Saturday, 23 August 2014 11:51

ማክሲም ጎርኪይ- “ሶሻሊስቱ ብዕረኛ”

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(3 votes)

           በአለማችን የስነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ከተነሱ ታላላቅ ደራሲያን መካከል “ፖለቲካ ምኔ ነው!” ብለው ጥግ የያዙ በርካታ ደራሲያን የመኖራቸውን ያህል በዘመናቸው የነበረውን የፖለቲካ ትኩሳት የድርሰቶቻቸውን ጭብጥ(theme) ያደረጉ፤ በዚህም ስለ ነጻነት፣ እኩልነት፣ የሰው ልጆች መብትና ሰብዕና… በብርቱ ያቀነቀኑ ደራሲያንም በየዘመኑ ተነስተዋል፡፡ እነዚህ ፀሐፍት አይበጅም ያሉትን ስርዓት በድርሰቶቻቸው በፅኑ ታግለዋል፡፡ ይጠቅማል ያሉትን ስርዓትም ብዕሮቻቸውን ቀስረው አገልግለዋል፡፡ በድርሰቶቻቸው የዘውዱን ስርዓት ከተቃወሙና የሶሻሊዝም ስርዓት እንዲመሰረትና እንዲያብብ በብርቱ ከታገሉ የአለማችን ታላላቅ ደራሲያን መካከል ለዛሬ የረጅምና አጫጭር ልቦለዶች ደራሲና  ፀሐፌ ተውኔት ስለነበረው ሩሲያዊው የብዕር ሰው ማክሲም ጎርኪይ (1868-1936) በጥቂቱ ለማለት ወደድኩ፡፡
ታላቁ የሩሲያ የሳይንስና የታሪካዊ ልቦለድ ደራሲ የነበረው አሌክሴይ ቶልስቶይ (1883-1945) ማክሲም ጎርኪይን “የክላሲካል እና የሶቭየት ስነ ፅሑፎችን የሚያገናኝ ሕያው ድልድይ” ይለዋል፡፡ ደራሲና ፖለቲከኛ የነበረው ጎርኪይ በሀገረ ሩሲያ ዛሬ ጎርኪይ ተብላ በምትጠራው የቀድሞዋ ኒዥኒኖብጎርድ ከተማ በ1968 ነው የተወለደው፡፡ እውነተኛ ስሙ “አሌክሴይ ማክሲሞቪች ፔሽኮቭ” ቢሆንም በመላው ዓለም የሚታወቀው ግን ማክሲም ጎርኪይ በሚለው የብዕር ስሙ ነው፡፡
ከዝቅተኛው ማህበረሰብ የተገኘውና ከልጅነት እስከ ጉልምስና ዘመኑ በከፍተኛ ችግር የተንገላታው ጎርኪይ እንደ አንዳንድ የአለማችን ታላላቅ ደራሲያን ቻርለስ ዲከንስ፣ ማርክ ትዌይን፣ አልቤርቶ ሞራሺያ እና ኤሜሊ ዞላ… መደበኛ ትምህርቱን እንኳን ማጠናቀቅ ያልቻለ ደራሲ ነው፡፡

ጐርኪይ ገና በአፍላ ዕድሜው በሀገሩ ህዝቦች ላይ ይመለከት የነበረው ድህነት እና ስቃይ እጅጉን ያሳስበው ነበር፡፡ የዚህም ተፅእኖ በወጣትነትና ጉልምስና ዘመኑ በጻፋቸው ድርሰቶቹ ላይ በጉልህ ይታያል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ወደ ስነ ጽሑፉ አለም ብቅ ያለው ጎርኪይ ተቀባይነትና ዝናን ለማትረፍ ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ስሙ በመላው ዓለም በአጭር ጊዜ ውስጥ ናኘ፡፡ ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ ጎርኪይ ይህን የሚያህል ዝና እና አድናቆትን የተጎናጸፈው ሊዮ ቶልስቶይንና አንቶን ቼኮቭን የመሳሰሉ ታላላቅ ደራሲያን በነበሩበት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
ጎርኪይ ገና ወደ ስነ ጽሑፉ መድረክ ብቅ ከማለቱ በድርሰቶቹ የዘውዱን አገዛዝ በይፋ መቃወምና ስለ ድሆች መታገል ጀመረ፡፡ በዚህም በቄሳራዊው መንግስት ጥርስ ውስጥ በመግባቱ በ1905 ተካሂዶ በነበረው የመጀመሪያው ህዝባዊ አመፅ ሙከራ ወቅት ተይዞ ታሰረ። ጎርኪይ ግን በዚህ አልተበገረም፡፡ ከእስር ከተለቀቀም በኋላ የዘውዱን አገዛዝ የሚቃወሙና “ሰፊውን ህዝብ” ለፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያነሳሱ ረጅምና አጭር ልቦለዶችን፣ እንዳሁም ተውኔቶችን ለህዝብ አቀረበ። በፖለቲካዊ ተግባሮቹና የዛሩ መንግስት ተቃዋሚ ከነበረው የቦልሸቪክ ፓርቲ ጋር በነበረው ግንኙነት ምክንያት በተደጋጋሚ ከመታሰሩም በላይ እስከ መጋዝም ደርሶ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ መንገላታት ግን የዘውዱን ስርዓት ከመቃወምና ሶሻሊዝምን ከማቀንቀን አላስቆመውም፡፡
ማክሲም ጎርኪይ ክላሲካል ለሆነው ለሩስያ “የስነ ጽሑፍ ማህበራዊ ወግ” ከፍተኛ ዋጋ ይሰጥ ነበር፡፡ እንደውም የአንጋፋዎቹ ደራሲያን የሊዮ ቶሊስቶይና አንቶን ቼኮቭ ውለታ እንዳለበት ይናገር ነበር፡፡ “በእነርሱ ስራዎች የስነ ጽሑፍን ጥበብ ብቻ ሳይሆን ሀገሬን ሩሲያንና ሩሲያውያንን እንዲሁም የሩሲያውያንን መንፈሳዊ አኗኗርና ስነ ልቡናዊ ምኞት ተገንዝቤአለሁ” ይላል፡፡
ማክሲም ጎርኪይ ታላቁ የሩሲያ የጥቅምት አብዮት ከመፈንዳቱ በፊት በድርሰቶቹ ለወዛደሩ ትግል መሳካትና ለድሆች ነጻነት ከፍተኛ ትግል ሲያደርግ የቆየውን ያህል ከአብዮቱም በኋላ አዲስና ተራማጅ ስነ ጽሑፍ ለመመስረት በፅኑ ታግሎአል፡፡ በዚህም በ1903 በዓለም እጅግ አድናቆትን ያተረፈለትን ልቦለዱን “Mother’s ጽፎአል፡፡ ጎርኪይ ይህን ልቦለድ የጻፈው በ1902 ሶርሞቮ ላይ በ“የወዝ አደሮች ቀን (May Day)” የተካሄደውን ሰልፍን መነሻ አድርጎ ነው፡፡ (ይህ መጽሐፍ በዘመነ ደርግ “እናት” በሚል ርዕስ በአማርኛ ቋንቋ ታትሞአል።) “Mother” በመጀመሪያ የታተመው በ1907 ሲሆን ወዲያውኑ በአለም ከፍተኛ ተቀባይነትን አገኘ። ይህንን የጎርኪይን ድርሰት የወቅቱ የሩሲያ አብዮት መሪ ሌኒን ሳይቀር “የጊዜው አስፈለጊ መጽሐፍ” በማለት አወድሶታል፡፡ ሩሲያዊው የስነ ጽሑፍ ፕሮፌሰር ቦሪስ ቡርሶቭም “የሩሲያ የኢንዱስትሪ ወዝ አደሮችን ቅድመ አብዮት እንግልት የሚያሳይ መስታወትና የዓለም ሰርቶ አደሮችን ለአመፅ፣ ለአርነት ትግል፣ ለሶሻሊዝም ምስረታ የሚቀሰቅስ ብርቱ ጥሪ ነው፡፡” ብሎታል፡፡
የጎርኪይ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በዚህ ልቦለዱ በጉልህ እንደተንጸባረቀ ይነገራል፡፡ የልቦለዱ ዋና ዋና ገፀባህሪያት የሆኑት “እናት”፣ ልጅዋ ፓቬልና ጓደኛው ኒሎቨና ታሪክ፣ ድርጊትና ምልልሶችም ይህንኑ የጎርኪይን ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብና ምኞት በቅጡ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ብዙዎች “የሶቪየት ስነ ጽሑፍ መስራች ነው፡፡” የሚሉት ማክሲም ጎርኪይ፤ ቀዳሚውን የሩሲያን የስነ ጽሑፍ ስልት ይከተል የነበረ ቢሆንም አዳዲስ ነገሮችን ካመጡ የሩሲያ ታላላቅ ደራሲያንም አንዱ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በብዙ ደራሲያን ስራ የበለጸገውን የሩሲያን ክላሲክ የስነ ጽሑፍ ባህል እንዲቀጥል በማድረግ አድሶና አሻሽሎ ለተተኪው አዲስ “ሶሻሊስት” ትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ጥረት አድርጎአል፡፡ ተሳክቶለታልም፡፡
የ1905ቱ የሩሲያ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከከሸፈ በኋላ በሀገሪቱ የነበረው ሁኔታ አመቺና አስተማማኝ ባለመሆኑ ጎርኪይ ሀገሩን ለቅቆ ለመሄድ ተገደደ፡፡ መኖሪያውንም ካፕሪ በተባለችው የኢጣሊያ ደሴት አድርጎ በስደት ከቆየ በኋላ፣ በ1913 በተደረገው የምህረት አዋጅ  ወደ ሀገሩ ተመልሶ ለቮልሼክ ፕሬስ ጽሑፎችን ይልክ ጀመር፡፡ ቆይቶም የራሱን መጽሔት ለማቋቋም በቃ፡፡
የጥቅምቱ ሶሻሊስት አብዮት በድል ከተጠናቀቀና የመጀመሪያው “የሠራተኛው መደብ” መንግስት ከተመሰረተ በኋላ ጎርኪይ በጤንነቱ መታወክ የተነሳ እምብዛም በሩሲያ ለመቀመጥ ባይችልም በርከት ያሉ ልቦለዶችን፣ አጫጭር ታሪኮችን፣ ሂሳዊ መጣጥፎችንና ተውኔቶችን በመጻፍ ለአዲሱ “የሶሻሊስት ስነ ጽሑፍ” መዳበር ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክቶአል፡፡ የሶቪየት ህብረትን ተራማጅ የደራሲያን ማህበር በመመስረትም ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውቶአል፡፡
ይህ ሶሻሊዝምን የድርሰቶቹ ጭብጥ አድርጎ የድሆችን ጎስቋላ ሕይወት በስራዎቹ በጉልህ በመሳል፣ የዘውዱን መንግስት ሲቃወምና የሶሻሊዝምን ስርዓት ለመመስረት ሲታገል የኖረው “ሶሻሊስቱ ብዕረኛ” ማክሲም ጎርኪይ፤ ከዕድሜው አርባ አራቱን አመታት ለስነ ጽሑፍ ስራና ለሶሻሊዝም ማበብ መስዋዕት አድርጎአል፡፡ በእነዚህም ዓመታት Mother ጨምሮ The Lower Depths፣ Danko’s Burning Heart፣ Tales of Italy፣ Summer Folk፣ Children of the Sun፣ Twenty-six Men and a Girl እና ሌሎች በርካታ ረጅምና አጭር ልቦለዶችንና ተውኔቶችን ጽፎአል፡፡ ማክሲም ጎርኪይ ይህቺን ሲታገልባት የቆየባትን ዓለም የተሰናበተው በ1936 ዓ.ም በ68 ዓመቱ ሲሆን ህይወቱም ያለፈችው የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ በሰጡት መርዝ ነበር፡፡ ማክሲም ጎርኪይ እጅጉን “ሶሻሊስቱ ብዕረኛ” የሚያሰኘውን ድርሰቱን “Mother’s በተመለከተ የተናገረውን ጠቅሼ የዛሬው ጽሑፌን ላብቃ፡፡ “Only mothers can think of the future - because they give birth to it in their children.” (ስለመጪው ዘመን ማሰብ የሚችሉት እናቶች ብቻ ናቸው፤ ምክንያቱም በልጆቻቸው ውስጥ አምጠው ወልደውታልና” እንደማለት ነው - በግርድፉ ሲተረጐም፡፡)
መልካም ሰንበት!!

Read 2004 times