Saturday, 09 August 2014 12:00

የተራራ ሩጫ በኢትዮጵያ ሊጀመር ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

               በአቢያታና ሻላ ሃይቆች ተራራማ ስፍራዎች ዙሪያልዩ  የሩጫ ውድድር መዘጋጀቱን አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም አስታወቀ፡፡  
የተራራ  ሩጫው ነሐሴ 11  በአብያታና ሻላ ሃይቆች ዙሪያ ሲካሄድ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው እንደሚሆን የውድድሩ አዘጋጆች ገልፀዋል፡፡ ኢትዮ ትሬል 2014 (Ethiotrail) በሚል በሦስት የውድድር መደቦች ስያሜ የሚካሄደው የተራራ ሩጫው የ42 ኪ.ሜ፣ የ21 ኪ.ሜ የ12 ኪ.ሜ ውድድሮች ይኖሩታል፡፡ አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም የተራራ ሩጫው ከዚህ በፊት በጐዳና እና በትራክ ውድድሮች ተወስኖ ለነበረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አንድ ተጨማሪ የውድድር ዕድል  ይፈጥራል፡
በተራራ  ሩጫው በ42 ኪ.ሜ፣ በ21 ኪ.ሜ እና በ12 ኪሎሜትር ውድድሮች ከ250 በላይ ተሳታፊዎች ይኖራሉ፡፡ 165 ያህሉ ከ10 አገራት (ከአሜሪካ፣ ቺሊ፣ ፖላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ካታሎና) የመጡ እንደሆኑ አዘጋጆች ገልፀው ፤ እነዚህ ስፖርተኞች ተሳትፎ እንዲያደርጉ አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም ለ2 ወራት ለመላው አውሮፓ በመዘዋወር ቅስቀሳ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
አራት አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሐናት ለውድድሩ ሽፋን የሚሰጡት ሲሆን ሱፕር ስፖርት እና ታዋቂው የሯጮች መጽሔት ራነርስ ዎርልድ ይገኙበታል፡፡
በዚህ የተራራ ሩጫ ላይ የሚሳተፉና የሚያሸንፉ አትሌቶች በተለይ  ከ1-5 ደረጃ የሚያገኙት በዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሳተፉ እቅድ መኖሩንም አውቋል፡፡
በውድድሩ አዘጋጅነት ከሠራው አይአርአይ ጋር የምስራቅ አፍሪካ የአካባቢ ጥበቃ ኔትዎርክ (HORECK) እና የብሔራዊ ፓርኮች ጥበቃና አስተዳደር የሆነው የመንግስት ተቋምና የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ በአጋርነት ተሳትፈዋል፡፡  ውድድሩ ለአትሌቶች ከሚፈጥረው ተጨማሪ የውድድር እድል ባሻገር ለዘላቂ ልማት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የሚደግፍና የቱሪዝም አገልግሎትን ለማስተዋወቅ ምቹ መድረክ ነው ተብሏል፡፡
የብሔራዊ ፓርኮች ጥበቃና አስተዳደር ኃላፊ የሆኑት አቶ ኩመራ ዋቅጅራ የተራራ ሩጫው በአቢያታ እና ሻላ ሃይቆች ዙርያ ለሚገኘው ብሄራዊ ፓርክ ህልውና የሚያግዝ ብለውታል፡፡ ብዙዎቹ የአገሪቱ ብሄራዊ ፓርኮች በከፍተኛ ተራራማ ስፍራዎች ላይ መገኘታቸው ተመሳሳይ የስፖርት ውድድሮች በብዛት ለማካሄድ ይጠቅማል ያሉት አቶ ኩመራ፤ ለአገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ሚና የሚጫወት ጥሩ  ውድድር ነው ብለዋል፡፡
የተራራ ሩጫውን ለማዘጋጀት ለ1 ዓመት ተኩል እንቅስቃሴ መደረጉን የገለፁት አዘጋጆቹ ዓለምአቀፍ ደረጃ ማሟላቱን ለመፈተሽ ከስፔን አገር ለውድድሩ ዓይነት ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች 3 ጊዜ ተመላልሰው ጥናት አድርገዋል ብለዋል፡፡

Read 2473 times