Saturday, 23 August 2014 12:00

የተሰነጠቀ መነፅር ዕይታ ያወላግዳል

Written by  መስፍን ጌታቸው /የ“ሰው ለሰው” ድራማ ደራሲ/
Rate this item
(1 Vote)

(ካለፈው የቀጠለ)

ባለፈው ሳምንት መጣጥፌ መጨረሻ ላይ በገባሁት ቃል መሰረት፣ የዛሬ ፅሁፌን ሳምንት ያነሳሁትን ጥያቄ በመድገም እጀምራለሁ፡፡ እውነት አስናቀ በፖሊስ ቁጥጥር ስር አልዋለም ማለት ይቻላል እንዴ?...
እኔ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ አስናቀ ዙሪያው ገደል ሆኖበት፣ ወደ መጨረሻ ውድቀቱ የተገፋው በፖሊስ ሀይል ነው፡፡ ክፍል 56 አካባቢ ለሽያጭ ያዘጋጀው ህገ ወጥ የመኪና መለዋወጫ በመጨረሻ ድንገት ከእጁ ብን ብሎ እንዲጠፋ የተደረገው በፖሊስ ጥረት ነው። ትውልድ የማጥፋት አቅም የነበራቸው ወተቶችም ቢሆኑ ፖሊስ በትዕግስትና በማስተዋል በሰራው ጠንካራ ስራ ነው ምንም አይነት ጉዳት ሳያደርሱ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት፡፡
በመጨረሻስ?...በመጨረሻ ፍሬዘር አስናቀን በቁጥጥር ስር ለማዋል በስፍራው ተገኝቶ ነበር፡፡ ሽጉጡን ፊትለፊት ወድሮ የማንኛውም ወንጀለኛ የመጨረሻ እጣ ፈንታ ምልክት የሆነውን ካቴና ከፍ አድርጎ እያሳየው ባለበት ወቅት ነው ማህሌት ደርሳ የተኮሰችው፡፡
እዚህ ጋ አንባቢያን በመጨረሻ ካሜራው የአስናቀን ፊት በሰንሰለቱ ቀለበት ሾልኮ ያሳየውን ትዕይንት ለአፍታ በአይነ ህሊናቸው መለስ ብለው እንዲቃኙት እጠይቃለሁ፡፡
ይህ ምን ማለት ነው?.....እንዲህ የሆነውስ በምን ምክኒያት ነው?....እነዚህ ጥያቄዎች በበርካታ የኪነ-ጥበብ ስራዎች በተለይም ደግሞ በፊልም፤ በድርሰትና በስዕል ስራዎች በተደጋጋሚ  ጥቅም ላይ ሲውል ስለሚታየው ተምሳሌታዊነት (ሲምቦሊዝም) እንድናስብ ያደርጉናል፡፡
ሲምቦሊዝም ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ በተለያየ መንገድም ጥቅም ላይ ሲውል ሊታይ ይችላል፡፡ እኔ እየጠቀስኩት ባለሁት መንገድ ሲገለፅ ግን መፃኢ እድልንና የመጨረሻ እጣ ፈንታን አመልካች ተደርጎ ሊገለፅ ይችላል፡፡ ብዙ ስራዎችም በዚህ መንገድ ተሰርተው ለዕይታ በቅተዋል፡፡
ለምሳሌ አንድ ገፀ-ባህሪ በጣም አደገኛ የሆነ ማዕበል ወይም ደግሞ አውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ቢታይ ማዕበሉና አውሎ ንፋሱ የዚያ ሰው መጪ ህይወት በከፍተኛ መከራ፣ ውጣ ውረድና ስቃይ የተሞላ እንደሚሆን የሚጠቁሙ ተምሳሌቶች ናቸው፡፡
እዚህ ጋ በአንድ ርዕሱን በማላስታውሰው ፊልም ላይ ዳይሬክተሩ “ካርሎስ ቀበሮው” በመባል የሚታወቀውን አለም አቀፍ ሽብርተኛ፤ ጭካኔና ምህረት የለሽነት ለማመልከት የተጠቀመበትን ቴክኒክ በጥሩ ሲምቦልነት መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ፊልሙ ሲጀምር ካርሎስ አብራው የተኛችውን ቆንጆ ሴት ትቶ በመነሳት መስኮት ዳር ቆሞ ሲጋራ ሲለኩስ ነው የሚያሳየው፡፡ ወዲያው አንዲት ሸረሪት መጋረጃውን ተጠግታ ድሯን እያደራች ቁልቁል ስትወርድ ያያትና፣ ሲጋራ በለኮሰበት ክብሪት ልብልብ አድርጎ ይገላታል፡፡ ታዲያ ሸረሪቷ በእሳት ተለብልባ ስትሞት፣ እሱ ፊት ላይ እርካታና ሞቅ ያለ ፈገግታ ይታያል፡፡
ይሄ ድርጊት ያለምንም ጫጫታና ግርግር የሰውየውን ማንነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ እኛም የሞከርነው ይሄንኑ ነው:: ከላይ የገለፅኩትን ፊልም ያህል የተዋጣ ባይሆንም አስናቀ በመጨረሻ በህግ የተሸነፈ መሆኑን ለማሳየት በማሰብ ነው የህግ የበላይነትና የወንጀለኛ የመጨረሻ ውድቀት ማሳያ በሆነ ሰንሰለት ቀለበት አሾልከን የአስናቀን ፊት ያሳየነው፡፡ በኛ እምነት የህግን አሸናፊነት ለማሳየት ይሄ በቂ ምልክት ይመስለኛል፡፡
የማህሌትና የአስናቀ ፍፃሜ
በዚህ ንዑስ ርዕስ የሚነሳው ሀሳብ በአብዛኛው እላይ ከተነሳው ሀሳብ ጋ ይተሳሰራል፡፡ ማህሌት አስናቀን እንድትገድለው ለምን ተፈለገ ?..ለምንስ በህግ ቁጥጥር ስር ሲውል አላየነውም?.. ደራሲው ደህና መጥቶ መጥቶ እንዴት ብዙ ስትሰቃይ የኖረችውን ማህሌትን ወንጀለኛ ያደርጋል?..ኢትዮጵያዊ እናቶችን ያልሆኑትን እንዲሆኑ አርጎ ማሳየት ነው ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ናቸው በዚህ ዙሪያ ተደጋግመው የተነሱት፡፡
እዚህ ጋ ሀሳቤን በዝርዝር ለመግለፅ ከመጀመሬ በፊት በድጋሚ አንባቢያን እስከዛሬ ድረስ ካዩአቸው ፊልሞች፤ ቴያትሮችና ድራማዎች መካከል በተለይ ከ“ሰው ለሰው” ድራማ የታሪክ አወቃቀር ጋር የሚመሳሰል አወቃቀር ያላቸው ታሪኮች በምን አይነት አጨራረስ ፍፃሜ እንዳገኙ እንዲያስታውሱ እፈልጋለሁ፡፡
መቼም ሁሌም ባይሆንም በአብዛኛው የእኩይ ገፀ-ባህሪ ፍፃሜ ውድቀትና ሽንፈት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የኔ ጥያቄ የመጨረሻዋን የሽንፈት ፅዋ የሚጋቱት በማን አማካኝነት ነው?..በፖሊስ ነው ወይስ እድሜያቸውን ሙሉ ሊያጠፉት ደፋ ቀና ሲሉና ሲያሰቃዩት በኖሩት በመልካሙ ገፀ-ባህሪ አማካኝነት ነው?..የሚል ነው፡፡
መልሳችሁ በፖሊስ ወይም  በሌላ አካል ሳይሆን ተቃራኒያቸው በሆነው ገፀ-ባህሪ ነው የሚል እንደሚሆን በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል፡፡ ታዲያ ይሄ የሚሆነው ለምንድን ነው?.. የ“ሰው ለሰው” ፍፃሜስ ከዚህ በተቃራኒው ፍሬዘር አስናቀን በቁጥጥር ስር አውሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስደው የሚያሳይ ቢሆን ኖሮስ የተመልካቹ ምላሽ ምን አይነት ሊሆን ይችል ነበር፡፡ በእርግጠኝነት ከዚህ በጣም እጅግ እጅግ የበዛና መገመት ከሚቻለው በላይ የጠነከረ ብቻ ሳይሆን የከፋ ቅሬታና ተቃውሞ ይነሳ ነበር፡፡
ብዙ ጊዜ የመጥፎ ገፀ-ባህሪውን ውድቀትና የመጨረሻ ቅጣት ከመልካሙ ገፀ-ባህሪ ወይም ደግሞ ገፀ-ባህሪዎች እጅ አውጥቶ ለሌላው ወገን መስጠት እንደ ትልቅ ውድቀት ብቻ ሳይሆን በተመልካቹ የጋለ ስሜት ላይ በጣም የቀዘቀዘ ውሀ እንደ መቸለስም ነው የሚቆጠረው፡፡
አብዛኛዎቹ ፊልሞችና ቴአትሮች መጨረሻ ከላይ የጠቀስነው አይነት የሚሆነውም ሌላ በምንም ሳይሆን በዚሁ ምክኒያት ነው፡፡ ምስኪኑ ገፀ-ባህሪ ብዙ ጊዜ ባላንጣው ከሆነው ገፀ-ባህሪ ብዙ ቁጥር ካላቸው ተከታዮች ጋር እጅግ በጣም እልህ አስጨራሽ የሆነ ትንቅንቅ ገጥሞ ይተርፋል ብሎ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ተጎድቶ የጠላቱን ተከታዮች ከረፈረፈ በኋላ የዋነኛ ባላንጣውን ህይወት ሲያጠፋ ነው ፊልሞች የሚያልቁት፡፡ ፖሊሶች የሚደርሱትም በአብዛኛው እሱ ጦርነቱን በድል አድራጊነት አሸንፎ ከጨረሰ በኋላ ነው፡፡
እዚህ ጋ አንድ ጥሩ ምሳሌ ለማሳያነት መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት በሀገራችን ተከታታይ ድራማዎች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስምና ዝና ማትረፍ የቻለ ድራማ “የቀን ቅኝት” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ በሬዲዮ ተላልፎ ነበር፡፡ ድራማው ከ 250 ክፍሎች በላይ የነበረው ሲሆን በበርካታ ሙያተኞች ዘንድ የላቀ ውጤታማነቱ ተመስክሮለታል፡፡ “የቀን ቅኝት” በሚተላለፍበት ሰአት የከተሞች እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ይቀዘቅዝ እንደነበር በጥናት ተረጋግጧል። ከሀገራችን አልፎ በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች በርካታ ጥናቶች ተሰርተው በመፅሀፍ ታትመው ወጥተዋል፡፡ ስኬቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ሞዴል ሊሆን እንደሚችል ስለታመነበት ሌሎች ታዳጊ አገራትም የባህሪ ለውጥ ለማምጣት በማሰብ የሚያዘጋጇቸውን ድራማዎች በዚህ መሰረት እንዲያዘጋጁ እስከማድረግ የደረሰ ውጤት አስገኝቶአል፡፡
ድራማውን ሰርቶ ያቀረበው ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን እንደመታደል ሆኖ እኔም ከድራማው ሶስት ደራሲዎች መሀል አንዱ ነበርኩ፡፡ ታዲያ ከሀገር ውስጥ አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ይሄን ሁሉ ክብርና አድናቆት ማግኘት የቻለው የ“ቀን ቅኝት” ድራማ፤ በአጨራረሱ ከፍተኛ የሆነ የአድማጮች ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡
ድራማው በአብዛኛው ከ“ሰው ለሰው” ጋ የሚመሳሰል ነው፡፡ ዳምጠው የሚባል እንደ አስናቀ አይነት እኩይ ገፀ-ባህሪም ነበረው፡፡ ድራማው የሚያልቀውም ዳምጠው በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ሲያልፍ ነበር፡፡ ይህ አጨራረስ ለማመን የሚከብድ ከፍተኛ የአድማጭ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ የተቃውሞው ምክኒያት ደግሞ ይሄን ሁሉ ጥፋት ሲያደርስ የኖረው ዳምጠው እንዴት በአንዴ በሚገላግል ጥይት ይሞታል፡፡ በጣም በሚያሰቃይ ሁኔታ የእጁን አግኝቶና ማቅቆ መሞት ነበረበት የሚል ነበር፡፡
ዳምጠው በጥይት መገደሉ ቀርቶ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውል ድራማው አልቆ ቢሆን ኖሮስ?..ሳይሰቃይ በመሞቱ በጣም የተከፋው ተመልካች፣ አንድ ቀን ሊያመልጥ ይችላል ወይም ደግሞ የእስር ጊዜውን ጨርሶ ይፈታል በሚል ስጋትና ተኝቶ ሲቀለብ ሊኖር ነው በሚል ቁጭት የበለጠ ያዝን ነበር፡፡
በነገራችን ላይ ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ከዚህ ትምህርት በመውሰድ በቀጣይ የሚሰሩት ተከታታይ ድራማዎች በጠቅላላ አጨራረሳቸው የአድማጩን ስሜት በጠበቀ መልኩ በጥንቃቄ እንዲሰሩ እከመወሰን መድረሱን አስታውሳለሁ፡፡ እንግዲህ እኛም ስለ “ሰው ለሰው” አጨራረስ ስናስብ መጀመሪያ የተፋጠጥነው ከዚህ እውነታ ጋር ነው፡፡ በ“ቀን ቅኝት” አጨራረስ ወቅት የተነሳው ተቃውሞ በ“ሰው ለሰው” እንዲደገምና የተመልካቹ ስሜት እንዲጎዳ አልፈለግንም፡፡
በዚህ የተነሳ የህግ የበላይነትን ለማሳየት አስናቀ ለረጅም ጊዜ በህግ ሀይል ተገፍቶ መቃብር ጫፍ ላይ እንዲደርስ፣ የመጨረሻ እጣ ፈንታውም በካቴናው ምልክትነት እንዲገለፅ በማድረግ ድራማውን በዚህ ሁኔታ ማጠናቀቅ ብቸኛው ምርጫችን ነበር፡፡ በመሆኑም አስናቀ በማህሌት እጅ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱን አጥቶና ከህንፃው ላይ ወድቆ ማለቁ በጣም ተገቢ ነበር፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሳው ነጥብ የማህሌት ወንጀለኛ መሆንና ከኢትዮጵያውያን እናቶች ደግነትና ርህራሄ ተቃራኒ የሆነ ድርጊት እንድትፈፅም በማድረግ የእናቶቻችንን ምስል የሚያበላሽ ስህተት ተፈፅሞአል የሚለው ነው፡፡ ማንኛውም ድራማ፤ ፊልምም ሆነ ቴአትር የሚለካውና የሚመዘነው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ባሳየው ታሪክ መሰረት ብቻ ነው፡፡ ታሪኩ ካለቀ ቦኋላ ምን ይከተላል የሚለው የደራሲውም ሆነ የዳይሬክተሩ ራስ ምታት አይደለም፡፡ ቀደም ሲል በምሳሌነት በጠቀስናቸው ፊልሞች ላይ እንደታየው፣ ባላንጣውን ከነተከታዮቹ ረፍርፎ መጨረሱን አይተን ፊልሙ ካለቀ በኋላ የሱ መፃኢ እድል ወንጀለኛ መሆን አለመሆኑ እንደማያስጨንቀን ሁሉ የማህሌትም ጉዳይ ሊያስጨንቀን አይገባም፡፡
እናትነትም ቢሆን በሀገር በድንበር ተከልሎ የሚለይ አይመስለኝም፡፡ እንኳን የሰው ልጅ ቀርቶ እንስሳትም ቢሆኑ ለልጆቻቸው ባላቸው ፍቅር አይታሙም፡፡ እንዲያውም ቤተሰቦቿን አብዝታ የምትወድ ጥሩ እናት፤ የቤተሰቦቿ ህልውና ላይ አደጋ የሚያጋልጥ ችግር ሲገጥማት እራሷን በመሰዋት ሳይቀር ከማጥፋት ወደኋላ የማትል በመሆኗ ነው የምትታወቀው፡፡
ፍሬዘርና የአስናቀ ልጅ የሆነው ልዑል እንዴት አስናቀን ቆመው ያስገድሉታል በሚል ለተነሳ ነጥብ፣ ግድያው ሲፈፀም በስፍራው መገኘታቸውም ቆሞ እንደማስገደል ካልተቆጠረ በቀር ሁለቱም ቆመው አላስገደሉትም፡፡ ጥይት ደግሞ ከሴኮንድ በጣም ባነሰ የማይክሮ ሴኮንድ ነው ጥፋት የሚያደርሰው በሚል ሀሳቡን ያነሱት ሰዎች ደግመው እንዲያስቡበት ጠቁሞ ማለፉን መርጫለሁ፡፡
ልጅ አባቱ ሲገደል በስፍራው ተግኝቶ መመልከቱን በተመለከተም በእርግጥ ነገሩ በጣም ከባድ መሆኑ አይካድም፡፡ ነገር ግን እንደ አስፈላጊነቱ ታሪኩን ተከትሎ አባት ልጁን ወይም ደግሞ ልጅ አባቱን ሲገል ሊታይ የሚችልበት አጋጣሚም እንደሚኖር አለመዘንጋት ያስፈልጋል፡፡
ለዚህ ጥሩ የሆነው ትክክለኛ ማሳያ ዝነኛው `አካፑሉኮ ቤይ` ነው፡፡ የ“አካፑሉኮ” ቤይ ታሪክ የሚያልቀው እኩይ ገፀ- ባህርይ የሆነው ማክስ በጣም በምትወደውና በምትሳሳለት እናቱ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ሲያልፍ ነው፡፡
የእነሶስና ታሪክ
ይሄ ታሪክ ገና ከጅምሩ በጣም አነጋጋሪ ሊሆን እንደሚችል አውቀንና አምነን ነበር የጀመርነው፡፡ ታሪኩን አስፈላጊ ያደረጉት ሁለት መሰረታዊ ምክኒያቶች ሲሆኑ እነሱም ድራማውን መጠነኛ የኮሜዲ መልክ እንዲኖረው ማድረግና በከፍተኛ ደረጃ ስለ እርቅና ስለ መቻቻል መልዕክት ማስተላለፊያ እንዲሆን ማሰባችን ነው፡፡
በኛ እምነት ሁለቱን ሀሳቦቻችን በሚገባ አሳክተናል፡፡ ሶስና የድራማው ልዩ ቅመም ሆና ተመልካቹን በከፍተኛ ደረጃ ስታስደስት ኖራለች፡፡ ብዙ ሰዎችም በነሱ ታሪክ ስለ ይቅርታና መቻቻል ትልቅ ትምህርት ማግኘታቸውን በተደጋጋሚ ሲገልፁ ተሰምተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሀገራችንን ሁኔታ መለስ ብለን ለመቃኘት ብንሞክር፣ ብዙ ሰዎች ቁጡና ትዕግስት የለሽ ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ “አመሰግናለሁ” ማለትና “ይቅርታ” መጠየቅ አይታወቁም እስኪባል ድረስ በትናንሽ ቅራኔዎች አስፈሪ የሆነ ከባድ የጠላትነት ስሜት ውስጥ በመግባት ተራርቆ መቅረት ዕለት ተለት ክስተት ሆኖአል፡፡    ስለዚህ የ“ሰው ለሰው”ን ታሪክ ስናዋቅር፣ ይሄን አደገኛ የሆነ የጠላትነት ስሜት ብናክም በጥቃቅን ግጭቶች ትላልቅ ጠላትነት ውስጥ ለሚገቡ ወዳጆችም፤ በጣም ከባድና ከይቅርታ በላይ የሚመስል ጉዳይም በይቅርታ ሊታለፍ እንደሚችል ማሳየት በጣም ጥሩ ውጤት ሊያመጣ ይችላል በሚል ነው ታሪካችንን በዚህ መንገድ ያዋቀርነው፡፡
እዚህ ጋ ትልቅ ጥያቄ የተነሳው ሞገስ የልጁን አባትነት አሳልፎ በመስጠቱ ነው፡፡ ልብ አድርጉ! አሳልፎ የሰጠው ስሙን ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ለፍቅርና ለሰላም ሲባል ይሄ ቢደረግ ለምን ያስገርማል፡፡
ሞገስ አሳልፎ የሰጠው ስሙን ብቻ ነው፡፡ አባትነት ከስም ባሻገር ብዙ መገለጫዎች አሉት፡፡ አባትነት ፍቅር ነው፡፡ አባትነት ስሜት ነው፡፡ አባትነት መንፈሳዊ ትስስር ማለት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ሞገስ ከስሙ ውጪ ሌሎች የአባትነት መገለጫ የሆኑትን ተግባሮች ሁሉ እንዳይፈፅም የሚከለክለው ምንም ምክኒያት የለም። ጉዳዩ ከፍቅርና ከእርቅ በላይ የሶስቱ ትስስር መቼም ቢሆን ሊፈርስ ይችላል ተብሎ በማይታሰብበት መንገድ ነው እልባት ያገኘው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ በየትኛውም ሰብአዊና ህጋዊ ሚዛን ብንመዝነው፣ ከሱ ይልቅ እናቱ ነች ህፃኑን የማሳገድ መብት የሚኖራት፡፡ በዚህ ላይ ልጅን አሳልፎ በጉዲፈቻ የመስጠት ባህል ያለው ማህበረሰብ ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ በተለያዩ ምክኒያቶች በወላጅ አባቶቻቸው ሳይሆን በአያቶቻቸው ፤ በአሳዳጊዎቻቸውና በሌሎች ስም የሚጠሩ ብዙ ሰዎች በሀገራችን እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ እውነታዎች ከግምት አስገብተን ስንመዝነው ነው የሞገስን ድርጊት ተገቢ ሆኖ የምናገኘው፡፡
በመጨረሻም ፅሁፌን ከማጠናቀቄ በፊት ይሄን ሁሉ ስል “ሰው ለሰው” ምንም ስህተት የማይገኝለት እንከን አልባ ድራማ ነው ለማለት እየሞከርኩ አለመሆኑን በትልቁ ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡
በትክክል ከፈተሽነው በጣም ብዙ እንከኖችና ጉድለቶች ሊኖሩበት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የአስናቀ መጨረሻ ላይ ሽጉጥ ይዞ አለመተኮስ፣ የተወሰኑ ገፀ-ባህሪያት ታሪኮች በአግባቡ እልባት ሳያገኙ መቅረት ወዘተ … ከብዙ በጥቂቱ ሊገለፁ ይችላሉ፡፡
እውነቱን ለመናገር እኛ ከብዙ ድክመቶቻችን አንድ ትልቅ እርምጃ ወደፊት ተጉዘናል፡፡ ከኛ በኋላ የሚመጡ ሙያተኞች ሁለት ሶስት ብለው ይበልጥ እንደሚራመዱ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለተሻለ ስኬት እንዲበቁም ልባዊ ምኞቴን ከበዛ ትህትና ጋር ልገልፅላቸው እወዳለሁ፡፡
አክብረው ያስከበሩንን ውድ ተመልካቾቻችንንም ከታላቅ ምስጋና ጋር ያክብርልን፤ እድሜ፤ጤና፤ሰላምና ፍቅሩን አብዝቶ ይስጥልን እላለሁ፡፡

Read 1772 times