Saturday, 06 September 2014 11:30

“ይድረስ ለእግዚአብሔር…”

Written by  ኃይለገብርኤል እንደሻው
Rate this item
(1 Vote)

    እሁድ ረፋዱ ላይ በአካባቢዬ ከሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ ቁጭ ብያለሁ፡፡ ወቅቱ ክረምት ቢሆንም፣ ዕለቱ ፀሐያማና ሰማዩም ጥርት ያለ ነው፡፡ በዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው ፀጥታ ደስ የሚያሰኝ ስሜትን ለልብ ይለግሳል፡፡
ወገባቸው ላይ አዳፋ ነጠላ ያሰሩ እናቶች፣ የቤተክርስቲያኑን ቅፅር ግቢ ይጠርጋሉ፡፡ አልፎ አልፎ ለመሳለም ወጣ ገባ ከሚሉ ሰዎች በስተቀር ግቢው ጭር ያለ ነው፡፡
የተቀመጥኩበትን የግንብ አጥር እየታከከ ከተዘረጋው ጣውላ የለበሰ ረጅም የግንብ መቀመጫ ላይ ራቅ ራቅ ብለው የተቀመጡ ወንድ ወጣቶች፣ አዛውንትና ጎልማሶች ይታያሉ፡፡ አንዳንዱ የፀሎት፣ ሌላው ደሞ ሌላ ዓይነት መጽሐፍ ያነባል፡፡ ዓይኖቻቸውን ከድነው ወደ ኋላ ግንቡ ላይ የተደገፉም አሉ፡፡ አካባቢው የወንዶች ስለሆነ፣ ሴቶች አይታዩም፡፡
 ድንገት በዛ ያሉ ሰዎች ፊት ለፊት ከሚታየው የቤተክርስቲያኑ የውጭ በር አጠገብ በደራሽ ውሃ ዓይነት ግር ብለው ሲሳለሙ ተመለከትኩ፡፡ ከአፍታ በኋላም በቀጥታ የግቢውን ሰፊ የአስፋልት ሜዳ በማቋረጥ ወደ ውስጥ ዘለቁ፡፡ ሁሉም በዕድሜ ከፍ ከፍ ያሉ እናቶች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ የውሃ ጄሪካንና ባልዲ አንጠልጥለዋል፡፡ እንስራ ያዘሉ፤ ጣሳ፣ ሸንኬሎ፣ ጠርሙስ፣ ማንቆርቆሪያ፣ ሳፋና ቅል የያዙም ይታያሉ፡፡ የለበሱትን አዳፋ ነጠላ አዘቅዝቀው መልበሳቸው አስከሬን ለመሸኘት የወጡ አስመስሏቸዋል፡፡ ከመሃከላቸው ጉልህና ጥቃቅን ጽሁፎች የሰፈሩባቸውን ትላልቅ ክርታሶች ከፍ ከፍ አድርገው የተሸከሙ እናቶችም አሉ፡፡ አካሄዳቸው የቀዘቀዘ ስሜት የሚነበብበት፣ የሰላማዊ ሰልፍ ዓይነትና ፍፁም ፀጥታ የተሞላበት ነው፡፡
እነዚህ ልዩ ሰላማዊ ሰልፈኞች፤ የቤተክርስቲያኑ መሳለሚያ በር አጠገብ ሲደርሱ፣ የያዟቸውን የውሃ መቅጃ ዕቃዎች መሬት ላይ በማኖር፣ ትላልቅ የክርታስ ጽሁፎች የተሸከሙት ደሞ በጥንቃቄ ግድግዳው ላይ በማስደገፍ፣ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ፡፡ ከሩቅ ለሚያያቸው፣ መሬት ላይ የተርከፈከፉ አዳፋ ቡትቶዎች ይመስላሉ፡፡ በየጥጋጥጉ ያለ ታዛቢ ከየተወሸቀበት እየወጣ ግርምታ በተቀየጠበት ዕይታ ያስተውላቸዋል፡፡ እኔም ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ወደ ሰዎቹ ተጠጋሁ፡፡ የቤተክርስቲያኑን ግድግዳ ተደግፈው ከተኮለኮሉት ትላልቅ ጽሁፎች መካከል አንደኛው ገዘፍ ያለና ከሁሉም ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ አንዲት ሸበቶ፣ ፀጉራቸው ካሰሩት ሻሽ አፈትልኮ የወጣ፣ እናት መሬት ላይ እንደተደፉ የዚህን ትልቅ ጽሁፍ መቆሚያ እንጨት በአንድ እጃቸው አቅፈው ይዘዋል፡፡ ጽሁፉ ረዘም ያለ፣ ጎላ ጎላ ተደርጎ በጥቁር ቀለምና በሚያምር የእጅ ጽሁፍ የተጻፈ ነው፡፡ ቀልቤን  ስለሳበው ቀረብ ብዬ ለማንበብ ሞከርኩ፡፡
‹‹ይድረስ ለእግዚአብሔር፣›› የሚለው ርዕስ በእርግጥም ሁለመናን ይስባል፡፡ ርዕሱ በቀይ ነው የተጻፈው፡፡“…ውድ ታላቁና የሁሉ የበላይ የሆንከው ፈጣሪያችን፣ ያንተን ደህንነት መጠየቅ ስለማያስፈልግ እንዴት ነህ በማለት ጊዜህን ላባክንብህ አልፈልግም፡፡ የእኔን ደህንነት አንተም ስለምታውቀው፣ ለጊዜው ክብርህ ይስፋ፣ መንግስትህ ባስቸኳይ ወደ’ኛ ትምጣ ከማለት ሌላ ምንም የምለው የለኝም፡፡ ይልቁንም የዛሬውን ደብዳቤ ለመፃፍ የተገደድኩበትን ምክንያት አስቀድሜ በመግለጽ ወደ ጉዳዬ እገባለሁ፡
“ውድ እግዚአብሔር፡- የደብዳቤዬ ይዘት ልመናና አቤቱታ ነው፡፡ ወዳንተ የፃፍኩበት ምክንያት ደሞ አንተ እንደምድራችን ንጉሦች፣ ለአቤቱታና ለሰላማዊ ሰልፍ ፍቃድ የማትጠይቅ፣ ቅድመ-ሁኔታ የማታስቀምጥ፣ በቀጠሮ የማታጉላላ፣ አማላጅ አምጡ የማትል፣ የፖሊስ አጀብ የማትሻ፣ ሌላው ቢቀር ለደብዳቤ መስደጃ የሚሆን ቴምብር፣ ቀረጥና ሌሎችንም አምጡ የማትል ሃያል፣ የሁሉ ፈጣሪና በሁሉም ቦታ የምትገኝ በመሆንህ ነው፡፡ እንደምታየው በበሶ የታሸ የመሰለ ነጠላ ለብሼ ተደጅህ መምጣቴ፣ ንፅህናን ሳልፈልግ ቀርቼ እንዳልሆነ አንተም አትስተው፡፡ ጨርቄን የምጨፈጭፍበት አንድ ጣሳ ውሃ ባጣ ነው፡፡ እግሬ እንደመጅ ሻክሮ፣ ገጤም ዱቄት የተነፋበት ብረት ምጣድ መስሎ ፊትህ ለመቅረብ የተገደድኩበት ምክንያትም ይሄው ብቻ ነው፡፡
“የኔ መድሐኒአለም፣ኧረ ለመሆኑ ውሃና መብራት የምትከለክለን ምክንያቱ ምን አጥፍተን ነው? ኑሮው እንዲሁም አምሮበታል እንኳንስ የውሃና የኮረንቲው ችግር ተጨምሮበት! … ይቅርታ የኔ መድሐኒአለም ፣ እኔ የማውቀው እዚህ አለሁበት ሃገሬ ላይ የሚጠጣ ውሃና የምግብ ማብሰያ መብራት ማጣቴን እንጂ፣ በማንና በምን ምክንያት ይጥፋ አልተመራመርኩም፡፡ ለዚህ ነው ስለችግሩ አንተን ለመጠየቅና ለመውቀስ የተገደድኩት፡፡ ምናልባት፣ ልብ አድርግ ፈጣሪ፣ ምናልባት ነው ያልኩት፣ ምናልባት ችግሩ ወደ’ዚህ ወደ’ኛም አካባቢ ከሆነ፣ አሁንም ቢሆን እኔ ምስኪን ያንተዪቱ ከርታታ ባልቴት የምወቅሰውና አቤት ብዬ የማስቸግረው አንተኑ ነው፡፡ ምነው ሸዋ!…ደሞ ‹ይህን ስትይ፣ያንን ለማለት አስበሽ ነው፣…ምንትሴ ቅብርጥሴ፣› ተብዬ ዘብጥያ መወርወር አልፈልግም፡፡ ከምድራዊ መፍትሄ አፈላላጊ ተብዬዎች ሁሉ የበላይ የሆንከውን፣ በሰበብና በምኽኝያት መንገድ መዝጋት የማታውቀውንና ሁሉንም እንደየስራው አደብ የምታስይዘውን ሁሉን ቻይ ፈጣሪ አንተን ማስቸገር ይሻለኛል፡፡ ከአንተ ሌላ የምሮጥበት ሜዳ፣ የምገባበት ቀዳዳ የሌለኝ ፍጡርህ እንደሆንኩ ታውቀዋለህ፡፡
“ጌታዬ፣ ምነው ጨከንክብኝ! ምነው የልጆቼን ጉሮሮ የማረጥብበትን፣ ዱቄት በጥብጬ አብሽ የምግትበትን፣ ለማቲዎቼ ቂጣ እጠፈጥፍበት ዘንድ የጤፍ ዱቄት የማቦካበትን ውሃ የምታሳጣኝ! አሁን ያለሁበት ቦታ ከተማ ቢሆንም፣ ከየስርቻው ኩበትና እንጨት ለቃቅሜና ደጃፌ ላይ ጉልቻ ጎልቼም ቢሆን ጥርስ ላወጡት፣ ለትልልቆቹ ጥሬ ቆልቼ ማብላት አያቅተኝም፡፡ የቸገረኝ የትንንሾቹ ነው፡፡ …አይ የኔ ነገር…እንጨት ብል አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ መቼም ማብሰያ መብራቱ ቢጠፋም… ይሄ የእታጉ ልጅ፣ አቡሽ፣ ውሎ ይግባና የእንጨቱን ችግር ገላግሎኛል፡፡ ከየሄደበት በመኪናው ለእናቱ እየጫነ ሲመጣ፣ እኔንም አልረሳኝ፡፡ እባክህ፣ ለሰራው ደግነት በረከትህን አዝንብለት! ተዝቆ ከማያልቀው የዕድሜ ጎተራህ አፈስ አርገህ መርቅለት!
“መቼም ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ ይባላል! …የማብሰያ መብራቱ ነገር በአያሌው የቸገረን ጉዳይ ሆኗል፡፡ የሰለጠንን መስሎን የሸክላውን ሰታቴና ምጣድ ወዲያ ብለን ስናበቃ፣ አሁን መብራት የሚሉት ነገር ጉድ ቢሰራን፣ ቅጥ አምባሩ ጥፍት ብሎብናል፡፡ በእንጨት ማብሰሉና መጋገሩ መቸ እንደ ጥንቱ ሆነና! በብረት ድስትና በእንጨት እሳት የሚበስለው ወጥና አጥሚት አሁን አሁን መላም የለው! … ሌላው ቢቀር፣ ምሽት ላይ የመንደሩ ሰው በየማደሪያው ገብቶ አልጋው ላይ እስኪሰፍር፣ ከጨለማ ይሻላል በሚል፣ተየደጃፉ ተጎልቶ ሲያንጎላጅ ነው የሚያመሸው፡፡ ይኸውልህ፣ አዳሜ ጀንበር በጠለቀ ቁጥር ሥራው ይሄ ሆኗል፡፡
“አሁን ለታ የተቦካ ሊጥ በፍራንክ የሚያስጋግሩ ሰዎች አሉ ቢሉኝ፣ ቡኻቃዬን ተሸክሜ ወደተባለው ስፍራ ሄድኩ፡፡ አላፊ አግዳሚው የለመደው በመሆኑ፣ የቾምቤ እናት ሊጧን ይዛ ባቡር መንገድ ላይ ትዞራለች ያለኝ አንድም ሰው አልነበረ፡፡ መቼም የወረፋው ነገር አይጣል ነው፡፡ ተራ ደርሶኝ አንድ-አምስት እንጀራ እንዳወጣሁ፣ አንድ ልጅ እግር ቢጤ መጥታ፣ ‹‹እማማ ፈጠን ፈጠን ይበሉ እንጂ! ብዙ ሰው ተራ እየጠበቀ እኮ ነው›› አለችኝ፡፡ እኔም፣ ‹‹ምነው፣ ልጄዋ! መቼም ሊጡን ተምጣድ ላይ አላወጣው›› ብላት፣ ‹‹ካልፈጠኑ መሄድ ይችላሉ፡፡ እንደውም ብዙ ለሚጋግሩት ነው ቅድሚያውን የምንሰጠው›› አለችኝ፡፡ ለካ ያችን ጎስቋላና ሽንቁሯ በጨርቅ የተወታተፈ ቡኻቃዬን አይታት ኖሯል ይሄን ማለቷ! አይ መጨካከን! ለአንድ እንጀራ ሁለት ብር እየተከፈለ ለሚጋገረው ይሄ ሁሉ ጥድፊያ የት ለመድረስ ነው!… ልጅቱ ብታጣድፈኝ አስፍቸው የነበረውን እንጀራ ገና ሳይበስል ተምጣዱ ላውጣው ብል፣ እንኩሮ ሆነና አረፈው፡፡ የተረፈች ሊጤን ሸክፌና አምስት እንጀራዬን በዳንቴል ሸፍኜ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡ መቼም ያን ለታ የገባኝን ብስጭት እኔና አንተ ብቻ ነን የምናውቀው፡፡ … ሆድ ብሶኝ ነው’ኮ! … ምናባቱንስና! አንዴ ለመድነውና ነውዪ ስለኮረንቲው ማውራቴ፣ የሱስ ነገር ላንተ ተሚወራ ቢቀር ነው የሚሻለው፡፡ እንደው ተውሃና ተኮረንቲውስ ያው ውሃው ቢኖር ይሻለናል፡፡ ጌታዬ፣ መቼም… ሁለቱም ቢኖሩ ደግ ነው፡፡ ግና ተሁለቱ ምረጭ ብትለኝ፣ እኔ’ቴ! የምን ኮረንቲ…ውሃው አስር እጅ ይበልጥብኛል፡፡ ያለውሃ ምን ዓይነት ኑሮ ይኖራል ብለህ ነው! … ኤዳልኝ ኤዳ!!
“የኔ መድሐኒአለም፣ ድሮ በንጉሡ ጊዜ አምስት እንስራ ውሃ በሁለት ፍራንክ (አምስት ሳንቲም) እንዳልገዛን፣ አሁን ለአንዲት ጄሪካን ውሃ አንድ ባውንድ ክፈሉ ይሉናል፡፡ አቤት ጭካኔ! አስከሬን ለሚታጠብበት! ምነው፣ የኔ ጌታ፣ ፍዳችንን አበዛህብን! … አንተ ሆነህ ነውዪ እንደምድሩ የዘመኑ ጭቃ ሹሞችና መኳንንት ቢሆንማ ኖሮ፣ ስለንጉሡ ትንፍሽ ማለት መዘዙ የከበደ በሆነ ነበር! ደሞ በዚህ በአሮጌ ዕድሜዬ ‹የቀድሞ ሥራት ናፋቂ› ብለው የልኬን ያስገቡኝ! … የሆነስ ሆነና፣ ጌታዬ፣ምነው እንዲህ ጨከንክብን! አንዱን ስታጠጣ ሌላውን በጥም መግደልህ፣ ምነው!
“አሁን ለታ ባለቤቴ ባሻ፣ ቢቸግረው እንደጥንቱ እንደጠዋቱ ተግቢያችን ውስጥ የውሃ ጉድጓድ ታልቆፈርኩ ብሎ ቢነሳ፣ የቤቴ ማቲ ሁላ አይሆንም በማለት አገረገረ፡፡ ‹‹ምነው፣ ለምን አይሆንም? ፊት የጉድጔድ ውሃም አይደል ጠጥተን የኖርነው፣›› ብሎ ቢጠይቅ፣ ‹‹አሁን ከተማይቱ ስላደገችና የጉድጓድ ውሃ በየምኽኛቱ ስለሚበከል ለጤናችን ደግም አይደል… ምንትሴ ቅብርጥሴ›› አሉና ነገሩን አጣጣሉት እልሃለሁ፡፡ ድንቄም…! ኧረ እናንተው፣ ታዲያ በውሃ ጥም መሞት ይሻላል ነው የሚሉት! ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ ጉዳይ ነው’ኮ እናንተው! ተንግዲህ ወዲያማ፣ አንተ ፈጣሪ ብቻ ነህ ሚሆነውን ምታውቀው!
በያ ሰሞን የጦሙ ለት ቤተክርስቲያን ለብሼ የምሄደውን ነጠላዬን የምለቀልቅበት ውሃ ባጣ፣ ይኸውልህ አሻሮ የተሰጣበት የመሰለውን ጨርቅ ተከናንቤ ግቢህን ስጠቀጥቅ ሰነበትኩ፡፡ አበስኩ ገበርኩ! …አይ የኔ ነገር… የምጠጣው የለ ስለሸማ መጨፍጨፊያው መቀባጠሬ!…ዘንድሮ የጤናዬን ነው ብለህ ነው! የተመቸው ገንፎ ያላምጣል፣አሉ! …
“ጌታዬ መድሐኒአለም ሆይ፣ አንተንም አስጨነቅሁህ፡፡ የት ልግባ ታዲያ! የምሮጥበት ሜዳ፣ የምገባበት ቀዳዳ ያጣሁ ያንተው ከርታታ አይደለሁ! … ምን ላድርግ! ያላንተ ማን አለኝና ብሶቴን ልተንፍሰው! አንተ ብቻ ነህ የድሃን ብሶት የምታደምጠው፡፡ የምድሩ ጌቶቻችንማ ታንጀት ጠብ በማይል እሰጥ አገባ ነው ሥራ ሲያስፈቱን የሚውሉት! …የኔ አባት፣ እውር አሞራን የምትመግብ የሰራዊት ጌታ፣ ምነው ረሳኸን! ጉሮሯችንን የምናርስበት፣ አብስለን የምንጎርስበት፣ አጥድተን የምንከናነብበት፣ ጭቅቅታችንን የምናራግፍበት ትንሽ ውሃ እንኳን የነፈግኸን በየትኛው ኃጢያታችን ነው!
“መድሐኒአለም ሆይ፣ በል እንግዲህ ችግሩ ቢጠናብኝ ነው ነገር መደረቴ… አሁንም ተራ ውሃ ብቻ ሳይሆን ተውሳኩን ሁሉ የሚከላ ጠበል የሆነውን ዝናብህን ትሰጠን ዘንድ ተደጅህ ተደፍቼ እለምንሃለሁ፡፡ እኔም ሆንኩ መሰሎቼ፣ የቻለ ጄሪካንና እንስራ፣ ያልቻለ ባልዲ፣ ሳፋ፣ ሸንኬሎ፣ ገረወይና፣ ቅል፣ ጠርሙስ፣ መዘፍዘፊያ… ባጠቃላይ ውሃ መያዣ የሆነውን ሁሉ ተሸክሞ በናፍቆት ይጠብቅሃል፡፡ ዝናብህ ለጥማችን መቁረጫ ብቻ ሳይሆን፣ ለክፋታችን ማንጫ እንደሚሆነን ፍፁም እምነቴ የፀና ነው፡፡ መቼም ለልመናዬ አንጀት አርስ ምላሽህን በመስጠት እንደምታስደስተኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ያንተው…”

Read 1920 times