Saturday, 16 August 2014 12:29

ኒሂሊዝም- በስብሐት “ኮተት”

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(1 Vote)

   “ኒሂሊዝም” (Nihilism) በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በምድረ አውሮፓ የተነሳ ርዕዮት ሲሆን ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለገለው ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ሄኔሪክ ጃኮቢ (1743-1819) ነው፡፡ ኒሂሊዝም እንደ የሚገባበት አውድ እና ዲሲፕሊን የተለያዩ መልኮች ቢኖሩትም አስኳሉ “ክህደት” ነው፡፡ ሃይማኖት ቢሉ እምነት፣ ባህል ቢሉ እውቀት፣ ህግ ቢሉ መተዳደሪያ ደንብ፣ ስነ ምግባር ቢሉ ስሜት… ከነጓዛቸው በኒሂሊዝም ይገፋሉ፤ ይካዳሉም፡፡ እውቁ አሜሪካዊው ፈላስፋና ደራሲ ኮርኔል ዌስት ኒሂሊዝምን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “Nihilism is a natural consequence of a culture (or civilization) ruled and regulated by categories that mask manipulation, mastery and domination of peoples and nature.”  
የሰው ልጅ በማህበር ሲኖር ህልውናውን የሚያስጠብቅባቸው፣ ባህሉን የሚያስከብርባቸውና ለትውልድ የሚያስተላልፍባቸው፣ እውቀቱን የሚሰፍርባቸው፣ ስሜቱን የሚገልጽባቸውና ስነ ምግባሩን የሚተረጉምባቸው እሴቶች አሉት፡፡ እነዚህ እሴቶች የሰው ልጅ ራሱ ፈጥሮአቸው በብዙም ሆነ በጥቂቱ ተገዝቶ የሚኖርባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ አንድ ማህበረሰብ እንደ ማህበር ራሱን የሚገልጥበትና ህላዌውን የሚያዘልቅበት ባህል አለው፡፡ ባህል ለተፈጥሮአዊ ጉዳዮች የሚሰጥ “ምላሽ” (expression) ነው፡፡ እምነት፣ ሃይማኖት፣ እውቀት፣ ሞራል፣ ልማድ፣ ህግ/መተዳደሪያ ደንብ፣ ኪነ-ጥበብ፣ ምርትና ማምረቻ መሳሪያ፣ አልባሳት፣ ወዘተ. . . የባህል ዘርፎች ናቸው፡፡ ተፈጥሮአዊ ባለመሆኑ አይነቱ ይለያይ እንጂ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ባህል አለ። ማህበረሰቡ ለዘርፎቹ ያለው አመለካከት ቢለያይም ለእሴቶቹ እውቅናን ይሰጣል፡፡ አስፈላጊነታቸውንም ያምናል፡፡
ኒሂሊዝም እነዚህን ሰዋዊ እሴቶች ይክዳል፤ አላስፈላጊነታቸውንም ይሰብካል፡፡ መሰረት የሌላቸውና አንዳችም ጥቅም የማይሰጡ መሆናቸውን በመግለጽ በሰው ልጅ ህላዌ ውስጥ ያላቸውን ህልውና ይገዳደራል። በዚህ ጽሑፍ ኒሂሊዝም፣ የስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ድርሰት በሆነው “ኮተት” ላይ እንደምን አቢይ ጭብጥ ሆኖ እንደቀረበ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ አስረጂዬም ድርሰቱ የማህበረሰብን የተከበሩ “ነባር እሴቶችን እና እሴቶቹ የተመሰረቱባቸውን የሃይማኖት፣ የፖለቲካ እና የስነ ምግባር መርሆዎች የሚቀናቀን”፣ የሚክድና የሚኮንን መሆኑ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ስነ ፅሑፍ ውስጥ አቢይ ጭብጡን ኒሂሊዝም ያደረገ ሌላ ድርሰት አላጋጠመኝም። የማህበረሰቡ እሴቶችና የእሴቶቹ መርሆዎች የሚያራምዱትን አንዳንድ አስተሳሰቦች በመቃወም (በተለይ ሊሻሻሉ ይገባል በማለት) በሳሉአቸው ገፀባህሪያት አማካይነት የሚሞግቱ በርካታ ድርሰቶች አሉ፡፡ እንደ አስረጂም “ፍቅር እስከ መቃብር”- በጉዱ ካሳ፣ “ሀዲስ”- በሀዲስ፣ “አርአያ”- በአርአያ እና “ሚክሎል”- በገልገሎ አማካይነት ያቀነቀናቸውን የለውጥ አስተሳሰቦች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሆኖም በእነዚህ ድርሰቶች የተነሱትና በእሴቶቹ ላይ የተደረጉት ትችቶች፣ እሴቶቹ እና የእሴቶቹ መሰረቶችን መኖርና አስፈላጊነት የሚቃወሙና የሚክዱ ሳይሆኑ እሴቶቹ እንዲታረሙና እንዲሻሻሉ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በመሆኑም የስብሐት “ኮተት” ኒሂሊዚምን በማቀንቀን፣ የሰው ልጅ ነባር እሴቶችና የእሴቶቹን መሰረቶች ህልውና በመቃወምና በመተቸት፣ አላስፈላጊነታቸውንም (“ኮተት” ናቸው በማለት) በመስበክ ብቸኛ የአማርኛ ልቦለድ ድርሰት ይመስለኛል፡፡ (ልብ በሉ ነው አላልኩም፡፡)
በአብዛኛው ማህበረሰብ ውስጥ (አይነቱና መጠኑ ይለያይ እንጂ) ልብስ ለሰው ልጅ መጠቀሚያው ነው፡፡ ራሱን ከብርድ እና ከፀሐይ ይከላከልበታል፤ ያጌጥበታል። የተለያዩ ማህበራዊ ክዋኔዎችንም ይከውንበታል፡፡ የሰው ልጅ ራሱን ከጠላት፣ አካሉን ከብርድ እና ከፀሐይ ለመከላከል፣ እየሰለጠነ ሲመጣም በምቾት ለመኖርና ለሌሎች ፋይዳዎች ሲል ጎጆ ይቀልሳል፡፡ እንደ ኑሮ አቅሙም የቤቱን ደረጃና ቁጥር ይወስናል፡፡ ይህ ጅማሬ ስልጣኔውን ተከትሎ አሁን ያለው የስነ- ህንፃ ጥበብ ደረጃ ላይ ደርሶአል፡፡ አይነቱና መጠኑ ይለያይ እንጂ የሰው ልጅ ውሎ መግቢያ ጎጆ አለው፡፡ እነዚህ እሴቶች አይነታቸውና መጠናቸው ከማህበረሰብ ማህበረሰብ ቢለያይም አይቀሬነታቸው አያጠያይቅም፡፡ የሰው ልጅ እንደ ግለሰብም ሆነ በማህበር አምኖ የተቀበላቸውና የሚጠብቃቸው፣ በጊዜ ሂደትም ስልጣኔውን ተከትሎ ያሻሻላቸውና የሚያሻሽላቸው እሴቶቹ ናቸው፡፡
በ“ኮተት” የእነዚህ እሴቶች አስፈላጊነት፣ ጠቃሚነትና የግድነት ይካዳል፡፡ አልባሳት፣ ቤቶች እና ቁሳቁስ/መገልገያ መሳሪያዎች በድርሰቱ ውስጥ አላስፈላጊ “ኮተቶች” ናቸው፡፡ የአቶ አልአዛር ውሻ ኮምቡጠር ኒሂሊዝምን የሚሰብክ/የሚያራምድ ገፀባህሪ ነው፡፡
“. . .የልብሳችሁ ብዛት! ሙታንታ- ካናቴራ- ሸሚዝ- ሹራብ- ኮት- ካፖርት- ባርኔጣ- ካልሲ. . . አልጋ ልብስ- ፎጣ! ኧረ ወዲያ! ኮተታም ዘር!. . .
. . .ደሞ የቤታችሁ ጣጣስ? ማድቤት- ምግብ ቤት- እንግዳ ቤት- ሽንት ቤት- እቃ ቤት- ወምበር- ጠረጴዛ- ሶፋ- ምንጣፍ- አልጋ- ቁምሳጥን- አግድም ሳጥን! ሌላ ኮተት ዝባዝንኪ ግሳንግስ!. . .”(166)
ሃይማኖት(Religion) ሰዋዊ እሴቶች ከሚመሰረቱባቸው መርሆዎች አንዱ ነው፡፡ በስሩም የሚደረጉ እና የማይደረጉ ተብለው የተቀመጡ በርካታ “ውሳኔዎችን” ይይዛል፡፡ ተከታዮቹም/ምዕመናኑም ለእነዚህ ስርዓቶች እንዲታመኑ የግድ ይላል፡፡ ሃይማኖት በሰው ልጅ እውቀት(intellectual)፣ ስሜት(emotion) እና ስነ ምግባር(moral) ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አለው። በመሆኑም ሰው ለሃይማኖቱ የሚሰጠው ቦታ እጅጉን ክቡር ምንአልባትም አይነኬ ነው፡፡ አንዱ የደስታ መግለጫ ሌላው የሀዘን ማሳያ ቢሆኑም ሠርግ እና ተዝካርም በማህበረሰብ ውስጥ ያላቸው ቦታ፣ ቅቡልነት እና ተፈጻሚነት (በተለይ በእኛ ሀገር) እጅጉን ትልቅ ነው፡፡
ህጎች/መተዳደሪያ ደንቦች(codes) የሰው ልጅ እንደግለሰብ ገደብ አልባ ፍላጎቱን(desire) የሚገራባቸው፤ እንደማህበርም እሴቶቹን የሚያስጠብቅባቸው “ገደቦች”(constraints) ናቸው፡፡ ህጎች ከሃይማኖት እና ከእምነት ቀኖናዎች መንጭተው፣ የሰው ልጅ ራሱን ስርዓት ያሲያዘባቸው ሲሆኑ በኋላም አሻሽሎ እና አዘምኖ  ዘመናዊውን ህግ የቀረጸባቸው ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ከንቁ አእምሮው(conscious mind) ይልቅ ኢ-ንቁ አእምሮው(unconscious mind) እጅጉን የሚገዛው እና የሚቆጣጠረው ፍጡር ነው፡፡ ስሜቱ፣ ፍላጎቱ እና ምኞቱ እጅጉን ገደብ አልባ ነው፡፡ ይህም መሰሎቹን እንዲጎዳ (ራሱንም ጭምር) ያደርገዋል፡፡ ይህንንም ለመከላከልና የሰው ልጅ ሰብአዊነቱን እንዲያስተውል ህግ/መተዳደሪያ ደንብን ፈጥሮአል፡፡ የ“ነጻነቱ”(mobility) እና “የገደቡ“(constraint) መጠን ይለያይ እንጂ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ህግ አለ፡፡ ያለ ህግ/መተዳደሪ ደንብ የሚኖር ማህበር የለም፡፡
ሃይማኖትም ሆነ እጅጉን ለሰው ልጅ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደማህበር አስፈላጊ የሆነው ህግ/መተዳደሪያ ደንብ በ“ኮተት” ይካዳል፡፡ ኮምቡጠር ሌሎች እሴቶች ላይ እና እሴቶቹ የተመሰረቱባቸው መርሆዎች ላይ የሚያደርገው ትችት፣ ሃይማኖት እና ህጎች/መተዳደሪያ ደንቦች ላይም በተመሳሳይ መልኩ በጉልህ ይታያል፡፡ ገፀባህሪው የሰው ልጅ ያለ ሰዋዊ እሴቶች መኖር ይችላል ብሎ ያምናል። ይህንንም ይሰብካል፡፡ አስተሳሰቡ ፍፁም ሊባል በሚችል ደረጃ ኒሂሊዝማዊ፣ ገፀባህሪውም ኒሂሊዝምን የሚያራምድ ኒሂሊስት ነው፡፡
“ኮተት” ኒሂሊዝምን ጭብጡ ያደረገ፣ ይህንንም በቅጡ ማሳካት የቻለ ድርሰት ነው፡፡ ለዚህም ደራሲው የተጠቀማቸው ሁለት ብልሀቶች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡ አንደኛው ደራሲው የሳላቸውን ሁለት ተቀናቃኝ ገፀባህሪያት (አቶ አልአዛር እና ኮምቡጠር) ተመጣጣኝ አቅም እንዳይኖራቸው ማድረጉ ነው፡፡ እሴቶቹን የሚቃወመው የኮምቡጠር አቅምና የሀሳብ ትጥቅ እሱን ከሚቃወሙት ከአቶ አልአዛር አቅም የላቀና የደረጀ ነው፡፡ በአንጻሩ ሀሳቡን የሚቀናቀኑት  አቶ አልአዛር ይህንን አስተሳሰብ የሚቃረኑ ቢመስሉም የቱም ጋ የኮምቡጠርን አስተሳሰብ የሚገዳደር ሀሳብ ሲሰነዝሩ አይስተዋልም፡፡ የሀሳብ ትጥቃቸው እጅግ ደካማ በመሆኑም ከማመናጨቅና ከመሳደብ ውጪ ለትችቱ ተፈታታኝ ምላሽ አይሰጡም፡፡ ይልቁንም ኮምቡጠር ብዙ እንዲናገር የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ደራሲው የኮምቡጠር ሀሳብ ሚዛን እንዲደፋና ተፅእኖ እንዲፈጥር ሲል የአቅም አለመመጣጠኑን ሆነ ብሎ በማድረግ በድርሰቱ ላይ የኒሂሊዝም ርዕዮት ጎልቶ እንዲወጣና እንዲያሸንፍ ያደረገ ይመስላል፡፡
ሁለተኛው ብልሀት ኒሂሊዝማዊ አስተሳሰብን የሚያራምደው ኮምቡጠር ውሻ ሆኖ መሳሉና እንዲሰክር መደረጉ ነው፡፡ ውሻ በመሆኑ የሰው ልጅ እሴቶች አይመለከቱትም፡፡ እሱ ውጪ ነው፡፡ ውጪ ያለ ደግሞ ይታዘባል፡፡ የታዘበ ደግሞ ትዝብቱን የሚናገርበት አጋጣሚ ይፈልጋል፡፡ ደራሲው ደግሞ አጋጣሚ ፈጥሮለታል፡፡ በአረቄ የራሰ ክትፎ አስኮምኩሞ “አስክሮታል”፡፡ የሰከረ ደግሞ የልቡን አይሸሽግም፤ ይናገራል፡፡ ይሉኝታ የለውም፤ አያመነታም፡፡ (“ሆድ ያባውን”… እንዲል የሀገሬ ሰው) ኮምቡጠርም ደራሲው የሰጠውን አቅምና አጋጣሚ በሚገባ ተጠቅሞ ኒሂሊዝምን ሰብኮአል፡፡ ሰውን “…ኮተታም ዘር!” እያለ፡፡
መልካም ሰንበት!!

Read 2023 times