Saturday, 09 August 2014 11:24

“የእኔ ነው!” አለማለት

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(3 votes)

            እኛን በተሻለ ከሚገልጹን ነገሮች አንዱ የእኛ የሆነን ነገር “የእኔ ነው!” ማለት አለመቻላችን ነው፤ ብል “ተሳስተሀል” የሚለኝ የዋህ እንደማይኖር እርግጠኛ ነኝ፡፡ አልተሳሳትኩም! “የእኔ ነው!” አንልም፡፡ ይህ ህመም ምን ያህል እንደተጣባን ልብ እንድንል፣ እስቲ ከምንፈጽማቸው ሆኖም ልብ ከማንላቸው አዘቦታዊ ጉዳዮች አንዱን አንስተን እንጀምር፡፡
እነሆ “የእለት ጉርሳችንን እና የዓመት ልብሳችንን” ለማግኘት ጎህ ቀዶ ከቤት እየወጣን ነው፡፡ የመንግስት ሚዲያዎች ያለመታከት “ልማታዊ መንግስት!” ነው፤ የሚሉን ኢህአዴግ፤ ወደንም በግድም በወሰደብን ብር “ሰርቼላችኋለሁ” ባለን “ኮብልስቶን” በሉት የድንጋይ ንጣፍ ላይ እያዘገምን ነው፡፡ አንዲት ሴት (ወንድም ሊሆን ይችላል) የግቢዋን በር ከፍታ በመውጣት በሳፋ የያዘችውን “እጣቢ” (ልብ በሉ “እጣቢ” ያልኩት ጨዋነት ይዞኝ ነው፤ ሳፋው የያዘውን ቃሉ ላይገልጸው ይችላል) ከፊት ለፊታችን መሀል መንገዱ ላይ ደፋችው፡፡ ይህንን ያህል ጥፋት ፈጽማ ምንም እንዳላደረገች ሁሉ ወደ መጣችበት ተረጋግታ እየተመለሰች ነው፡፡ እንደውም እጣቢውን ከቤቷ በማውጣቷ ብቻ ቀለል ያላት ትመስላለች፡፡
እኛም ዝም ብለን መንገዳችንን ቀጥለናል፡፡ እርግጥ ነው ልብሳችን ላይና የወለወልነው ጫማችን ላይ እንዳይረጭ ፈንጠር ብለን ቆመን ርጭቱን እናመልጣለን። አለፍ ካለም “እንዴት መንገድ ላይ ትደፋለች?!” ብለን በውስጣችን አጉረምርመን ይሆናል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ልጅቱን ለመገሰጽ፣ አቁሞ ስህተቷን ለማስረዳት… ፍላጎቱም ሆነ ተነሳሽነቱ የለንም፡፡ ለምን መስላችሁ? “የእኔ ነው!” ስለማንል! ግን እኮ መንገዱ የተሰራው እኛ ላባችንን አፍሰን ባገኘነው ገንዘብ ነው፡፡ በእርዳታ ነው ብትሉኝ እንኳን መንግስት ለጋሾችን የለመነው በእኛ ስም ነው፡፡
በእውነቱ የ“እኔ ነው!” አለማለት ያልተጣባው ሰው ማግኘት ይከብዳል፡፡ አንድ ዜጋ ብዙ ሚሊዮን ብሮች ፈሰውበት የተሰራውን መንገድ፣ የፌሮ ብረትና ብሎን ነቅሎ የሚወስደው መሰረተ ልማቱን “የእኔ ነው!” ስለማይለው ነው፡፡ እሱ በከፈለው ግብር በተሰሩ የውሃ መተላለፊያ መስመሮች ላይ ቆሻሻ እየጣለ መስመሩን የሚዘጋው፣ ራሱ የከፈለበትን ንብረት “የእኔ ነው!” ስለማይለው ነው፡፡
ተማሪዎች መምህሩ ከክፍል ቢቀር ወይንም ተገኝቶ በአልባሌ ነገር ክፍለ ጊዜያቸውን ቢያጠፋ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ “ክፍለ ጊዜው የእኔ ነው፤ ከፍየበታለሁ። ሰዓቱ ሰው የምሆንበት የእኔ እድሜ ነው!” አይሉም። ወደ አገልግሎት መስጫ ማዕከሎች ጎራ በሉ፡፡ ያለ ተገቢ ምክንያት የሚያጉላላውን የማዕከሉን ሰራተኛ “እባክህን ጊዜዬን አትግደልብኝ፤ አንተ እዚህ ያለኸው እኔን ለማገልገል ነው፡፡ ይህ አገልግሎት ግብር የከፈልኩበት የእኔ ነው!” የሚል ሰው አታገኙም፡፡
ግን ብታምኑም ባታምኑም እኛ “የእኔ ነው!” ማለት ስላቃተን እንጂ መንግስት እንኳን የእኛን ሰላምና ነጻነት እንዲያስከብርልን፣ እንዲያገለግለንም… ደሞዝ የምንከፍለው ሠራተኛችን ነው፡፡  ይህንን ግን ማሰብ አንችልም፤ ወይንም አንፈልግም፡፡ ለምን? መልሱ ከባድ አይደለም፡፡ ስለማይመስለን! እንደውም ይህንን የሚነግረንን ሰው፣ ጤንነቱን ሁሉ ልንጠራጠር እንችላለን። ለነገሩ “የእኛ ነው!” ማለት እንዳንችል መንግስታት፣ ባህላችን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ “የእኛ ነው!” የሚል ህዝብ ለመሪዎቹ እና ለጥቅመኞች ፈተና ነው፡፡ ስለሆነም እንዳይጠይቅ ፍርሀት ውስጥ ከተውታል፤ ልብ እንዳይል ማስተዋሉን የሚሻሙ ብዙ የቤት ሥራዎችና ሀሳብ ተጭኖበታል፡፡  
እውነት እውነት እላችኋላሁ! “የእኔ ነው!” አለማለታችን ለ“ጥቅመኞች” ተመችቶአል፡፡ “የእኔ ነው!” የማይል ህዝብ ለጭቆና እና ለብዝበዛ ምቹ ነው፡፡ ማንም እንደፈለገው ይሆንበታል፡፡ ከከፍተኛ የመንግስት ሃላፊ እስከ ወረዳ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ. . . ማንም እንደፈለገው ያደርገዋል፡፡ ማንም በንብረቱና በላቡ ላይ ያሻውን ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም “የእኔ ነው” የማይል ህዝብ አይጠይቅም፡፡ የማይጠይቅ ህዝብ ደግሞ የኖረ ቢመስለውም የለም!!
አስገራሚው ነገር ደግሞ “የእኔ ነው!” የማንለው ከሰዎች ጋር የምንጋራውን የጋራ ንብረት ነው፡፡ የግላችን (የብቻችን) የሆነውን ንብረት አናስነካም። በፍጹም!! ጉዳዩን ልብ እንድንለው በመነሻችን ወዳነሳነው ሀሳብ እንመለስ፡፡ ያቺ ሴት ከቤቷ ያወጣችውን “እጣቢ” የደፋችው ግቢያችን ውስጥ ቢሆን መልሳችን ምን ይሆን ነበር? እርግጠኛ ነኝ ዝምታና ማጉረምረም ብቻ አይሆንም፡፡ ለምን? በአጥር የከለልነው ግቢያችን ስለሆነ፡፡ ለዚህ እኮ ነው ያቺ ሴትም ቤቷ ውስጥ እንዳይቆይ የጠላችውን ቆሻሻ አውጥታ፣ የጋራ ንብረቷ የሆነው መንገድ ላይ የደፋችው፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ግን አራስ ነብር የምንሆንለት የግል ንብረታችንና ከሌሎች ጋር የምንጋራው የጋራ ንብረታችን የማይለያዩ መሆናቸውን ልብ አለማለታችን ነው፡፡
አሁንም በመነሻችን ያነሳነውን ሀሳብ ይዘን እንዝለቅ፡፡ ሴቲቱ እጣቢውን ከቤቷ አውጥታ የደፋችው ገንዘቧን አውጥታ ባሰራችው መንገድ ላይ ነው፡፡ አስተውሉ! ገንዘቡ የግል ንብረቷ ነው፡፡ ደግሞ እዚያው መንገድ ላይ ልጇ ሲጫወት ይታመማል፡፡ ልብ በሉ! ልጁ የእሷ ነው፡፡ እናም ለልጇ ማሳከሚያ ምንአልባትም ለመንገዱ ማሰሪያ ካዋጣችው የበዛ ገንዘብ ታወጣለች፡፡ ገንዘቡ እሷ ጉልበቷን አድክማ፣ ላቧን ሰጥታ… ያገኘችው የግል ንብረቷ ነው፡፡ የግል በምንለውና የጋራ በምንለው ንብረት መካከል ያለው አንድነት ይሄ ነው፡፡ ሁለቱም ውስጥ የእኛ ላብና ገንዘብ አለ፡፡ የሁለቱም ባለቤት እኛ ነን፡፡ ሁለቱም እኩል “የእኔ ነው!” ልንላቸው የሚገቡ የራሳችን ንብረቶች ናቸው፡፡ ሆኖም ይህንን ልብ አንልም፡፡ ታክሲ ውስጥ ረዳቱ አስር ሳንቲማችንን ያለ አግባብ እንዲወስድብን አንፈቅድም፡፡ “የእኔ ነው!” እንላለን። ለምን? አስር ሳንቲሙ የግላችን ስለሆነ፡፡ ሆኖም ታክሲው አቆራርጦ ሲጭነን አንናገርም፡፡ ለምን? የተነጠቅነው አገልግሎት ከሌሎች ጋር የምንጋራው ስለሆነ፡፡ ሌሎች ማሳያዎችን ላንሳ፡፡ ቤታችን ሆነን ጉድ ጉድ እያልን ነው፡፡ ለሥራችን ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይልን እየተገለገልን ነው፡፡ ሥራችንን ዳር ሳናደርስ ድንገት መብራቱ እልም አለ፡፡ እንናደዳለን፡፡ እመኑኝ ግን ፈጥነን የምንጠይቀው “መብራቱ የጠፋው እኛ ጋ ብቻ ነው ወይንስ ጎረቤትም ጠፍቶአል?” ብለን ነው፡፡ መልሱ “ጎረቤትም የለም፤ ሰፈሩ እንዳለ ነው የጠፋው” ከሆነ ምንም አናደርግም፡፡ እያጉረመረምን ገብተን እንቀመጣለን፡፡ መብራቱ የጠፋው እኛ ቤት ብቻ ከሆነስ? ምን ያህል እንጠይቃለን? እንሯሯጣለን? መፍትሔ እንሻለን?... ልምዶቻችንን እናስታውስ፡፡ ውሃ፣ ኔትወርክ፣ አገልግሎት፣ ፍትህ… የመሳሰሉትን ብቻችንን ስናጣ አራስ ነብር ነን! ከሌሎች ጋር ስንነፈግ ግን የተነጠቅን አይመስለንም። እንዲህ ነን! ግለኞች ነን ልበል?
“የእኔ ነው!” አለማለት ልብ የማንለው፣ ልብም ብንለው የማንደፍረው ችግራችን ነው፡፡ ለዘመናት አብሮን የኖረ ችግራችን! “የእኔ ነው!” የማይል ህዝብ ያላት ሀገር፣ ባለችበት መርገጧ ብቻ ሳይሆን ቁልቁል መሽቀንጠሯ የግድ ነው፡፡ “የእኔ ነው!” የማይል ህዝብ የሚኖርባት ሀገር፣ ጠያቂና ተቆርቋሪ እንደሌላት ምስኪን እናት ናት፡፡ ደክማ ብታሳድግም ግድ የለሽና ግለኛ ልጆችን ያፈራች እናት፡፡
“የእኔ ነው!” ማለት የሌሎችን መሻት ሳይሆን የራስን ማስከበር ነው!! ያኔ ጨቋኞችንና አምባገነኖችን ማስቆም፣ ጥቅመኞችንና አስመሳዮችን መግታት… እንደ ሀገርም በሁሉም መስክ የምር ወደፊት ፈቀቅ፣ ወደ ማማው ከፍ ማለት እንችላለን፡፡ በእርግጠኝነት!! ቸር ይግጠመን!

Read 4429 times