግስት ቃል አቀባይ፣ በኋላም የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ሮ ሠሎሜ ታደሰ እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡
ከብዙ ጊዜ በኋላ ማፊን አግኝቼ ሳወራት፣ በፖለቲካም ሆነ በአጠቃላይ በልማት /ዴቨሎፕመንት/ ዙሪያ ያላት አስተሳሰብ በእጅጉ አደገብኝ፡፡ ስልጠናው መነሻ ሆኗት ከዚያ በኋላ በርካታ መፃህፍትን እንዳነበበች፣ ከባለሙያዎች ጋር እንደምትወያይ፣ በተለያዩ አዕምሮን የሚገነቡ ስልጠናዎች ላይ በተደጋጋሚ እንደምትሳተፍ ገመትኩ፡፡ ሆኖም ግን በእነዚያ ቅልጥ ያሉ የፖለቲካና የአገር ወሬ ውስጥ ገብተን ውይይት ባደረግንባቸው ወቅቶች አንድም ቀን ፅንፍ ይዛ፣ ልክ አልፋ ስትከራከርና ስታወራ ሰምቻት አላውቅም፡፡
የፌስ ቡክዋ ማፊ
በእርግጥ እንደማናችንም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ፣ ማፊም ያየቻቸውንና ስህተት ነው ብላ የምታስባቸውን ፖለቲካዊ ትዝብቶች ፌስቡክ ላይ በመለጠፍና በማካፈል ትታወቃለች፡፡ ሆኖም ግን እኔ እስከማውቀው ድረስ አንድም ፅሁፏም ሆነ የለጠፈቻቸው ስዕሎች ፅንፈኝነትን ሲያሳዩ፣ አክራሪነትን ሲያበረታቱ፣ ሽብርተኝነትን ሲሰብኩ አላስተዋልኩም፡፡ ይልቁኑም በመንግስትም ሆነ በተቃዋሚዎች ዘንድ ስለሚታዩ ክፍተቶች በመጠቆም፣ ለአገር ጠቃሚ የሆነ አስተዋፅኦ ማድረጓን ብቻ ነው የማስታውሰው፡፡
ግጥም ወዳጅዋ ማፊ
“ግጥምን በጃዝ” በሚል ቀደም ብሎ በዋቢሸበሌ፣ ከዚያም በራስ ሆቴል ውስጥ በሚካሄደው ፕሮግራም ላይ ማፊን የፈለጋት አያጣትም፡፡ ግጥም ታደንቃለች፡፡ ነፍሷን ለነካላት ግጥም ከመቀመጫዋ ተነስታ በፉጨት በማደበላለቅ ሞራል ትሰጣለች። እንዳስተዋልኳት የእርሷ የነፍስ ግጥሞች በአገር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ ስሜታቸው በልዩ ሁኔታ ይገቡዋታል፡፡ ማፊ ግን ስትገጥምም ሆነ ግጥምን ለሽብር ዓላማ ስታውል አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡
ሰራተኛዋና ግድ የለሽዋ ማፊ
ትዝ እንደሚለኝ ከሆነ ማፊ ስራ የጀመረችው የርቀት ትምህርት በሚሰጥ ተቋም ውስጥ ሲሆን እስከታሰረችበት ጊዜ  ድረስ በጤና ጥበቃ ሚ/ር ውስጥ ትሰራ እንደነበር ነው የማውቀው፡፡ ማፊ ፀጉሩዋን እንደ ሴት በወጉ ለመሰራት፣ በአልባሳትና በኮስሞቲክስ ለመዘነጥ ምንም ግድ የሌላት እንደሆነች ታዝቤአለሁ፡፡ ሁልጊዜ ሳገኛት ጅንስ ሱሪና ቲ-ሸርት አድርጋ ከኋላዋ ቦርሳ ታዝላለች፡፡
የኢትዮጵያና ናይጄሪያ ጨዋታ ዋዜማ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከናይጄሪያ ጋር ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርግበት ወቅት ላይ ነው። በዋዜማው ማታ ካዛንችስ በሚገኘው “በዕምነት ሬስቶራንት” ከማፊ ጋር ያሳለፍነው ጊዜ አይረሳኝም። አብዛኞቻችን በዚያ ስልጠና ላይ ተሳታፊ የነበርን ጓደኛሞች፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለብሰን ከማፊ ጋር የመጨረሻውን እራት ተቋድሰናል፡፡ ያን ቀን ስለአገራችን በርካታ ጉዳዮችን አንስተን ያወራን ቢሆንም ማናችንም ፅንፍ ይዘን አልተከራከርንም፤ ከማናችንም ሽብርና ሽብርተኝነት የሚል ፅንሰ-ሃሳብ ሲንፀባረቅ አልተሰማም፤ ማናችንም ማንንም በጠላትነት አልፈረጅንም፡፡
በዚያ አስደሳችና የማይረሳ ምሽት ማፊ አንድ ነገር አስታወሰች፡፡ ስለ ስልጠናችን፡፡ ለእርሷ የፖለቲካ ህይወት መጀመሪያ፣ ያ…የዓለም ባንክና የብሪቲሽ ካውንስል ስልጠና መሆኑን ተናገረች። ቀደም ብሎ  ምንም የልማትም ሆነ የፖለቲካ ግንዛቤ እንዳልነበራት መሰከረች፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የሰማሁት መታሰሯንና የማታ ማታም በሽብርተኝነት ክስ እንደተመሰረተባት ነው፡፡
የሽብር ትርጉሙ ግራ አጋባኝ
ማፊ እስር ቤት ገባች ተብሎ የተነገረኝ ቀን፣ የሽብርና የሽብርተኛ ትርጉሙ ከዕለት ወደ ዕለት እየቀለለና ወደ እያንዳንዳችን ደጃፍ እየመጣ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡ በተለይም ደግሞ ጋዜጠኞችና ጦማሪያኑ በሽብርተኝነት ክስ እንደተመሰረተባቸው ስሰማ የሽብር ትርጉሙ ግራ አጋብቶኛል፡፡ ማፊ ሽብርተኛ ከሆነች ሽብር ቀላልና ብዙም የሚያስፈራ ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በማፊ ዕድሜና ተመክሮ የሚቀነባበር ሽብር የትም የሚያደርስ አይመስለኝም፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ ማፊ ጮክ ብላ ስለ ኢትዮጵያ ከመዘመር ውጪ አንድም ቀን የሽብርተኝነት ባህሪም ሆነ አስተሳሰብ ስታራምድ አልገጠመኝም፡፡ አራምዳለች ከተባለም የፍርድ ውሳኔውን ስሰማ ምን እንደሚሰማኝ አላውቅም፡፡
የማፊ ታናናሾችና ፖለቲካ
እንኳን የወጣት ሴቶችና የወጣት ወንዶችም ፖለቲካዊ ተሳትፎ እየቀጨጨና እየሞተ ባለበት በዚህ ወቅት (ፖለቲካ በራሱ ከሴቶች ለወንዶች የሚቀርብ ስለሚመስለኝ) እንደ ማፊ ዓይነቶቹ ልዩ የአገር ፍቅር ያላቸው፣ ፖለቲካን ለማወቅና ለመማር ብሎም በንቃት ለመሳተፍ የሚፈልጉ ወጣቶች መታሰር ጉዳቱ ከባድ ነው፡፡ የማፊ ታናናሾች ተመክሮዋን በመውሰድ የፖለቲካን መዝሙር በርቀት ብቻ መዘመራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እሱም ከደፈሩ ነው፡፡ ይህ ታላቅ የአገር ኪሳራ ነው፡፡ አገር መልሳ ልትከፍለው የማትችለው ታላቅ ኪሳራ! ከመስመር የወጣ አካሄድ አላት ተብሎ ቢታመን እንኳን መንግስት ሆደ ሰፊ ሆኖ በምክር ብቻ ሊመልሳት ይገባ ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ እቺን አንድ ፍሬ ወጣት “ሽብርተኛ” ብሎ መሰየሙ ትንሽ ነፍሳት ላይ  መድፍ እንደመተኮስ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መንግስትን  ትዝብት ላይ ይጥለዋል፡፡
እኔ በብዙ አጋጣሚዎች ስለማውቃት ማፊ እንዲህ ፃፍኩ እንጂ ስለተቀሩትም ታሳሪዎች የሚያውቋቸው ሰዎች ብዙ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ወጣቶች በተለይም ደግሞ ወጣት ሴቶች እንዲህ ከጅምራቸው በእስርና እንግልት ተደናግጠው ከፖለቲካው መድረክ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከመሰወራቸው በፊት የአገር ሽማግሌዎች፣ ልባም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ራዕይ ያላቸው የመንግስት ባለስልጣናት (ካሉ) እና መላው ዓለም ሊረባረቡላቸው ይገባል፡፡
ባለ ድብቅ ልቧ ማፊ?
ምናልባት መንግስት እንደሚለው፤ማፊ ከእኛ ከወዳጆቿ ተደብቃ ልቧን ለሽብርተኞች ቡድን ሰጥታ ይሆን?   ይህ ለእኔ ዝሆን በመርፌ ቀዳዳ አለፈች የማለት ያህል ቢሆንም መንግስት ግን “መረጃ አለኝ፤ ደርሼብሻለሁ” ብሏታል፡፡ እናም ባሳለፍናቸው በእነዚያ ተወዳጅና ተናፋቂ ጊዜያት ስም፣ ማፊን ከእንዲህ ዓይነቱ ክስ እንዲሰውራት ወደ ፈጣሪዬ ተማፅኖዬን  አቀርባለሁ፡፡

Read 5681 times