Saturday, 06 September 2014 11:14

ደጉ ደበበ ለዓለም ሰላም በተዘጋጀ የኳስ ግጥሚያ ተሳተፈ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       በሳምንቱ መግቢያ ላይ በሮም ከተማ በሚገኘው ስታድዮ ኦሎምፒኮ በተዘጋጀው የዓለም ሃይማኖቶች ሁሉን አቀፍ የሰላም ግጥሚያ ላይ የዋልያዎቹ የቀድሞ ዋና አምበል ደጉ ደበበ ተሳተፈ፡፡ የእግር ኳስ ግጥሚያውን በክብር እንግድነት የታደሙት የቫቲካኑ ጳጳስ ፍራንሲስ ሲሆኑ፤ የሰው ልጆች በጭራሽ ሰይፍ የማይማዘዙበት ዘመን እንዲመጣ ሃይማኖት እና ስፖርት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዓለም እግር ኳስ የታዩ ከ50 በላይ የአሁን ዘመንና የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋቾች በሰላም ግጥሚያው ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ለሁለቱ ቡድኖች ተሰላፊዎችን የመረጡት አዲሱ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጌራርዶ ታታ ማርቲኖ እና የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ናቸው፡፡ በሁለቱ ቡድን የተመረጡ ተጨዋቾች በግጥሚያው የሁለት ግብረሰናይ ተቋማትን የሚወክሉ ማልያዎችን ለብሰው ተሳትፈዋል፡፡ በሃቪዬር ዛኔቲ አምበልነት የሚመራው ፑፒስ እና  በጂያንሉጂ ቡፎን የሚመራው ስኮላስ ናቸው፡፡
በጨዋታው ተሳታፊ ከሆኑት የጊዜያችን ምርጥ ተጨዋቾች መካከል ሊዮኔል ሜሲ፤ ኤቶና ፒርሎ እንዲሁም ከአንጋፋዎች ዲያጐ ማራዶና፣ ዴልፒዬሮና ሮበርቶ ባጂዮ ይገኙበታል፡፡
 የዓለም ህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚኖርበት የታመነበት የሰላም ግጥሚያው በመላው ዓለም ሰላምን ለማስፋፋት ቅስቀሳ የተደረገበት ሲሆን በከፋ አደጋ ላይ ለሚገኙ የዓለም ህፃናት ድጋፍ የሚሆን ገቢም ተሰባስቦበታል፡፡  የሰላም ግጥሚያውን ስፖንሰር ካደረጉት መካከል ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ፋኦ፤ የመኪና አምራቹ ኩባንያ ፊያት እና ሌሎች ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ይጠቀሳሉ፡ በመላው ዓለም በአምስት አህጉራት በቴሌቭዥን የቀጥታ ስርጭት የነበረው ዝግጅቱ በጣሊያን፤ በኦስትርያ፤ በፈረንሳይ እና በጀርመን ልዩ  ትኩረት እንዳገኘም ታውቋል፡፡
በዓለም ሰላም እንዲሰፍን ለመቀስቀስ የተዘጋጀውን የእግር ኳስ ልዩ  ግጥሚያ በማስተባበር በቦነስ አይረስ የሚገኘውን ፑፒ ፋውንዴሽን መስራች የቀድሞው አርጀንቲናዊ ተጨዋች ሃቪዬር ዛኔቲ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
  ሃቪዬር ዛኔቲ  በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን አምበልነት ያገለገለ፤ በሚላን ከተማው ክለብ ኢንተር ሚላን ለ19 ዓመታት የተጫወተ እና አሁን የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖ እየሰራ ነው፡፡

Read 1829 times